Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውስብስብ!

ከቤላ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ተሳፍረናል። ‹‹እስኪ ሙዚቃውን ቀንሰው ሾፌር። ወገን በግጭት እየተፈናቀለና እየተራበ ትንሽ አይቀፍህም?›› ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ራሰ በራ በቁጣ ይናገራል። ‹‹እኔ መቼ የጭፈራ ዘፈን ከፈትኩ? ትዝታ እኮ ነው ጌታው…›› ሾፌሩ ይሟገታል። ‹‹መከራ ውስጥ ሆነን መከራን በትዝታ ማስታወስም ያው ነው፣ በል ቀንሰው አሁን…›› ተቆጣ ሰውዬው። ‹‹እሺ ምን ልክፈት?›› ብሎ ሾፌሩ በኋላ መመልከቻ መስታወቱ አጨንቁሮ ሙዚቃ ማስመረጥ ጀመረ። ‹‹በቃ በሙዚቃ ካልሆነ አትሾፍርም ማለት ነው?›› ሰውዬው ከንትርክ ሌላ የሚያውቅ አይመስልም። ‹‹ምነው አሁንስ በዛ፣ ብለን ብለን ሙዚቃ መስማት እንከልከል እንዴ? እባክህ አልሰማህም…›› ሾፌሩ በቁጣ መለሰለት። ‹‹…ከቻልክ ሄደህ ጉልበተኞች ላይ ወኔህን አሳይ። በገዛ መብቴ ማንም አያገባውም…›› ሾፌሩ  መከላከያውን ደረደረ። ወደ ወያላው ዞር ብሎም፣ ‹‹አንተ ሰውዬ ነገረኛ ሰው እንዳይሳፈርብን ሳትፈትሽ እንዳታስገባ ብዬ አልነገርኩህም እንዴ…›› ሲለው ወያላውም፣ ‹‹አንዳንዴ እንክርዳድ ስንዴ መስሎ ማለፉ የታወቀ ስለሆነ ቻለው…›› ብሎት ተሳሳቁ። ወይ ተረብ!

በነገር የተወጋው ሰውዬ ዝም ሲል ወያላው ነገር ለመቆስቆስ ይመስል፣ ‹‹ለሴቶች የሚገባቸውን ክብር እየሰጠን እናገለግላለን፡፡ ፀባይ ያላቸውንም በመልካም መስተንግዶ ተቀብለን እንሸኛለን፡፡ ከአቅም በላይ የሆኑትን ግን ላለመቀበል ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን…›› ከማለቱ፣ ‹‹ነገርኩህ ፍተሻ ለሁላችንም ደኅነነትና ጤና መልካም ነው እያልክ ማሳመን የአንተ ፋንታ ነው። ለነገሩ አንተ ቁምነገርና ቀልድ እየቀላቀልክ ቸልተኝነት ታበዛለህ..›› ብሎ ማሳሰቢያውን ጉዟችን ተጀመረ። ‹‹ጉድ እኮ ነው…›› ይላል መሀል ወንበር ላይ የተሰየመ ወጣት። ተሳፋሪዎች ባልሰማ ባላየ በየገዛ ሐሳባቸው ሰርጥ ውስጥ እየተሽሎኮለኩ ጆሮ የሚሰጠው ጠፋ። አሁንም እንደገና ወጣቱ፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው…›› ሲል አጠገቡ የተቀመጠች ገራገር፣ ‹‹ሌላ ቃል ካልፈጠርን በቀር ጉድ ብሎ ጉድ ማብሰር የማይቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል…›› አለችው። ‹‹ለዚህ ነው እንዴ ዝምታው? እኔ ደግሞ ዕርሜን ዛሬ ወሬ ቢያምረኝ ምነው ሰው ፊት ነሳኝ ብዬ አሳስቦኛል። ለማንኛውም ምን እያልኩ ነበር?›› አላት መለስ ብሎ። ‹‹ገና ምንም ሳትል?›› አለችው እየተሽኮረመመች። ‹‹እንደዚያ ከሆነማ ልበለዋ። ምን ልል ነበር መሰለሽ? ለመሆኑ ሰሞኑን ምንድነው የሚወራው በሞትሽ?›› ብሎ አስደነበራት። ‹‹ኧረ ጠላቴ ድብን ይበል፣ እዚያው ሞትህን ራስህ ተጎንጨው፡፡ ከእኔ ምን አለህ በሞትሽ የምትለኝ?›› አራስ ነብር ሆነችበት። የባሰ አታምጣ!

‹‹እባክሽ ይቅር በይኝ የወንዜ ልጅ፡፡ አሟሟታችንን ፈጣሪ ያሳምረውና  እስቲ ጉዳያችን ላይ እናተኩር…›› ወጣቱ ይቅርታው ከልቡ መሆኑን አስተዛዝኖ ለማሳመን ተጣጣረ። ‹‹የቱ ጉዳያችን?›› ብላ ጠየቀችው። ‹‹ቲክቶክን ላያችን ላይ ያነገሠው ነዋ…›› መለሰላት። ‹‹አሜሪካና አውሮፓ እንዘጋዋለን የሚሉትን ሰምተህ ነው?›› ከቁጣዋ ቀዝቀዝ ብላለች። ‹‹ኧረ እዚህም የሚዘጋው ቢገኝ እኮ ሰላማችን አይቃወስም ነበር…›› ሲላት ወዲያው ቁጡው ራሰ በራ፣ ‹‹ወጉንማ ማን ብሏችሁ? አድርጉት ብትባሉ ግን ለታይታ ካልሆነ አትሞክሩትም…›› አለ፡፡ ‹‹ቲክቶክ ሳያጠፋን በፊት እናጥፋው ብለን ብንነሳ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሆን አትጠራጠሩ…›› ብሎ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ወጣት ዙሩን አክሮት አረፈው። ‹‹የእኛ ልምድ ቀሰማ ከመልካሙ ቢሆን እኮ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን መልካሙን ትተን የማይረባውን እየቃረምን የማንም ውዳቂ መቀለጃ መሆናችን ነው የሚያሳዝነው…›› ብሎ ራሰ በራው በንዴት ሲበግን ሰማነው፡፡ ነገር ከሯል!

‹‹አበስኩ ገበርኩ…›› ይላሉ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ አዛውንት። ግርማ ሞገሳቸው ልዩ ነው። ‹‹ምነው አባት? ምን ሆኑ?›› አጠገባቸው የተቀመጠች አጭር ቀይ ኮረዳ ትጠይቃቸዋለች። ‹‹እኔ የምሆነው ሳይሆን እኛ የምንሆነው እየጨነቀኝ ነው እንጂ ምንም አልሆንኩ እስካሁን…›› መለሱላት በዕርጋታ። ‹‹ማን የሚሆነውን ያውቃል ብለው ነው?›› አለቻቸው ነገር ለማውጣጣት እየሞከረች። ‹‹እሱን ብዬ እኮ ነው ልጄ ሁኔታችን ጭንቅ የሚለኝ። ፈጣሪስ በረባ ባልረባው እየተናጀስን እርስ በርስ ስንናከስ ሳይሰለቸው ቀረ ብለሽ ነው?›› አሉ፡፡ ‹‹ምነው ካልጠፋ ነገር የእኛ ነገር ያስጨንቀዎታል? እኛ ለራሳችን የምንጨነቅ አይደለንም እኮ…›› የምትለቃቸው አትመስልም ወጣቷ። ‹‹አይ ልጄ አሁን ያልሽው እንኳን እኛን በሕይወት ያለነውን በሞት የተለዩንን አያት ቅድመ አያቶቻችንን ጭምር ከመቃብር ውስጥ ሆነው የሚያስጨንቅ ነው…›› ሲሉ ሁላችንንም አስደነገጠን፡፡ ከዚህ በላይ ምን የሚያስደነግጥ ነገር ይኖር ይሆን!

 ‹‹ምናለበት እንዲህ እንደ አባታችን አርቀን እያሰብን ለነገው ትውልድ የምትመች አገር ለመገንባት ራሳችንን ከገባንበት አባዜ ውስጥ ብናወጣ?›› ራሰ በራው የአዛውንቱን ጨዋታ ሲያደምጥ ቆይቶ ነው መናገር የጀመረው። ‹‹በቃ ወደፊት የእኛ ታሪክ መስማማት አቅቷቸው ዕድሜ ልካቸውን እየተባሉ የረባ ነገር ሳይሠሩ አለፉ ተብሎ ነው የሚጻፈው?›› አሁንም ሲናገር ማንም አይመልስለትም፣ ብቻውን ያነበንባል። ‹‹ምንድነው ሰውዬው የሚነጫነጭብን? ኮንትራት ይዞናል እንዴ?›› ትለኛለች ከመሀል ወንበር አንዷ ሹክክ ብላ። ይኼን ስትል የሰማት መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ጠይም ፈርጣማ፣ ‹‹ምናልባት ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ቲክቶክ ሲጠቀም ቆይቶ ይሆናል የተሳፈረው…›› አላትና ሳቀ። ‹‹ታዲያ እኛ የእንካ ሰላንትያ ሰሌዳ ነን እንዴ? አንዳች ደህና ነገር አይታየውም?›› ብላ ስትናገር፣ ‹‹ተይ እንጂ ልጄ ታላቅሽ እኮ ነው፣ እሱ ህፀፅ የመሰለውን ነገር ሲናገር በሚገባ አዳምጦ በጨዋነት ሐሳብ መለዋወጥ እያለ፣ እንደ ዘመኑ ፖለቲከኞች ጭቃ መቀባባትማ ልክ አይደለም…›› ብለዋት ገላገሉን፡፡ እውነታቸውን ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። በዚህ መሀል ከመሀል አካባቢ፣ ‹‹በእስራኤል የጋዛ ወረራ ላይ የዓለም መንግሥታት ምን እያሰቡ ይመስላችኋል?›› ብሎ ጥያቄ ያነሳል። ‹‹ምንስ ቢያስቡ ምን አገባን? እዚህ የጓዳችንን ረሃብና ችግር አንድ ነገር ሳናደርግ ምን ሌላ ቦታ ያሻግረናል?›› ትላለች ወዲህ። ‹‹እንዴ ምን ነካሽ አንቺ ሰብዓዊነት የግድ ይላል እኮ…›› ይላል ሌላው። ‹‹ሰብዓዊነት ዓለም አቀፋዊ መሆኑ ተዘንግቶ አይደለም እንዴ ወገን ከወገኑ በብሔርና በእምነት እንዲጨፋጨፍ የሚደረገው…›› ሲል ራሰ በራው፣ ‹‹እኛን ያስቸገረን እኮ እንዲህ ዓይነቱን ዓለም አቀፋዊ ዕሳቤ ማቆር የሚችል ትውልድ ዕጦት ነው…›› ብሎ ወጣቱ ዘው ብሎ ገባ። ‹‹በስንቱ ይሆን ይህ ትውልድ የሚጨቀጨቀው?›› ትላለች ከአጠገቡ ሌላዋ። ‹‹ለዚህ ትውልድ ከንቱ መሆን አስተዋጽኦ ያበረከተው ከእሱ በፊት የነበረው ትውልድ ቢሆንም፣ ትውልዱ ግን ለምን እንዲህ ልሆን ቻልኩ ብሎ መመርመር ካልቻለ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡ ማንም እየተነሳ ጣት መጠቋቆሚያ ሲያደርገው እየሸሸ ቲክቶክ ውስጥ ከሚደበቅ፣ አንገቱን ቀና አድርጎ ለመብቱም ሆነ ለነፃነቱ ዘብ መቆም መቻል አለበት…›› የምትለው ዝም ብላ የነበረች ወይዘሮ ናት፡፡ ግሩም ድንቅ ነው!

‹‹ስለየትኛው ትውልድ ነው የምታወሩት?›› ከወደ መጨረሻ አንዱ ይጠይቃል። ‹‹ኧረ ባትሰማ ይሻልሃል፣ እኛስ ሰምተን ምን ፈየድን? ከሃያ ምናምን ሚሊዮን በላይ ሕዝብ  ምግብ አጥቶ የዕርዳታ ያለህ ይባልለታል፡፡ የሕዝቡ ቁጥር 120 ሚሊዮን አልፎ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ነው ይባላል፡፡ መሬት፣ ውኃ፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮች፣ ማዕድናት፣ ወዘተ ሞልተውናል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የአገራችን ስም ከድህነት መዝገብ ለመፋቅ አይደለም የረባ ነገር መብላት አልቻልንም፡፡ የኢትዮጵያን ሜዳና ተራራ በምርቶች አትረፍርፈን በዓለም ገበያ ምግብ አቅራቢ መሆን ሲገባን፣ የፈረንጅ ምፅዋት ጠባቂ ሆነን እንቁለጨለጫለን…›› ብላ ዝም አለች፡፡ ‹‹ችግሮቻችን ብዛታቸው ብቻ ሳይሆን በጣም ውስብስብ ናቸው…›› ብለው አዛውንቱ ሳይጨርሱ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ማስወረድ ጀመረ። አራት ኪሎ ደርሰን ስንለያይ በሁላችንም ልብ ውስጥ የተቋጠረ የሚመስለው ውስብስቡ ችግራችን ይመስል ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት