Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የተጣራ 696 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጠቅላላ ሀብቱ 19 ቢሊዮን ብር ደርሷል

ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 88 በመቶ በማደግ 696 ሚሊዮን ብር መድረሱን ገለጸ፡፡ ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ ደግሞ 523.06 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታወቀ፡፡

ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በ2015 የሒሳብ ዓመት በማስመልከት ትናንት ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን 292 ብር ትርፍ ሊያስገኝ ችሏል፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት የባንኩ የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 182 ብር እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡ በባንኩ አጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ የስትራቴጂና ትራንስፎርሜሽን ረዳት ቺፍ ወ/ሮ መዓዛ ወንድሙ፣ ‹‹ይህ አፈጻጸም ባንኩ ለባለእክሲዮኖቹ የሚከፍለውን የትርፍ ድርሻ 29.2 በመቶ እንዲሆን አስችሎታል›› ብለዋል፡፡ የትርፍ ድርሻ ክፍፍሉ ከዚህ በፊት ባንኩ ከከፍለው የ18.1 በመቶ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ለማከፋፈል አቅዶት ከነበረው የትርፍ ድርሻ 23 በመቶው ጭማሪ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ይህ አፈጻጸም በባንኪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ የትርፍ ድርሻ ከከፈሉ ጥቂት ባንኮች ውስጥ አንዱ እንደሚያደርገውም ወ/ሮ መዓዛ አመልክተዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኘ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ46 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 30 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 14.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን ወ/ሮ መዓዛ ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

የባንኩን የካፒታል መጠን በተመለከተ የባንኩ የማርኬቲንግና የኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ፈቃዱ እንደገለጹት ደግሞ፣ ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የተከፈለ ካፒታል ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ የባንኩ ካፒታል በአንድ ዓመት ውስጥ በ404 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

ከካፒታል አሰባሰብ አንፃር መጠባበቂያን ጨምሮ አጠቃላይ ካፒታሉ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የጠቆሙት ወ/ሮ መዓዛ፣ ባንኮች ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያደርሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ በፊት ተፈላጊውን ካፒታል እንደሚያሟሉም ጠቅሰዋል፡፡

የባንኩ የብድር አቅርቦትን በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ ደግሞ በሒሳብ ዓመቱ 4.3 ቢሊዮን ብር ብድር ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሰጥቷል፡፡ ይህም የባንኩን አጠቃላይ የብድር ክምችት 13.6 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡ የባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን ከሁለት በመቶ በታች እንደሆነ አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች የብድር መጠን ዕድገት ከ14 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት የሚደነግገው መመርያ ተፅዕኖ አላሳረፈባችሁም ወይ? ለሚለው ጥያቄ ወ/ሮ መዓዛ፣ መመርያው በሁሉም ባንኮች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም ብለዋል፡፡ ሆኖም መመርያ በባንካቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ ያደረጋቸው አሠራሮች ውጤት እንዳስገኘላቸው ገልጸዋል፡፡

የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 19 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት የ34 በመቶ ብልጫ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ቢኒያም፣ የባንኩ አጠቃላይ ደንበኞች ከማሳደግ አንፃር በተደረገው እንቅስቃሴ

የባንኩን ደንበኞች ቁጥር በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 1.06 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ባንኩ በቀዳሚው ዓመት ከነበሩት ደንበኞች ቁጥር አንፃር ሲታይ የ75 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ የሚያመለክትን እንደሆነም አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በቀዳሚው የ2014 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት የነበሩት የደንበኞች ቁጥር 607,670 ነበር፡፡

ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ከ12 ዓመት በፊት ወደ ሥራ ሲገባ በ138.9 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ የባለአክሲዮኖቹ ብዛትም 20 ሺሕ መደረሱ የገለጸው ደቡብ ግሎባል ባንክ በመላ አገሪቱ 152 ቅርንጫፎች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች