Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማስታወቂያ ሰሌዳዎች በዲጂታል ስክሪኖች ሲተኩ የአፈጻጸም ችግር ማጋጠሙ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስታወቂያዎችን ለማዘመን የቢልቦርድ ማስታወቂያዎች ተነስተው በዲጂታል ስክሪን እንዲተኩ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ፣ የአፈጻጸም ችግር ማጋጠሙን፣ የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሥራ ማኅበር አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ ይህንን የገለጸው ታኀሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ሲሆን፣ በውይይት መድረኩ ላይ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት የተወከሉ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡

የቢልቦርድ ማስታወቂያዎችን በማስቀረት በዲጂታል ስክሪኖች ይተኩ በመባል ከከተማ አስተዳደሩ የወረደውን አቅጣጫ በመቀበል ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት የማስታወቂያ ድርጅቶቹ፣ በአሁኑ ወቅት ያሉትን የቢልቦርድ መስቀያ ብረቶችንና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የማንሳት ሒደት የአፈጻጸም ችግር ያለበት ነው ተብሎ በመድረኩ በስፋት ተገልጿል፡፡

ማስታወቂያዎችን የማዘመን ሐሳብ እንደሚደግፍና ለከተማዋ ውበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን፣ ነገር ግን የዲጂታል ማስታወቂያ ብቻ ማድረጉ በርካታ ወጣቶችን ሥራ አጥ ሊያደርግ እንደሚችል በማስታወቂያ ሥራ ለ22 ዓመታት የቆዩት የኤርሚያስ አድቨርታይዚንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ መንግሥቴ ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ማስታወቂያ በአገሪቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ከአንድ ዓመት በፊት በወጣ ማኑዋል መሠረት መሆኑን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ከዓመታት በኋላ በአንድ አቅጣጫ በፍጥነት ወደ ማፍረስ መግባት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ፈቃድ የመስጠትና ቁጥጥር እንዲያደርግ ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ከወረዳዎችና ከክፍላተ ከተሞች ጋር በመሆን የሚያዋቅረው የአፍራሽ ግብረ ኃይል በሕገወጥ መንገድ ነው የሚያፈርሰው ብለዋል፡፡

አፍራሽ ግብረ ኃይል የተባሉት የማፍረስ ሥራውን ሲያከናውኑ ጎን ለጎን ዘረፋ በማካሄድና የድርጅቶቹን ንብረት ከወሰዱ በኋላ፣ ለመመለስ እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ ተጨማሪ ክፍያ ያስከፍላሉ ብለዋል፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ 25 የማስታወቂያ ድርጅቶች በአጠቃላይ ከሁለት ሺሕ በላይ ሠራተኞች መያዛቸው ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

በከተማዋ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እስከ 50 ሺሕ ዶላር ድረስ በማስፈለጉና የስክሪኑ የዋጋ ውድነት፣ ከዕይታ አንፃር የጤና ችግር ሊያስከትል መቻሉ፣ እንዲሁም የስክሪኑ ጥበቃና ደኅንነት ጉዳይ  በተለያዩ የማስታወቂያ ድርጅቶች በኩል እንደ ሥጋት የተገለጹ ሐሳቦች ናቸው።

የከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ የሰጠው ከተማዋ በማስታወቂያዎች ምክንያት ውበቷ እየተበላሸ በመምጣቱ ውበቷን ለመጠበቅ ነው ሲሉ፣ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የከተማ ውበት ልማትና ክትትል ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ከበደ ተናግረዋል፡፡

‹‹አብዛኞቹ የማስታወቂያ ድርጅቶች የቢልቦርድ ማስታወቂያ ከሰቀሉ በኋላ ጊዜው ሲያበቃ ወቅቱን ጠብቆ ማንሳት፣ ውበቱን በአዳዲስ ዲዛይን የመቀየርና ብረቶቹን ቀለም ሲቀቡ አልነበሩም፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በተያዘው ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 142 ሺሕ ሕገወጥ የተለጠፉ ወረቀቶች፣ የተቀደዱ ባነሮችና የተበላሹ ብረቶችን መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ከማስታወቂያ ድርጅቶቹ ጋር በጋራ እንደሚሠራና በቀጣይ ውይይቶች የማዘጋጀት ዕቅድ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ ከተመሠረተ አራት ዓመታትን ማስቆጠሩን፣ በማስታወቂያ ዘርፍ የተሰማሩ የተለያዩ ባለሙያዎች አባላቱ እንደሆኑና ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደተመሠረተ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች