Sunday, March 3, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በባህል ላይ የዘመቱ ክፉ ልቦች

በብርሃነ ዓለሙ ገሣ

ባህል ለአንድ አገር ምን ማለት እንደሆነ ማብራራት ድካም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ህልውና የተያያዘው ወይም የተጋመደው ከባህሉ ጋር ነውና፡፡ ስለ ኅብረተሰብ ወይም ስለ ማኅበረሰብ በደምሳሳው ስለ ሰው ለመናገር፣ ያለፈውን ታሪክ ለማውሳት፣ የወደፊቱን ለማውጋት ለበጎም ሆነ ለክፋት ባህል የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ነበርን የማያውቅ ነውን ሊረዳ አይችልም፡፡

የሰው ልጅ ባህሉን፣ ልማዱን… በመመልከት ያለፈውን ታሪኩን፣ ማንነቱን መናገር፣ የወደፊት ራዕዩን መተንበይ ይቻላል፡፡ ስለ ባህል፣ ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን በባህላዊ የጥናት ጽሑፉ ላይ ያነጠበውን እዚህ ላይ እጠቅሳለሁ፡፡

በባህል ላይ የዘመቱ ክፉ ልቦች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቸሃ ዋቅ ኦግየት – ምዕመናን በጭሽት በዓላቸው ታድመው

‹‹ባህል የአንድ ሕዝብ ማንነት መገለጫ ነው፡፡ ታሪክ ግን የሕዝቡ የማንነት ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ ሃይማኖት በእምነት እንደሚረጋገጥ ሁሉ ታሪክ በማስረጃ ይረጋገጣል፡፡ ባህል ደግሞ በሁለቱም ማለትም በእምነትና በማስረጃ ይረጋገጣል፡፡ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ሥልጣኔ ምንጫቸው ባህል ነው፡፡ የሁሉም አገናኝ ድልድይ ባህል መሆኑ ጥንትም ዛሬም ያለ ሀቅ ነው፡፡ ደም በሰው አካል ውስጥ ሕይወት እንደሚዘራ ሁሉ፣ ባህል ደግሞ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሕይወት ይዘራል፡፡ የባህል ሞት ከህልውና መራቆት ወይም ከሰብዓዊ ክብር መገፈፍ ጋር የተሳሰረ ረቂቅ የማንነት ዕጦት ነው፡፡ ባህሉ የሞተበትን ሕዝብ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጥገና ብቻ ሕይወት ሊዘራ አይችልም፡፡ ባህልና እምነት የጠፋበት ኅብረተሰብ፣ እንደ ጥንታዊው ባህልና እምነት የጠፋበት ኅብረተሰብ፣ እንደ ጥንታዊው ኩሽ ከግብፅ፣ ቀይ ህንዶች ከአሜሪካና ጥቁር አቦርጂኒያሎች ከአውስትራሊያ በቀላሉ ከምድረ ገጽ ይጠፋል…››፡፡

በዚሁ ጋዜጣ በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ ስለ ጉራጌ ብሔረሰብ (በተለይ ሰባት ቤት ስለሚባለው ምዕራቡ ቤተ ጉራጌ) ባህሎች፣ ሥነ ቃሎች፣ የሕይወት ውጣ ውረዶች፣ ድሎችና ሽንፈቶች በርካታ መጣጥፎችን ለንባብ አብቅቻለሁ፡፡ በዚህ ጋዜጣ አማካይነት ባህሉን በሚመለከት የተሳሳቱ በርካታ ወገኖች አቋማቸውን መርምረዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም መርምር፣ የተሻለውን ያዝ›› (ኵሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንዑ) የሚለውን የመጽሐፉን ቃል በተግባር በመፈተሽ ያወጡትን ሰይፍ ወደ አፎቱ እንዲመልሱ ተገደዋል፡፡ በአደባባይ ከማቅራራትና ከመቃወም ተቆጥበው ቢመራቸውም እውነታውን ለመረዳት ሰነዶችን ማገላበጥ፣ አዋቂዎችን መጠየቅ፣ ማንነታቸውን መመርመር ጀምረዋል፡፡

በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ፣ ሃይማኖቶች ወደ እዚያ ምድር ከመድረሳቸው በፊት ብሔረሰቡ/ማኅበረሰቡ ይተዳደር የነበረው በእነዚህ ባህላዊ እምነቶች እንደነበር በርካታ የታሪክ፣ የባህልና የሥነ ሰብ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ በተለይ በተለይ የውጭ አገር አጥኚዎች (አንትሮፖሎጂስቶች) እምድብር ከተማ ላይ ተቀምጠው ቆጮ በልተው ቡና ጠጥተው ጥናቶችን አጥንተዋል፣ መጽሐፎችን ለኅትመት ብርሃን አብቅተዋል፡፡

ቦዠ፣ የፍትሕና ርትዕ የመብረቅ መልዓክ፣ ደሟሚት፣ የማኅፀንና የልምላሜ መልዓክ፣ ዋቅ፣ የጦርነትና የዝናብ መልዓክ ሲሆኑ፣ ለእያንዳንዳቸው ፈጣሪ የሰጣቸውን ሥልጣን በመጠቀም የማኅበረሰቡ ሕይወት በተገቢው መንገድ እንዲቀጥል ሁነኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በተደጋጋሚ ስለ ባህሎቹ በአዲስ ዘመን፣ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያና በሪፖርተር ጋዜጦች እንዲሁም ‹‹ታንታዊ›› በሚል ርዕስ በ2013 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው መጽሐፌ ስለ ባህሎቹ ምንነትና ማንነት ለማመልከት ተግቻለሁ፡፡

እኔ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ በሙያ የሥነ ጽሑፍና የጋዜጠኛ ባለሙያ ነኝ፡፡ ጋዜጠኛና ጸሐፊ ብሆንም የተወለድኩበትንና ያደግኩበትን ማኅበረሰብ ባህል ችላ ብዬ አላውቅም፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከወጣትነት እስከ ጉልምስና፣ አሁን ደግሞ ወደ አዛውንትነት ምዕራፍ ለመሸጋገር በማኮብኮብ ላይ እስካለሁበት ጊዜ ድረስ ስለ ባህሎቹ በጥልቀት፣ ያለመሰልቸት ለመመልከት ዓይኔን ገልጫለሁ፣ ጆሮዬንም አቅንቻለሁ፡፡

ከሦስቱ ባህሎች የሚወጡ የማኅበረሰቡ እሴቶች ድንቅና ልዩ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ቦዠን እንውሰድ፡፡ ቦዠ ፍትሕና ርትዕ እንዲጠበቅ፣ የተወላጆች ንብረትም ሆነ ልዕልና እንዲከበር የኃላፊነት ሚናን ይጫወታል፡፡ ሌብነት ወይም ፍትሕ ጎድሎ በታየ ጊዜ ፈጣሪ ለቅጣት ቦዠን (መብረቅን) ይልካል፡፡ ቀላል ጥፋት ከሆነ ቀለል ያለና ዳግም ጥፋት እንዳይሠራ ለማስጠንቀቅ ያህል ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ እንሰት ላይ፣ መኖሪያ ቤት አንዱ ክፍል ላይ፣ የባህር ዛፍ ንብረት ላይ ወዘተ. ግለሰቡ ከበድ ያለ ጥፋት ያጠፋ እንደሆነ የመኖርያ ቤቱን እስከማቃጠል፣ ከፍ ሲልም የሕይወት ማጥፋት ዕርምጃ እስከ መውሰድ ይደርሳል፡፡ እያንዳንዱ ድርጊት ማኅበረሰቡ በደነገገው ድንጋጌ መሠረት ይከናወናል፡፡ ቦዠ፣ ንብረት ላይ ወይም ሕይወት ላይ ዕርምጃ ከወሰደ ሥርዓቱን የሚያጋፍሩት የቦዠን መልዓክ ተወካዮች ‹‹ማጋዎች›› ናቸው፡፡ ማጋዎች ለእያንዳንዱ ተግባር የሚገባውን እንዲፈጸም አድርገው፣ ኃጢዓተኛ ተብሎ የተፈረጀውን ግለሰብ ከጥፋቱ እንዲነጻ የቢተር ማውጣት ሥነ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡

ስለ ባህሎቹ ዘርዘር ያለ መረጃና ማስረጃ ለመያዝ በተለያዩ ጊዜያት የጻፍኳቸውን መጣጥፎች በሪፖርተር ጋዜጣና  በ‹‹ታንታዊ›› መጽሐፍ መመልከት ይቻላል፡፡

የዛሬው ጽሑፌ ዓብይ ምክንያት፣ በሰባት ቤት ጉራጌ ውስጥ ከሚገኙት አንዱ ስለሆነው የጎማረና የቸሃ ዋቅ ‹‹ኦግየት›› መጠነኛ ምልከታ ለማድረግ ነው፡፡ የወገፐቻ ደብር በቸሃና በጎማረ ቤተሰቦች (ቤተ ጉራጌዎች) አማካይ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ የቸሃና የጎማረ ዋቅ ኦግየት ክብረ በዓል በየዓመቱ ከኅዳር 15 እስከ 21 ባሉ የማክሰኞ ቀናት ይከበራል፡፡ በበዓሉ ላይ የሚቀርበው ትዕይንት ጣትን በአፍ የሚያስጭን፣ እጅግ ውብና ማራኪ መሆኑን ማንም በዓሉን የታደመ ሰው የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡

ለጎማረና ለቸሃ ዋቅ ኦግየት በዓል ምዕመናን ስለታቸውን፣ ገንዘብ፣ ግምጃ፣ ማር፣ ወይፈን፣ ዶሮ ወዘተ. ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ስጦታቸውንም ለባህሉ ተወካይ (ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ) ለወገፐቻ ደማም ያበረክታሉ፡፡

በተለይ ወይፈን፣ በሬ፣ ጊደር፣ ወዘተ ያመጡ ወገኖች ያመጡትን እንስሳ በባህሉና በሥርዓቱ መሠረት እዚሁ ወገፐቻ ላይ አርደው የበሉትን በልተው፣ የተረፋቸውን ወደቤታቸው ይዘው ይመለሳሉ፡፡ ለወገፐቻ ደማም በፈቃደኝነት አንድ ብልት ሊሰጡ ይችላሉ፣ ካልሰጡም የሚያስገድድ ሕግም ሆነ ደንብ የለም፡፡

በዚሁ የቸሃ ዋቅ ኦግየት ክብረ በዓል ደምቆና ጎልቶ የሚታየው ከጎማረ፣ ከቸሃ፣ ከኧዣ፣ ከግየታና አካባቢው የሚመጡ ፈረሰኞች የሚያካሄዱት ግልቢያ በጉራግኛ ‹‹ግይባት›› የሚባለው ነው፡፡ የሚካሄደው የፈረሰኞች ውድድር በቸሃ ዋቅ ውዳሴ በድራና ቀረርቶ እየታጀበ በፉጨት እየታገዘ አቧራው ይጨሳል፡፡ ወገፐቻ በአንድ እግሩ ይቆማል፡፡

በዚህ በዓል ላይ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችና ከባህር ማዶ ጭምር የሚመጡ ቱሪስቶች፣ የባህል አጥኚዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ጋዜጠኞችና ዘጋቢዎች… ይታደማሉ፡፡ ወገፐቻ የማኅበረሰቡ ነባር ቅርስ፣ ታሪክና የማንነት መገለጫ ከመሆኑ በተጨማሪ የአካባቢው የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅም ‹‹የዋቅ ዘገር›› በተለያዩ የአገር በቀል ዛፎች ተከብቦ አምሮና ተውቦ ይገኛል፡፡ ወገፐቻ ሁሌም እንዳማረበት ለዘመናት ኖሯል፡፡ ወደፊት በዚህ ውበቱ ይቀጥላል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችሉት የባህሉ ባለቤት የሆኑት የምዕራቡ ቤተ ጉራጌ በተለይ በተለይ ደግሞ የቸሃና የጎማረ ቤተ ጉራጌዎች ናቸው፡፡

የወገፐቻን ህልውና ለማጥፋትና በነበር ለማስቀረት በ‹‹ሃይማኖት›› ስም ዘመቻ ተጀምሯል፡፡ ባህል ረቂቅና ምጡቅ ነው፡፡ ሃይማኖትም እንዲሁ፡፡ እነዚህ ባህሎችን ከጉራጌ ምድር ለመሰረዝ ጦራቸውን የሰበቁ ሃይማኖትን ተገን ያደረጉ ወገኖች አይደለም ስለ ባህላቸው ቆምኩለት ብለው ምለው ለሚገዘቱለት ሃይማኖታቸው እንኳ ዕውቀት የላቸውም፡፡ ምሁራን ያጠኑትን ጥናት አንድ ገጽ ሳያነቡ አባቶችን፣ አያቶችንና ቅድመ አያቶችን ሳይጠይቁ ጠባብ ጭንቅላታቸው በመራቸው መንገድ እየተመሩ፣ ‹‹ባዕድ አምልኮ›› ብለው ፈርጀው ማኅበረሰቡን ያደነጋግራሉ፡፡ በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤና አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው ‹‹ዝመት በለው››ን ያውጃሉ፡፡

ለእነሱ ፍርፋሪ ማግኛ አንዳንድ ገራገርና የዋህ የብሔረሰቡ ተወላጆች ከገዛ ባህላቸው ጋር ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ ያደፋፍራሉ፣ ይሰብካሉ፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ካሳ ተከፍሎ፣ ይቅርታ ተጠይቆ የማይመለሰውን ነባርና ጉምቱ የብሔረሰቡ ባህልን ለማጥፋት ይተጋሉ፡፡ የባህል ፀሮች ጎሳን ከጎሳ ጋር በማላተም፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር በማጋጨት እነሱ በሃይማኖት ስም መኪና ይቀያይራሉ፡፡ ረብጣ ብር ይመነዝራሉ፡፡

ጉራጌ ድርቅና ጦርነት ሲያጋጥመው ወደ ፈጣሪ ‹‹መልዕክት ያደርስልኛል፣ ከፈጣሪም ግብረ መልስ ያመጣልኛል›› ብሎ ለቸሃ ዋቅ ኦግየት ኃላፊነት ሰጥቷል፡፡ ኦግየት ለዚህ ውለታው ዓመታዊው የ‹‹ጭሽት›› በዓሉ ይከበርለታል፡፡ የባህሉ ተከታዮች ወደ ወገፐቻ ጉዞ ሲያደርጉ የሚታየው ትዕይንት/ክዋኔ ደግሞ ሌላ ትልቅ ፊልም ይወጣዋል፡፡ የወገፐቻ ደማም ያበዜ በሚባለው ቦታ ካለው መኖሪያ ቤታቸው በባህሉ ተከታዮች ታጅበው የዋቅ ማሞገሻና ማወደሻ የሆነውን በድራ እየተንጎረጎረ ሥፍራው የበዓሉ ቦታ ይደርሳሉ ወገፐቻ፡፡ የጉራጌ ትውፊት በሚገለጽበት ወገፐቻ፣ እንዲሁም በመንገድ ላይ የሚከወኑት ክዋኔዎች ሁሉ ትርጉም አላቸው፡፡ ጭሽትን ለማክበር ሲመጡ ምዕመናን የሚይዙት ረዥም በትር መሰል ገምባውየ፣ ወገፐቻ ላይ በክብር የቆመው የዋቅ ዘገር፣ የስለት መቀበያ ቦታ ቋንቁር፣ ከዋቅ ዘገር ፊት ለፊት የቆመው ውቃብ ወዘተ፡፡

እዚህ ላይ ስለ ዋቅ ማወደሻና ማሞገሻ በተጓዳኝም የፈጣሪ ታላቅነት፣ ተባባሪነትና ፍትሐዊነት የሚገለጽበት ‹‹በድራ›› ሳይጠቅሱ ማለፍ ታሪኩን ጎዶሎ ያደርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሐፍ ዲፓርትመንት ውስጥ ስማር ዛሬ በሕይወት የሌሉት ተወዳጁ መምህሬ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በአንድ ክፍለ ጊዜ፣ ስለ ረዥም ቃላዊ የግጥም ዓይነት ረዘም ያለ ማብራሪያ ከሰጡን በኋላ፣ ተማሪዎች አስተያየት እንድንሰጥ ጋበዙን፡፡ የዚህ ዓይነት ቃላዊና ዜማ ያለው ግጥም  በኢትዮጵያ እንደሌለ ነገሩን፡፡ እኔ እጄን አውጥቼ በሰባት ቤት ጉራጌ ለዋቅ ማወደሻና ማሞገሻ በድራ የተባለ አንድ ሰው ብቻውን በራሱ ፉጨት እየታጀበ ከሁለት ሰዓት በላይ የሚያንጎራጉረው አለ፡፡ ርዝመቱም ከሁለት ሰዓት በላይ ሲሆን፣ የግጥሙም ምጥቀትና ጥልቀት ደግሞ የጉራግኛ ቋንቋ ምን ያህል ጉልበት እንዳለው በምሳሌነት ማሳየት የሚችል ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነም በቴፕ የተቀረፀ በድራ ስላለኝ ማምጣት እንደምችል በልበ ሙሉነት አረጋገጥኩላቸው፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን፣ ሰነዱን ይምጣም አይምጣም ሳይሉ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ ተለያየን፡፡ እኔ ሁሌም ይሄው ባገኘሁት አጋጣሚ አነሳዋለሁ፡፡

የሥነ ሰብ አጥኚዎች አንድ ሊሉ ይገባል፡፡ ይህ ድንቅ የባህል ቦታና ትዕይንቱ የሚካሄድበትን ወገፐቻ ህልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ፀረ ባህሎች፣ ጭሽት እንዳይከበር የተለያዩ ሥልቶችን በመንደፍ ዘመቻ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ዘመቻቸውን ውጤታማ ለማድረግ የባህሉን ቦታ በቤተ ክርስቲያን ሽፋን ለማጥፋት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ባልጠፋ ቦታ የባህሉ ሥፍራ የሆነው ወገፐቻን በቁጥጥራቸው ሥር በማዋል አንዳንድ የወረዳ ጀሌዎቻቸውን ተማምነው ዕርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፡፡ የጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ የቸሃ ወረዳ አስተዳደር፣ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ነባር ባህሎች በመጤዎች ሲበረዙ፣ ሲከለሱና ሲጠፉ ቆመው እያዩ ናቸው፡፡ የባህሉ ተወካይ ነን የሚሉትም ቢሆኑ ከመሰሪነት የተላቀቁ አይደሉም፡፡ እብለታቸው ከልክ በላይ ነው፡፡

የጉራጌ ማኅበረሰብ/ብሔረሰብ ማንነቱ አደጋ ላይ የሚወድቀው ወይም የወደቀው በራሱ ተወላጆች መሆኑ ይህ ማረጋገጫ ነው፡፡ በርካታ ባለ ደንታዎችን በስልክና በአካል አነጋግሬያለሁ፡፡ በርካታ ቃለ ምልልሶችን በሬዲዮና በቴሌቪዥን አድርጌያለሁ፡፡ በብዙ የሚቆጠሩ መጣጥፎችን በአዲስ ዘመን፣ በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በሪፖርተርና በተናገር ጋዜጦች፣ እንዲሁም በአገር ውስጥና በውጭ በሚታተሙ መጽሔቶች ስለ ጉራጌ ብሔረሰብ ባህል የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ፡፡ ከልብ የምወደው የጫሙት ሽካ ረዥም የጉራግኛ ልበ ወለድ መጽሐፍ ደራሲ ጓደኛዬ፣ ዘመዴና አማካሪዬ ገብረ ኢየሱስ ኃይለ ማርያም እንዳለው፣ ‹‹ጉራጌዎ! የቀነና አህር ተዋካንከም፣ የጅወና አህር ተስሬመንከም›› ማለት ባልችልም፣ ሰሚ ሲጠፋ ቀጣፊዎችና ፀረ ባህል የሆኑ ወንጀለኞች ሲከበሩና ሲወደሱ ማየት ግን በእጅጉ ያማል፡፡

ሰፊው የጉራጌ ሕዝብ ለማንነቱ፣ ለባህሉ፣ ለቋንቋ፣ ለሥነ ቃሉ ከወዲሁ ካልታገለ ታሪኩ ከምድረ ገጽ እንደሚጠፋ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነቈ የልጃገረዶች የነፃነት በዓል፣ ሰንቸ የደሟሚት ክብረ በዓል፣ ንፑዋር የቦዠ ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ ጎተነ ዓመታዊው የገበሬው ዕረፍት ማድረጊያ ጊዜ፣ ይዳር ሞየቶች፣ አንትሮሽት  የእናቶች በዓል፣ ግሩየ የጉራጌ ዘመን መለወጫና የእንሰት በዓል፣ ምየት የቤተ ዘመድ ሸንጎና የቤተሰብ ቆጠራ፣ ወርቸ የከብቶች በዓል ወዘተ፡፡ አንዳንዶቹ ባህሎች በመጥፋት ላይ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ለመጥፋት በሒደት ላይ ናቸው፡፡

ጉራጌ ሲያከብራቸውና ሲንከባከባቸው ኖሮ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ እየጠፉ ነው፡፡ የብሔረሰቡ አባላት የራሳቸውን ጥለው የሌሎችን በማወደስና በማመሥገን ታሪካዊ ቦታዎችን፣ ባህላዊ ሥፍራዎችን ማውደም ጀምረዋል፡፡ አንዱ ዘማሪ ነኝ ባይ ዳተኛ ክሊፑን የዋቅ ዘገርን እያመለከተ እየተራገመና እያስረገመ ዘምሮ የዋቅ ዘገር እንዲቃጠል አድርጓል፡፡ ይህ አጥፊ በሠራው መጥፎ ሥራና በሠራው አስነዋሪ ሥራ የጠየቀው የለም፡፡ ይባስ ብሎ ሌሎች የቀሩትን የብሔረሰቡ ነባር እሴቶች ለማጥፋት መርሐ ግብር ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ምን ልንለው እንችላለን? ቀልብ ይስጠው ከማለት ሌላ፡፡ አውቀን በመታበይ፣ ሳናውቅ በስህተት ለሠራነው ሁሉ ፈጣሪ የእጃችንን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሔር በስማ በለው የሚታለል የከንቱዎች አምላክ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ለማምለክ መጀመሪያ ልቦናችንን ለኔትወርኩ ክፍት ማድረግ አለብን፡፡ በማስመሰል አገር አይመራም፣ በማስመሰል ሃይማኖት አይቀጥልም፡፡

በመጨረሻም፣ አንድ ሰሞን የኬንያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆሞ ኬኒያታ ተናገሩት በተባለው ዝነኛ አባባል መጣጥፌን አጠናቅቃለሁ፡፡ ‹‹ነጮች/አውሮፓውያን መጽሐፍ ቅዱስ ሰጡን፡፡ አንብቡ ብለውን አነበብን፡፡ ተንበርክካችሁ ጸልያችሁ መሬት ሳሙ አሉን፡፡ መሬት ሳምን፡፡ መሬት ስመን ቀና ስንል መሬታችንን ቀምተውን አገኘን›› የነገ ተነገ ወዲያ ሰው ይበለን፡፡ ከትውልድ ተወቃሽነት አንድዬ ይጠብቀን፡፡ አሜን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles