Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዘላቂ ድጋፍ የሚሹ የጎዳና ወጣቶች

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በተለያዩ አካባቢዎች ኑሮዋቸውንና መተዳደሪያቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የቁጥራቸው መብዛት አንዱና ዋነኛው አሳሳቢ ጉዳይ ቢሆንም፣ ለተለያዩ ሱሶችና አደገኛ ዕፆች ተጋላጭ መሆናቸው ደግሞ አሳሳቢነቱን አስከፊና አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አገር ተረካቢ ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች በዚህ አስከፊ አዘቅት ውስጥ ተዘፍቀው ማየትም የተለመደ ሆኗል፡፡ እነዚህን ወጣቶች ከዚህ አስከፊ ሁኔታ አውጥቶ ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ማኅበረሰቡንና የሌሎችን ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ በየካ ክፍለ ከተማ በጎ አድራጊ ግለሰቦች ወደ ጎዳና የወጡ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ምርታማ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ‹‹ኒውማ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት›› አቋቁመዋል፡፡ ወይዘሪት መሠረት በየነ ከመሥራቾቹ የቦርድ አባላት አንዷና የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ዘላቂ ድጋፍ የሚሹ የጎዳና ወጣቶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- ኒውማ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት መቼ እንደተቋቋመና ዓላማውንም  ቢያስረዱን?

ወ/ሪት መሠረት– ኒውማ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት የተቋቋመው በመስከረም 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ዓላማውም ወደ ጎዳና የወጡ ወጣቶችን እየተቀበለ እንክብካቤ፣ የሕክምና አገልግሎት እንዲሁም የተለያዩ የሙያና የቴክኒክ ሥልጠናዎችን በመስጠት አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ ድርጅቱ ወጣቶችን ተቀብሎ ሥልጠና የሚሰጠው ለሦስት ወራት ነው፡፡ በመጀመርያው ወር አስፈላጊውን ምክርና ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በሰውነታቸው ውስጥ የዳበሩ የተለያዩ ሱሶች ከደማቸው እንዲወጣ ይሠራል፡፡ በሁለተኛው ወር የሥነ ምግባር፣ የተግባቦትና በተለያዩ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥልጠናዎች ይቀስማሉ፡፡ በሦስተኛው ወር ደግሞ ወደ ራሳቸው ተመልሰዋል ተብለው ስለሚጠበቁ በይበልጥ የሥራ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቆይታና የሥልጠና ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በቀጣይ ምን ያገኛሉ?

ወ/ሪት መሠረት፡- እኛ ከተጠናወታቸው አደገኛ ሱስ አላቅቀንና ነፃ አድርገን አሠልጥነናቸውና አደራጅተናቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም ከየካ ክፍለ ከተማና ከወረዳ አሥር መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው፡፡ የቆይታ ጊዜያቸውን አጠናቀው ከወጡት ወጣቶች 12ቱ የድርጅቱ ቋሚ ሠራተኛ ሆነው ተቀጥረዋል፡፡

ሪፖርተር፡-  በአሁኑ ጊዜ ምን ያህል ወጣቶችን ከጎዳና አንስታችሁ እየተንከባከባችሁና እያሠለጠናችሁ ነው?

ወ/ሪት መሠረት፡- በአሁን ጊዜ 150 ወጣቶችን ተቀብለን እንክብካቤና ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል 50 ያህል ወጣቶች ከሱስ በማገገም ላይ ናቸው፡፡ ወጣቶቹ በጎዳና በቆዩባቸው ዓመታት የሲጋራ፣ የማስቲሽ፣ የጫት፣ የሺሻ፣ የአልኮል መጠጥና ልዩ ልዩ አደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚዎች ነበሩ፡፡ ይህም ለከፋ የጤንነት ችግር ዳርጓቸዋል፡፡ ስለሆነም አስፈላጊው ሕክምናና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንዲያገግሙ በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ የቀሩት ወጣቶች ደግሞ የተወሰነ ዕርዳታ ተሰጥቷቸው ከሱስ የፀዱ ወይም የተላቀቁና የተለያዩ ሥልጠና እየተሰጣቸው አምራች ዜጋ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ወጣቶቹን ከሱስ ለማላቀቅ በሚከናወነው ሥራ ሳይኮሎጂስቶችና ሳይካትሪስቶች ሙያዊ ዕገዛ በማድረግ ተባብረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቶችን ከጎዳና ለማንሳት በምታደርጉት እንቅስቃሴ የሚገጥማችሁ ችግር አለ?

ወ/ሪት መሠረት፡- ምንም ዓይነት ችግር እስካሁን አላጋጠመንም፡፡ ወጣቶቹም በሙሉ ፈቃደኝነት ነው የሚነሱት፡፡

ሪፖርተር፡- በመሠልጠን ላይ ካሉት ወጣቶች በተጨማሪ በተጠባባቂነት የያዛችኋቸው ወጣቶች አሉ?

ወ/ሪት መሠረት፡- አዎ፡፡ በአሁኑ ጊዜ 850 ወጣቶች በፈቃደኝነት ተመዝግበው ወደ ማዕከሉ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ከአስከፊው ኑሮና ከተጠናወታቸው ሱስ ተላቀው አምራችና ጥሩ ዜጋ ለመሆን ያደረባቸውን ጉጉት ከእንቅስቃሴያቸውና ከዝግጁነታቸው ለመረዳት ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ የፋይናንስ ድጋፍ ከየት ያገኛል? የውጭ ድርጅቶች ድጋፍ አለ?

ወ/ሪት መሠረት፡- ድርጅቱ ለሚያከናውነው ሥራ የሚፈለገውን ፋይናንስ የሚያገኘው ከአባላትና ከቦርድ መዋጮ ሲሆን፣ ሐሳቡንና ሥራውን በአካል ተገኝተው የተረዱ አገር በቀል ድርጅቶችና ግለሰብ በጎ አድራጊዎች እንዲሁ የአቅማቸውን ያህል የዕርዳታ እጆቻቸውን ይዘረጉልናል፡፡ በተረፈ የውጭ ድርጅቶችን በእንቅስቃሴያችን አላከተትንም፡፡ ከእነሱም ምንም ዓይነት ድጋፍና ዕገዛ አናገኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የገቢ ማሰባሰቢያ አዘጋጅታችሁ ነበር? በገቢው ምን ለማከናወን አቅዳችኋል?

ወ/ሪት መሠረት፡- የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አከናውነናል፡፡ ዓላማውም የድርጅቱን እንቅስቃሴ በየክፍለ ከተማው እንዲስፋፋ ለማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በሚያካሂደው የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከመንግሥት ምን ያህል ድጋፍና ዕገዛ እየተደረገላችሁ ነው?

ወ/ሪት መሠረት፡- በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አሥር ጽሕፈት ቤት ከጎናችን ሆኖ አስፈላጊውን ዕገዛና ትብብር እያደረገልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩን በዘለቄታዊነት ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ወ/ሪት መሠረት፡- በአሁኑ ጊዜ ጎዳና ላይ ለወጡ ወጣቶች መንፈሳዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራትና የአልባሳት ዕርዳታ ሲደረግላቸው ይስተዋላል፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ ዘለቄታዊነት የለውም፡፡ ስለሆነም ሁሉም ማኅበረሰብ በአንድ ላይ ሆኖ በወጣቶች አዕምሮ ውስጥ ለውጥ ማምጣትና አምራች ዜጋ ሊያደርጋቸው የሚያስችሉ ድጋፎችን በቋሚነት መስጠት አለበት፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን መረባረብ፣ መደጋገፍና በአንድ ላይ መቆም ያስፈልጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...