Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሹዋሊድ ክብረ በዓሏን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው ሐረር

የሹዋሊድ ክብረ በዓሏን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው ሐረር

ቀን:

ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ፣ በ1998 ዓ.ም. (2006) ታሪካዊቷን  የሐረር ከተማ፣ በግንብ የታጠረችውን ተዳሳሹን ጁገልን በዓለም ቅርስነት መዘገበ፡፡ ከአሥራ ሰባት ዓመት በኋላ ደግሞ የማይዳሰሰውንና የረመዳን ጾም ፍጻሜን ተከትሎ የሚከበረውን የሹዋሊድ ክብረ በዓልን በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ አድርጎ የመዘገበው ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ነው፡፡

ምዝገባውን ያከናወነው በቦትስዋና ካሳኔ የተሰየመው ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የበይነ መንግሥታዊው ኮሚቴ ነው፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የመጀመርያው የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ኅዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም. የተመዘገበው፣ የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እውነተኛው መስቀል የተገኘበት የመስቀል በዓል እንደነበር ይታወሳል፡፡

የሹዋሊድ ክብረ በዓሏን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው ሐረር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኅዳር 25 የተመዘገበውን የሸዋል ዒድ ጨምሮ ኢትዮጵያ እስካሁን ያስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች አምስት ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ተመዝጋቢዎች የሲዳማው ፊቼ ጫምባላላ፣ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት እና የጥምቀት ክብረ በዓል ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የሹዋሊድ ክብረ በዓልን በአገር አቀፍ ቅርስነት የመዘገበው ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብ ሒደቱ አራት ዓመት ያህል ወስዷል፡፡ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርሱ በዩኔስኮ እንዲመዘገብለት አገራዊው የቅርስ ተቋም ከላከውና ዩኔስኮ በድረ ገጹ ካሠፈረው ያገኘነውን የሹዋሊድ አከባበር መግለጫ በከፊል እዚህ ላይ ቀርቧል፡፡

የሹዋሊድ በዓል በዩኔስኮ ሰነድ 

በምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል፣ ከአዲስ አበባ ከተማ በ525 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው የሐረር ከተማ፣ በሐረሪ ተወላጆች ዘንድ በየዓመቱ እየተከበረ የሚገኘው የሹዋሊድ በዓል የብሔረሰቡ ትልቅ የማንነት መገለጫ እሴት ነው፡፡ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቁ የፆም ወቅት የሆነውን የረመዳን ወር ጾም ማንኛውም ለአቅም አዳምና ሔዋን የደረሰ የእምነቱ ተከታይ መጾም ሃይማኖታዊ ግዴታው ነው፡፡ የረመዳን ወር ጾም ከተጠናቀቀ በኋላ የዒድ አልፈጥር በዓል በሹዋል ወር የመጀመረያው ቀን ይከበራል፡፡

በሃይማኖቱ የረመዳን ወር ጾም እንደተጠናቀቀ የሹዋል ወር ጾም ይጀምራል፡፡ የሹዋል ጾም ከሹዋል ወር ሁለተኛው ቀን አንስቶ ባሉ ተከታታይ ስድስት ቀናት ይጾማል፡፡

ይህ ጾም በሹዋል ወር የሚጾም በመሆኑ ስያሜውን ከወሩ መጠሪያ አግኝቷል፡፡ ሹዋል በሐረሪና የእስልምና ሃይማኖት የዘመን አቆጣጠር የአሥረኛ ወር መጠሪያ ነው፡፡ የሹዋል ጾምን ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሕይወት ዘመናቸው ሲጾሙት የነበረ ጾምና በሹዋል ወር ስድስት ቀናትን የጾመ ዓመቱን በሙሉ እንደጾመ ይቆጠራል የሚል አስተምህሮት ያላቸው በመሆኑ፣ የሹዋል ጾም በዚሁ መነሻነት በሐረሪዎች ዘንድ ከጥንት ጀምሮ መጾም እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

የክብረ በዓሉ ቀን

ከዚያም የሹዋሊድ በዓልን ያከብራል፡፡ የሹዋሊድ በዓል የስድስቱን ቀናት ጾም መጠናቀቅን አስመልክቶ በሐረሪዎችም ወይም የእስልምና ሃይማኖት የዘመን አቆጣጠር የአስረኛ ወር ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይከበራል፡፡ ይህም ከሹዋል ወር ስድስተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ የሹዋሊድ በዓል ከሚውልበት ስምንተኛው ቀን (ዕለት) ድረስ ነው፡፡ ሐረሪዎች የሹዋሊድን በዓል ያለ ምንም የፆታ ዕድሜና ማኅበራዊ ደረጃ ገደብ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ በደመቀ ሁኔታና ባህላዊ እሴቶቻቸውን በሚያንፀባርቅ መልኩ እያከበሩት ይገኛል፡፡

ዋናው የበዓሉ ሥነ ሥርዓት የሚጀምረው በሰባተኛው ቀን ምሽት ወይም በዋዜማው ምሽት ሲሆን፣ በስምንተኛው ቀን የሹዋሊድ በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ውዳሴዎችና ባህላዊ ጭፈራዎች ታጅቦ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል፡፡ በዚህ የበዓል ሥነ ሥርዓት ላይ ሐረሪዎች የብሔረሰቡን ባህልና ወግ በጠበቁ አልባሳትና ጌጣ ጌጦች አሸብርቀው ይታደማሉ፡፡ በበዓሉ ላይ እንደ አመጣጣቸው ወንዶች በአንድ በኩል ሴቶችም በተመሳሳይ ከወንዶች አጠገብ በመሆን ክብ ሠርተው ይቀመጣሉ፡፡ ሙሪዶች ደግሞ በተዘጋጀላቸው ቦታ በመሆን የበዓሉን ሥነ ሥርዓት ለመጀመር ይዘጋጃሉ፡፡

የበዓሉ ማድመቂያ  ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች

ለበዓሉ ማድመቂያ የተለያዩ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የተለያየ መጠን ያላቸው ከበሮዎችና የከበሮ መምቻ ዱላ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች እንደሚቀርበው የውዳሴ ዜማ፣ ይዘትና የጭፈራ ዓይነት የተለያዩ የዓመታት ሥልቶችን በመከተል የተለያዩ ድምፆችን ለማውጣት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከእንጨት ተቀርፆ የተሠራ በብሔረሰቡ አጠራር ‹‹ከበል›› በመባል የሚታወቀው የእጅ ማጨብጨቢያ፣ እንዲሁም የዚክሪ ወይም ውዳሴ መጽሐፍ ተጠቀሾች ናቸው፡፡ የበዓል ሥነ ሥርዓቱ ምሽቱን በየደረጃው በሚቀርቡ ዝክሪዎች ይጀመራል፡፡ አጀማመሩም በሁለቱም አዋቾች በተመሳሳይ መልኩ ‹‹አዋዮው ነቢ አዋዮው ነቢ መሐመድ መሐመዶ ስላሜ›› በሚል የዜማ ሥልት በአባቶች ምርቃት ነው፡፡

የሹዋሊድ ክበረ በዓል በተለይ በወጣቱ ክፍል ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ በዓሉ ‹‹ዋሐቺ ዋ ዶርማ ዒድ›› (የወጣቶችና የልጃገረዶች ዒድ) በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ መነሻነት ወጣቶች ሹዋሊድን ጌይ አዳ (የከተማ ወይም የአገር ባህል)፣ ጌይ ደድ (የከተማ ወይም የአገር ፍቅር)፣ ሊሚኻድ (የሐረር ቁንጅና)፣ ዚማነት ዒድ (የሐረሪነት መገለጫ) በማለት ይገልጹታል፡፡

በሐረሪ ብሔረሰብ የተለያዩ የመተጫጫ መንገዶች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሹዋሊድ ቀን እንደሆነ የብሔረሰቡ የባህል አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ ይህ የበዓል ዕለት አንድ ወጣት ወንድ ለትዳር የምትሆነውን ልጃገረድ የሚመርጥበትና የሚያገኝበት ነው፡፡ በመሆኑም ዕለቱ ለወጣቶች ለወደፊት ሕይወታቸው ወሳኝ የሆነ ቀን ነው፡፡

የሹዋሊድ ክብረ በዓል ፋይዳዎች

የሹዋሊድ ክብረ በዓል በርካታ ፋይዳዎች አሉት፡፡ የሹዋሊድ በዓል መነሻው ሃይማኖት ቢሆንም፣ የአከባበር ሥርዓቱ ወይም ይዘቱ ባህላዊ ነው፡፡ በበዓል ሥነ ሥርዓቱ ላይ በየደረጃው ያሉ የብሔረሰቡ አባላት በተለይም ልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች ከምጊዜውም በላይ በብሔረሰቡ በአልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቀውና ተውበው የሚሳተፉበትና የሚታደሙበት ነው፡፡ የሹዋሊድ በዓል የሐረሪ ብሔረሰብን ባህላዊ አለባበስና አገረሰባዊ ጭፈራዎችን ከመጠበቅ ለትውልድ ከማስተላለፍ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...