Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የአገሪቱን ሥርዓተ መንግሥትና ሕገ መንግሥት ሳትቀበል ድርድር የሚባል ነገር የለም›› ፊልድ ማርሻል...

‹‹የአገሪቱን ሥርዓተ መንግሥትና ሕገ መንግሥት ሳትቀበል ድርድር የሚባል ነገር የለም›› ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም

ቀን:

ከግጭት ዓውድ ወደ ሰላማዊ ሒደት ለመምጣት በሚደረግ ድርድር ውስጥ ለመግባት የአገሪቱን ሥርዓተ መንግሥትና ሕገ መንግሥት በግድ መቀበል ይጠይቃል ሲሉ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ ከሰሞኑ ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፣ የአገሪቱን ሥርዓተ መንግሥትና ሕገ መንግሥት ካልተቀበለ አካል ጋር ድርድር የሚባል ነገር የለም ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና ኦነግ ሸኔ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ያካሄዱትን ድርድር በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ከጅምሩ ይህን መርህ ተቀብሎ በዚህ መርህ ጥላ ሥር መነጋገር፣ መደራደርና መወያየት ይቻላል የሚል መግባባት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም የመጨረሻው ውጤት እንደተጠበቀው ሳይሆን መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የተካሄደውን ድርድር የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ምሁራንና መንግሥትም ይፈልጉታል ያሉት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ፣ በተለይ ከሕወሓት ጋር ከነበረው ድርድር ጋር በተያያዘ ያኛውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከተቻለ ይህንንም በዚሁ መንገድ ለምን አንፈታውም በሚል በሙሉ ፈቃደኝነት በ2015 ዓ.ም. መንግሥት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› እያለ ከሚጠራውና በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር የመጀመሪያውን ዙር ድርድር በታንዛኒያ ዛንዚባር ማካሄዱን አስረድተዋል፡፡

የመጀመሪያው ንግግር ጥሩ ርቀት መሄዱን፣ በዚህም መካሰስ ቀርቶ ለሚቀጥለው ዙር ምቹ ሁኔታ እናመቻች በሚል ተደራዳሪዎች መለያየታቸውን አስታውሰዋል፡፡፡

በቅርቡ ያለ ውጤት በተጠናቀቀው ሁለተኛው ዙር ድርድር ከሁለቱም ወገኖች በመጀመርያው ዙር የተሳተፉና ሌሎችም ተጨምረውበት ከሳምንት በላይ የፈጀው ሒደት አዝማሚያው ጥሩ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ የማያግባቡ ነጥቦች በመምጣታቸው የተጠበቀው ውጤት ሊመጣ እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡

ይህ የሆነው ለብዙ ቀናት ድርድሩ ከተካሄደና በመጨረሻ ለሕዝብ ይፋ የሚደረግበት ደረጃ ላይ ከተደረሰ በኋላ፣ ያልተጠበቁና የተግባቡባቸውን ነጥቦች የሚያፈርሱ ጥያቄዎች በመምጣታቸው ሳይሳካ መቅረቱን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ትግል እናደርጋለን እየተባለ ያለው ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ መብት ከዚህ በፊት ልክ ነው ተገፍቶ ነበር፡፡ የመሬት ጥያቄ ነበረው፣ የመሬት ጥያቄ የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ግን የደርግ መንግሥት መልሶታል፡፡ ሁለተኛ ብሔራዊ ጥያቄ ነበረ፣ ይህን ጥያቄ ኢሕአዴግ ሲመጣ መልሶታል፣ ክልል ተከልሏል፡፡ የራሱን ክልላዊ መንግሥት እንዲያቋቁምና ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር፣ ራሱን በራሱ እንዲመራ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የቀረው ጉዳይ በኢሕአዴግ ጊዜ ማዕከላዊ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የመግባት፣ የክልሎችን አመራር የመቀያየርና በዚህ ግባ በዚህ ውጣ የማለት ችግሮች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

ኦሮሞም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ለውጥ ጥያቄና ትግል እንዲያመራ ያደረገው ይኼው መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ደግሞ ከለውጥ በኋላ መቶ በመቶ ተመልሶ ያደረ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ክልሎች ራሳቸውን ችለው የራሳቸውን የውስጥ ጉዳይ በራሳቸው እየጨረሱ፣ እያስተዳደሩና እየመሩ ነው፡፡ በመሆኑም ማዕከል ላይ ሆኖ ከፌዴራል ክልሎችን የሚቆጣጠር ኃይል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን የክልል መንግሥታት ነፃነት አለ፣ አንዱ በለውጡ የታረመውና ኢሕአዴግ ያደርግ የነበረው የክልሎች ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ሲሆን፣ ለውጡን እንዲመጣ ያደረገው ይኼው ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መረጋገጡን ገልጸው፣ አሁን ጥያቄ ባለመኖሩ ‹‹በሸኔ›› በኩል እዚህ ላይ ይህ ጎደለ የሚለው ነገር እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

‹‹የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ ያልተገሰሰ በመሆኑ፣ ክልሎችና ብሔሮች ሙሉ መብት አላቸው፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ በኢሕአዴግ ዘመን በሕገ መንግሥቱ፣ በአወቃቀርና፣ በአደረጃጀት በከፊል ተመልሷል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ በከፊል ቢመለስም ማዕከላዊ መንግሥት ጣልቃ እየገባ ክልሎቹን ጠቅላይ ግዛት በማድረጉ አመፅ መፍጠሩን ጠቅሰው፣ ከለውጡ በኋላ ግን ይህ የጠቅላይነት አስተሳሰብ መቅረቱን አስረድተዋል፡፡

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑ፣ ወደ ትጥቅ ትግል የሚወስድ ጭቆና አለ ተብሎ እንደማይታሰብም ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የታገለበት የመሬት ጥያቄ መመለሱን፣ እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች መብቶች ጥያቄ ኢሕአዴግ በከፊል መልሶት የጎደለውን ደግሞ የለውጡ መንግሥት እንደሞላው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ወደ ትጥቅ ትግል የሚያስገባ መሠረታዊና የማይታረቅ ቅራኔ ባለመኖሩ፣ ከዚያ በመለስ ይህ ጎደለ ያ ጎደለ የሚል ጥያቄ ግን ሊቀርብ እንደሚችል ተናግረው፣ እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ ደግሞ በትጥቅ ትግል ሳይሆን በንግግር ሊፈታ የሚችል ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና ኦነግ ሸኔ በታንዛኒያ ድርድር ወቅት ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ የቋንቋ ጥያቄ መሆኑን ጠቅሰው፣ ነገር ግን አይደለም በመንግሥት በሁሉም በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ፓርቲዎችና በሌሎችም ኦሮሚኛ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት የሚል መግባባት ስለመኖሩ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ጥያቄው የሚያጣላና ወደ ጠመንጃ የሚያስገባ ነገር አይደለም ብለዋል፡፡ መንግሥት ኦሮሚኛም ሳይሆን ሌሎች ሰፊ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች  በፓርቲ ደረጃ መሻሻል አለበት የሚለው ላይ መምከሩ መረጃ እንዳላቸው የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥት ሳይሻሻል ሕግ ጥሶ ኦሮሚኛ ቋንቋን አመጣለሁ ማለት ትክክለኛ ሕጋዊም እንዳልሆነና ጉልበተኝነት ነው ብለዋል፡፡

‹‹እነሱ ካቀረቡት ጥያቄ እኔ እንዲያው ትርጉም ያለው ጥያቄ ያቀረቡት የምለው ይህን ነው፤›› ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፣ ይህም ቢሆን በጣም ቀላልና በሰላማዊ ትግል ሊፈታ የሚችል እንጂ የትጥቅ ትግል ውስጥ የሚያስገባ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወደ ትጥቅ ትግል ሊያስገባ የሚችለው በጣም ወሳኝ የሆነ የኢኮኖሚና የማንነት ጭቆና ሲኖርና ይህንንም በሰላማዊ መንገድ ማሳካት ሳይቻል ሲቀር መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን መነጋገር በሚቻልበት ወቅትና ጥያቄው ተመልሶ ባለበት ወደ ትጥቅ መሄዱ ተገቢ መንገድ አይደለም ብለዋል፡፡

ከኦነግ ሸኔ ጋር በነበረው ድርድር ዋናው ያለ መግባባት ችግር በማለት ያነሱት ሕገ መንግሥቱን፣ የአገሪቱን ሕጎች፣ የሥርዓት አወቃቀር፣ ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ የግጭት አፈታት ላይ የመረዳት ችግር የነበረ በመሆኑ ተደራዳሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በመማማር ማሳለፋቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በምርጫ የመጣና ተቀባይነት ያለው መንግሥት መሆኑ ላይ መግባባት ቢደረስም፣ መግባባቱን የሸረሸረውና ድርድሩ ላይ የተነሳው ጥያቄ ሥልጣን አካፍለኝ የሚለው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ 

መንግሥት ሥልጣን ላካፍል ቢልም መብት ስለሌለው ማካፈል አይችልም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ መንግሥት ማድረግ የሚችለው ማሳተፍ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት ሥልጣኑን በጉልበት ያገኘው ባለመሆኑና በምርጫ ሥልጣን የያዘ በመሆኑ፣ የሕዝብን ድምፅ ማካፈል ስለማይቻል ሥልጣን ሊያካፍል እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

በመንግሥትና በኦነግ ሸኔ መካከል ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊኖር እንደሚችል የጠቆሙት ፊልድ ማርሻሉ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም መማማርም ትግልም ስለተደረገ ቀጣይ ዕድል እንዲኖር የሚያደርግ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡

ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሚደረግ ሦስተኛ ድርድር ‹‹ወደ ሰላም ለመምጣት ወይም እስከ መጨረሻው ላለመነገጋር›› የሚወሰንበት የመጨረሻ ንግግር ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ኦነግ ሸኔ በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በታንዛኒያ ዛንዚባር፣  እንዲሁም በዚህ ዓመት ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ በዳሬሰላም ያደረጓቸው ሁለት ዙር ንግግሮች ያለ ውጤት መጠናቀቃቸው ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...