Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ አገሮች ለውጭ ብድር የሚከፍሉት ዕዳ እንደሚጨምር ዓለም ባንክ ተነበየ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓለም አቀፉን የአገሮች የውጭ ብድር ዕዳ ዓመታዊ ሪፖርት (International Dept Report) ዓርብ ታኅሳስ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው የዓለም ባንክ (WB) ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ አገሮች ለውጭ ብድር ዕዳ ማቅለያ የሚከፍሉት ገንዘብ እየጨመረ እንደሚሄድ ገለጸ፡፡ ወደ 122 አገሮች የተበደሩትን 3,000 አዳዲስ ብድሮችን ጨምሮ ከ45 ሺሕ ያላነሱ የብድር ዓይነቶችን የገመገመው ሪፖርቱ፣ ዕዳ አከፋፈላቸው እየጨመረ እንደሚሄድ ግምቱን አስቀምጧል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ አገሮች ለውጭ ብድር የሚከፍሉት ዕዳ እንደሚጨምር ዓለም ባንክ ተነበየ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

እ.ኤ.አ. በ2022 ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ‹‹ለውጭ ብድር ማቃለያ 443.5 ቢሊዮን ዶላር ከፍለዋል›› ይላል የዓለም ባንክ ሪፖርት፡፡ ዕዳው እያደገ እንደሚሄድና ከአሥር እስከ 40 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ አስታውቋል፡፡ በዓመቱ በአጠቃላይ የዓለም ዕዳ ቁልል 23.6 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ ታይቶበታል የሚለው ሪፖርቱ፣ እየጨመረ የመጣውን ዓለም አቀፍ የዕዳ ጫና ለማቃለል፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ አገሮች ከውጭ ንግድ የሚያገኙትን ከፍተኛ ገንዘብ መልሰው ያወጣሉ ይላል፡፡

ባለፈው አሥር ዓመታት የዓለም ተበዳሪ አገሮች የዕዳ ጫና ተከታታይ በሆነ ሁኔታ መጨመሩን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ የተጠራቀመ የውጭ ብድር ዕዳም 28.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ያትታል፡፡

ከዚህ ውስጥ የዓለም ባንክ ዕዳ 41 በመቶ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ስምንት በመቶ፣ የግል አበዳሪዎች 19 በመቶ እንዲሁም ቻይና 20 በመቶ የአበዳሪነት ድርሻ እንዳላቸው ነው የገለጸው፡፡ የኢትዮጵያ ብድር እ.ኤ.አ. በ2010 ከነበረበት 7.2 ቢሊዮን ዶላር ዛሬ ላይ እጅግ ከፍተኛ ጫና ወደሚፈጥር ዕድገት መሸጋገሩንም በአኃዝ ያስቀምጣል፡፡

በተያያዘ ዜና የአገሮችን የብድር መክፈል አቅም የሚመዝነው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ገምጋሚ ድርጅት ፊች (Finch) የኢትዮጵያን ዕዳ የመክፈል ቁመና ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡

የአገሪቱን ዕዳ የመክፈል አቅም ከ‘CC’ ደረጃ ወደ ‘C’ ደረጃ ያወረደው ድርጅቱ፣ በዚህ ረገድ እየተዳከመች መምጣቷን አመልክቷል፡፡ የዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ኢንቨስተሮችና የገንዘብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የሚኖራቸው መተማመን እንደ ፊች ያሉ ድርጅቶች ከሚያወጡት የግምገማ ሪፖርት ጋር በቀጥታ ሊያያዝ እንደሚችል ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ ኢትዮጵያ የዛሬ አሥር ዓመት የተበደረችውን አንድ ቢሊዮን ዩሮ ቦንድ ዓለም አቀፍ ብድር አከፋፈል በሚመለከት ከአበዳሪዎች ጋር ከስምምነት መድረስ እንዳቃታት በሰፊው ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡ ሰኞ ታኅሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀነ ገደቡ ያበቃው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮ ቦንድ ብድር፣ 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ መውለዱ ተነግሯል፡፡ ዕዳውን አገሪቱ የምታቀልበት ተጨማሪ የ14 ቀናት የዕፎይታ ጊዜ እንዳላት ቢነገርም፣ አገሪቱ ግን በአከፋፈሉ ላይ ከአበዳሪዎች ጋር ለመግባባት እንደተቸገረች ሲነገር ቆይቷል፡፡

ይህን በሚመለከት የምላሽ መግለጫ የሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ያለበትን ዓለም አቀፍ የብድር ዕዳ ለማቃለል በሁሉም መንገድ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ብድር ዕዳ ዓይነት አለያይታ እንደማታይና ሁሉንም የመክፈል ግዴታዋን በአግባቡ እንደምትወጣ ለአበዳሪዎቹ ቃል ገብቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች