Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በትግራይ ክልል የፋይናንስ ተቋማት ለተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች በተሰጡ ብድሮች ላይ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ብድሩ ከእነወለዱ 60 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተነግሯል

በትግራይ ክልል የፋይናንስ ተቋማት ለተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የሰጡት ብድር ከእነወለዱ ወደ 60 ቢሊዮን ብር እየተጠጋ መሆኑና ብድሩን ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ተገለጸ፡፡

በትግራይ ክልል በወቅታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይና ከባንክ ብድር ጋር በተያያዘ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ በጦርነቱ ምክንያት የባንክ አገልግሎት እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ለክልሉ ተበዳሪዎች ባንኮችና ማክሮ ፋይናንሶች የሰጡት ብድር 31 ቢሊዮን ብር እንደነበር አንድ ጥናት አመላክቷል፡፡ በትግራይ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በሌሎች ተባባሪ አካላት ድጋፍ በተዘጋጀው መድረክ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያቀረቡት አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር) ባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለክልሉ ተበዳሪዎች የሰጡት ከ14 እስከ 19 በመቶ የወለድ ምጣኔ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ግን 18 በመቶ ወለድ ምጣኔ የተበደሩ ናቸው፡፡

ብድሩ በጦርነቱ ወቅት ሊከፈል ያልቻለ በመሆኑና ባለፉት አምስት ዓመታት ወለዱ እየጨመረ መጥቶ፣ አሁን ላይ አጠቃላይ ዕዳው ወደ 60 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ አሁን ባለው የትግራይ ክልል አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር ይህንን ብድር ለመክፈል የማይቻል መሆኑን ለጥናታቸው ካነጋገሯቸው በተለያዩ ቢዝነሶች ላይ ያሉ ተበዳሪዎች መገንዘብ መቸላቸውን ጠቅሰዋል፡፡  

ጥናት አቅራቢው ከኅብረተሰቡ ማሰባሰብ በቻሉት መረጃ፣ በትግራይ ክልል ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አይደለም ይህንን ብድር ለመክፈል ይቅርና የቢዝነስ ተቋማቱን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው፣ የብድሩን ጫና ለመቀነስ ጉዳዩ በተለየ መንገድ ሊፈታ ካልቻለ አበዳሪዎችም ሆኑ ተበዳሪዎች በእጀጉ እንደሚጎዱ ጠቁመዋል፡፡  

አሁን ባለው ሁኔታ ብድር የሰጡት ባንኮች ለበተዳሪዎች መፍትሔ ሊያመጡ ያልቻሉ ከመሆናቸውም በላይ፣ አበዳሪ ባንኮች ዕዳቸው እንዲከፈላቸው ጥቄያቸውን እየገፉ መምጣቱ፣ ተበዳሪዎችን ጭንቅ ውስጥ እንደከተተም ማሳያዎችን በማጣቀስ አስረድተዋል፡፡ ስለዚህ ከባንኮችና ከተበዳሪዎች በላይ ስለመሆኑ በግልጽ እየታየ ስለሆነ፣ መንግሥት ጉዳዩን በትኩረት ዓይቶ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተበዳሪዎች እየጠየቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡  

የትግራይ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው፣ ክልሉ ያለበትን ይህንን ችግር ለማቃለል በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተወሰኑ የሐሳብ ድጋፎች ቢታዩም፣ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጡ አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ትግራይ ወድማለች፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችም ዜሮ ሆነዋል›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ እየገፋ የመጣው የባንኮች ‹‹ብድሩን ክፈሉ›› የሚለው ጥያቄ የክልሉን የንግድ ኅብረተሰብ ሌላ ችግር ውስጥ እንደከተተው ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩ መፍትሔ ካልተበጀለትና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ድጋፍ የማያደርጉ ከሆነ አደጋው ከባድ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በተለይም ክልሉ በተደረገው ጦርነት ከባንኮች መዘጋት ጀምሮ በሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስላልነበረ፣ ከዚያም በኋላ ቢዝነሱን ለማስቀጠል ቢታሰብ እንኳን ብዙዎቹ በመውደማቸው፣ እንዲሁም ተጠጋግነው ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉትን ለማስቀጠል አቅም መጥፋቱ፣ ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ዜሮ በሚባል ደረጃ መውረዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ክልል ሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከባንክ ብድር ጋር የተያያዙ በመሆኑ፣ በባንክ ብድር በክልሉ የተገነቡ ኢንቨስትመንቶች መዘረፋቸውንና መውደማቸው የባንክ ብድር ለመመለስ ካለማስቻሉም በላይ ጉዳዩ የሕልውና ጉዳይ ሆኗልም ይላሉ፡፡

ምንም ባልተሠራበትና በወደመ ንብረት ባንኮች ብድሩን ከእነወለዱ አምጡ ሲባል ደግሞ ከየት መጥቶ ሊከፈል እንደሚችል ግራ የሚያጋባ ስለሚሆን፣ መንግሥት ፖለቲካዊ ዕርምጃ በመውሰድ ለችግሩ መቋጫ እንዲያበጅም ጠይቀዋል፡፡

ጥናት አቅራቢው በበኩላቸው በተለይ ብድር ተበድረው ንብረታቸው የወደመባቸው ተበዳሪዎች፣ ብድሩ ይነሳልን ማለታቸውን ጠቅሰው፣ ካነጋገሯቸው 80 በመቶ የሚሆኑ ተበደሪዎች፣ ‹‹ብድሩን ስላልሠራንበት ወለዱን ልንከፍል አይገባም›› ማለታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ዋናውን ብድርም ለመክፈልም ቢሆን የአብዛኛዎቹ ቢዝነሶ ስለቆሙ፣ ብድሩን ለመክፈል የማይችሉ መሆናቸውን እንደገለጹላቸው ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ተበዳሪዎች ደግሞ እንደመፍትሔ ያቀረቡት አዳዲስና ራሱን የቻለ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ፣ በተለየ መንገድ የሚስተናገዱበት አሠራር ካልተፈጠረ፣ ብድሩን መክፈል እንደሚቸገሩ እንደነገሯቸው አታክልቲ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡  

የተበዳሪዎችን ሐሳብ በመያዝ የክልሉ ፕሬዚዳንትና የክልሉ ንግድ ምክር ቤት በደብዳቤ ጭምር የፌዴራል መንግሥትን የጠየቁ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ አታክልቲ፣ በጉዳዩ ላይ ንግግር ቢደረግም መፍትሔ ሊሰጥ ባለመቻሉ ሁኔታውን አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ በተለያዩ ደረጃዎች ላሉ ብድሮች መፍትሔ ካልተበጀ፣ ባንኮቹም ገንዘባቸውን ለማግኘት የሚችሉበት ዕድል የሌለ ከመሆኑም በላይ ኢኮኖሚውን ይጎዳል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ጫና ከማጠቃለል አንፃር በተለይ ለክልሉ ተበዳሪዎች የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ያስተላለፈው ውሳኔም፣ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አለመቻሉን ጥናት አቅራቢው አመልክተዋል፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው በበኩላቸው፣  የትኛውም ዓይነት የፖሊሲ ውሳኔ ሲወሰድ፣ ፖሊሲ ወሳጁ አካል ሊወስድ የሚችለው የፖሊሲ ዕርምጃ፣ በሕግ ከተሰጠው ማንዴት ጋር የተያዘውን ብቻ በመሆኑ ከዚህ ውጪ ማድረግ ሕጋዊ እንደማይሆን ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በሕግ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር ማድረግ ያለበትን ሁሉ ሲያደርግ መቆየቱንና በባንኩ የኃላፊነት ደረጃ ላሉ ጉዳዮች ዕርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ተዘግተው የነበሩ 560 የሚደርሱ ቅርጫፎቹን መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ከማድረግ ጀምሮ፣ ክልከላ የተደረገባቸውን አሠራሮች ሁሉ በማሻሻል ባንክ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የጥሬ ገንዘብ ችግርን ለመቅረፍም ከፍተኛ የሚባል ገንዘብ ወደ ክልሉ መላኩንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በክልሉ የተበዳሪዎች የብድር መክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉንም የገለጹት አቶ ፍሬዘር፣ ጦርነቱ በትግራይና በአፋር ክልል የተደረገ ቢሆንም፣ በትግራይ ክልል ለረዥም ጊዜ የቆየ፣ የጉዳቱ መጠንም በዚያው ልክ አስከፊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፣ በብሔራዊ ባንክ በኩል የተወሰዱ ዕርምጃዎች ስለመኖራቸውም አብራርተዋል፡፡ በተለይ በጦርነቱ ምክንያት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው መስተጓጎል የገጠማቸውና ከዚህ በፊት እንደ ቢዝነስ ያገኙት የነበረው ገቢ የተቋረጠባቸው፣ በዚህ ምክንያት የወሰዱትን የባንክ ብድር መመለስ ያልቻሉትን ተገቢው ዕርዳታ ተደርጎላቸው ብድሩ አገግሞ ወደ መስመር መግባት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ሁሉ መደረጉንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ በጦርነቱ ምክንያት ተጨማሪ ብድር ባንኮች መስጠት የሚችሉ ስለመሆኑ ሁሉ ለባንኮች ተገልጾላቸው እንዲሠሩበት ተደርጓል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት አንድ ብድር እየተራዘመ ሊቀጥል የሚችለው እስከ ስድስት ጊዜ ብቻ ቢሆንም፣ በዚህ ጦርነት ምክንያት ከዚህ በፊት በብድራቸው የተራዘመላቸው ካሉ ተጨማሪ ዕድል እንዲሰጣቸው ተደርጓል በማለት ባንኩ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት የሄደበትን ርቀት አመላክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አንድ ተበዳሪ የተበላሸ ብድር ውስጥ የገባ ተበዳሪ ሌላ ተጨማሪ ብድር ከሌላ ባንክ ማግኘት ባይችልም፣ ለትግራይ ክልል ተዳሪዎች ይህንን የብሔራዊ ባንክ አሠራር ተፈጻሚ እንዳይሆን አድርጓል፡፡ ይህም በጦርነቱ ምክንያት ብድሩ ችግር ውስጥ ለገባበት ተበዳሪ እንዳይሠራ መደረጉም ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ዕገዛ ለማድረግ የተሄደበት መንገድ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁንም ተጨማሪ መፍትሔዎች የሚታዩ ስለመሆኑ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ለጉዳዩ እያንዳንዱ አስፈጻሚ ተቋማት የፖለቲካ መፍትሔ የሚፈልጉ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት መንግሥት ዝም ያላለ መሆኑን ለመጠቆም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አዲስ የመልሶ ግንባታ ኮሚቴ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ስለተቋቋመ፣ ይህ ኮሚቴ ሌሎች የልማት አጋሮችን በማካተት የበለጠ ይሠራል ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ በዕለቱ በተለያዩ መንገዶች የቀረቡ ጥያቄዎችን የሚመለከት ስለሆነ ጉዳዩ በዚህ መድረክ የመታየት ዕድል እንዳለው አመላክቷል፡፡ በዚህም ብሔራዊ ኮሚቴ ውስጥ ብሔራዊ ባንክ አባል በመሆኑ እሱን የሚመለከቱ ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጥበት ስለመሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

አቶ አሰፋ ግን ይህ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም ይላሉ፡፡ አሁንም መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ‹‹በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ተረድተው እርማቸውን አውጥተዋል፤›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ አሁን ደግሞ ዕዳ እንቅልፍ ነስቶናል በማለት በክልሉ ውስጥ ያለውን ችግር አመልክተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት መካከል አንዳንዶቹ ከሰጡት አስተያየት መረዳት እንደተቻለው፣ የባንክ ዕዳው መፍትሔ ይፈለግበት የሚባልበት አንዱ ምክንያት ለማስያዣት የተያዙ አንዳንድ ንብረቶች በመውደማቸው ነው፡፡ የወደመ ንብረትን ደግሞ ባንኮች በጨረታ ሊያወጡ አይችሉም፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ በክልሉ ውስት መያዣ የሆኑ ንረቶችን በጨረታ ለመሸጥ ቢሞክር ማን ይገዛዋ? የሚል ሥጋትም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ንብረቶች ሊገዛ የሚችል አቅም ያለውስ ማን ነው? በማለት ችግሩ ምን ያህል ውስብሰብ እንደሆነና መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ ይወስን የምንለው ለዚህ ነው ብለዋል፡፡    

ከጥናት አቅራቢው መረዳት እንደተቻለው ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል 4.3 ሚሊዮን የቁጠባ ደብተር አስቀማጮቾች ነበሩ፡፡ እነዚህ ቆጣቢዎች 70 ቢሊዮን ብር በባንኮች ውስጥ የነበራቸው ናቸው፡፡

የባንክ አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ ያገኙት ገንዘብ 70 ቢሊዮን ነው፡፡ አንድ ዶላር 31 ብር በሚመነዘርበት ወቅት ያስቀመጡት ገንዘብ ባንክ ሲከፈት የአንድ ዶላር ምንዛሪ 54 ብር ቢሆንም፣ አስቀማጮቹ ያገኙት ገንዘብ ምንም ለውጥ የሌለው መሆኑ ጉዳት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ገብረ ሕይወት አገዋ (ዶ/ር) የባንክ ዕዳው መፍትሔ ይፈለግልን ብለን የምንጠይቀው፣ ያሉ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት በመውደማቸው ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በእሳቸው እምነት ችግሩ የሚፈታው በመንግሥት ብቻ ነው፡፡ ለመንግሥት ይህ ዕዳ አይከብደውምና የክልሉን ኢኮኖሚ ለማስቀጠል ቀዳሚ መፍትሔውም ይህ ብቻ ነው፡፡ ችግሩ እስኪቃለል ድረስ በትግራይ ክልለ ላሉ ቢዝነሶች የታክስ ዕፎይታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ በበኩላቸው መፍትሔ ያሏቸውን የተለያዩ ሐሳቦች የጠቆሙ ሲሆን፣ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ የፖሊሲ ውሳኔ መወሰኑ ለእሱም ይጠቅመዋል ብለዋል፡፡

በጥናታቸው ላይ እንዳመለከቱት የትግራይ ክልል እስከ ጦርነቱ ድረስ ለአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚው የነበረው ድርሻ 8.3 በመቶ አካባቢ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ይህ ድርሻው የለም ወይም ወርዷል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ክልሉ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገቱ ሊኖረው የሚችለውን አስተዋጽኦ ለማስቀጠል እንደ ወርቅ ያሉ ምርቶችን ለብሔራዊ ባንክና ለማዕከላዊ ገበያው ለማቅረብ የዚህ የዕዳው ጉዳይ መፍትሔ ሊበጅት እንደሚገባ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ መፍትሔ ይፈለግ የሚባለው እንዲህ ያለው አገራዊ ጥቅም ጭምር ስላለው ብቻ ሳይሆን ተበዳሪዎቹንም ሆነ አበዳሪ ባንኮችን የሚጠቅም በመሆኑ ነው፡፡ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘ ከዚህ በኋላ የተወሰነ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ አንዳንድ ቢዝሶችን መልሶ ለማስቀጠል፣ ለምሳሌ የኢትዮጵያ በሔራዊ ባንክ ያወጣው የ14 በመቶ ገደብ በክልሉ ውስጥ ተፈጻሚ እንደይሆን ማድረግም ጠቀሜታ አለው ተብሏል፡፡ ከአታክልቲ (ዶ/ር) የዚህ መመርያ መነሳት አንዳንድ ባንኮች ብድር ለመስጠት እያሳዩ ያሉትን ፍላጎት እየገደበ መሆኑን በተጨባጭ የተመለከትነው በመሆኑ፣ መፍትሔው በብዙ አቅጣጫ መታየት እንደሚኖበት አመልከተዋል፡፡ በትግራይ ክልል በተካሄደው አስከፊ ጦርነት ያጋጠመው የኢኮኖሚ ውድመት መልሶ ለመገንባት ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይቶችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡

በዕለቱ የተካሄደውን መድረክ ያዘጋጁ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበር፣ የሰላም ሚኒስቴርና ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ (CIPE) የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ በአፋርና በአማራ ክልል ያለውን ተመሳሳይ ችግር ለማስጠናት መፍትሔ የሚገኝበት መንገድ ለማመቻቸት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች