Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ተቋማት ካልተጠናከሩ ተደራራቢ ችግሮችን መቅረፍ አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜያት በንድፈ ሐሳብ እንጂ በተግባር አልሳካም ብለው ካስቸገሩ ነገሮች መካከል አንዱ፣ መንግሥታዊ ተቋማትን ዘመኑን የሚመጥን የዕድገት ደረጃ ላይ ማድረስ አለመቻል ነው፡፡ ተቋማትን ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ማደራጀትም ሆነ መገንባት ባለመቻሉ ምክንያት አገር በበርካታ መስኮች እየተጎዳች ነው፡፡ ጠንካራ ዘመናዊ ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እየከበደ ነው፡፡ ዘመኑን የሚመጥኑ ተቋማት ሲኖሩ አመራሮችም ሆኑ ሠራተኞች በሕግ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ እያንዳንዱ ሥራቸውም ቁጥጥርና ክትትል ስለሚደረግበት በሐሰተኛ ሪፖርት ማጭበርበር አይቻልም፡፡ ጠንካራ ተቋማት ዕውቀት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ስለሚመሩ ተገልጋዮች አይማረሩባቸውም፡፡ በሚሰጡት አገልግሎት የተገልጋዮች እርካታ ወይም ቅሬታ በግልጽ ስለሚቀርብ፣ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሊኖር የሚችለው ግብረ መልስ የተድበሰበሰ አይሆንም፡፡ ተቋማት ባለመዘመናቸው ምክንያት ሙስና ብሔራዊ ሥጋት ቢሆን አይደንቅም፣ የአገር ሀብት የኮንትሮባንዲስቶች ሲሳይ ሲሆን አያስገርምም፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ጠፍቶ ግለሰቦች ቢፈነጩ አያስደነግጥም፡፡ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡

አንዳንድ ምሳሌዎችን ብናነሳ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የማዕድን ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች በኮንትሮባንድ ከአገር በገፍ እንደሚወጡ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎች ካቀረቧቸው ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል፡፡ በመንግሥትና በፀጥታ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ አካላት ከኮንትሮባንዲስቶች ጋር እጅና ጓንት ሆነው በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸው ብቻ ሳይሆን፣ ድርጊቱ ሕገወጥ ነው ተብሎ እንዲያቆሙ ሲነገራቸው ‹ምን አገባችሁ› የሚሉ መኖራቸው በግልጽ ነው የተነገረው፡፡ በኮንትሮባንድ ምክንያት አገር ከባድ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል እንደሚያጋጥማት ማንም በቀላሉ የሚረዳው ነው፡፡ በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ተልከው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ እንደ ወርቅ፣ ቡና፣ ጫት፣ የቁም እንስሳትና መሰል ምርቶች በሕገወጥ መንገድ ተጓጉዘው ከአገር እየወጡ ጥቂቶችን እያበለፀጉ ነው፡፡ በሌላ በኩል አገር የውጭ ብድር ዕዳ ጫና ተከምሮባት ለመክፈል ያለው ችግር እየታየ ነው፡፡ ጠንካራ ተቋማት ኖረው ሕጋዊ ተጠያቂነቱ የዚያን ያህል ቢሆን ኖሮ ጥቂት ሕገወጦች አይፈነጩም ነበር፣ አገርም ለችግር አትዳረግም ነበር፡፡

በብዙዎቹ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ዳተኝነት፣ እንዝህላልነት፣ አድርባይነት፣ ሕገወጥነት፣ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት፣ በሥልጣን መባለግ፣ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለማይመለከታቸው አሳልፎ መስጠት፣ ሌብነት፣ የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎችን መደበላለቅና የመሳሰሉት ድርጊቶች ያለ ከልካይ የሚፈጸሙት ተቋማዊ ጥንካሬ ባለመኖሩ ነው፡፡ ተቋማዊ ጥንካሬ እንዳይኖር ከሚያደርጉ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች መካከል ብቁ አመራሮችና ባለሙያዎችን አለመመደብ፣ በብሔርና በጥቅም ትስስር በመቧደን ተቋማትን በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ትጉህና ቅን ሠራተኞችን ሞራላቸውን በመንካት ጥለው እንዲወጡ ማድረግ፣ ዕድገትና ጥቅማ ጥቅሞችን በአድሎአዊነት መስጠትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ለአገራቸው ከፍተኛ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ዜጎች እየተገፉ፣ በጥቅም ሰንሰለት የተሳሰሩ ሕገወጦች ተገልጋዮችን ደም ዕንባ እያስለቀሱ ተቋማቱን መጫወቻ ያደርጋሉ፡፡ ተገልጋዮች በተደጋጋሚ አቤቱታቸውን በጩኸት ጭምር ሲያሰሙ አዳማጭ አይኖርም፡፡ ከሰላምና ከፀጥታ፣ ከኑሮ ውድነትና ከፍትሕ ጋር የተያያዙ ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ ማግኘት ሲችሉ አስቸጋሪ የሆኑት፣ ተቋማት በሚፈለገው መጠን እንዲጠነክሩ ባለመደረጉ ነው ቢባል መካድ አይቻልም፡፡

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ዋና ተጠሪነቱ ለሕዝብ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግሥት ዜጎች መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸውን ተረድተው በሥርዓት እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥታዊ ተቋማት አወቃቀርና የሹማምንቱ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ወሰን ግልጽ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕጉ ዜጎችን ካልታደገ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት በታማኝነትና በቅንነት ካላገለገሉ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎች በሥርዓት ካላስተዳደሩ፣ የገበያውን ጤናማነት እየተቆጣጠሩ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት ካላሰፈኑ፣ ለሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ካልተወጡ፣ ግዴለሽነትና ሕገወጥነትን የሚያስፋፉ አካላት እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ ከተደረገ፣ ወዘተ መንግሥት አገር እያስተዳደርኩ ነው ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም፡፡ ይልቁንም አሉታዊ ድርጊቶችን የሚያከናውኑ ግለሰቦችና ቡድኖች እየቦረቦሩት ነው ማለት ይቀላል፡፡ ስለዚህ ምን ታስቧል? በእጅ ላይ ያለ አፋጣኝ መፍትሔስ ምንድነው? ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚኖረው መንግሥት አሠራሩ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሲታይበት ነው፡፡

በብዙ ዴሞክራሲያዊ አገሮች የመንግሥት ሥልጣን የሚገኘው ከሕዝብ በሚገኝ ፈቃድ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለ የሕዝብ ነፃ ፍላጎት ነው፡፡ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችለው ነፃነትና እኩልነት የሚሰማው ኅብረተሰብ ሲኖር ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክርና የሕግ የበላይነት መኖር ናቸው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ትግል በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ቢያንስ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር የሚያግዙ አንቀጾችን በውስጡ ይዟል፡፡ ዜጎች ያለ ምንም መሸማቀቅ የሚፈልጉትን የፖለቲካ አማራጭ እንዲመርጡ ዕድሎችን አመቻችቷል፡፡ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ምን ያህል አመኔታ አላቸው? ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥቱ ድረስ ለዜጎች አቤቱታ የሚሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል? የመሳሰሉ ጥያቄዎች ሲነሱ መልስ የለም፡፡

በመላ አገሪቱ በሕዝብ ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ስለማይሰጥ አንፃራዊው ሰላም ደፍርሶ በቦታው ግጭት ይተካል፡፡ ለምሳሌ በከተሞች ውኃ ከሳምንት በላይ ይጠፋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በየቀኑ ይቆራረጣል፣ ለቀናትም ይጠፋል፡፡ የትራንስፖርት ችግር አሁንም ድረስ መፍትሔ ያጣ ፈተና ነው፡፡ የበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ቢሮክራሲ ያስመርራል፡፡ ሙሰኞች በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ በርካታ አቤቱታዎች ይሰማሉ፡፡ ቅሬታ ሰሚ ግን አልተገኘም፡፡ የሕዝቡን ሕጋዊ መብቶች ማን ያክብር? እነዚህ ከላይ የተነሱት መጠነኛ ችግሮች ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ በመሆናቸው አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ካለመጠናከራቸውም በላይ በኃላፊነት የሚቀመጡ ተሿሚዎች አቅም ዘወትር ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ጥንካሬ ተላብሰው ከዘመኑ እኩል መራመድ ሲገባቸው፣ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ ወደኋላ ቀርተዋል፡፡ በተከታታይ ሥልጠናዎችና ስብሰባዎች ጠብ የሚል ነገር ማግኘት ካልተቻለ፣ ለዘመናዊ መንግሥታዊ ተቋማት ግንባታ የሚያግዙ ባለሙያዎችን ድጋፍ ማፈላለግ የግድ ነው፡፡ በሁሉም መስኮች በፍጥነት በመንቀሳቀስ ተቋማት ካልተጠናከሩ ተደራራቢ ችግሮችን መቅረፍ አይቻልም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...