Friday, March 1, 2024

ፖለቲካዊ ንግግር በምን መንገድ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዋናነት ሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚዎች ወደ ፖለቲካ ንግግር እንዲገቡ የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡ መንግሥትና ሕወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር አንዱ ሌላኛውን እንቅፋት ሆነብኝ እያሉ ሲከሱ ቆይተዋል፡፡ የፖለቲካ ንግግሩ መቼ ነው የሚጀመረው የሚለው ጉዳይ ላለፈው አንድ ዓመትም በእንጥልጥል ቆይቷል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራን የሚከታተለውና ቅሬታ ሰሚ (Monitoring Verification & Compliance Mechanism-MVCM) የሚባለው የጋራ ኮሚቴ ሦስተኛ ስብሰባ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዳይተገበር ያደረጉ እንቅፋቶችን መመርመሩ ታውቋል፡፡ ይህ ስብሰባ የሕወሓት፣ የመንግሥትና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች የታደሙበት ሲሆን በማጠቃለያውም የጋራ ኮሚቴው የሰላም ስምምነቱ ቀጣይ የትግበራ ምዕራፎች እንዲጀመሩ አቅጣጫ ማስቀመጡን፣ ከሰሞኑ ከወጣው የኅብረቱ መግለጫ መመልከት ተችሏል፡፡

ፖለቲካዊ ንግግር በምን መንገድ? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህመት ጋር

ሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚ ወገኖች በዚህ ስብሰባቸው ግፋ ቢል ከሁለት ወራት ባልበለጠ የጊዜ ገደብ የደረሱበትን ውጤት እንዲያሳውቁ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በሌላ በኩል የስምምነቱን ትግበራ የሚከታተለው፣ የቁጥጥርና ቅሬታ መስማት ሥራዎችን የሚያከናውነው የጋራ ኮሚቴ (MVCM) እስከ አንድ ዓመት ኃላፊነቱ እንዲራዘም መወሰኑም ታውቋል፡፡

የስምምነቱ ቀጣይ የትግበራ ምዕራፍ መሆኑ የተነገረው የፖለቲካ ውይይት መጀመር ጉዳይ በምን መንገድ ይሄዳል የሚለው ጉዳይ በሰፊው እያወያየ ነው፡፡ ሁለቱ ወገኖች የሚያደርጉት የፖለቲካ ንግግር ምንን ያጠቃለለ ነው የሚለው የተለያዩ ግምቶችን እያሰጠ ነው፡፡

ሒደቱ በጅምር ቆሟል የሚባለውን የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሥራን ለማገዝ፣ የአፍሪካ ኅብረት የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መሰጠቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ተግባር ተቋቁሞ የነበረው በተሾመ ቶጋ (አምባሳደር) የሚመራው የተሃድሶና የመልሶ ማቋቋም ኮሚሽን ሥራው በበጀት እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ፈተና እንደሆነበት በተደጋጋሚ ሲናገር ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ በፖለቲካ ንግግሩ ይካተታል ተብሎ የሚገመተው ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋምና ወደ ሰላማዊ ሕይወት የማስገባት ምን ውጤት ይገኝበታል የሚለው ተጠባቂ ሆኗል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ የፖለቲካ ንግግሩ ዋነኛ የትኩረት ጉዳይ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው በሽግግር ፍትሕ ማስፈን ላይ የሚካሄደው ንግግር ይመስላል፡፡ ሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚ ወገኖች ከዚህ ቀደም በሽግግር ፍትሕ ማስፈን ጉዳይ ላይ ልዩነት ሲያራምዱ እንደቆዩ የሚታወስ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥት ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮችን በተመለከተ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ እንዲካፈል ጋብዞ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ግብዣ የሽግግር ጊዜ አስተዳደሩ በሰጠው ምላሽ በመድረኩ ላይ መገኘት እንደማይችል ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ደብዳቤው አስታውቆ ነበር፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በዚሁ ደብዳቤው ላይ ስለሽግግር ፍትሕ ጉዳይ የማነሳቸው ጥያቄዎች አሉ ሲል የተለያዩ ነጥቦችን አስቀምጧል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚያዝያ ወር የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የመሩት የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን ወደ መቀሌ በመሄድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቀራረፅ፣ ሒደትና አደረጃጀትን በተመለከተ ውይይት መደረጉንና የራሱን ሐሳብ በዚያው አጋጣሚ ማንፀባረቁን ያስታውሳል፡፡

በዚህ የመቀሌ ውይይት የፌዴራል መንግሥቱ የጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አንደኛ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ያልተከተለ፣ ሁለተኛ የትግራይን ልዩ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ፣ ሦስተኛም የትግራይን ወሳኝ ተሳትፎ ያላካተተ መሆኑን በግልጽ ማስታወቁን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ደብዳቤ ያወሳል፡፡

በጊዜው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ጉዳዩን ከማፋጠን በዕርጋታ መምራት እንደሚያስፈልግ ተገልጾ ነበር ሲል ደብዳቤው ያስረዳል፡፡ ከዚህ በዘለለ የትግራይ ሕዝብ ጊዜ የማይሰጡ ጥያቄዎችና ፍላጎቶችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት መተማመንን መገንባት ሊቀድም እንደሚገባ አመልክተን ነበርም ይላል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ደብዳቤ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ተቻኮለ ቢልም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህ ጉዳይ በቶሎ መጀመር እንዳለበት አጥብቆ ሲወተውት መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ከሰሞኑ በአሜሪካ ኮንግረስ (ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት) የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ፊት የኢትዮጵያ ጉዳይ በተነሳበት ወቅት፣ የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ሒደቱ ተንቀረፈፈ የሚለው ጥያቄ በጉልህ መቅረቡ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

የጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደብዳቤ የትግራይ ምሁራን በተለይም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ አቀራረፅ፣ ሒደትና አደረጃጀትን በሚመለከት አስተዳደሩ ያነሳቸውን ቅሬታዎች የሚደግፉ ሐሳቦች ማንፀባረቃቸውን ነው ያወሳው፡፡

ይህን የዘረዘረው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ደብዳቤ በማጠቃለያው፣ ‹‹የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሠረት በማድረግ በእኛ በኩል የሚነሱ ሐሳቦችን በጥልቀትና በግልጽ አንስተን ለመወያየት እንዲቻል የፊት ለፊት የሁለትዮሽ ውይይት ይመቻችልን፤›› በማለት ነው በጊዜው ጥያቄ ያቀረበው፡፡

የዛሬ አንድ ዓመት ማለትም እ.ኤ.አ. ጃኑዋሪ 2023 ተረቆ የቀረበው የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ ረቂቅ ውስጥ ሒደቱ በምን መንገድ መመራት እንዳለበት የሚጠቁም ዝርዝር ሐሳብ ተቀምጧል፡፡ እውነት ማፈላለግ፣ ዕርቅ፣ ይቅርታ፣ ካሳ አሰጣጥም ሆነ ሌሎችም የሽግግር ፍትሕ ሒደቶች ከዚህ ቀደም የነበሩ የአገሪቱን ልምዶችና ዕውቀቶችን በቀመረው መንገድ መዘጋጀታቸውን ነው ሰነዱ ያሠፈረው፡፡

ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ሲያመረቅዝ የቆየ ቁስልና ቁርሾ ያለባት አገር እንደሆነች የሚያብራራው የሽግግር ፍትሕ ማስፈጸሚያ የፖሊሲ አማራጩ፣ ዓለም አቀፍ ልምድና ዕውቀቶችን በመቀመር መንገድ መዘጋጀቱን ይገልጻል፡፡ የሰብዓዊ መብቶችን ባሟላና ተጎጂዎችን ባማከለ መንገድ ሒደቱ እንደሚከወንም ያብራራል፡፡ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታም ታሳቢ በማድረግ መረቀቁን ነው ይህ ሰነድ የሚገልጸው፡፡

የመንግሥት የሽግግር ፍትሕ ሰነድ ይህን በግልጽ ቢያስቀምጥም፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግን በዚህ በኩል መተማመን እንደሌለው ነው በጳጉሜው ደብዳቤና በሌሎች አጋጣሚዎችም ደጋግሞ ያስታወቀው፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና የፌዴራል መንግሥት በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ያለ ልዩነት መነሻው ሒደቱ ከምን ይጀምር በሚለው ጉዳይ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሕወሓት የትግራይ ባለሥልጣናት የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ከትግራይ ጦርነት ጉዳይ እንዳይወጣ ይፈልጋሉ ይላሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ (በሰሜን ኢትዮጵያ) ጦርነት የታጠረ ብቻ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን እስከያዘበት እስከ 1983 ዓ.ም. ያሉና ከዚያም ያለፉ የኢትዮጵያ ቀውሶችና ችግሮች በሽግግር ፍትሕ ሒደቱ እንዲዳኙ የመፈለግ አዝማሚያ አለው ይላሉ፡፡

የሕወሓት (የትግራይ) ባለሥልጣናት ሒደቱ ከትግራይ ጦርነት አይለፍ የሚሉት ደግሞ ወደኋላ መመለሱና የጊዜ ርቀቱ መስፋቱ፣ እነሱንም ወደ ተጠያቂነት የመክተት አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችል በመሥጋት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የሽግግር ሒደቱ በውስን የጊዜ ርቀት የታጠረ ይሁን የሚል ፍላጎት ማንፀባረቃቸውና ይህም ከመንግሥት ወገን ጋር በጉዳዩ አላግባባ እንዳላቸው ግምት እያሰጠ ነው የሚገኘው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ለኮንግረሱ ከሰሞኑ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር ፈተና የሆኑ ጉዳዮችን በሰፊው አንስተዋል፡፡ ‹‹ስምምነቱ ከተፈረመ ጀምሮ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ ለዜጎችና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንዲደረግ አሜሪካ ስትደግፍ ቆይታለች፡፡ አሜሪካ ዓለም አቀፍ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ ቡድን ገብቶ ሁኔታውን እንዲያጣራም የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን አንቶኒ ብሊንከን አሜሪካ የሰብዓዊ ወንጀል የፈጸሙ ወገኖች ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደምትፈልግ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ከስምምነቱ በኋላ በትግራይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቀውስ መቀነሱን በአዎንታዊነት ተመልክተነዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ብዙ ለውጥ እንጠብቃለን፡፡ የኤርትራ ጦር ከያዛቸው የትግራይ አካባቢዎች ለቆ መውጣት አለበት፡፡ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራው ሊቀጥል ይገባል፡፡ የሚያጨቃጭቁ የወሰን አካባቢዎች ጉዳይም መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በዚህ የተነሳ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ገና ዳር ያልደረሰና በሒደት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ የሰላም ዕጦት ችግሮች ዕልባት ማግኘት አለባቸው፤›› በማለት ነበር፣ የአሜሪካና የኢትዮጵያን ግንኙነት የሚወስኑ ስላሏቸው ጉዳዮች ልዑኩ በሰፊው የተናገሩት፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና የፌዴራል መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ባሉበት ከሰሞኑ ያደረጉት ስብሰባም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲተገበሩ ጫና እያደረገባቸው ላሉ ለእነዚህ ጉዳዮች መልስ ለመስጠት የሚያስችል መግባባት የተደረሰበት መሆኑ እየተነገረ ነው የሚገኘው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ወገን በተቀመጠው የሁለት ወራት የጊዜ ገደብ እጅግ አጨቃጫቂ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ በምን ሁኔታ ከመግባባት ይደርሳሉ የሚለው ከወዲሁ ጥያቄ እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡

ለአብነት በቅርቡ የፕሪቶሪያው ስምምነት አንደኛ ዓመት ሲከበር መንግሥትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በየፊናቸው በሰጧቸው መግለጫዎች፣ የፖለቲካ ንግግር በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋሞች ፍፁም የተራራቁ እንደሆኑ የሚያመለክቱ መረጃዎች አንፀባርቀዋል፡፡

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በወቅቱ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹መሬታችን መጀመሪያ በእጃችን ሳይገባ ስለአጨቃጫቂ ቦታዎች ማውራት ምንድነው? የኤርትራና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ መሬት ነቅለው ሳይወጡ እንዴት ስለአጨቃጫቂ ቦታዎች ልናወራ እንችላለን?›› ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡

የፕሪቶሪያው ስምምነት በትግራይ ክልል የጥይት ጩኸትን ማስቆሙ፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች ድጋሚ እንዲጀመሩ ዕድል መፍጠሩ በአዎንታዊነት የሚቀበሉት አጋጣሚ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ሕወሓትን ከሽብር መዝገብ እንዲሰረዝ የማድረጉና ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ እንዲመሠረት የማድረጉ ሒደት ለፖለቲካ ውይይቶች መጀመር መንገድ የሚጠርግ ነው ብለው ቢያምኑም፣ ይሁን እንጂ በዚህ በኩል በሚጠብቁት ልክ የተሻለ ውጤት እንዳላዩ ነው የገለጹት፡፡ ለትግራይ ክልል በጀት መለቀቁን እንደ ትልቅ መሻሻል እንደሚመለከቱት የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ ይሁንና የፕሪቶሪያው ስምምነት ያስቀመጣቸውንና በፖለቲካ ውይይት ዕልባት ማግኘት ያለባቸው አጀንዳዎችን ከዳር ለማድረስ ብዙ ጥረት እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ከዳር ለማድረስ መንግሥት ብዙ ርቀት መሄዱን ጠቅሶ ነበር፡፡ ‹‹አከራካሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ አቋም ወስዶ ሠርቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም ወገን በሚጠቅም መንገድ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ብልፅግና በሚያረጋግጥ መንግድ መፍትሔ መስጠት አለበት፤›› የሚለው የመንግሥት መግለጫ ተፈናቃዮች፣ ወደ እነዚህ ቦታዎች ተመልሰው በሕዝበ ውሳኔ ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝ መንግሥት መወሰኑን አስታውቆ ነበር፡፡

መንግሥት በተለይም የኢፌዴሪ መከላከያ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የትግራይ ክልልን የመቆጣጠርና ሕግ የማስከበር ሥራዎችን የመረከብ ሙሉ መብት እንዳለው መግለጫው ያትታል፡፡ ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ሕዝብ ሥነ ልቦና፣ እንዲሁም የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ እንዳይረበሽ በማሰብ መከላከያ በስፋት እንዳይሠፍር መደረጉን ያተተው መግለጫው፣ መንግሥት ለፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መተግበር ብዙ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም በዚያኛው ወገን ግን ‹‹እግር የመጎተት ሁኔታ ይታያል›› በማለት ነበር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን የወቀሰው፡፡

ዓርብ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት አካባቢ ዘግይቶ በወጣ መረጃ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር የሰላም ስምምነቱን ቀጣይ የትግራይ ክልል ምዕራፍ ለማፋጠን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ተሰምቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -