Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅሮች ፅዳት ይሻሉ!

ከትናንት እስከ ዛሬ የፖለቲካ ክስረቶቻችን ማሳያዎች ብዙ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ የፖለቲከኞች መስተጋብር በመርህ ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ፣ ልዩነትን ማስተናገጃ በርካታ አዎንታዊ አማራጮች እያሉ አሉታዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ይበዛል፡፡ የብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጣዊ ግንኙነት በዴሞክራሲ ዓምዶች ላይ ያልተመሠረተ ስለሆነ፣ አለመግባባት ሲያጋጥም በስክነት ጊዜ ወስዶ ከመነጋገር ይልቅ ትርምስ መፍጠር የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ፓርቲዎች፣ ግንባሮች፣ ስብስቦችና ኅብረቶች ፈራርሰዋል፡፡ በርካታ ፖለቲከኞችም ከአንዱ ፓርቲ ወደ ሌላው እየተሽከረከሩ የረባ ሥራ ሳያከናውኑ ባክነው ቀርተዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ሠፈርም ቀደም ሲል በዘመነ ኢሕአዴግ በሕወሓት አመራሮች መካከል በ1993 ዓ.ም. በተፈጠረው መሰንጠቅ ሳቢያ፣ የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳንት ጨምሮ በርካታ የፓርቲው አመራሮች ለእስርና ለስደት የተዳረጉበት ታሪክ አይረሳም፡፡ በዘመነ ብልፅግናም የለውጡ አንደኛው መሪ ከሆኑት ግለሰብ ጀምሮ፣ በቀደም ከኃላፊነት እስከተነሱት ግለሰብ ድረስ ሒደቱ ቀጥሏል፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ቁምነገር ሰዎች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ወይም መልቀቃቸው ሳይሆን፣ ልዩነትን በሰላምና በጨዋነት የማስተናገድ ቀናነት መጥፋት ነው፡፡

የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አላባውያን ከሆኑት መካከል አንደኛው የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ ማንም ሰው ከሕግ በላይ መሆን ካለመቻሉም በላይ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ ነው የሚታመነው፡፡ በፓርቲ ውስጣዊ ሕገ ደንብም ሆነ ለመንግሥት አሠራር ቅልጥፍና በተደነገጉ ሕጎችም፣ እያንዳንዱ ግለሰባዊም ሆነ ተቋማዊ እንቅስቃሴ በሕግና በሥርዓት መመራት አለበት፡፡ አንድ ግለሰብ በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ኃላፊነቱ ደስተኝነት ሳይሰማው ሲቀር፣ ሕጉና ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት የኃላፊነት ጠገጎችን ተከትሎ ቅሬታውን በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ቅሬታ የሚቀርብለት አካልም ሕጉን ተንተርሶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚኖሩ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች የፓርቲንም ሆነ የመንግሥትን ሥራ የሚበድሉ ሲሆኑ፣ በሰላምና በጨዋነት መከናወን ያለባቸውን ግንኙነቶች ይረብሻሉ፡፡ ልዩነቶች ሲፈጠሩ ወደ መነጋገሪያው ጠረጴዛ መሄድ ሲገባ ለጭቅጭቅና ለጠብ የሚጋብዙ ድርጊቶች ላይ ማተኮር፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጥፋቱ የገዘፈ እንደሆነ በተደጋጋሚ የታየ ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካው መስክ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ጥፋት በጣም እየገዘፈ ነው፡፡

ይህንን ችግር በተመለከተ በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በእጅጉ ሊያጤኑት የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ የገዥውም ሆነ የሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች ውስጣዊ ጥንካሬ ሊገኝ የሚችለው፣ በፓርቲዎቻቸው ውስጥ አስተማማኝ የዴሞክራሲ ባህል ሲኖር ነው፡፡ አባላትና ደጋፊዎች የፓርቲውን ፕሮግራምና ውስጠ ደንብ በሚገባ ሲያውቁ፣ ፓርቲው የቆመለትን ማኅበረሰብ ፍላጎትና ዓላማ ሲረዱና ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድን ሲለማመዱ ለተመሪነት ብቻ ሳይሆን ለመሪነትም ራሳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡ በጥቅም የተቧደኑ አመራሮችና አጃቢዎቻቸው የፓርቲውን መርህ መጣስ ሲጀምሩ፣ በሕግና በሥርዓት በማስቆም ፈር ማስያዝ ይችላሉ፡፡ ከስሜት ይልቅ ለምክንያት ስለሚያደሉ እንደ ወራጅ ውኃ በተቀደደላቸው ቦይ አይፈሱም፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም እያንዳንዱ አመራርና ሠራተኛ በሕግና በሥርዓት ሲመራ፣ ለብልሹ አሠራሮችና ለሕገወጥነት የሚያመቻቹ ድርጊቶች ይመክናሉ፡፡ ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ ሕግና ሥርዓት የሚጥሱና ተቋማትን የዝርፊያ ማዕድ ለማድረግ የሚከጅሉ አይሳካላቸውም፡፡ ሕግና ሥርዓት ሳይከበር ሲቀር ግን ፓርቲዎችም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት የሥርዓተ አልበኞች መቀለጃ እንደሚሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

በመንግሥታዊ አሠራር ውስጥም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጣዊ መስተጋብር ተገማችነት ቀላሉ መገለጫ ሆኗል፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍም ሆነ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ሲዘጋጅ፣ ቀጣዩ ድርጊቱ ምን ሊሆን እንደሚችል በቀላሉ ከታወቀ ልክ አይሆንም፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ቢሆንም፣ አንዳንድ ሚስጥራዊ ጉዳዮች ግን አደባባይ ላይ መሰጣት የለባቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ሥርዓት ባለው መንገድ መከናወን የሚገባቸውና ኃላፊነት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተግባራት በቀላሉ ተገማች ሲሆኑ፣ ለመንግሥት አሠራር ብልሹነት ማሳያ ይሆናሉ፡፡ ብልሹነት የሚኖረው ደግሞ በሕግና በሥርዓት መመራት ቀርቶ የዘፈቀደ ዕርምጃ ሲለመድ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ከሕግ ጋር የሚጣረስ ልማድ እየተበራከተ የመንግሥት ዕርምጃዎች በቀላሉ ተገማች ሲሆኑ፣ ዜጎች በሕግ የበላይነት ሳይሆን በጉልበት እንደሚገዙ ይሰማቸዋል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም ጥቂቶች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት አሠራር ሲንሰራፋ፣ በፓርቲ አባላት መካከል ቅራኔ እየተፈጠረ ሚስጥራዊ መረጃዎች ስለሚያፈተልኩ ፓርቲው በቀላሉ ተገማች ይሆናል፡፡ በሕግና በሥርዓት መምራትና መመራት ሲኖር ግን ጥብቅ ዲሲፕሊን ስለሚኖር ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ አይሆኑም፡፡

በተደጋጋሚ ስለግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት መርህ ሲነሳ በመንግሥትም ሆነ በፓርቲዎች መዋቅሮች ውስጥ ያሉ ሰዎች ግድ አይሰጣቸውም፡፡ የፖለቲካ ባህሉ ምክንያታዊነትንና ሞጋችነትን ስለማያበረታታ ይህ መርህ ስሙ እንዳይነሳ የሚፈልጉ በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህ መርህ ከበሬታ የሚሰጡ ጥቂቶች ቢኖሩም ሰሚ ስለሌላቸው ተስፋ እየቆረጡ፣ በየቦታው ሥርዓተ አልበኝነት እየሰፈነ በርካታ ፓርቲዎች ፈርሰዋል፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት መዋቅሮች ብቃት አልባና ደካማ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በገዥው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ‹ተመልከት ዓላማህን› ከማለት ይልቅ ‹ተከተል አለቃህን› የሚሉ በመብዛታቸው፣ ለሕግና ለሥርዓት መከበር የሚሰጠው ቦታ በጣም አናሳ እየሆነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በየቦታው አድርባይነት፣ አስመሳይነት፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ስም ማጥፋት፣ የእርስ በርስ መተማመን መጥፋት፣ ጥርጣሬን መዝራት፣ ጥላቻ ማራገብና ዘለፋ ተለምደዋል፡፡ የችግሩ መነሻ የሆነው መሠረታዊ ጉዳይ ቀርቶ ግለሰቦች ላይ በማተኮር ለማንኮታኮት የሚደረገው ርብርብ ለመልካም ተግባር ሲሆን አይገኝም፡፡ በዚህም ምክንያት በፓርቲዎችም ሆነ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ መጠማመድ በርክቷል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ለማስገንዘብ እንደተሞከረው መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቅቱን የሚዋጅ አቅምና አስተውሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የመንግሥት ሥራ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ብቻ ሲከናወን ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳ መፍትሔ አይጠፋም፡፡ ስህተት ሲፈጠርም ለማረም አያዳግትም፡፡ ከሕግና ከሥርዓት ማፈንገጥ ሲጀመር ግን ብዙ ነገሮች ይበላሻሉ፡፡ የመጀመሪያው ዋነኛ ችግር ሕዝብ በመንግሥት ላይ ሊኖረው የሚገባ መተማመን ይጠፋል፡፡ ሕዝብና መንግሥት በመሀላቸው ሊኖር የሚገባው መተማመን ሲጠፋ፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ካለመቻሉም በላይ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ሽንቁሩን የበለጠ ያሰፉታል፡፡ በሒደትም ሕገወጦች የበላይነት እየያዙ ሕዝብ መሠረታዊ መብቶቹ ይጣሳሉ፣ ፍትሕ ይነፈጋል፣ መልካም አስተዳደር አይታሰብም፣ እንዲሁም ሙስና መደበኛ ሥራ ይሆናል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም የእርስ በርስ መከፋፈል የሚፈጠር ሲሆን፣ ሕዝብ ፊት ቀርቦ ተመራጭ ሊያደርግ የሚያስችል ቁመና ስለማይኖር ከባድ ፈተና ያጋጥማል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የታየና አሁንም በስፋት የቀጠለ ነው፡፡ ስለዚህ ውስጥን ማፅዳት ካልተቻለ አዙሪቱ ይቀጥላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...