Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ውዝግብ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹አስገዳጅ ትዕዛዝ›› እንዲሰጥ ተጠየቀ

በአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ውዝግብ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹አስገዳጅ ትዕዛዝ›› እንዲሰጥ ተጠየቀ

ቀን:

የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የወላጆችና የመምህራን ኅብረት፣ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር የተደረገው ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን ‹‹አስገዳጅ ትዕዛዝ›› እንዲሰጥለት ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቀረበ፡፡

በኅብረቱ ሰብሳቢ ፍፁም ዳግማዊ (ዶ/ር) ተፈርሞ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል ሥራ አስፈጻሚ በተላከው ደብዳቤ፣ ተማሪዎች የመጀመሪያውን ተርም ያለ ምንም መጽሐፍ አቅርቦት ማሳለፋቸውን፣ በኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ደረጃ አለመማራቸውን፣ በቂ መምህራን ሳይሟሉ በመማር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ‹‹በከፍተኛ ሁኔታ›› የተስተጓጎለው የመማር ማስተማር ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ኅብረቱ ይህንን ጥያቄ ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ለተወሰኑ ቀናት የመማር ማስተማር ሒደት በመስተጓጎሉ ነው፡፡ የመምህራን የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ አለመመለስና በወላጆች ላይ የተደረገ የክፍያ ጭማሪም ሌላው የችግሩ መነሻ መሆኑ በደብዳቤው ተገልጿል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በ2015 ዓ.ም. ማገባደጃና በ2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ከመምህራን ተወካዮችና የወላጅ ኮሚቴ ጋር በተካሄዱ ውይይቶች ትምህርት ቤቱ ለአስማተሪዎች ደመወዝ የሚጨምር ከሆነ ወላጆች ክፍያ ለመጨመር ተስማምተው እንደነበር ተገልጿል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ትምህርት ቤቱ በወላጆች ላይ የ75 በመቶ የክፍያ ጭማሪ በማድረግ፣ የመምህራንን ደመወዝ ደግሞ ከ60 እስከ መቶ በመቶ በሚደርስ ምጣኔ ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቅ ነበር ተብሏል፡፡

የወላጆችና የመምህራን ኮሚቴዎች ከትምህርት ቤቱ ጋር ከተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች መረዳት እንደተቻለው፣ ለመምህራን የተገባው የደመወዝ ጭማሪ ቃል ባለመከበሩ መምህራን ተቃውሞ ማሰማታቸውና ትምህርት መቋረጡ ታውቋል፡፡

ትምህርት ቤቱ የተስማማበትን የመምህራን ደመወዝ ጭማሪ ባለመተግበሩ ቃል የተገባውንና የኑሮ ውድነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጭማሪ መጠኑን ከ75 እስከ መቶ በመቶ እንዲያደርግ፣ መምህራን እንደገና መጠየቃቸውን ሪፖርተር የደረሰው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

መምህራን በተለያዩ ጊዜያት በደብዳቤ ጥያቄ በማቅረባቸው፣ የትምህርት ሚኒስቴር ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁን የወላጆችና የመምህራን ኅብረት አባላት ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ የመማሪያ መጻሕፍትና የመምህራን መመርያ እንዲያቀርብ ጥያቄ መቅረቡን አክለዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ መምህራንና ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት ስብሰባ በማድረግ መፍትሔ ለመጠየቅና የሠራተኛ ማኅበር ለመመሥረት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ ለመምህራን ተወካይነት የተመረጡ አራት መምህራንና አንድ የላይብረሪ ሠራተኛ ከሥራ መሰናበታቸውን የኅብረቱ አባላት አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት ታኅሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ መምህራን ተቃውሞ አሰምተዋል። የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ አባላት የመማር ማስተማር ሒደቱ ወላጆች በሚፈልጉትና ቃል በተገባላቸው መሠረት መተግበር ባለመቻሉ፣ የመምህራንና የተማሪዎች መጻሕፍት አቅርቦት በተባለው ጊዜ ባለመቅረቡና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት አጠቃላይ የወላጆች ስብሰባ ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ማድረጋቸውን አባላቱ ተናግረዋል፡፡

 በስብሰባው የተገኙ 232 ወላጆች በ2016 ዓ.ም. በትምህርት ቤቱ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍና መፍትሔ  ለመፈለግ ይወክሉናል በማለት በፊርማቸው አረጋግጠው ከመረጧቸው ወላጆች ጋር በመሆን፣ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር ለመነጋገርና ለችግሮች ዕልባት ለመስጠት ሙከራ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ኅዳር 16 ቀን በጠቅላላ ጉባዔ ከተመረጡ ወላጆች ጋር በመሆን ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ከስብሰባው ስድስት ሰዓታት ቀደም ብሎ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር በደረሳቸው የስልክ ጥሪ መሠረት በወላጆች ከተመረጡ የኮሚቴ አባላት ጋር ለመነጋገር እንደማይቻል እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ለትምህርት ቤቱ ባለአክሲዮንና የአንድነት የትምህርትና ሥልጠና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ሳባ አንሳሮ (ኢንጂነር) ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሲሆን፣ የተነሱት ችግሮች መኖራቸውን አምነዋል፡፡

‹‹የመመህራን የደመወዝ ጥያቄ በትምህርት ቤቱ በኩል ምላሽ አግኝቷል፡፡ ዘንድሮ በመስከረም ወር የመጀመሪያ ዙር የደመወዝ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት ለሁሉም ሠራተኞች የሁለት ሺሕ ብር ጭማሪ አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት አምስት ሠራተኞች ከሥራ የተሰናበቱት በደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ሳይሆን፣ በሥነ ምግባር ምክንያት ነው ሲሉ ሳባ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

የወላጆች የመጻሕፍት አቅርቦት ጥያቄ ትክክል መሆኑን ገልጸው፣ በአጠቃላይ በሃርድ ኮፒ የመጻሕፍት ዋጋ 80 ሚሊዮን ብር በመድረሱ፣ በኦንላይን በክፍያ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ተማሪዎች ሳይስተጓጎሉና መምህራንን በማሟላት የመማር ማስተማር ሒደቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...