Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ባንክ 1.57 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ሁለት ቢሊዮን ብር፣ ከታክስ በኋላ ደግሞ 1.57 ቢሊዮን ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገለጸ፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት 63 በመቶ ብልጫ ያሳየ መሆኑን፣ ባንኩ ቅዳሜ ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አሰፋ ስሜ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መገንዘብ እንደተቻለው ደግሞ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ የተገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የ278 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው፡፡ በቀደመው ዓመት ባንኩ ከታክስ በኋላ አግኝቶ የነበረው ትርፍ 1.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው የትርፍ መጠን ከፍ ማለት፣ የባንኩን የትርፍ ድርሻ መጠን ሊያሳድግለት መቻሉ ታውቋል፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስገኘው ትርፍ 307 ብር ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ግን ይህ የትርፍ ምጣኔው ወደ 324 ብር ከፍ ሊል ችሏል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ በዋና ዋና ቁልፍ መለኪያዎች ከቀዳሚው ዓመት በአማካይ የ33 በመቶ ዕድገት ያስመገበ ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ በብድርና ዓመታዊ ገቢን በማሳደግ ከፍተኛ ውጤት እንዳገኘ ገልጿል፡፡

በተለይ ከገቢ አንፃር ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ አቅዶ ከነበረው በአራት በመቶ ብልጫ በማሳየት 8.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ሊያገኝ ችሏል፡፡ በ2014 ባንኩ አጠቃላይ አግኝቶት የነበረው ገቢ 5.8 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ የ2015 ገቢው በ43 በመቶ መጨመሩን የሚያመላክት ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የኦሮሚያ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ከቀዳሚው ዓመት በ24 በመቶ በማደግ 54.3 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተጠቅሷል፡፡

በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የሰጠው ብድርም ከቀዳሚው ዓመት በ33 በመቶ በማደግ 42.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ብድር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው የአገር ውስጥ አገልግሎትና ንግደ ዘርፍ ሲሆን፣ ለዚህ ዘርፍ ከተሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ 25 በመቶውን ድርሻ ይዟል፡፡  

የባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔንም ዝቅ ያደረገ መሆኑን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት 2.04 በመቶ፣ በ2015 ወደ 1.6 በመቶ ዝቅ ማድረግ ስለመቻሉ ታውቋል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በተበላሸ የብድር መጠን ዙሪያ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ተበዳሪዎች በብዙ ግልጽ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ምክንያቶች ብድራቸውን በጊዜ መመለስ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ የተበላሸ ብድሩን በዚህን ያህል ደረጃ ማውረድ ከፍተኛ መሻሻል ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ይህ የተበላሸ የብድር መጠን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከተቀመጠው የአምስት በመቶ ዝቅተኛ ምጣኔ፤ እንዲሁም ከኢንዱስትሪው አማካይ ምጣኔ በእጅጉ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የኦሮሚያ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ማጠናቀቂያ አጠቃላይ ሀብት መጠኑን 66 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት 27 በመቶ ዕድገት ማሳየት ችሏል፡፡ አጠቃላይ ካፒታሉ 25 በመቶ በማደግ  9.1 ቢሊዮን መድረሱን የሚጠቁመው የባንኩ መረጃ፣  የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 5.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ ከቀዳሚው ዓመት 23 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ነው፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃር በተናቀቀው የሒሳብ ዓመት 371 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ መቻሉንና ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ33 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመጀመር ተጠቃሽ የሆነው ኦሮሚያ ባንክ፣ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ብቻ የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 8.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከወለድ ነፃ የሰጠው ብድር ፋይናንስ ያደረገው ደግሞ 5.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የሀብት መጠኑን ከማሳደግ አኳያ ባንኩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህም መካከል ከገላን ከተማ ለኢንቨስትመንት በወሰደው 20 ሔክታር ቦታ ላይ በአራት ምዕራፍ እያስገነባ ያለው የገላን የልህቀትና ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም ሌላ ጎማ ቁጠባ አካባቢ ባለ 34 ወለል የባንኩ የሽግግር ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታም በጥሩ ፍጥነት በመካሄድ ላይ መሆኑንና በአሁኑ ሰዓት ከምድር በላይ 18ኛ ወለል ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

ኦሮሚያ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት 103 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ብዛት 503 ማድረስ ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች