Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የእንቧይ ካብ!

ሰላም! ሰላም! አንዱ ቀን ሌላውን ተክቶ ሳምንቱ ተገባዶ ሌላ ሳምንት እየተተካ ስንገናኝ ደስ ይላል፡፡ ፈጣሪ አምላካችን ምሥጋና ይድረሰውና ለዚህ ሳምንት በሰላም ስላደረሰን በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ወጋችንም በደስታ ሲጀመር ወጉም ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ይሰለቃል፡፡ እናም በዚህ ሳምንት ትንሽ ፈታ እንበል፡፡ ሰላምና እሳት ሳይታሰብ ገጥመው ‘እፍ አሉ…’ አሉ። ደግሞ ሁለቱም ያለ ቆስቋሽና ያለ አጋፋሪ አይሆንላቸውም እኮ። ‘እፍ…’ አባባላቸው አጋፋሪዎቻቸውንና ቆስቋሾቻቸውን ገሸሽ አስባለ። ሰላም ወበቅ በዛባት፡፡ እሳትም አጓጉል ቅዝቃዜ ይሰማው ጀመር። ያለ ባህሪው መስሎና ተመሳስሎ መኖር የሚያውቅ መቼም ከፍጥረት ሁሉ እንደ ሰው ልጅ የለም። በመካከል አንዱ ሲጠቀም ሌላው ከአስብቶ አራጁ ይውላል። ‹‹ወይ አለመተዋወቅ ወይ አለመታደል…›› ይላሉ አዛውንቱ ባሻዬ እንዲህ ዓይነቱ ሲገጥማቸው። እናስ? እሳትና ሰላም ምክር ተቀመጡ። እኔ ስብሰባ አላልኩም። ይኼ በየቀኑ ተገልጋይ በቀጠሮ እየተጉላላ ስብሰባ ላይ ነን ዓይነቱን ማለቴ ነው። ‹‹ግን እኔ ምለው ስብሰባው ለመሰብሰብ ከሚሆን ለምን ላለመሰብሰብ አይሆንም…›› አለ አንዱ መቼ ዕለት ከክልል መሸኛ ይዞ የመጣ ዘመዱን መታወቂያ ሊያስወጣለት ሦስት አራት ቀናት ሲመላለስ ታክቶት። ስልችት ይላል እኮ!

እኔ ደግሞ ድምፄን ከፍ አድርጌ፣ ‹‹ካልተሰበሰብንማ አንደኛውን ማኅበረሰብ ሆኖ መኖር ምን ያስፈልጋል? አንደኛውን በዱር በገደሉ እንደ አማፂ አንኖርም?›› ማለት። ይኼን ስል አንዱ ሰምቶኝ፣ ‹‹አማፂ ወስኖ ነው የሚያምፀው ልብ ካለህ ሞክረው…›› አይለኝ መሰላችሁ? አያችሁ ግን? የእኛ ችግር እንደ ዓሳ ሞት መቼ ከአናታችን ሆነ? ጭራው ላይ ነው ስላችሁ። ‹‹እና ለምን ጭራውን አንቆርጠውም?›› ብሎ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳቀብኝ። አባቱ ሰምተውት፣ ‹‹የነብርን ጭራ አይዙም ከያዙም አይለቁም የሚለውን አባባል አላውቀውም እንዳትል ብቻ…›› አሉት። እስኪ አሁን አርፈን ጭራን ለዝንብ ማባረሪያነት እየተጠቀምን እንደ መኖር በገዛ እጃችን ጭራን በሽሙጥ ፖለቲከኛ ማድረግ ምን ይባላል? እናማ በፆታ እኩልነት ተሠርቶ የማይታወቅ ሥራ ሠርተናል እያሉ ዋኖቻችን አኃዝ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹አኃዙ የተጋነነ ነው፣ እኛንና ኑሯችንን አይመስልም፣ እባካችሁ መሬት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምዳችሁ ሪፖርት አቅርቡ ስንላቸው አይሰሙንም፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባዱን ሥራ የሚሠሩት ሴቶቻችን መቼ ነው ከወንድ እኩል ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙት ስንል ሰሚ የለም፡፡ መፈክሩ ግን ያደነቁረናል…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እውነቱን እኮ ነው!

በሌላ በኩል የችግራችን ብዛቱ ህልቆ መሳፍርት አጥቶ ይታያል፡፡ ‹‹ይኼ ትውልድ ከሚያየው ይልቅ ምልክት አጥብቆ ይሻል ይባል የለም ወይ?›› ብዬ ባሻዬን ስጠይቃቸው፣ ‹‹እሱ ለእኛ አይደለም…›› ብለው በአጭሩ መለሱልኝ። ደህና አድርጌ ስለማውቃቸው ነገር ሲያሳጥሩ ይገቡኛል። እናንተም ይገባችኋል አይደል? ሌላው ቢቀር ባሻዬን በአካል ባታውቋቸውም ከብዙዎቹ አወዛጋቢ አነቃቂ ሥልጠና ሰጪ ነን ከሚሉት በእጅጉ የተሻሉ ናቸው። ከየትም የተቃረመ ‹‹የስህበት ሕግ›› የሚል የሰይጣን ቁራጮች የጻፉትን መነባንብ ባልበሰለ ጭንቅላት ተሸክመው፣ ሌላውን ለመበከል ከሚጣደፉ ጥራዝ ነጠቆች ተርታ ባለመሆኔም ፈጣሪዬን አመሠግናለሁ፡፡ ‘ኤጭ! አትሰልቸና! አንዱን አንስቶ አንዱን መጣል ምንድነው?’ ዓይነት ስትሰላቹ ይታወቀኛል። እስኪ ጎብዙና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው፣ ሁሉንም መርምራችሁ የተሻለውን ለመያዝ አዕምሮአችሁን ተጠቀሙ፡፡ ማለቴ አቅም ካላችሁ መጀመሪያ ፍሬውን ከገለባው ለዩ፡፡ የሰው ልጅ እዚህ ምድር ላይ ሲኖር ጥሮ ግሮ እንዲያልፍለት እንጂ በአቋራጭ የሚገኝ ሀብት እያለመ በድህነት እንዲኖር አልተፈረደበትም፡፡ አሁን ግን ‹‹የስህበት ሕግ›› የሚባል ምናባዊ ሥልጠና እየተሰጠው ያለፋበትን ያልማል፡፡ ይህ ሕልም ወደ ቅዠት ሲቀየር ራሱን ያጠፋል፡፡ ይህንን ሁሉ የነገረኝ የምኮራበት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ መሆኑን ስነግራችሁ በአክብሮት ነው፡፡ ይመቻችሁ!

እና ቅድም ምን እያልኳችሁ ነበር? አዎ ባሻዬ ‹‹ለእኛ አልተጻፈም…›› አሉኝ አልኳችሁና ወደ ሌላ አሳሳቢ ርዕስ ገባሁ። አሁን ወደ ጣቢያዬ ተመልሻለሁ። እንዲያው ለመሆኑ እንኳን ለአገራችን አበቃን ነው የሚባለው ወይስ እንኳን ለክልላችን አበቃን ነው? እኔ ምን አውቄ ታዲያ? ባሻዬን፣ ‹‹ለእኛ የተጻፈው ምን ይላል?›› አልኳቸው። ‹‹ለምን አትተወኝም ልጅ አንበርብር?›› አሉኝ ሐሳብ በጣም ደቁሷቸው። ‹‹ማን አለኝ ብዬ ልተወው?›› ስላቸው አንጀታቸውን ልበላ፣ ‹‹አልተጻፈማ፣ ያልተጻፈውን ከየት ላምጣው?›› ብለው ተቆጡ። ‹‹እኔ ብራና ቀለሙን ላዘጋጅ። መቼም ይኼ ትውልድ በብራና የተጻፈን ጽሑፍ በመናቅና ከልክ ባለፈ አግዝፎ በማየት የሚስተካከለው ስለሌለ፣ አንድም በመናቅ አንድም ለአምልኮ በደረሰ አድናቆት እርስዎ ቢጽፉት ያዋጣል…›› ማለት። የደላላ ነገር ሁሉ በያዋጣልና አያዋጣም ዥዋዥዌ ሲወዛወዙ መኖር አይደል። ባሻዬም በአግራሞት፣ ‹‹ማ እኔ? ‘ይህ ትውልድ ያለ ምልክት አያምንም። ምልክት ሲያይም ምልክቱን ለማየቱ ሌላ ምልክት ይሻል’ ብዬ ነው የምጽፈው? አላደርገውም…›› ብለው ተቃወሙ። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ እንበልና ምልክት ምንድነው ብለን እንጠይቅ? እንዴ እኔ እኮ አድማ እንምታ ሳይሆን እንጠይቅ ነው ያልኩት፡፡ ምን ያስደነግጣችኋል? ደግሞ መልሱ በእጃችን መስሎኝ። ግድ የለም እጅ እጃችሁን ስታዩ አመድ አፋሽነታችሁ ከኑሮ ውድነት ጋር ተጎዳኝቶ እንዳይሸነቁጣችሁ መልሱ ይኼው፡፡ ምልክት ማለት ‘ቅንጣት ታህል ዘር በስብሳ ፍሬ ስታፈራ፣ ማለትም አንድም ስታኮራ አንድም ስታስፈራራ’ ማለት ነው።  ማለት ያው ማለት ማለት ነው፡፡ እናንተን መቼ አጣኋችሁ፣ አጥንት  አትጋጡ ስትባሉ ወተት ማለታችሁ መቼ ጠፋኝ። ሞኝህን ፈልግ አለ ያገሬ ሰው!

ሞኝ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? ‘አወይ ልጅነቴ ማርና ወተቴ’ የምንላት ነገር። ‹‹ምን ነገር አላት?›› አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በቀደም ዕለት። እሱ ደግሞ ምሁርነቱን መሰሰት አንዳንዴ ይቀናዋል መሰለኝ። አሁን እስኪ መዋለ ንዋይን በፍትሐዊነት ለማከፋፈል ይሳሳ ይሆናል። ነዳጅ ወጣ ቢባል አንቀጽ ሰላሳ ሰጠኝን ቀዳችሁ ስጡኝና ወደ የምሄድበት ልሂድ የሚል ቢኖርም አይደንቅ ይሆናል። ነዳጅ እኮ ነው አሜሪካን በአራቱም የዓለም ማዕዘናት እያንከራተታት ወንጀል የሚያሠራት። ያላየነውን አናውራ የሚባለው መቼም ተጠያቂነትና ኃላፊነትን አውቆ ለሚሠራ ተቋም እንጂ ለአላዋቂ አይመስለኝም። ‹‹እንዲያው ለመሆኑ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መንግሥት አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለበት አንቀጽ መኖሩን ስንቱ ባለሥልጣን ያውቃል…›› ብዬ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ብጠይቀው፣ ‹‹ከጥቂት አመራሮች በስተቀር አብዛኛው በደመነፍስ ነው የሚራመደው…›› ካለኝ በኋላ ተስፋ እንዳልቆርጥ የአገር ጉዳይ ሆኖብኝ፣ ተስፋ እንዳይኖረኝ የግድ የለሾችና የአላዋቂዎች መብዛት እያስፈራኝ አለሁ እላችኋለሁ፡፡ ይህም መኖር ከተባለ አትሉም እንዴ!

እናላችሁ አንደ ቀን ደግሞ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነገር ሊፈልገኝ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምን የሚነገር ነገር አላት?›› ሲለኝ፣ ‹‹የሚነገር ነገር ባይኖራት ኖሮ በቆሎና በሽሮ አድገን የት ያየነውን ማርና ወተት ነው የምናስታውሰው?›› አልኩት። በበኩሌ ከማር ይልቅ የላስኩት ስኳር ነው ትዝ የሚለኝ። ‹‹ምግብ እንደ አልማዝና ብርቅ የሆነባት አገር ላይ ጀግንነትን ብቻ እየተረክን ያሳለፍነው ጊዜ ሲቆጭ፣ አሁንም ደግሞ እሱም አነሰ ተብሎ ነው መሰል ማንም ከየስርቻው እየተነሳ በብሔር ጥያቄ ስም የለቅሶ ፖለቲካውን እያስነካ ያደማናል፡፡ ከትናንት የማይረባውን ጥሎ የተሻለውን ይዞ የራሱን ታሪክ መሥራት የሚገባው ትውልድ፣ በዕርዳታ እህል አድጎ በስተርጅናውም ዕርዳታ እየለመነ እርስ በርሱ ይጨካከናል፡፡ ያልበሰሉ ፖለቲከኞች ደግሞ በዚያች ትንሽ ጭንቅላታቸው ያደሩትን የፖለቲካ ሴራ እየጎነጎኑ እንጀራቸውን ያበስላሉ፡፡ ምስኪኑ ሕዝብ ግን የዕርዳታ ስንዴና ዘይት የሚያቀምሰው አጥቶ ፍግም ይላል፡፡ ስለዚህ እኛም ሆንን አገራችን ምን የሚነገር ታሪክ አለን የምለው ለዚህ ነው…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ የብራ መብረቅ በሉት!

የምግብ ነገር ከተነሳ አይቀር እነሆ አንድ ገጠመኝ። ሰሞኑን ነው። ‹‹አዲሱ ትውልድ ልጅነቱን ዲጂታላይዝድ በሆነ መንገድ እያጣጣመ እንደሆነ ለዘመኑ ሰው አይነገርም፣ ለቀባሪው ማርዳት ነው። እየጣመው ይሁን እየመረረው ብቻ ጥናት ያስፈልገዋል…›› ስል፣ ‹‹ወይ አንተ ጉደኛ…›› አለኝ አንድ የዘመኑ ኢንቨስተር ደንበኛዬ። ዓመት ገደማ ልጆቹን በማልጠራው ዋጋ  አንድ ‹‹ዓለም አቀፍ›› ትምህርት ቤት አስገብቶ ለማመላለስ እንዲመቸው፣ ትምህርት ቤቱ አካባቢ አንድ ጥሩ ቪላ መግዛት ፈልጎ አጋዛሁት። ‹‹እንዴት ነው?›› ስለው፣ ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ፣ ልጆቹ አጥኑ ሲባሉ ስማርት ቲቪ ቀይርና እናጠናለን፣ አንብቡ ሲባሉ አዲስ ቨርዢን ታብሌት ካልተገዛልን ከደብተር አናነብም እያሉ የምን ጥናት ነው እነሱ ላይ የሚሠራው። ካልክስ ጥናቱ ለወላጅ ነው የሚያስፈልገው…›› ብሎ ልጅ በማሳደግ እያየ ያለውን አበሳ አጫወተኝ። ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል (በነገራችን ላይ ሦስት ልጆች አሉት) አንዱ ‘ጊሌ’ ግዛ ሲለው አንዷ ‘የትግራይን ክልል ባህላዊ አለባበስ ይዤ ስለምቀርብ በወርቅ አንቆጥቁጠኝ’ ስትለው፣ ሌላው ጦርና ጋሻ ከሙሉ ልብሱ ጋር እያለው ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ማውጣቱን ደረሰኝ እያሳየ ነገረኝ። እኔ ምለው ደረሰኙን አትጣለው፣ በታክስ ኦዲት ጊዜ ይወራረድ ይሆናል ልበለው እንዴ ደውዬ? አጣሩና ንገሩኝ እስኪ!

‹‹መቼም ይኼ ነገር ሕገ መንግሥቱ ላይ አልተጻፈም…›› ሲለኝ ኢንቨስተሩ ሳቄ መጣ። ውሎ አድሮ ቤቱን ሊሸጠው እንደሆነና ገዥ እንድፈልግ ነገረኝ። ግራ እንደገባኝ  ገዥ ይዤ ሄጄ ቤቱን ሳሳይለት ልጆቹን ተዋወቅኳቸው። የሚገርማችሁ በዓሉ አልፎም ወንዱ ልጅ ጊሌውን ሴት ልጁም ወርቋን፣ ባለጦርና ጋሻውም አናወልቅም እንዳሉ ነበሩ። በዚህ ዕድሜያቸው ስለአገራቸው ሕዝብና ባህል ያላቸው ዕውቀትና ፍቅር ዛሬ እንዲህ ከሆነ ሲያድጉ እንዴት ይጎመራ ይሆን እያልኩ ደስ አለኝ። መቼም ልጅ ይወደኛል ብዬ ላጫውታቸው ቀረብ ብዬ ማሙሽዬ ሚሚዬ ከማለቴ ሴቷ፣ ‹‹ዳዲ… is he crazy?›› ትለዋለች። ወንዶቹም ያው (በእንግሊዘኛ ነው) ‹‹ለምን ወደ አዕምሮ ሕሙማን መርጃ አትወስደውም?›› ይሉታል። ምን አድርጌያቸው እንደሆነ አትጠይቁኝም? እንደ ሕፃን አባበለን ብለው ደብሯቿው ነዋ። የቱን ይዘን የቱን እንደምንጥል ተውትና ብቻ አንድ ትልቅ ሰው ቤታችን ሲመጣ እንዴት እንሆን እንደነበር እኛን የትናንትናዎቹን አስቡን። እናስ? አሥር ዓመት ያልደፈነ አንድ ሕፃን በሙሉ ሰው ሒሳብ ልታይ እያለ ኪሳራውን ጠቅላላ ወላጅ ላይ መከመር ይቻላል? አቤት ይኼኔ ሌላ ነገር ላወራ መስሏችሁ ሰፍ ብላችሁኋል አይደል? ወይ እኛና ወሬ!

እንሰነባበት? አዎ ይሻለናል። ያ ኢንቨስተር ደንበኛዬ፣ ‹‹ልጆቼ አንድ ቋንቋ ብቻ እየተማሩ እንዴት ይዘልቃሉ?›› ብሎ ቤቱን ከሸጠ በኋላ ነገረኝ። እናማ ይዟቸው ወደ ቀድሞ ቤቱ ተመለሰ፡፡ እናት አሜሪካ አባት እዚህ ሆነው እንደሚኖሩ ስሰማም ተዘበራርቆብኛል። በነገራችን ላይ የሰላምንና የእሳትን መጨረሻ ነገርኳችሁ? ያልነገርኳችሁ መጨረሻ ስለሌላቸው ነው። ምክንያቱም ገና ከስብሰባ አልወጡም። እኛም እነሱም መቼ እንደምንወጣ አናውቅም። ሥራችን ነገር ብቻ ሆኗል። እያደርን ወደኋላ እያየን መገንፈልና መገፋፋት አልሰለቸን ብሏል። ‹‹እንዲያው ነገሩን ነው እንጂ እሱማ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ማለት አያስፈልግም›› ብሎ መተው ይሻል ይሆን ብዬ ተውኩት። ልተወው እልና ግን የማያስተው ነገር ሲገጥመኝ ያብሰለስለኛል፡፡ የሆነስ ሆነና፣ ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ካልረገጠች እርካብ፣ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ… የእንቧይ ካብ…›› ያሉትን ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን እያስታወስን እላችኋለሁ፡፡ መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት