Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየልብ ሕክምና ማዕከሉ በስልክ የሚሰማው መርዶ

የልብ ሕክምና ማዕከሉ በስልክ የሚሰማው መርዶ

ቀን:

ከሁለት ዓመታት በላይ ወረፋ በመጠበቅ ቆይተዋል፡፡ ወረፋ የሚጠብቁት ውጭ አገር ዕድል ገጥሟቸው፣ አሊያም ደግሞ ለኑሯቸው የሚሆን ሸቀጥ ለመግዛት አይደለም፡፡ በለጋ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጃቸውን ሕይወት ለመታደግ እንጂ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ በልብ ሕመም የተሰቃየችውን ልጃቸውን ለማሳከም ያልገቡበት ቦታ የለም፡፡ ለማሳከምም ከክፍለ አገር ተነስተው አዲስ አበባ ቢመጡም የጠበቁትን አላገኙም፡፡

አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ ከሕክምና ወጪ በተጨማሪ የአልጋና የሌሎች ወጪዎች አቅላቸውን ሲያስተው፣ ወደቀዬአቸው ተመልሰው ከኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መረጃ ማዕከል ‹‹ወረፋችሁ ደርሷል›› የሚል መልዕክት እየጠበቁ ነበር፡፡

የልብ ሕክምና ማዕከሉ በስልክ የሚሰማው መርዶ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሁለት ዓመታት በኋላ ‹‹የያዙት ወረፋ ደርሷል፡፡ ልጅዎት መታከም ትችላለች›› የሚል መረጃ ከማዕከሉ ይደርሳቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ነበር ልጃቸው ከብዙ ስቃይ በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ለማዕከሉ ሠራተኞች ያረዱት፡፡

ይህንንም ታሪክ ሳግ እየተናነቃቸው ያጫወቱን የማዕከሉ ነርስ ሲስተር ሰላምነሽ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ሲስተር ሰላምነሽ በማዕከሉ በርካታ ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በርካታ የልብ ታማሚዎች ወረፋ ጠብቀው ሲደወልላቸው ሕይወታቸው አልፏል የሚል ነገር በተደጋጋሚ መስማታቸውን ለሪፖርተር ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ እንዲህ ዓይነት መርዶ ሲሰሙ ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ እንደሚዋጡ ገልጸው፣ ከዚህ በፊት 30 ሕሙማን ወረፋ ሲጠብቁ ቆይተው፣ አሥራ አንዱ ወረፋው ደርሷቸው ሲደወልላቸው ሕይወታቸው ማለፉን ከወላጆቻቸው እንደተነገራቸው ያስታውሳሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳከም የሚመጡት ከክፍለ አገር እንደሆነ፣ ብዙ ጊዜ ተመላልሰው ልጆቻቸውን ሲያስታምሙ ቆይተው አጋጣሚ ወረፋ ደርሷቸው ሕክምናውን እንዲያገኙ ሲደወልላቸው፣ ‹‹ሞተዋል›› የሚል ዜና መስማት እንደሰለቻቸው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ማዕከሉ የግብዓት ችግር ሲገጥመው በርካታ ሕፃናት ልጆች ለረዥም ዓመታት ወረፋ እንዲይዙ የሚደረግበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፤›› የሚሉት ነርሷ፣ በልብ ሕመም ምክንያት በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን አጥተዋል ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል ውስጥ የልብ ክፍተት በሽታ ተጠቂ የሆነ ልጃቸውን ለማሳከም ደፋ ቀና ከሚሉት መካከል ወ/ሮ ዘብይዳ አብደላ ይገኙበታል፡፡

ወ/ሮ ዘብይዳ የልብ ክፍተት በሽታ ተጠቂ የሆነውን አንድ ልጃቸውን ለማሳከም ከዚህ በፊት ወደ ተለያዩ ሆስፒታሎች ማቅናታቸውን ለሪፖርተር ይናገራሉ፡፡

ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በዚህ በሽታ መጠቃቱን የሚናገሩት እኚህ እናት፣ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መረጃ ማዕከል የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ወረፋ ከያዙ ሦስት ዓመታት መቆጠራቸውን ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በፊት የሕክምና አገልግሎቱን ልጃቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኝ ከፍተኛ ወጪ ማውጣታቸውን የተናገሩት እኚህ እናት፣ አሁን  ወደ ማዕከሉ እየተመላለሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ልጃቸው ቀዶ ሕክምና እንዲያደርግ መጠራታቸውን፣ ነገር ግን በወቅቱ ሌላ ተደራራቢ በሽታ ስለያዘው ሕክምናው ሳይደረግለት መቅረቱን ይናገራሉ፡፡

የልጃቸው ሕመም በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ እንግልት እንዳይገጥማቸው ሥጋት እንዳደረባቸው ገልጸው፣ ተመላላሽ ሕክምና ሲያደርጉም ለተጨማሪ ወጪ እየተደረጉ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

የልብ ሕክምና ከፍተኛ የሆነ ወጪ የሚጠይቅ ስለሆነ፣ መንግሥት ከዚህ ሌላ ሆስፒታል መገንባት ይኖርበታል የሚሉት እኚህ እናት፣ የኑሮ ውድነት እንዲህ በናረበት ወቅት እዚህ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ይናገራሉ፡፡

በተለይ ባለቤታቸው ጥሩ ገቢ እንደሌላቸውና አትክልት ቤት ውስጥ ተቀጥረው እንደሚሠሩ፣ ልጃቸውን ሌላ ቦታ ወስዶ ለማሳከም አቅም እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡

ሌላዋ በማዕከሉ ታናሽ እህቷን ለማሳከም የመጣችው ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸችው፣ እንደ አገር የልብ ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ስለሌለ ትልቅ ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት ወደተለያዩ የሕክምና ተቋማት ወስደው ሕክምና እንድታገኝ ማድረጋቸውን፣ ሕመሙ የልብ ክፍተት ስለሆነ ቀስ በቀስ ሊሸፍን ይችላል መባላቸውን ትናገራለች፡፡

በዚህም የተነሳ እስካሁን የቀዶ ሕክምና አለማድረጓንና በማዕከሉ በየስድስት ወራት እየመጣች ምርመራ እንደምታደርግ ገልጻ፣ መንግሥት የሕክምና አገልግሎቱን ለማኅበረሰቡ በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ መሥራት ይኖርበታል ትላለች፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ ዓሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የልብ ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት ስላለ በማዕከሉ ከሰባት ሺሕ በላይ ሕፃናት ሕክምና ለማግኘት ወረፋ ይዘዋል፡፡

በተለይ ለልብ ሕክምና የሚሆኑ ግብዓቶች አገር ውስጥ ስለማይገኙ ሕሙማን በተፈለገው ልክ አገልግሎት እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በቀን ለሁለት ሕሙማን ቀዶ ጥገና ሕክምና እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

ለልብ ሕክምና የሚውሉ አላቂ ግብዓቶች በተፈለገው ልክ ስለማይገኙ ማዕከሉ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ከሚችልበት አቅም በጣም ዝቅ ብሎ እየሠራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በአብዛኛውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለትንሽ ጊዜ መጥተው ከማዕከሉ ጋር በቅንጅት የሚሠሩ የውጭ አገር የበጎ ፈቃደኛ ድርጅቶች አማካይነት ለልብ ሕክምና የሚሆኑ ግብዓቶች እንደሚያገኙ አቶ ህሩይ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሥራቸው ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን፣ ማዕከሉ ከተመሠረተ ጀምሮ አንድ ጊዜ ብቻ ከመንግሥት በኩል ድጋፍ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት ማዕከሉ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ገልጸው፣ በቅርቡ ግን ልማት ባንክ በራሱ ወጪ በድጋፍ መልኩ ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግል መድኃኒትና አላቂ ዕቃዎችን በማምጣቱ፣ ለአንድ ሰው ይሠራ የነበረው ቀዶ ሕክምና ለሁለት መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ማዕከሉ ከአቅሙ አንድ ሦስተኛውን ያህል ብቻ እየሠራ ሲሆን፣ በዓመትም ከ450 እስከ 500 የሚሆኑ ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡  

ማዕከሉ የተሻለ አቅርቦት ሲያገኝ በዓመት ከ1,500 በላይ ሕፃናትን ማከም እንደሚችል ጠቅሰው፣ የትኛውም የልብ ሕሙማን ወደ ግል ሆስፒታሎች ሄዶ ሕክምና ለማግኘት ቢፈልግ ከ600 ሺሕ ብር በላይ ሊያወጣ እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ከጤና ሚኒስቴር በኩል ጥናት ተደርጎ የተወሰኑ ግብዓቶች ወደ አገር ውስጥ መግባቱን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አቅርቦቱ በቂ እንዳልሆነና ችግሩም በማዕከሉ ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አላቂም ሆነ የመድኃኒት ግብዓቶችን የሚያቀርቡት የግል ተቋሞች መሆናቸውን፣ ለአንድ ታካሚ የልብ ቫልቭ በኦፕራሲዮን ለመቀየር ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

ለአንድ የልብ ሕመምተኛ ሦስት ጊዜ የልብ ቫልቭ ለመቀየር ቢፈለግ እስከ 9 ሺሕ ዶላር እንደሚያስወጣ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህንንም አቅርቦት እንደ አገርም ሆነ እንደ ተቋም ከፍ ማድረግ ካልተቻለ የተሻለ ሥራ መሥራት አይቻልም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ የልብ በሽታ ዓይነቶች እንዳሉ፣ እነዚህንም ለማከም ማዕከሉ 80 በመቶ ያህል አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መረጃ ማዕከል ሁለት ዓይነት አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን፣ አንዱ የአንድ ሕመምተኛን ደረት በመክፈት ችግሩን መፍታት፣ ሌላው ደግሞ በደም ሥር ውስጥ ተገብቶ የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎትና ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ተመጣጣኝ እንዳልሆነ፣ በአገር አቀፍ ደረጃም የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛ ማዕከል መሆኑ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል፡፡  

የልብ ሕመም ሕክምና አገልግሎት በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ማዕከሉ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመው ያለው የአላቂ ግብዓቶች ቶሎ ቶሎ አለመተካት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የአቅርቦት ችግርን መፍታት ከተቻለ ማዕከሉ አሁን እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በሦስት እጥፍ በመስጠት የልብ ሕሙማንን ችግር መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡

የልብ ሕሙማንን ችግር በተወሰነ መልኩ ለመፍታት ማዕከሉ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመነጋገር በየአካባቢው ያሉ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ቢያንስ የልብ ክፍተት ቀዶ ሕክምና ለሚፈልጉ ሕሙማን ባሉበት አካባቢ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ወደ ሥራ ሲገባ በመጀመርያዎቹ ሦስትና አራት ዓመታት በቂ የሕክምና ባለሙያ እንዳልነበረ ገልጸው፣ መንግሥት የሆስፒታል ግንባታና የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በተገቢው መንገድ መሥራት እንደሚኖርበት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

የልብ ሕመም በሁለት የሚከፈል ሲሆን፣ አንደኛው ከወሊድ ጀምሮ የሚፈጠር እንደሆነ፣ ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ የትኛውም ሰው ጤናማ ሆኖ ካደገ በኋላ ከቶንሲል ጋር በተያያዘ የሚፈጠር መሆኑን የተናገሩት የማዕከሉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምሕረተአብ ኤርሚያስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በማዕከሉ ለሁሉም ዓይነት የልብ በሽታዎች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕመሙ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠቃው ሕፃናት ልጆችን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አልጋ ይዘው ቀዶ ሕክምና እያደረጉ ለሚገኙ ሕፃናት ልጆች ሙሉ ለሙሉ ወጪውን እንደሚሸፍን፣ ነገር ግን ተመላላሽ የሕክምና አገልግሎት የሚጠቀሙ ሕሙማን የላቦራቶሪና ሌሎች ወጪዎችን ራሳቸው የሚሸፍኑ መሆኑን ምሕረተአብ (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡

ማዕከሉ ይህ ሊደረግበት የቻለበት ዋነኛ ምክንያት አልጋ ይዘው ቀዶ ሕክምና ለሚያደርጉ ሕፃናት ወጪውን ለመቆጠብ ሲባል እንደሆነ ጠቅሰው፣ አንድ ሕፃን ልጅ ቀዶ ሕክምና ሲሠራለት በቀን አንድ ሺሕ ብር ድረስ እንደሚፈጅና ይህንንም ማዕከሉ እንደሚሸፍን ገልጸዋል፡፡

አንድ ታካሚ የተጠቀመበት ግብዓት መልሶ ጥቅም ላይ ስለማይውል ብዙ ጊዜ የግብዓት ችግር እንደሚገጥማቸውና በዓመት ስድስት ሺሕ ቀዶ ሕክምና ከሚሠሩ የግል ተቋሞች ጋር በመጫረት ግብዓቱን እንደሚያገኙ ጠቁመዋል፡፡

ለልብ ሕክምና የሚሆኑ ግብዓቶችን የሚያመጡት ከውጭ አገር ስለሆነ፣ አብዛኛውን ጊዜ ማዕከሉ የግብዓት እጥረት እንደሚያጋጥመው፣ በዓመት ከ1,500 በላይ ታካሚዎች ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡ አብራርተዋል፡፡

ማዕከሉ የሕክምና አገልግሎቱን ሲሰጥ የተለያዩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውና በ‹‹6710›› የጽሑፍ መልዕክት ማኅበረሰቡ እንዲልክ በማድረግ ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በቅርብ የተጀመረ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንዳለ፣ ይህም መርሐ ግብር አንድ ግለሰብ የአንድ የልብ ሕሙማን ሕክምና ሙሉ ለሙሉ ወጪ የሚሸፍንበት አሠራር መዘርጋታቸውንም አክለዋል፡፡

ይህ አሠራር ከተጀመረ ገና ሁለት ወራት መሆኑን፣ እስካሁንም ስድስት ሕፃናት አንድ ግለሰብ ብቻዋን እያሳከመች መሆኗን ገልጸው፣ የሚረዱ ሰዎች ከሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች ወጪዎችን ለታማሚዎቹ እንደሚሸፈንላቸው ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...