Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተለያዩ ተፅዕኖዎች ውስጥ ሆኖ ሀብቱን 46 ቢሊዮን ብር ያደረሰው ቡና ባንክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት እየሰፋ መሄድ የውጭ ምንዛሪ አሰባሰብ ላይ እየፈጠረ ያለው ተፅዕኖ ዓመታዊ ገቢው ላይ ተፅዕኖ ቢያሳርፍም፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔውን በ14.5 በመቶ ማሳደጉን ቡና ባንክ ገለጸ፡፡

ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚሊዮን አዳራሽ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዓለማየሁ ሰውአገኝ (አምባሳደር) የቀረበው ሪፖርት ያስቀደመው ባለፉት ሦስት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች በባንክ ኢንዲስትሪው ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ በማመላከት ነበር፡፡

‹‹ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያጋጠሙ የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ፣ ከዓለም አቀፍ ጫና ጋር ተደምሮ ኢኮኖሚያችን በተፈለገው ፍጥነጥ እንዳያድግ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በተለይ ከውጭ ምንዛሪ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ እያጋጠመ ያለው ችግር በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት እየሰፋ መሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ምንም እንኳን መንግሥት ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ችግሩን ለመቀነስ ሙከራ እያደረገ ቢሆንም፣ በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጪ ምንዛሪ ተመን ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ፣ አጠቃላይ በውጭ ምንዛሪ አሰባሰብ ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ አሰባሰብ ላይ የተፈጠረው ክፍተት እንደ ባንክ ከግብ ዕቅዳቸው ቀላል የማይባል ድርሻ  በሚይዘው ከውጭ የሚላክ የሃዋላ እንቅስቃሴ ላይ ጫና በማሳረፍ የሚገለጽ ጭምር ስለመሆኑ ከቦርድ ሊቀመንበሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደዚህ ያሉ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ገቺ ምክንያቶች በባንክ ኢንዱስትሪው ጉዞ ላይ ተፅዕኖ ቢያሳርፍም ባንካቸው በሒሳብ ዓመቱ ጠንካራ ያሉትን ውድድር ጭምር ተቋቁሞ አትራፊነቱን ማስቀጠል እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

ከዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቱ መረዳት እንደተቻለው፣ ባንኩ ከታክስ በፊት 1.36 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ከታክስ በኋላ ያገኘው የትርፍ መጠን ደግሞ 949.2 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከታክስ በኋላ የተገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የ59 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያሳየ ነው፡፡ ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ ደግሞ በ172.4 ሚሊዮን ብር ወይም በ14.5 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በሌሎች የሒሳብ ዓመቱ አፈጻጸሞችን በተመለከተ፣ የቁጠባ ገንዘብ ከማሰባሰብ አንፃር ከቀዳሚው ዓመት የ34.6 በመቶ ዕድት በማሳየት 9.4 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ይህም አጠቃላይ የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 36.6 ቢሊዮን ብር ማድረስ አስችሎታል፡፡

ለባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት በሒሳብ ዓመቱ የአስቀማጭ ደንበኞቹ ቁጥርን በ55.6 በመቶ ከፍ በማድረግ 3.05 ሚሊዮን ማድረስ በመቻሉ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ በአንድ ዓመት ብቻ አዳዲስ 1.08 ሚሊዮን አስቀማጭ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻለም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በ2015 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ በ82 በመቶ ወይም 1.63 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡  

ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 735.1 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ከዚህ ባሻገር ከወለድ ነፃ አስቀማጮችን ቁጥር በ183,632 በመጨመር 295,541 ሺሕ ማድረስ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች 11.3 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠት አጠቃላይ የብድር ክምችቱን 34.8 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ይህም በቀዳሚው ዓመት ከሰጠው ብድር አንጻር ሲታይ የ34.5 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ 48.6 በመቶ የሚሆነው ለወጪና ገቢ ንግድ ዘርፍ መሆኑ ታውቋል፡፡

የተበላሸ የብድር መጠኑ ወይም የመክፈያ ጊዜ ያለፈባቸው ብድሮች ምጣኔውን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ በቀደመው ዓመት 4.1 በመቶ የነበረውን የተበላሸ ብድር ምጣኔ በ2015 መጨረሻ ላይ ወደ 3.48 በመቶ ማውረድ መቻሉን ነው፡፡

ባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔውን በዚህን ያህል ደረጃ ሊቀንስ ከቻለባቸው ምክንያች አንዱ ምክንያት፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪስክ ኤንድ ኮምፕሊያንስ ንዑስ ኮሚቴ ከሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ባሻገር፣ የባንኩ ማኔጅመንት ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀምሮ ሥራው እስከሚመለከታቸው የቅርንጫፍ ሠራተኞች ድረስ በቅንጅት መሥራት በመቻሉ እንደሆነ ዓለማየሁ (አምባሳደር) ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ገደብ የተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ በማውጣትና የብድር ማስመለስ ሒደቱን በመከታተል፣ እንዲሁም አፈጻጸሞችን በየጊዜው ገምግመው ማስተካከያዎችን በማድረግ፣ በየደረጃው ያደረጉት ጥብቅ ክትትል ለዚህ ውጤት መገኘት ተጠቃሽ እንደሆነም የቦርዱ ሊቀመንበሩ አክለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተም በ2015 የሒሳብ ዓመት 175.5 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም አኃዝ ካለፈው በጀት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ26.6 ሚሊዮን ዶላር ወይም በ17.8 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ቡና ባንክ ዓመታዊ ገቢውን በ47.6 በመቶ በማሳደግ 6.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን ወጪው ደግሞ በ5.28 ቢሊዮን ብር መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ቡና ባንክ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 46.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ የሀብት መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ12.3 ቢሊዮን ብር ወይም የ36 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነው፡፡

የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 4.28 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ962.2 ሚሊዮን ብር ወይም በ29 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ቡና ባንክ በመላ አገሪቱ ያሉትን ቅርንጫፎች 465 አድርሷል፡፡ ከእነዚህ ቅርንጫፎቹ ውስጥ 122ቱን ቅርንጫፎች የከፈተው በ2015 የሒሳብ ዓመት ነው፡፡ ባንኩ አጠቃላይ 4,100 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ከ13 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች