Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፖለቲካ ውሳኔ ያስፈልገዋል የተባለው የትግራይ ክልል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በትግራይ ክልል ወቅታዊ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ስለመምጠቱ እየተገለጸ ነው፡፡ ችግሩ ሥር የሰደደ ከመሆኑ አንፃር መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ የማይሰጥበት ከሆነ ችግሩ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን ለአገርም የሚተርፍ ይሆናልም የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይና በተለይም ባንኮች በክልሉ ለሚገኙ ተበዳሪዎች የሰጡት ብድር ዙሪያ በተደረገ ምክክር ላይም የጉዳዩ አሳሳቢነት በተለያየ መንገድ ተንፀባርቋል፡፡ በዕለቱ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት አታክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተንኮታክቷል ነበር ያሉት፡፡

ጉዳቱ ጥልቅ ለመሆኑም የተያዩ ማሳያዎችን በመጥቀስ ያብራሩት ጥናት አቅራቢው በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች እንቅስቃሴዎች ከመቅረጣቸውም በላይ የወደመውን ንብረት መልሶ ለመገንባት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ያለመኖር ክልሉን ወደቁልቁል እየወሰደው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለየ ሁኔታ ድጋፍ የማይደረግለት ከሆነ የከፋ ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑ የንግድ ኅብረተሰብ የተሰጡት አስተያየቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

የትግራይ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረሥላሴ እንደገለጹትም በክልሉ ያለው ወቅታዊ ኢኮኖሚ ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው፡

ኢንቨስትመንትና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ ይህንን መልሶ ለመገንባት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም ውጤት እየመጡ ያለመሆኑን ያስረዱት አቶ አሰፋ በተለይ በክልሉ ላሉ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰጠን ብድር ለመክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ መንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ ሊወሰን ካልቻለ ችግሩ በክልሉ ብቻ የሚያቆም ያለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በክልሉ በተካሄደው አካዴሚ ጦርነት የሰው ሕይወት ከመጥፋቱም በላይ ለብዙ ዘመናት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፣ ተቃጥለዋል፣ ተዘርፈዋል›› ያሉት አቶ አሰፋ አብዛኞቹ ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ናቸው ይላሉ፡፡ የተዘረፉትን በጣም ጥቂት የሚባሉትን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ቢሞክርም በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በዋግ ንረት ምክንያት ነገሩ የማይቀመስ ሆኗል ብለዋል፡፡

ይህንን ውድመት መልሶ ለመተካትም እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል የትግራይ ከጦርነት በኋላ እየገጠመ ያለው ችግር ደግሞ የህልውና ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት አታክልቲ (ዶ/ር) ችግሩ ከቅም በላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በተለይ በክልሉ ለሚገኙ የተለዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰጠውን ብድር መልሱ የሚለው ጥያቄ ከጦርነቱ በኋላ ኅብረተሰቡን እንቅልፍ የነሳ መንግሥት የፖሊሲ ዕርምጃ ካልወሰደ በቀር ብድሩን ሊመለስ የማይችል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በአታክልቲ (ዶ/ር) በቀረበው ጥናት ከተለያዩ ባንኮች በክልሉ ለሚገኙ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰጠው ብድር ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ስለመድረሱ አስታውሰው ይህ የብድር መጠን ከነወለዱ ሲሰላ አሁን ላይ ወደ 60 ሚሊዮን ብር መጠጋቱን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህንን የመክፈል አቅም የሊለ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖማው እንዲነቃቃ ሊወሰዱ የሚገባቸው ዕርምጃዎች አለመወሰዳቸው ችግሩን እንዳባባሰው ጠቅሰዋል፡፡

በትግራይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳዩ መረጃዎች በሙሉ በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መቆሙን የሚያመላክቱ ስለመሆኑ የገለጹት ጥናት አቅራብው በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ያሉት እንቅስቃሴዎች ተንገራግጨው ቆመዋል፡፡

በክልሉ ያለው አጠቃላይ የአቅርቦት ሰንሰለት በመቋረጡ አቅራቢዎች በሙሉ ሥራቸውን አቁመዋል፡፡ የንግድ ድርጅቶች ተንኮትኩተዋል ሊባል በሚችል ደረጃ የሚገልጹ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በቱሪዝም በግብርና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ በተለያየ ደረጃ ሲሠሩ የነበሩ ኩባንያዎች አሁን ላይ ምንም እንቅስቃሴ የማያደርጉ በመሆኑ የመፍትሔ ያለ እያሉ ነው፡፡ በግብርና ዘርፍ ያለው ሁኔታም ቢሆን ችግር ውስጥ የወደቀ መሆኑን የገለጹት ጥናት አቅራቢው ለእርሻ ግብዓትም ሆነ የሚያቀርበው የለም፡፡ ግብዓት ለመግዛት ቢፈለግ እንኳን ለግብዓቱ የሚሆን ፋይናንስ እየቀረበ ያለመሆኑ ቀጣዩን ጊዜ የማይተነብይ አድርጎታል፡፡

በተለይ ዘመናዊ እርሻ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ኩባንያዎች ለኢንቨስትመንትቸው የሚጠቀሙባቸው ካምፖቻቸውና የእርሻ መሣሪያዎቻቸው በሙሉ የወደመና የተዘረፈ በመሆኑ አንሠራርተው ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም፡፡ ሠራተኞች ተበታትነዋል፡፡

ትግራይ ውስጥ የነበሩት የቢዝነስ ዓይነቶች 422 እንደነበሩ ያስታወሱት ጥናት አቅራቢው እነዚህ የቢዝነስ ዓይነቶች በሙሉ አሁን ላይ ችግር ውስጥ በመግባታቸው የቢዝነስ እንቅስቃስው የለም፡፡

በእነዚህ የቢዝነስ ዓይነቶች ሥር ከነበሩት ለምሳሌ ኤክስፖርት ተኮር ኩባንያዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶችን የሚያመርቱ 6,778 እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች አሁን እየሠሩ አይደለም፡፡ በዚህ አካባቢ የደሰውን ጉዳት በየዘርፉ ወደሙ ያሏቸውን የተቋማት በቁጥር ጭምር በጥቀስ ማብራሪያ የሰጡት አታክልቲ (ዶ/ር) በክልሉ ያልተጎዳ የቢዝነስ ዘርፍ ያለመኖሩንም አመልክተዋል፡፡

በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ስለመሆኑ የገለጹት አትክልቲ (ዶ/ር) የባንክና የአነስተኛ የብድር ተቋማት ቅርንጫፎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ንብረታቸው ተዘርፏል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሀን ሠራተኞቻቸው ጭምር የተገደሉባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ጉዳቱ በዚህ ብቻ የሚገለጽ ያለመሆኑን የገለጹት ጥናት አቅራቢው ካለው ችግር አንፃር አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም እየመጡ ያለመሆኑ ችግሩን እንዳባሰው ጠቅሰዋል፡፡

የሚመጡ እንኳን ቢኖሩ ለኢንቨስትመንታቸው የሚሆን ቦታና የመሳሰሉትን ለማግኘት እንደ ማዘጋጃ ቤታዊ ያሉ ሥራዎች ተደራጅተው ባለመጀመራቸው መስተናገድ አይችሉም፡፡

እንዲህ ያሉት ተደራራቢ ችግሮች በኅብረተሰቡ ላይ እያሳደሩ ያሉት ተፅዕኖ ከባድ ከመሆኑም በላይ ያለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ ለሚባል የዋጋ ንረት ጭምር እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡

ዕቃዎችን በቀላሉ ገዝቶ ለማምጣት ከባድ ከመሆኑም በላይ ገንዘብ ያላቸው የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የሚሠሩት መሆኑ ገበያውን እንደፈሉገ እየሰቀሉት መሆን የችግሩ አንድ አካል ሆኗል፡፡

በክልሉ ያለው አሁናዊ ኢኮኖሚ ሁኔታ ክልሉ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ያበረክት የነበረውን አስተዋጽኦ አሳጥቷል፡፡ ከጦርነቱ በፊት ክልሉ ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ የነበረው አስተዋጽኦ ከ8.4 በመቶ በላይ መሆኑን የገለጹት ጥናት አቅራቢው አሁን ይህ ሊኖር ባለመቻሉ የትግራይ ጉዳት አገራዊም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ ከክልሉ መቅረብ የሚገባው ወርቅና እንደ ሰሊጥ ያሉ ምርቶች ለማዕከላዊ ገበያ ሊቀርብ አለመቻሉ በራሲ የሚያሳየው ነገር ስላለ የክልሉን ችግር መፍታት አገራዊ ችግርንም መፍታት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ሐሳብ ያጠናከሩት አቶ አሰፋ በበኩላቸው በተለይ በክልሉ ላይ የተጤነው የዕዳ ጫና መፍትሔ እስካልተበጀለት ድረስ ሁሉም ተጎጂ ይሆናል ብለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት አካላት ጋር በተለያየ ደረጃ እየተመከረበት ቢሆንም መፍትሔ አልመጣም፡፡ ሆኖም ይህንን ጥረት በመቀጠል መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ የሚሄዱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ክልሉ የሁሉም ወገን ዕገዛ እንደሚሻ የገለጹት አቶ አሰፋ አሁን ላይ ከሰላም ሚኒስቴር እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታው አቶ ታዬ ደንደና በዚህ ጦርነት ወጪ አውጥተን ብዙ ጥፋት ደርሷል አሁን ደግሞ ይህንን ክልል መደገፍ ግድ የማል በመሆኑ ሁሉም ወገን በየዘርፉ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ የዕዳ ጫናውንም ለመቀነስ በሕጋዊ መንገድ ጫናው ያጠቃለለበትን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለበት በመሆኑ ይህንን ጫና ሊያቃልል የሚችል መፍትሔ የሚሻ ነው፡፡ የነበረው ዕዳ ሳያንስ አሁን የተጨመ የመጣው የባንክ ብድር ይከፈል እየተባለ በመሆኑ አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ደግሞ መክፈል የሚቻልበት ዕድል ስለሌለ ማቆሚያው ሊታወቅ የሚችል እንሆነም አብራርተዋል፡፡

አሁን በክልሉ ያለው የፋይናንስ እጥረትን ለመቅረፍ በተወሰነ ደረጃ ብድር ለመስጠት እየተደረጉ ያሉ ሙከራዎችም እንቅፋት እየገጠማቸው እንደሆነም ከተደረገው የዳሰሳ ጥናት መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

አታክልቲ (ዶ/ር) እንደተናገሩትም በቅርብ ጊዜ ብድር ለመስጠት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች በቅርቡ የወጣው የብሔራዊ ባንክ የባንኮች የብድር ምጣኔ ገደብ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ መመርያው ትግራይንም የሚመለከት በመሆኑ ብድር ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶችን እያደረገ በመሆኑ ይህ መመርያ በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጻሚ እንዳይሆን መደረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ አታክልቲ ሌላው መፍትሐ ብለው የጠቀሱት ደግሞ አሁን ሥራ ላይ ያሉት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች በተለይ ሊታይ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡

የተወሰነ ድጋፍ ተደርጎ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ተቋማት የሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሪም ለመለዋወጫዎች በሚል የተፈቀደ በመሆኑ ይህም ሊፈተሽ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ በጦርነት የነበረን አካባቢ እንዲያገግም ለማድረግ ነባር ሕጎችን በማስቀጠል ውጤት ስለማይመጣ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ያለው ሌላው አሳሳቢ ችግር የሥራ አጥነት መበራከት መሆኑን በጥናታቸው ተመልክተውታል፡፡ በቅርቡ 16 ሺሕ ሰዎችን በመውሰድ የተደረገ ጥናት እደሚያመለክተው እነዚህ ውስጥ 81 በመቶው ሥራ የሌለው መሆኑን ያረጋገጠ ሆኗል ብለዋል፡፡

ይህንን መረጃ የተለየና አሳሳቢ የሚያደርገው ቀደም ብሎ ሥራ አጥ የሚባለውና አሁን ሥራ አጥ በሆነው መካከል ሰፊ ልዩነት በመኖሩ ነው ይላሉ፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ ‹‹የድሮ ሥራ አጥ ዕገዛ እየተደረገለት ሥራ ለማግኘት ተስፋ የሚያደርግ ነው›› ይላሉ፡፡

አሁን ግን በክልሉ ያለው የሥራ አጥ ሥራ የነበረው ቤተሰብ ያለው እንዲያውም በጦርነቱ ሳቢያ ወደ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ገብቶ ቀላል ሳይሆን ከባድ መሣሪያ መፍታትና መግጠም የሚችል ነው ሥራ አጥ የሆነው›› በማለት የአሁኑ ሥራ አጥ ወታደራዊ ልምድ ያለው ጭምር በመሆኑ አደገኛ ነው ይላሉ፡፡

አደገኛ የሚሆንበትም ምክንያት መልሶ ወደ ሥራ ካልገባ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ችግር ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለአገርም አደጋ እንደሚሆን ሥጋትቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ አሁን ላለው ችግር መባባስ አንዱ ምክንያት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ተፈጻሚ ይሆናሉ የተባሉ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች አለመሠራታቸው ነው ተብሏል፡፡

የመልሶ ግንባታው ኢኮኖሚ በማኅበራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ላይ የሚሠራ ከመሆኑ አንፃር የታክስ ማበረታቻች ሌላው የመፍትሔ አካል ሊሆን እንደሚገባ ያመላከቱት ጥናት አቅራቢው የኢኮኖሚ ሁኔታው ወደ ታች እየወረደ ስለሚሆን የታክስ ማበረታቻ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

በዕለቱ በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው በተለይ ከባንክ ሥራ ጋር በተያያዘ ባንኩ የወሰናቸውን የተለያዩ ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ያብራሩ ሲሆን ከዚህም በኋላ ሊመለከታቸው የሚገቡ ጉዳዮች ካሉ የሚመለከትና መፍትሔ የሚሰጥባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች