Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበተቋማቶቻችን ውስጥ የተንሰራፋው የወሬ ሰደድ እሳትና መፍትሔው

በተቋማቶቻችን ውስጥ የተንሰራፋው የወሬ ሰደድ እሳትና መፍትሔው

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

«ለወሬ የለው ፍሬ» ሲባል የምንሰማው ከድሮ ጀምሮ ስለሆነ አዲሳችን አይደለም። «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው» የሚለውን አባባል ከዚህ መብለጡን አልቆጠርነውም እንጂ፣ ከጥንት ጀምሮ የምናውቀው ነው። ወሬ ያልኖረበት ጊዜና የማይገኝበት ቦታ የለም። የቡና ላይ ወሬ… የመጠጥ ቤት ወሬ… የጫት ላይ ወሬ… የታክሲ ውስጥ ወሬ… የቤተሰብ ወሬ… የጓደኛች ወሬ… የሥራ ቦታ ወሬ… ጧት ወሬ… ምሽት ወሬ… በየቦታው መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ወሬ ሞልቷል፡፡ ወሬ የሚያዝናናውን ያህል ሌላ የሚያዝናና ነገር የሌለ እስኪመስል ድረስ ወሬ ሁለመናችን ውስጥ ዘልቆ ገብቷል፡፡

መቼም ምሁራን ሲባሉ የማይፈትሹት፣ የማይመረምሩትና ሳይንሳዊ ግንዛቤ እንዲኖረው የማይፈልጉት አንዳችም ክስተት የለም። የማያጠኑት ጉዳይ የላቸውም ለማለት ነው። ስለሁሉም ነገር ሁሉን አቀፍ ዕውቀት እንዲገኝ ይጥራሉ። እናም ፕሮፌሰር ኬይት ዴቪስ ስለወሬና ወሬኝነት በስፋት ማጥናታቸው ለዚህ ይመስለኛል። ወሬ ምንድነው? ወሬኝነትስ? ጥቅሙስ? ጉዳቱስ? መፍትሔውስ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የእኚህ ፕሮፌሰር ጥናት በማገናዘቢያነት ሳይጠቀስ አይታለፍም።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ወሬ በየትኛው ሥፍራ በማንኛውም ጊዜና ወቅት ነበር፣ አለ፣ ይኖራልም። የሰው ልጅ በማኅበረሰብ ደረጃ መሰባሰብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአደን፣ የእርሻ፣ የከብት ርቢ፣ ወዘተ አስመልክቶ ሳያወራ የኖረበት ጊዜ የለም። ወሬ የማኅበራዊ ክስተት ፈርጅ ነው። አፍ የተፈጠረው ለማውራት ቢሆንም፣ አንዳንዶቻችን ግን አፋችን ላይ እንደ መብራትና ውኃ ቆጣሪ ቢበጅልን ኖሮ ዕዳ በዕዳ ሆነን መስመራችን ይቋረጥብን ነበር። የምናወራው ብዙ ነው ማለት ነው።

እኛ እንደምናስበው ወሬ በአንዳንድ ወሬኞች የወሬ ሱስ የተነሳ ወይም ዝም ብሎ ከመሬት እንደ እንጉዳይ የሚፈላ ነገር አይደለም። ወሬ በሁሉም ዓይነት መሥሪያ ቤቶች በማንኛውም ዓይነት የኃላፊነት ደረጃ ላይ ባሉ ሰዎች መካከል ይኖራል። ሠራተኞች ያወራሉ፣ ካቦዎች ያወራሉ፣ ኃላፊዎች ያወራሉ… ሴቶች ያወራሉ… ወንዶች ያወራሉ… ትንሹም ትልቁም ያወራል። የዛሬ ነጥባችን ስለሁሉም ወሬና የወሬ ዓይነት ሳይሆን በመሥሪያ ቤት ውስጥ በሠራተኞች መካከል ያለውን የወሬ ዘርፍ ላይ ማውራት ነው።

በየመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ውስጥ ያለው የወሬ ዓይነት በተመራማሪዎች ቋንቋ «ግሬፕቫይን» የሚባለው ነው። እንደ ወይን ጠጅ የሚጥምና ሲዛመትም እንደ ወይን ሐረግ በየአቅጣጫው የሚስፋፋ ነው። ለሠራተኞች የወሬን ያህል የሚጥማቸውና የሚያስፈልጋቸው ነገር የለም። ይህንን ስለወሬ የብዙ ዓመታት ጥናት ያደረጉ የወሬን ጠቃሚና ጎጂ ጎን የመረመሩት ሊቃውንት አረጋግጠዋል።

ወሬ በወሬኛ ግለሰቦች ሊፈበረክ ቢችልም በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚመጣ፣ የመተናፈሻና ከጭንቀት የመገላገያ መንገድ ነው። ሠራተኞች ስለቅጥር፣ ስለዕድገት፣ ስለዝውውር፣ ስለቅጣት፣ ስለቅነሳ፣ ወዘተ ያወራሉ። ደመወዝ ሊጨመር ነው ይባላል፣ ሥራ አስኪያጁ ሊነሳ ነው ይባላል፣ እገሊት የእገሌ ውሽማ ናት ይባላል፣ ከሚስቱ ሌላ ዲቃላ ወልዷል ይባላል፣ ዕቃ ግዥው ሊታሰር ነው ይባላል፣ ሒሳብ ሹሙ ይኼን ያህል ገንዘብ አጉድሏል ይባላል፣ እገሌ የእገሌ ጆሮ ጠቢ (ዊኪሊክስ) ነው ይባላል፣ ሁሉም ነገር ይባላል፡፡ ‹‹ብለዋል››፣ «አሉ››፣ ‹‹ተባለ» እየተባለ ይባላል። ወሬ ተጠያቂ ወይም ኃላፊ የለውም። ምንጩ ከየት እንደሆነ ሳይታወቅ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ ከአብዛኛው ሠራተኛ ጆሮ ይደርሳል። በየመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ወሬ አነፍንፈው ለማግኘትና ለማንፈስ የተለየ ፍላጎትና ችሎታ ያላቸውና በዚህም የሚደሰቱ ሰዎች አሉ። «ሚስጥር» ናቸው የሚባሉ ጉዳዮችን አስቀድመው ለማግኘት ወይም ጫፍ ካገኙ እየቀጠፉ ለማቀጣጠል ሥራዬ ብለው ቆርጠው የሚነሱ ሰዎች አሉ። እነዚህን ወሬ አነፍናፊና አሠራጮች ምሁራኑ «ሩመር ሞንገር» ይሏቸዋል።

ለወሬ መናፈስ የመጀመርያው ምክንያት ሠራተኛው ስለሚሠራበት ድርጅት አሠራር በቂ መረጃ ኢንፎርሜሽን ለማግኘት አለመቻሉ ነው። በማንኛውም መሥሪያ ቤት መደበኛው የኢንፎርሜሽን ፍሰት በበላይ ኃላፊዎች መካከል የሚደረግና እዚያው ተወስኖ የሚቀር ነው፣ ግልጽነት የለም። ሠራተኛው የማኔጅመንቱን ሐሳብ የሚያገኝበት መደበኛና ሕጋዊ መንገድ የለም፡፡ ምን እየተሠራ እንደሆነ መረጃ አያገኝም፡፡

በግል ድርጅቶች ደረጃ በአሥር ዓመት ውስጥ አንድም ጊዜ ሠራተኞችን ሰብስቦ ያላነጋገረ ድርጅት አውቃለሁ። የድርጅቱ ሠራተኞች የሥራ መዘርዘር (Job Description) አልተሰጣቸውም፡፡ ምን መሥራት እንዳለባቸው፣ እንዴት መሥራት እንዳለባቸው፣ በምን እንደሚመዘኑና የሥራቸው መለኪያ ምን እንደሆነ የሚነግራቸው የለም።

አብዛኞቹ የድርጅቱ የአስተዳደር ማንዋል ምን እንደሚል አያውቁም፡፡ የሠራተኛ አዋጅ ስለመብትና ግዴታቸው የደነገገውን የሚያነብላቸውና የሚያሳውቃቸው የለም ማለት ይቻላል። ደመወዝ መቼ እንደሚጨመርላቸው፣ የደመወዝ ስኬሉ ምን እንደሚል አይነገራቸውም። ሠራተኞቻቸው ፊት ቀርበው በግልጽ መነጋገርና ለሠራተኞች ጥያቄ መልስ መስጠት የማይችሉ፣ ወይም የማይፈልጉ፣ ወይም የሚፈሩ ብዙ ኃላፊዎች አሉ።

አሠሪዎች ሳይሆኑ ባሪያ ፈንጋዮች መባል የሚገባቸው ሰዎች ሞልተዋል። አብዛኞቹ የግል ድርጅቶችና ተቋማት ሠራተኛውን በፍርኃት አሸማቀው የሚያሠሩ ናቸው። በማኅበር መደራጀትን አይወዱም። ለዚህ የሚንቀሳቀስ ሠራተኛ መኖሩን የወሬ ወሬ ከሰሙ አንገቱን ለመቅላት አይመለሱም። በወር አንድ ቀን ለግማሽ ሰዓት ያህል እንኳን የግምገማ መድረክ አይከፍቱም።

ሠራተኛው ስለድርጅቱ ምን እንደሚሰማው ፊት ለፊት ጠይቆ ወይም በአማካሪ አስጠንተው ማወቅ አይፈልጉም። የራሳቸው ጆሮ ጠቢ በሚያቀርብላቸው የአሉባልታ ወሬ ማስተዳደር ሳይሆን፣ መግዛት የሚፈልጉ ባለድርጅቶች እጅግ ብዙ ናቸው። «የት አባቱ ይሄዳል? ምን ያመጣል?» በሚል ዕብሪት በሠራተኞቻቸው ላይ የሚያላግጡ ለዚያውም የተማሩ ሰዎችን አውቃለሁ።

ይህ ሁኔታ ለወሬ ሰፊ በር ይከፍታል። ሠራተኛው ስለራሱ የወደፊት የሥራ ሁኔታ ሥጋት ያድርበታል፣ ይጨነቃል። የሥራ ዕድገት ለማግኘት ወይም ሌሎች የሥራ ጓደኞቹ ጭማሪ ሲደረግላቸው «እኔን ይረሱኝ ይሆን?» እያለ ያስባል። የደመወዝ ጭማሪ ቢደረግ እንኳን ጭማሪውን የሚያገኙት እነማን ሊሆኑ ይችላሉ እያለ የራሱን ደረጃ ለማወቅ በሐሳብ ራሱን ያስጨንቃል።

የቅነሳ ወሬ ከተነሳማ የቅነሳው ሰለባ የመሆን አለመሆኑ ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳዋል። ከዚያ ድርጅት ቢቀነስም ሆነ በሌላ ዘዴ ቢወጣ ሌላ ሥራ ማግኘት የሚችል አይመስለውም። የራሱን ሥራ ፈጥሮ መኖር የሚችል መስሎ አይታየውም። «እግዜር አለ» ማለትን እንኳ ይረሳል። ከሥራ መሰናበትን ከኑሮ አስከፊነትና ከቤተሰብ መፍረስ፣ በዚህም የተነሳ ከሰው በታች ከመሆንና ከዕርግማን ጋር ያያይዘዋል።

ስለዚህ ሌት ተቀን ጆሮውን ቀስሮ ወሬ ፍለጋ ይቅበዘበዛል። ወሬ ያገኛሉ የሚላቸውን ሰዎች እየጋበዘ ጭምር ወሬ ለማግኘት ይገደዳል። ቃለ ጉባዔ ያዥና የአለቃውን ጸሐፊ እየተግባባ ወሬ ይቃርማል። ሥራን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ አለቆቹ የሚያዙትን ለማወቅ ሁኔታዎች ስለማይፈቅዱለት የራሱን ግምት መነሻ አድርጎ ጭንቀቱን ይተነፍሳል።

«እጅግ በጣም ሚስጥር ነው… ለማንም እንዳትናገር…›› እያለ እንደ እሱ የተጨነቀ ሌላ ሠራተኛ ሹክ ይለዋል፡፡ እንደዚህ ተባለ፣ አሉ፣ ይባላል እየተባባሉ ወሬውን በየአቅጣጫው ይዘሩታል። የድርጅቱን ምድረ ግቢ በወሬ ያጥለቀልቁታል። እንደ ፕሮፌሰር ኬይት ዴቪስ ጥናት ወሬ የሚናፈሰው ተመሳሳይ ደረጃና ደመወዝ ባላቸው ሠራተኞች መካከልና አካሄዱም አግድማዊ (ሆሪዘንታል) ነው። የሠራተኞቹ ሥጋት በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ወሬያቸውም በዚያው መጠን የተለያየ ነው።

የተራ ሠራተኞች ቡድን ለብቻው የራሱን ሥጋት የተመለከቱ ወሬዎችን ያናፍሳል። በየደረጃው ያሉ አለቆች ቡድንም የየራሳቸውን ወሬ ያናፍሳሉ። አንዳንድ ደካማ ኃላፊዎች ከበታች ስላሉት ሠራተኞች ወሬ ፍለጋ ወንዱ በፈገግታ ሴቷን በመኝታ ለመቅረብ ይጣጣራሉ። የመሥሪያ ቤት ወሬ አንዳንዱ ጠቀሜታ አለው። ጎጂነቱም የዚያኑ ያህል ነው። ወሬ ሠራተኞች ያለባቸውን ሥጋትና ጭንቀት ተንፍሰው የሚገላገሉበት ቢሆንም፣ ወሬ ስለተወራ ሠራተኛው ከፍርኃት ነፃ ይሆናል ማለት ሳይሆን፣ የተወጠረ የጭንቀት ስሜቱን ለመቀነስና ለማርገብ እንደሚረዳው የሚያረጋግጡ ጥናቶች አሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ወሬ የሚቀባበሉ ሠራተኞች በጊዜያዊነትም ቢሆን እርስ በእርሳቸው የሚተማመኑ ተመሳሳይ ሥጋት ያለባቸው በመሆናቸው፣ ስለሥራቸው ለመነጋገር የወሬው መኖር ዕድል ስለሚሰጣቸው በሠራተኞች መካከል የመግባባትና የአንድነትን ስሚት የሚፈጥርና ድርጅታዊ ፍቅርን (ስፕሪት ዲከር) የሚያሳድግ ሊሆን እንደሚችልም የምሁራኑ ጥናት ያሳያል።

አንዳንድ ሰዎች ከአለቆቻቸው መሀል ከአንዱ ለመተኛት የሚገደዱበት ዋናው ምክንያት ለዝሙት ሳይሆን፣ ስለሥራ ሁኔታቸው ካለባቸው ጭንቀት ለመገላገልም ነው የሚሉ አሉ። በየትኛውም መሥሪያ ቤት ሁሉም ዓይነት ኢንፎርሜሽን በመደበኛውና በሕጋዊው የሥልጣን ደረጃና በደብዳቤ ብቻ ሊከናወን ስለማይችል፣ በተዘዋዋሪ መንገድ በወሬ አማካይነት እንዲናፈስ እየተደረገ መደበኛውን የግንኙነት መስመር በማገዝ እንደሚያጠናክርም ምሁራንና አጥኚዎች ያምኑበታል።

የወሬ ሌላው ገጽታ ፍጥነቱ ነው። የወሬ ነገር እንደ ሰደድ እሳት እርስ በርሱ እየተቀጣጠለ ከመቅፅበት አገር ለማዳረስ የሚችል ፍጥነት ያለው በመሆኑ፣ አንዳንድ ጉዳዮችን በደብዳቤ ለማስተላለፍ ሲባል የሚደርሰው የጊዜ መጓተት ለማስቀረት ይረዳል። በተጨማሪም መሥሪያ ቤቱ በትክክል ከተጠቀመበት የሠራተኛውን ስሜት ለመለካትና ለማወቅ ወሬ ሊያገለግለው ይችላል።

የወሬ ዋናው ጉዳት የተጣመመ ወይም የተዛባ ኢንፎርሜሽን የሚያስተላልፍ መሆኑ ነው። ወሬ መሠረተ ቢስ መረጃዎችን ይዞ በንፋስ ክንፍ እየበረረ ላገኘው ሰው ሁሉ ያደርሳል። ለምሳሌ የቅርብ አለቅየው ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ተጠርቶ ጥቂት ደቂዎች ያህል የቆየ እንደሆነ፣ ገና እሱ ከቢሮ ሳይወጣ መዓት ወሬዎች ተፈጥረው ይጠብቁታል። ዕድገት ሊሰጡት ነው፣ ማስጠንቀቂያ ሊሰጡት ነው፣ ስለእገሌና እገሌ ሊናገር ነው፣ ወዘተ የሚሉ ወሬዎች ምድረ ግቢውን አዳርሰው ሊያገኛቸው ይችላል።

ሁለተኛው ነገር ወሬ ማንንም የማያከብርና የማይፈራ በመሆኑ ቅዱስ የተባለውን ሰው ሰይጣናዊ ባህሪ ሊያላብሰው፣ ትልቁን ኃላፊ ከትንሿ ሠራተኛ ጭን ውስጥ ሊከተውና ስሙን በጭቃ ለውሶ መልካም ገጽታውን ሊያጠፋ ይችላል። ወሬ አደገኛ ነው። በወሬ የሚናፈስ መልዕክት ያልተሟላ መረጃ የያዘ ስለሚሆን የተሳሳተ ትርጉም ሲያገኝና ስሚው ይዘቱን በትክክል ሊረዳው ስለማይችል አለመግባባትን የመፍጠር አደጋ አያጣውም።

ሌላው የወሬ ጥፋት በፍጥነቱ አማካይነት የሚከሰተው ነው። የወሬ አካሄድ በጣም ፈጣን በመሆኑ የተሳሳተ መረጃ ያዘለ ወሬ በዚያ ፍጥነት ሲናፈስ ሠራተኞች ዘንድ ደርሶ፣ ማኔጅመንቱ የዕርምት ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት ወይም ስለተወራው ወሬ ማስተባበያ ከመስጠቱ በፊት በሠራተኛውና በማኔጅመንቱ መካከል ከፍተኛ ግጭትን ሊያስከትል ይችላል። ለእንዲህ ዓይነቱ ችግር መፍትሔ አለው።

ትጉህ ሥራ አስኪያጆችና አስተዳዳሪዎች በድርጅታቸው ውስጥ ወሬ እንዲኖር ስለማይፈልጉ ወሬን ለመቋቋም ይጣጣራሉ። እነሱ ያላወቁት ነገር ወሬን ማቆም ወይም ጨርሶ ማጥፋት የማይቻል መሆኑን ነው። በተፈለገው ማንኛውም ዘዴ ቢሆን በመሥሪያ ቤቱ የሚናፈሰውን ወሬ ማስቆም አይቻልም። በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ነው።

ወሬን ለማስቆም ከፍተኛ ዕርምጃ በተወሰደ ቁጥር ወሬው እየባስበት ይሄዳል። አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ፣ በአገራችን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ያለው፣ የመጻሕፍት ድርጅት በየሱቁ ውስጥ ያሉት የሽያጭ ሠራተኞች ካውንተሩ ላይ በካሸሯ ጠረጴዛ ዙሪያ እየተሰባሰቡ ሲያወሩ መዋላቸውን አልወደደውም፡፡ ይህ አፍ ገጥሞ ሲያወሩ መዋል የሚቀርበትን ዘዴ እንዲያፈላልግ ጓደኛዬን አማካሪ አድርገው ሥራ ሰጡት፡፡ ሠራተኞች ወሬ ላይ ስለሆኑ መጽሐፍ ፍለጋ የሚመጣውን ደንበኛ በተገቢው መንገድ ሊያስተናግዱ አልቻሉም። አንድ መጽሐፍ የት ጋ እንዳለ እንኳ አያውቁም። መጻሕፍቱን በተገቢው መንገድ እንዲደረድሩ በአርዕስት፣ በደራሲና በይዘት (በካታጎሪ) ተለይተው እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡ ወሬ ተውና ይኼን አጥኑ ቢባሉ አልሆነም። በአርዕስት ቢጠይቋቸውም ሆነ የደራሲው ስም ተነግሯቸው ሲጠየቁ መኖር አለመኖሩን መልስ ለመስጠት በጣም ተቸገሩ።

በመደብሩ ውስጥ በእነሱ ኃላፊነት ያሉት መጻሕፍት እየተሰረቁ ይወሰዱባቸዋል፣ አያስተውሉም። የጠፉ መጻሕፍት ዋጋ ከደመወዛቸው ይቀነሳል። እነሱ ግን እዚያው ወሬያቸው ላይ ናቸው። በመደብሩ ውስጥ ለእያንዳንዳቸው የሚቆሙበት መደርደሪያ (ሼልፍ) ተመደበላቸው። አንቺ እዚህ ጋር ቁሚ የአንቺ መቆሚያ ደግሞ ይኼ ነው ተብሎ ቦታ ተሰጣቸው።

እነሱ ግን ቦታቸውን ትተው ካውንተር ላይ መቆማቸውን ቀጠሉበት። አለቃ ሲመጣ ብቻ ይበታተናሉ፣ አስቸገሩ። የተሞከረው ዘዴ ሁሉ አላዋጣም፣ ሌላ ዘዴ ተፈለገ፡፡ የመጀመሪያው ሥራ ስለመስተንግዶ (ሆስፒታሊቲ) ሥልጠና በባለሙያ እንዲያገኙ አደረግን አለኝ። ከቅርብ አለቆቻቸው ጋር ሳምንታዊ ስብሰባ ተወሰነ፡፡ ከአባላት ጋር ደግሞ በወር አንድ ጊዜ ስብሰባ ማድረግ ተጅመረ።

በኋላም ስለድርጅቱ ሙሉ መረጃ ከጓደኛዬና ከድርጅቱ ባለቤት ማግኘት ቻሉ። የሥራ መመዘኛና ግምገማን ተግባራዊ ተደረገ። የድርጅቱ የአስተዳደር ማንዋል ተዘጋጅቶ ውይይት ተደረገበት፡፡ ስለመብትና ግዴታቸው የሠራተኛ አዋጅ የሚለውን እንዲያውቁ ተደረገ። እንደልባቸው እንዲናገሩና በራስ መተማመን እንዲኖራቸውም የተለያዩ ተግባራት ተከናወኑ። ማንም ሠራተኛ ጥፋቱ እጅግ በጣም ከባድ ካልሆነ በቁጥር ሁለት ወይም ሦስት ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ ሳይሰጠው እንደማይባረር መተማመን ላይ ተደረሰ።

ያለ ማስጠንቀቂያ ከሥራ የሚያሰናብቱ ከባድ ጥፋት የሚባሉትንና ቀላል ጥፋት የሚባሉት ደግሞ የትኞቹ እንደሆኑ በጽሑፍ ተሰጣቸው። ስለዝውውር፣ ስለዕድገት፣ ስለደመወዝ ስኬል ሁሉንም እንዲያውቁ ተደረገ። በመጨረሻም ተሰባስቦ አፍ ገጥሞ ማውራት ለዕድገትና ለደመወዝ ጭማሪ ጠንቅ መሆኑ ተነገራቸው። እነሱን ለመከታተል አለቆች በየጊዜው መምጣት እንደማያስፈልግና በደንበኞች አስተያየት መሠረት ክትትል እንደሚደረግ ተናግሮ የሐሳብ መስጫ ሳጥን ተቀመጠ።

ከሳጥኑ የሚሰበሰቡ ሐሳቦችም እነሱ ፊት ተከፍተው እንደሚታዩና እንደሚመዘገቡ፣ እንዲያውቁ ተደረገ። በውሳኔ አሰጣጥ ላይም ይሳተፉ ጀመር። ውጤቱ አስደሳች ነበር። ወሬው ቆመ ባይባልም ሥራ ትቶ አፍ ገጥሞ ካውንተር ላይ ተሰባስቦ ሲያወሩ መዋል ግን 80 በመቶ ያህል መቀነሱ፣ በውጭ ገምጋሚዎችና በራሳቸው ክትትል ተረጋገጠ። እነሱም አረፉ፣ እኛም ተገላገልን በማለት ጓደኛዬ አውግቶኛል።

በአጠቃላይ በቢሮክራሲውና በአንዳንድ የግል ድርጅቶችም ውስጥ ያውም ዘመን አመጣሹ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ጋር ተጋምዶ የሚንበለበለውን ወሬና የሥራ መበደል ለማስቀረት፣ በጥናትና በጥበብ መፍትሔ መፈለግ ይበጃል፡፡ በተቋማት ውስጥ ወሬን ማስቀረት ባይቻል እንኳን መቀነስና በዲሲፕሊን መግታት አያቅትም፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...