Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበገጠር መሬት አስተዳደር ዙሪያ የሚወጡ ሕጎች ለፌዴራል መንግሥት ብቻ እንዲተው ተጠየቀ

በገጠር መሬት አስተዳደር ዙሪያ የሚወጡ ሕጎች ለፌዴራል መንግሥት ብቻ እንዲተው ተጠየቀ

ቀን:

የገጠር መሬት አስተዳዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ የሚወጡ ሕጎች ለፌዴራል መንግሥት ብቻ እንዲተው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ ይህንን ያለው ታኅሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በአዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ከአስረጂዎች ጋር በነበረው ውይይት ነው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ፣ በረቂቅ አዋጁ መሬትን በተመለከተ ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠውን ሥልጣን ለክልሎች ማካፈሉ ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መሬትን በሚመለከት ጉዳዩ ወጥ የሆነ ሕግ ቢኖር ተመራጭ መሆኑን ጠቁመው፣ ነገር ግን በረቂቁ ላይ ከፌዴራል መንግሥት በተጨማሪ ክልሎች ሕግ እንዲያወጡ መፈቀዱ አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በምክንያትነት ያነሱት ሰብሳቢዋ፣ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 52 (2) መሬትን በሚመለከት የሚወጡ የሕግ ደንጋጌዎች ሥልጣን የተሰጠው የፌዴራል መንግሥት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ክልሎች የፌዴራል መንግሥቱ ባወጣው ሕግ ለምን አይተዳደሩም? ያሉት ሰብሳቢዋ፣ ጉዳዩ ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በመሬት ጉዳይ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለፌዴራል እንደተሰጠ፣ የማስተዳደሩ ጉዳይ ለክልሎች መተውን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በረቂቅ አዋጁ ከላይ የተነሱ ጉዳዮችን ሳይመልስ የሚያፀድቅ ከሆነ፣ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የተዥጎረጎረ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲኖር ዕድል ሊፈጥር ይችላል በማለት ያላቸውን ሥጋት ጠቁመዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከፍተኛ የመሬት ሕግ ባለሙያ አቶ አበባው አበበ፣ በገጠር መሬት ጉዳይ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመርያና ሌሎች ሕጎች በፌዴራል ደረጃ ለማውጣት ታሳቢ የተደረገ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሒደት ግን ከዚህ ቀደም የነበረው ልምድና አሠራር ክልሎች በገጠር መሬት ላይ ሕግ ሲያወጡ በመቆየታቸው፣ በአንድ ቅጽበት የነበረውን ለመቀየር መቸገራቸውን አቶ አበባው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ በረቂቅ አዋጁ ላይ ክልሎች ከፍተኛ ተቃውሞ ማንሳታቸውን የገለጹት ባለሙያው፣ በየክልሎች ያለው ነባራዊ ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ በፌዴራል በወጣ አፈጻጸም ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት በፌዴራል ደረጃ የረቀቀው አዋጅ ላይ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ማስቀመጥ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ እንደ ምክንያት ያነሱት ለአንድ ክልል የሚሠራው ድንጋጌ፣ ሌሎች ላይ እንደማይሠራ፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን የአሠራር ልምድ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ ታሳቢ በማድረግ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ክልሎች እንዲያወጡ መፈቀዱን አስረድተዋል፡፡

በሕገ  መንግሥቱ አንቀጽ 51(5) መሠረት መሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና ታሪካዊ ቅርሶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለፌዴራል መንግሥት እንዲሰጥ መደንገጉን አንስተዋል፡፡

በአንቀጽ 52 (2) ‹‹መ››ን መሠረት አድርጎ ክልሎች መሬት እንዲያስተዳድሩ መደንገጉን የገለጹት አቶ አበባው፣ በአንቀጽ 50 (9) የፌዴራል መንግሥቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በአንቀጽ 51 ከተሰጠውን ሥልጣን መካከል በውክልና ሊሰጥ እንደሚችል የሚያስረዳ ድንጋጌ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ ሌሎች ሕጎችን ያነሱት አቶ አበባው፣ የካሳ ክፍያ ሕግ ሲወጣ አዋጅና ደንቡን የፌዴራል መንግሥት እንዲያወጣ መደረጉን፣ ነገር ግን መመርያው ግን ለክልሎች በውክልና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ 456/1997 ዓ.ም. ሲወጣ በአንቀጽ 17 ላይ የተገለጸው፣ አዋጁን ለማስፈጸም ሲባል ክልሎች ዝርዝር ሕግ እንዲያወጡ እንደሚፈቅድ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሕገ መሠረት በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ መሆኑን፣ በፌዴራል ደረጃ አዋጅ፣ መመርያና ደንብ አጠናቅቆ ለክልሎች ቢሰጣቸው ለአፈጻጸም አስቸጋሪ እንደሚያደርገው፣ ከክልሎች ጋር መግባባት ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

የክልሎችን ፍላጎት መነሻ በማድረግ ሕገ መንግሥቱን ሳይፃረር ውክልና መስጠት በሚያስችለው መሠረት ክልሎች ዝርዝር ሕጎችን እንዲያወጡ በረቂቅ አዋጁ መደንገጉን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ አነስተኛ ማሳ መጠን በረቂቅ አዋጁ በዝርዝር አለመቀመጡን የገለጹት አቶ አበባው፣ አነስተኛ የማሳ መጠን እንደ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ እንደሚለይ በምሳሌነት አስቀምጠዋል፡፡

ከ0.5 ሔክታር ብሎ የሚያስቀምጡ ክልሎች መኖራቸውን፣ 0.66 ሔክታር አነስተኛ የማሳ መጠን እንደ ክልሎች እንደሚለያይ ይገልጻል፡፡

ስለዚህ ይህንን ጉዳይ በፌዴራል ደረጃ የአነስተኛ የማሳ መጠን ይህ ነው ብሎ ቢቀመጥ ተፈጻሚነት አያመጣም በሚል ዝርዝር ጉዳዮችን ለክልሎች መስጠቱን አስረድተዋል፡፡

ክልሎች ደግሞ በሚያቀራርባቸው እንዲቀረፁ መተውና በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ክልሎች በሚያወጡት ዝርዝር ድንጋጌዎች እንዲካተቱ ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...