Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም ከየአካባቢው ወረዳና ቀበሌ አመራሮች ጋር በመሆን ‹‹ሕገወጥ›› ያሏቸውን ማስታወቂያ ሰሌዳዎች ሲያስነሱ ሰንብተዋል፡፡ ለፀሐይ መከለያ የተሠሩ ሼዶችና በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ናቸው ያሏቸውን ግንባታዎች በማፈራረስና በማስነሳት ተጠምደዋል፡፡ በዘመቻ መልክ እየተወሰደ ያለው ሰሞናዊ ዕርምጃ ግን ብዥታ የሚፈጥር ነው፡፡ ሕግና ደንብ እናስከብራለን የሚሉት አካላት ድንገት ብንን ብለው የሚወስዱት ዕርምጃ ብዙ ጊዜ ግራ ከመጋባት ባለፈ፣ የአሠራራቸው ሕጋዊነት ራሱ ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው፡፡ 

ሕገወጥ የተባሉት ማስታወቂዎች ሰሌዳዎችና ለፀሐይ መከለያ ተብለው የተዘረጉ ጥቃቅን መከለያዎች አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ነበሩና ድንገት ይነሱ የተባለበት ምክንያትም ግራ ያጋባል፡፡ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ነው እንዲፈርሱ ወይም እንዲወገዱ የሚደረገው የሚል ጥያቄ ማስከተሉም አይቀርም፡፡ ዛሬ ሕገወጥ የተባሉት ማስታወቂያዎች ሕገወጥ ከሆኑ ሕግ አስከባሪው አካል ቀድሞውኑ ነበር ዕርምጃ መወሰድ የሚገባው። የንግድ ተቋማቱ ለማስታወቂያዎቹ ብዙ ወጪ ካወጡ በኋላ መልሰው እንዲያፈርሱ ማድረግ ፈፅሞ አግባብ ሊሆን አይችልም፡፡  

አንዳንዶቹ ማስታወቂያዎች ሲሰቀሉ ያዩ ደንብ አስከባሪዎች የወረዳ አመራሮች በእከክልኝ ልከክልህ ዓይተው እንዳላዩ በመሆን ያለፏቸው እንደሆኑም መገመት አያቅትም፡፡ ስለዚህ ደንብ አስከባሪዎቹም ሆኑ ይህንን የመቆጣጠር ሕጋዊ ኃላፊነት ያለባቸው የወረዳና የቀበሌ አመራሮች በፈለጉት ጊዜ የሚፈቅዱትና በፈለጉት ጊዜ ከልካይ የሆኑት በየትኛው የሕግ አግባብ ነው? የምንልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሠራሩ ላይ ችግር እንዳለ ማሳያ የሚሆነን በአንዳንድ ወረዳዎች ሕገወጥ ተብለው የተነሱ ማስታወቂያዎችና ግንባታዎች በሌላ ወረዳ አልተነኩም፣ አልፈረሱም፡፡ ስለዚህ አሠራሩ ወጥነት የሌለው መሆኑን ያሳያል፡፡  

በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ይዞታ ላይ የሚንጠልጠሉና የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች እንዴት ነው አገልግሎት ላይ መዋል ያለባቸው? የሚባለው ጉዳይ ግልጽ ባለመሆኑ ብዙዎች ሲቸገሩ እያየን ነው፡፡ የራሳቸውን ማስታወቂያ የንግድ መደብራቸው መስኮት ላይ ለማንጠልጠል የሚከላከለው ወይም የሚፈቅደው ሕግ ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ደንብ አስከባሪዎች ‹‹ሕገወጥ ነው›› በሚል እያነሱና እያስፈረሱ የሚቀጥሉት እስከ መቼ ነው? በተመሳሳይ መንገድ የተሰቀለ ማስታወቂያ በአንዱ ወረዳ ሕጋዊ፣ በሌላው አካባቢ ሕገወጥ የሚሆንበት ምክንያቱ ምንድነው? በእርግጥ ይህንን የሚመለከት ጥርት ያለ ሕግ ካለ መከበር አለበት፡፡ ሕግ አስከባሪው ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ሕግ እንዲከበር የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበትም የሚጠራጠር መኖር የለበትም፡፡ ተገልጋዩም እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ከሕጉ ጋር የተስማማ ማድረግ ይጠበቅበታል ብቻ ሳይሆን ግዴታው ነው፡፡ ነገር ግን ሕጎች በዘፈቀደ ከተተረጎሙ ሕግ እየተተገበረ አይደለም፡፡ ሕግ ለአንዱ የሚሠራ ለሌላ የማይሠራ መሆን የለበትም፡፡ በሕግ ማስከበር ስም ሌላ ሕገወጥ ተግባር እንዲፈጸም በር መክፈት የለበትም፡፡ 

በዘመቻ የሚወሰዱ እንደ ሰሞኑ ዓይነት ዕርምጃዎች ትልቁ ችግር ሕጋዊ የሚባሉትን ሁሉ አብሮ የሚደፈጥጥ መሆኑንም መታዘብ ተችሏል፡፡ አንድ ሁለት ቦታዎች ይህንን መመልከት ችያለሁ፡፡ የማስታወቂያ ሰሌዳቸውን ለመስቀል ይመለከተዋል ከተባለ መንግሥታዊ ቢሮ ክፍያ ፈጽመው ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ማስታወቂያቸውን እንዲያነሱ ታዘው አፍርሰዋል፡፡ 

ለደንብ አስከባሪዎቹ ማስታወቂያውን በሕጋዊ መንገድ ስላለመሰቀላቸውና ለዚህም ክፍያ የፈጸሙበትን ደረሰኝ ቢያሳዩም ሰሚ አላገኙም፡፡ ለዚህም ነው የደንብ ማስከበር ተግባሩ ጤናማ ያልሆነ የጠራ አሠራር የሌለው ነው የሚባለው፡፡ ሕጋዊ ነው ተብሎ መንግሥት የጠየቀውን ዋጋ ለመክፈል ተስማምቶ ማስታወቂያውን በውድ ዋጋ አሠርተው የሰቀሉ ሕጋዊ የንግድ ድርጅቶች ‹‹የለም ሕጋዊ አይደላችሁም ይህንን አንሱ ካላነሳችሁ እኛው እናነሳዋለን›› ሲሉ ማድመጥ በራሱ ያማል፡፡ 

ከሰሞኑ ዕርምጃ ሌላው የታዘብኩት ነገር ሕገወጥ ናቸው የተባሉ የማስታወቂያዎች ሰሌዳዎችና ፀሐይ መከላከያዎችን ባለቤቶቹ የማያነሱ ከሆነ ሕግ እናስከብራለን የሚሉት ወገኖች ማስታወቂያዎቹን የሚያነሱበት መንገድ በእጅጉ አሳዛኝ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ማስታወቂያዎች ከድርጅቱ ግንባታ ጋር የተያያዘ፣ መነሳትም ካለበት በጥንቃቄ ቢሆንም፣ በዘፈቀደ የሚወሰደው ዕርምጃ ንብረት ላይ ጉዳት ሲያደርስ ተመልክቻለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱ ብዙ ችግሮችን የሚያስከትል ብቻ ሳይሆን፣ በሕገወጥ ስም የሚነሱ ማስታወቂዎችም ሆኑ ሌሎች ንብረቶች በአግባቡ እንዲነሱ ማድረግን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ እንደ ቀላል ነገር መታየት እንደሌለበት አንዳንድ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየቦታው በአነስተኛና መካከለኛ መደብሮች ይዞታ ላይ የሚሰቀሉ  አነስተኛ ማስታወቂያዎች በትልልቅ ኩባንያዎች ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ናቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን የንግድ ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ በይዞታቸው ላይ የሚያኖሩት ማስታወቂያ ገንዘብ የወጣበት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ንብረት ናቸው፡፡ አንድ ንብረት ደግሞ ሕጋዊም ይሁን ሕገወጥ መነሳት ወይም መወገድ አለበት ከተባለ ሕጋዊ አካሄድን መከተል ያስፈልጋል የሚባልበት አንዱ ምክንያት የሚደረገው ጉዳት ለመቀነስ ቢሆንም ይህ አይታሰብም፡፡ ንብረት እያወደሙ ሕግ እያስከበርን ነው ማለት በፍፁም ሕጋዊ አይሆንም፡፡ ጉዳዩን ጠለቅ ብለን ከተመለከትን በሕግ ማስከበር ስም ብዙ ወጪ የወጣበትን ንብረት በዘፈቀደ ቀንጥሶ መጣልና ጥቅም አልባ ማድረግ ጉዳቱ የድርጅቶቹ ወይም የግለሰብ ነጋዴዎች ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ በየትኛውም ቦታ ያለ ንብረት የአገርም ነው፡፡ 

አንድ የማስታወቂያ ሰሌዳ ሲዘጋጅ ለማስታወቂያው ያለ ጥርጥር 90 ከመቶ በላይ የሚሆነው ግብዓት የሚመጣው ከውጭ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጣ ዕቃ ደግሞ አገር በሌላት የውጭ ምንዛሪ የሚመጣ ነው፡፡ ጉዳዩ ንብረቱን የግለሰቦች አድርጎ መውሰድ የለበትም፡፡ ይወገድ የተባለው የማስታወቂያ ሰሌዳ ሕገወጥ ቢሆን እንኳን ሕጋዊ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቀዳሚው መፍትሔ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕገወጥ ከተባለም አወጋገዱ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ 

አየሩ ሁሉ የእኔ ነው ያለው የአዲስ አበባ አስተዳደርም ቢሆን ዛሬ የሚያነሳቸው ማስታወቂያዎች ሕጋዊ እንዲሆኑ የከተማዋ ገጽታ በማያበላሽ መልኩ እንዲሰቀሉ ለማድረግ አሠራሩን በተገቢው መንገድ ሳያስረዳ የሚስጥር ሕግ ያለ ይመስል ሕገወጥ ብሎ ማፍረስ ትክክለኛ አካሄድ አይሆንም፡፡ ሕግ እንዲያስከብሩ የመደባቸውም ደንብ አስከባሪዎች ሥነ ምግባር እንዲህ ያለውን አሠራር በአግባቡ የሚተገብሩ ናቸው ወይ? ብሎ ማሰብንም ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ ትልልቅ ኩባያዎች እኮ በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች በተለይ መደብሮች ላይ የሚሰቅሏቸው ማስታወቂያዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ማስታወቂያዎች መሰቀል አይችሉም ከተባለ በግልጽ መነገር አለበት፡፡ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ያለው ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ከደንብ አስከባሪዎች የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ትክክል አይደለም ተብሎ አቤት የማይባልበት መሆኑ ነው፡፡ ዕርምጃቸው ትክክል አይደለም ብለው የሚሞግቱት ካሉ የሚሰማቸው የለም፡፡ በቂ መከራከሪያ ያላቸው ወገኖች ሕጋዊ መሆናቸውን አስረድተው ድርጊቱን ለማቆም ያለመቻላቸው በራሱ አሠራሩን ግድፈት በግልጽ ያሳያል። ሕጋዊ ነኝ ያሉ መረጃቸውን አቅርበው ሳለ መረጃቸውን አረጋግጦ በአግባቡ መልስ መስጠት ካልተቻለ የዜጎች መብት እየተነካ ነው ማለት ነው፡፡  ስለዚህ ደንብ ማስከበር በሕግና በአግባቡ ይመራ አሠራሩም ግልጽ ይሆን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት