Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ምሁራንም ሆኑ የሲቪል ማኅበረሰቦች በፖሊሲ ቀረፃና መሰል እንቅስቃሴዎች ለመንግሥት ያስፈልጋሉ›› አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር)፣ የቀድሞ ፖለቲከኛና የውኃ ሀብት ተመራማሪ

በምርጫ 97 ጊዜ በእጅጉ ከሚታውሱት ውስጥ ቅንጅት ለአንድትና ዴሞክራሲ የነበው ሚና ሲሆን፣ በጊዜው የታሪክ አሻራ አኑሮ ያለፈ ስብስብ ነበር፡፡ ቅንትን ከመረቱት አራት የፖለቲካ ድርቶች መካከል የኢዴአፓ መድን ከፍተኛ አመራር እንዲሁም የቅንአመራር አባል የነበሩትና የአዲስ አበባ ዩቨርቲ ምሁሩ አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር) ይታወሳሉ፡፡ በወቱ በነበረው የፖለቲካ ትግል ስማቸው ከየሚነሱ ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው፡፡ ምርጫውን ትከትሎ ከገዥው ፓርቲ ኢአዴግ ጋር በነበችግር ምክንያት ስዊድን ተሰ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚስትር ብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ልጣን ሲመጡ ለምሁራን ባደጉት ጥሪ መሠረት ወደ አገራው ተመልሰው በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማካሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ሲሳይ ሳህሉ አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባልና አመራር፣ አሁን ደግሞ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ የተጓዙባቸውን ሦስቱን መንገዶች እንዴት ያዩዋቸዋል?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- እንግዲህ ሦስቱም ሥራዎች ናቸው፡፡ በሙያዬ የውኃ ሀብት መሐንዲስ ነኝ፣ አሁን የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አማክራለሁ፡፡ ፖለቲከኛም ነበርኩ፣ በተለይ እስከ 1997 ዓ.ም. በአመራርነት አገልግያለሁ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ በርካታ የፓርቲ አመራሮች እስር ቤት ታጎሩ፡፡ እኔና ባለቤቴ ካልታሰሩት ውስጥ ነበርን፡፡ በዚህም የተነሳ እንደ ፖለቲከኛ መንቀሳቀስ ባንችልም ከእስር ቤት ውጪ ነበርን፡፡ ቆይቶ ግን የእኛ ተራ ደርሶ ችግር ውስጥ ልንገባ ስንል አገር ውስጥ መቆየት አልቻልንም፣ ልጆች ለማሳደግ ስንል ስደት ገባን፡፡ በስደት ጊዜ ከአገርህ ስትወጣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ተገቢ ነው የሚል እምነት እኔና ባለቤቴ አልነበረንም፡፡ ይሁን እንጂ አርፎ መቀመጥም ደግሞ ችግር አለው፣ ጭንቅላትህም አይቀበለውም፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚደረገው እንቅስቃሴ ትክክለኛ ዓላማ ይዞ እየሄደ ነው ወይ የሚለውን ጉዳይ መረመርኩ፡፡ በምርምር ውጤቱ መሠረት ‹‹መግባባት›› የሚባል መጽሐፍ ጻፍኩ፡፡ መጽሐፉ በ2010 ዓ.ም. ታትሞ የመጀመርያው ዕትም ተሽጦ አለቀ፡፡ እንደገና ያንኑ መጽሐፍ ሦስት አዳዲስ ምዕራፎች ጨምሬ በማሻሻል ለማሳተም ፈልጌ ነበር፡፡ ነገር ግን ዋጋው ውድ በመሆኑ አብዛኛው አንባቢ ገዝቶ ማንበብ ስለማይችል፣ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ እንዲያነብ በነፃ እንዲሠራጭ እያደረግኩ ነው፡፡ መጽሐፍ በይዘቱ የተለየ ነው፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ነው ወደ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መጥቼ በነፃ የማማከር ሥራ እየሠራሁ ያለሁት፡፡

ሪፖርተር፡- በ1997 ዓ.ም. በነበረው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትግል ሙቀት፣ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በትልቁ የሚነሳ ታሪክ ነው፡፡ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ የሚጠበቀውን ግብ እንዳልመታ ይወሳል፡፡ በዚህ የፖለቲካ ትግል ምን ዓይነት ሚና ተጫውቻለሁ ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- የፖለቲካ ፓርቲ ለአገር የሚያደርገው አስተዋጽኦ በጣም ትልቅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በርካታ ፓርቲዎች ወደ አንድ መጥተው ቢሠሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን በአገራችን በገዥነት መደብ ሥልጣን ላይ ያሉ ወገኖች ይብዛም ይነስም ረዥም ዕድሜ ሊኖራቸው ቢችልም፣ ፓርቲዎች ግን ጠንካራ ሆነው መቀጠል የሚያስችል ዘላቂ ቁመና አልፈጠሩም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመጀመሪያው የሀብት ችግር ነው፡፡ ምናልባት ዓላማና ቁርጠኛ የሆነ የትግል ጽናት ኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአባላት የሚገኝ መዋጮ አቅም አይሆንም፡፡ ቢሮ ከፍቶ ለመንቀሳቀስና ቀጥሮ ማሠራት የሚያስችል አቅም የለም፡፡ ሌላኛው አለመታደል ደግሞ በሥልጣን ላይ ያሉ ወገኖች አጋዥ አይፈልጉም፡፡ ዓይናቸው፣ ልባቸውና መንፈሳቸው የሚያርፈው እነሱ ሥልጣን ላይ ሆነው የኢትዮጵያን ሕዝብ መግዛት ላይ እንጂ ማስተዳደር አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ አመለካከት ቢሻሻል የእነሱን መሰል የተለያዩ ፓርቲዎች ከሚያቀርቡት ሐሳብ ጋር እየተፋጩ ህልውናቸው እንዲቆይ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚያ አልፎ ደግሞ ለአገር የተሻለ ነገር ከታሰበ እንዲህ ዓይነት ፓርቲዎች ዓላማቸውንና ፍላጎታቸውን ሊያሳካ የሚችል ድጋፍ በፓርላማ ተወስኖ ሊደረግላቸው ይችላል፡፡ በተለይ በቂ ቁመና አላቸው ተብለው የሚታሰቡትን ሕዝብ አማራጭ እንዲኖረው በማሰብ የግድ ሥልጣን ላይ ባይኖሩም፣ ሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ በተጨማሪ ሌላ ዕይታና አስተሳሰብ ያላቸውን ፓርቲዎች ሕዝቡ እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህን ማድረግ ይቻል ነበር፣ ግን ባለመደረጉ ለዚያም አልታድልንም፡፡ እኔ ፓርቲ እያልኩ የምናገረው ወይም የፖለቲካ ትግል የምልህ በወቅቱ ያለውን የአገር ሕግና ሥርዓት ጠብቆ፣ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በሕግ ሥር ሆኖ የሚንቀሳቀሰውን የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ ነገር ግን ሕገወጥ በሆነና ሕግ በማይፈቅደው መንገድ ጠመንጃ ይዞ ለሥልጣን የሚሮጠውን እንደ ፓርቲነት አልቆጥረውም፡፡ ፓርቲ ማለት በሰላማዊ መንገድ የሚደረገውን ትግል የሚከተለውን ነው፡፡ ይህ ደግሞ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ትልቅ ሥራ ነው፣ ቀላል አይደለም፡፡ ሌላው ችግር የፓርቲዎች መብዛት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 100 የሚጠጉ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ለአንድ አገር ቢያንስ ሦስት ቢበዛ ደግሞ ስድስት መሆን እንዳለባቸው ነው የሚታመነው፣ ከዚያ ውጪ ግን ትርጉም አልባ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን የበዛ ቁጥር እንዴት መቀነስ ይቻላል?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- መቀነስ ይቻላል፡፡ በፓርቲ ደረጃ ነግሠው መኖር የሚፈልጉ አመራሮች ችግሩን ተመልክተውና ለአገር አስበው ሰብሰብ ለማለት ቆርጠው መነሳት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ስትሰባሰብ አንድ ጉዳት አለች፡፡ እሷም ምንድናት ወንበር ትታጠፋለች፡፡ ምክንያቱም ሦስት አራት ፓርቲዎች የነበሩ በአንድ ሊቀመንበርና በአንድ ምክትል ሊቀመንበር ይመራሉ፡፡ ያንን የሚያደርጉት ትግሉ ለሕዝብ ከሆነ ነው፡፡ ለግል ጥቅም ከሆነ ለትግል መሰባሰቡ ኪሳራ ነው የሚያመጣባቸው፡፡ ለሕዝብ ከሆነ ግን በመሰባሰብ ወንበር ቢታጠፍም ሆነ ማንኛውም የኃላፊነት ደረጃ ቢደርስህ ትልቅ ፓርቲ ውስጥ መካተት ከትንሽ ፓርቲ የተሻለ ነው፡፡ ዓላማን ግብ ለማድረስ ጠንካራ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ መንቀሳቀስ እኔ አሁንም ምክሬ ነው፡፡ ቅንጅት የሚባለው የፓርቲዎች ስብስብ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላም የነበረው የውህደት ሒደት አይረሳም፡፡ አራት ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው ሊያገኙለት ከሚችሉት በላይ አንድ በመሆናቸው ቀርፈፍ ያለ ሳይሆን ዝላይ ያለው ለውጥ ተፈጥሯል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት እርግጥ ነው አራቱ ፓቲዎች አንድ ቅንጅት ሲፈጥሩ እንደ አንድ ፓርቲ ነበር የምንሠራው፡፡ ሊቀመንበሩ አቶ ኃይሉ ሻውል እኔ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆኜ አብርን ሠራን፡፡ ለእኛ ግን ያ ሹመት አልነበረም፡፡ በወቅቱ ዓላማችንም በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጥ እንጂ በፓርቲ የሚኖረን ሥልጣን አልነበረም፡፡ በዚያን ጊዜ ‹‹ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ›› የሚል የኃይሉ አርዓያ (ዶ/ር) አባባል የሁላችንም መፈክር ነበረ፡፡ እኛም ያንን ተቀብለን ካለመተባበር መተባበር ይሻላል የሚል አቋም ያዝን፡፡ ትብብር በመፍጠራችን በሕዝቡ ዘንድ አመኔታው እያደገ ሄዶ በአካልም ያላየን በወሬ እየሰማ ‹‹አይ ፖለቲካ›› ሲል የነበረው ሁሉ አንድ ላይ ስንመጣ ተጨማሪ አባል፣ ተጨማሪ ድጋፍ አመጣ፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መንግሥትን ይፈሩ የነበሩ ሁሉ በርቱ እያሉ ለሻይ፣ ለቡና፣ ለቢሮ ኪራይም ይሁን በርቱ የሚሉ፣ ከጎናችሁ ነን የሚሉ እየበረከቱ መጡ፡፡ እና ይኼ ነው ሚስጥሩ፡፡ ፓርቲዎች ሲሰባሰቡ የገንዘብ ድጋፍ፣ ተጨማሪ የሰው ኃይል፣ የአዋቂዎች ክምችት፣ የጠነከረ ወኔና መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ በእኛ ጊዜም የኢሕአዴግ ደጋፊዎች የነበሩ፣ መታወቂያቸውም የኢሕአዴግ የሆኑ ፓርቲያቸውን በመሰልቸትና ዓላማውን ባለመውደድ የተነሳ በይፋ ባይደግፉንም በተለያዩ ቦታዎች ስንንቀሳቀስ አይዟችሁ  አሉን፡፡ በፊት ቢሆን የሚተናኮለን ሳይቀር ቢያንስ ዓይተው እንዳላዩ ሆኑ፡፡ ደበቅ ብለውም በርቱ ይሉንና ይመክሩን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በቅንጅት ውስጥ የእርስዎ አስተዋጽኦ ወይም ሚና ምን ነበር?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- በፓርቲው ውስጥ የቅንጅትን የሁለት ጣት ዓርማ የፈጠርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ በፓርቲው አሠራር መሠረት ሥራ አስፈጻሚው ለምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ሲመርጥ፣ እንደ አጋጣሚ በሕመም ምክንያት እኔ በቦታው አልነበርኩም፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ የተመረጠው ጥቁር አንበሳ ነበር፡፡ ከዚያ እኔ ተሽሎኝ ስመጣ ይህን ጉዳይ ማስጨረስ የእኔ ኃላፊነት ስለነበር ያንን ጥቁር አንበሳ ምልክት ይዤ ወደ ምርጫ ቦርድ ሄድኩ፡፡ ይህ ምልክት የሶማሌ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ስለያዘው መጠቀም  አትችሉም ተባልን፡፡ እንደገና ተመልሰን ተሰባስበን ሌላ ማሻሻያ አድርገን ምልክቱን መፍጠር ስለማንችል፣ በድንገት የራሴ ጭንቅላት ውስጥ ይብላላ የነበረውንና በበፊቱ ስብሰባ ብኖር ላቀርበው የነበረ የሁለት ጣት ምልክት በብዙ አገሮች የተለመደ በመሆኑ፣ የራሴን ጣት አራት ኪሎ ከሚገኝ ፎቶ ቤት አስንስቼ ወደ ቢሮ ሄድኩ፡፡ ለጓደኞቼም በስልክ እየደወልኩ ነገርኳቸውና ለቦርዱ አስረከብኩ፣ ምልክት ሆኖ ፀደቀ፡፡ ይህ በ1997 ዓ.ም. ለነበረው አገራዊ ምርጫ በጭንቅላቴ የታገልኩበት ሥራ ነበር፣ እንዳሰብኩት ተሳክቶልኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ቅንጅት እንደ አንድ ስብስብ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ ነገር ግን የአጭር ጊዜ ትዝታ ሆኖ ነው የቀረው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በቅንጅት ድክመት? ወይስ በገዥው ፓርቲ ጫና?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- እኔ እንግዲህ ቅንጅት ሲፈርስ አልነበርኩም፣ ምክንያቱም በይፋ ስለመፍረሱም አላወቅኩም፡፡ መጀመሪያ ከቁንጮ አመራሮች ውስጥ ጥቂቶች ነን ሳንታሰር የቀረነው፡፡ ያ ማለት ፓርቲው ያለ አመራር ስሙ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን የነበረውን ክብር፣ ዝና፣ አቅምና ማንኛውም በጎ ነገር ሊቀጥል አይችልም፡፡ በዚያ ምክንያት መፍረስ የምትለው ላይ ባይደርስም በጣም ሊዳከምና ስሙ ብቻ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ የነበሩት አመራሮች አብዛኞቹ እስር ቤት ቢሆኑም፣ ውጭ ያለነው አመራሮች ህልውናው እንዲቀጥል ሙከራ አድርገን ነበር፡፡ ከዚያ ሙከራ ውስጥ ቅንጅትን አዲሱ የውህደት ስም ለመስጠት በማሰብ እነዚያ ውህደት ሊፈጥሩ ያሰቡ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት የነበራቸውን የግል ሰርተፊኬት መመለስ ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም ሁለት መታወቂያዎች መያዝ አይቻልም፡፡ በዚያም የተነሳ በመኢአድ፣ በቀስተ ደመናና በኢዴሊ በኩል ተሳካ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ በምመራው ፓርቲ  ኢዴአፓ መድኅን በኩል ሳይሳካ ቀረ፡፡ ይህ የሆነው ኢዴአፓ መድኅን በውህደት ምዝገባ ላይ እኔ እንደ መሪ ፊርማ ስፈርምበት፣ የተፈረመው ላይ የድርጅት ማኅተም መደረግ ነበረበት፡፡ ነገር ግን የድርጅት ማኅተም የያዘው አቶ ልደቱ አያሌው የፓርቲው ጸሐፊ ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ እኔ ስላልነበርኩ ምክትል ሊቀመንበሩ ኃይሉ አርዓያ (ዶ/ር) አቶ ልደቱ ማኅተም አልመታም ብሎ እንቢ ሲላቸው፣ ሌላ ማኅተም አስቀርፀው ፊርማውን ሲያስገቡ ክስ ቀረበባቸው፡፡ የተጭበረበረና የተሰረቀ በሚል ማለት ነው፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የእኛን ጉዳይ ምክንያት ማድመጥ እንኳ አልፈለገም፡፡ እኛ ግን አሁንም በአራት ፓርቲዎች ሊደረግ የነበረውን ውህደት በሦስት ፓርቲዎች፣ ማለትም ከእኛ ፓርቲ ውጪ እንዲመሠረት ጥረት አድርገናል፡፡ ምርጫ ቦርድ የሦስቱን ፓርቲዎች ውህደት ተቀብሎት ነበር፡፡ በዚህ መሀል ውህደቱን ከመሠረቱት የአንዱ ፓርቲ መሪ ጉዳዩን ምርጫ ቦርድ አስፈጽመን ስንመለስ የደኅንነት ሰዎች ጠለፉትና ሲያስፈራሩት ይህ ሰው መቀጠል አልችልም አለ፡፡ ውህደቱን ለመመሥረት ካቀዱት አራት ፓርቲዎች ሁለት ቀሩ፡፡ ከዚያም የቅንጅት ውህደት በእንጥልጥል ቀረ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ቅንጅት ፈረሰ ወይስ ምን ገጠመው ነው የሚባለው?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- አቆመ ልትለው ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም ተፈጠረ አትለውም፣ ከመጀመሪያውም ለምርጫ የተፈጠር ነበር፡፡ በመጀመሪያ ተልዕኮው በጥምረት ምርጫ ተወዳደረ፡፡ ከምርጫ በኋላ ግን በውህደት ነበር ፓርቲ ሊሆን አስቦ የነበረው፡፡ ይህ ውህደት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ትልቅ ክስተት ይሆን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች እናንተንም ጨምሮ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ስታደርጉ ከውስጣዊ መገፋፋታችሁ ባለፈ ከመንግሥት የበረታ ክንድና ጫና የተነሳ ከሰላማዊ ትግል ወደ በረሃ ትግል የመሄድ አዝማሚያ በተጋጋሚ ሲታይ ነበር፡፡ አሁንም በአንድም በሌላ ምክንያት ጥያቄ አለን የሚሉ አካላት ጫካ ገብተዋል፡፡ እርስዎ ይህን ከሰላማዊ ትግል ወደ ጫካ ትግል የመሄድ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- ኢትዮጵያ በጫካውም ሆነ በሌላ መንገድ ያለውን ትግል አየችው፡፡ አሁን እንግዲህ እየተባለ ያለው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል አስቸገረን ነው፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል ስታየው ደግሞ ሲዋጉ የኖሩት ሁሉ የት ደረሱ? አለመድረሳቸው ሳይሆን የደረሰው ኪሳራ ከባድ ነው፡፡ እኛ እኮ የታሰርነው በራሱ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ነገር ግን መገዳደሉን ነው እንደ ትልቅ ኪሳራ ማየት አለብን፡፡ ወያኔ በብዙ ኢምፔሪያሊስቶች ማዕቀፍና ድጋፍ ሥልጣን ላይ መውጣት መቻሉ እንጂ፣ በጠመንጃ ብቻ የፈጠረው ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ ባለቤት መጀመሪያ ሕዝብ ነው፡፡ ፖለቲካ በውክልና የተሰጠን ሥልጣን በአግባቡ ሊጠቀም የሚችል ተመራጭና ተወካይ ሲኖር እንጂ፣ ከዚያ ባለፈ በጉልበት የሚካሄድ ትግል ፖለቲካ አይደለም፣ የሠለጠነ ፖለቲካም አይባልም፡፡ እናም በዚህ አስተሳሰብ ምንም ይሁን ምን ሰው ላይ ተረማምደህና ገድለህ የምታገኘው ሥልጣን፣ ወገንና ወገን ተጨፋጭፎ የሚገኝ የፖለቲካ ጥቅም ሕዝባዊ ጥቅም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰላማዊ ትግል ወደ ጫካ የገቡ አካላት ሕዝባዊ ድጋፍ አለን ይላሉ፣ ለትግላቸውም ዝባዊ መረት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ እርስዎ ስለዚህ ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- እኔ ሕዝባዊ ድጋፍ አላቸው ብዬ አላምንም፡፡ ምንድነው ያለው ነገር ስትል ምንጊዜም ጠመንጃ ስትይዝ አቅም አለህ፣ በዚህ አቅም ታስፈራራለህ፡፡ ሌላውም አንተን የሚይዝህ በጠመንጃ አፈሙዝ አስፈራርቶ ነው፡፡ በረሃ ከሚሄደውም አሠለፍነው፣ አንበረከክነው የሚለውን እያየነው ነው፡፡ ከመንግሥት ኃይል የበለጠ የሚፈራ ኃይል የእነሱ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ኃይል የዲፕሎማሲን ተፅዕኖ ይፈራል፣ ትንሽም ይሁን ትልቅ ሕግና ሥርዓት አለ፡፡ ይህም ብዙ ሙከራ አለበት፡፡ መንግሥት በጥይት ተኩሶ ለመግደል ድፍረቱም አይኖረውም፡፡ የመንግሥት አካል ሊያስር ሊያሰድድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ያለ ፍርድ በመንግሥት የሚገደሉት በጣም ውስን ናቸው፡፡ በዚያኛው በኩል ስትገባ ግን ዳኛውም ጠመንጃ ነው፡፡ ፍርዱም ስቀለው ግደለው እንጂ ይግባኝ የለውም፡፡ እና የጠመንጃ ትግል ያለበት ውስጥ ስትገባ ከአንደኛው በስተቀር ከሌላ ቃል እንዳትሰማ፣ ከሌላ ሐሳብ እንዳትቀበል የታፈንክ ነህ፡፡ ሁለተኛ በጥቃቅንም ሆነ በጎሉ ችግሮች ያደነዝዝሃል፡፡ ለምሳሌ አሁን ትግራይ ውስጥ የነበረውን ተመልከት፡፡ አይደለም በበረሃ ሆነው ሥልጣን ይዘውም የትግራይ ሕዝብ እንደ እኔና እንደ አንተ ቁራጭ ጋዜጣ እንኳ ማንበብ አይችልም ነበር፡፡ በር ዘግተህ አፍነኸው ከእኔ ጋ ነው ብትል አሳማኝ አይደለም፡፡ ለቀቅ አድርገኸው ለሚለውና ለሚያደርገው ነፃነት ሰጥተኸው ማኖር የሚባል ፖለቲካ በታጣቂዎች ውስጥ አይሠራም፣ ብትነጋገርም በሹክሹክታ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ዘመን ተሻጋሪ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ማየት የሚቻለው ምን ቢደረግ ነው?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- እንግዲህ እዚህ ዳኝነት ውስጥ ገብቼ ባልናገር ይሻለኛል፣ አታነካካኝ፡፡ በአጠቃላይ ድክመት እንዳለ ቅድም ነግሬሃለሁ፡፡ የድክመቱ ምንጭ ዋነኛው ለመሰባሰብ ወኔ ማጣት ነው፡፡ ካልተሰባሰብክ ደግሞ አትጠነክርም፡፡ ሁለተኛው ተሰባስበው ቢመጡ ደግሞ የፋይናንስ አቅም የለም፡፡ ለምሳሌ ገዥው ፓርቲ በእኛም ጊዜም ሆነ አሁን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመንግሥትን ሀብት ይጠቀማል፡፡ ለዚህም ነው ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ድጋፍ ይሰጥ የምለው፡፡ ከሲቪል ሰርቪስና ከተሿሚነት ጋር በተገናኘ የገዥው ፓርቲ በመንግሥት መደገፍ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት የሚጠቀሙባቸው አማራጮች አሉ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጠንከር ለአገር ይጠቅማል በሚል ድጋፍ ቢያደርግላቸው መልካም ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሰባሰቡ፡፡ ምክንያቱም የተሰባሰበ ሲመካከር፣ ሲነጋገር፣ ሲወያይና ሲከራከር ይበስላል፡፡ ያ ሲሆን ሕዝቡ በራሱ ሚዛን እየመዘነ ይመጣል፡፡ ለፓርቲዎች መነሳሳት ይጨምራል፡፡ ፓርቲዎች ሲሰባሰቡ ይጠነክራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ቁጥራቸው የበዛ ፓርቲዎችን ለመምረጥ ደረጃ ለማውጣትም ይቸገራል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ አሁን ምን ይነት የፖቲካ መስመር ላይ ነዎት?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- የፖለቲካ ፓርቲ አባል አልሆንም፡፡ አሁን የበለጠ ነፃ ነኝ፡፡ ነገር ግን ወጣቶችን በማሠልጠንና በማማከር መሳተፍ እችላለሁ፡፡ ለብልፅግናም ሆነ ለሌሎች ፓርቲዎች ወጣቶች ሥልጠና እሰጣለሁ፡፡ ከብልፅግና አልገጠመኝም፣ ነገር ግን ጥሪ አቅርቤያለሁ፡፡ ባጠናሁትና በማውቀው ለማሠልጠንና ለማማከር፣ እንዲሁም ለጋዜጠኞችም ሥልጠና እሰጣለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት አምስት ዓመታት የለውጥ ጎዳና የተባለውን ሒደት እንዴት አዩት? ብዙዎች የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲያንፀባርቁ ይደመጣሉ?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- ተስፋ ላልከው ተስፋዬ ሁልጊዜም ትልቅ ነው፣ በሁለት ምክንያቶች፡፡ አንደኛው ተስፋ ከቀዘቀዘ የመጨረሻ ጎጂ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ችግር አለ፣ ችግሩ የሚታረም ነው፡፡ ጎልተው ከማያቸው አሁናዊ ችግሮች አንደኛው ሙስና ነው፡፡ ይህ ፈታኝ የሆነ አገራዊ ማነቆ ነው፡፡ ይህ እየታየ ያለው በአቅርቦት ረገድ ከፍተኛ እጥረት ስላለ ነው፡፡ ለእጥረቱ መፈጠር ደግሞ ብልሹ አሠራር ትልቅ ሚና እየትጫወተ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገልግሎት ዘርፉ ዜጎች አገልግሎት ፈልገው ሲሄዱ አልግሎት መስጠት ያለበት አገልግሎቱን ያሰናክላል፡፡ የግል ፍላጎት ለማሟላት ሲል በገንዘብ ብቻ ከፍ ዝቅ የሚሉ አገልግሎት ሰጪዎችን አይቻለሁ፡፡ ዜጎች የአገልጋዩን ፍላጎት ለማሳካት በኪሳቸው ገንዘብ ይዘው መሄድ አለባቸው፡፡ ይኼ እንግዲህ ከጦርነት በላይ አገር የሚያፈርስ ከባድ አደጋ ነው፡፡ በተመሳሳይ ጦርነት ውስጥ በሆነች አገር የማይጠበቁ ትልልቅ ሥራዎችን ታያለህ፡፡ ብዙ ጥሩ የሚባሉት ተግባራት በአጠቃላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ ፈቃድ እንጂ መዋቅራዊ አይደሉም፣ ቋሚ የሆኑም አይደሉም፡፡ ስለዚህ የሴቶችን ተሳትፎ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በካቢኔ ማሳተፍና መሰል ተግባራት በቋሚነት እንዲተገበሩ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያገለግላሉ፣ ዩኒቨርሲቲ የምሁራን ስብስብ መገኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በመንግሥትና በምሁራን መካከል መገፋፋት እንጂ መቀራረብ ባለመኖሩ አገሪቱ ተጎጂ እንደሆነች ይወሳ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ወቅት ከምሁራን ጋር መምከራቸውም ይታወሳል፡፡ አሁን ያለው የምሁራንና የመንግሥት ግንኙነት ምን ይመስላል ይላሉ?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- ምሁራንም ሆኑ የሲቪክ ማኅበረሰቦች በፖሊሲ ቀረፃና መሰል እንቅስቃሴዎች ለመንግሥት ያስፈልጋሉ፡፡ ይህ የግድ መደረግ አለበት፡፡ በፖለቲካም፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚውም፣ በታሪክም ሆነ በሌላው ዘርፍ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን የማይነካ ነገር የለም፡፡ ከእኔ በላይ ላሳር ብለህ ካልተውከው በስተቀር እነሱን ካማከርክ ሁልጊዜ ተጠቃሚ ትሆናለህ፡፡ ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ መጨረሻ ላይ ይህን እቀበላለሁ፣ ይህንን አልቀበልም ማለት የራሱ የባለሥልጣኑ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን የእኔን ብነግርህ እንደ ግል አልፈራምም፣ አልደፍርምም፡፡ አንድ ሹም በሕግ የተደነገገ መብትና ግዴታና በሕዝብ የተሰጠ ኃላፊነት አለው፡፡ እኔ ደግሞ ለማንም ሕዝብ ተጠያቂ ባለመሆኔ የፈለግኩትን ላደርግ እችላለሁ፡፡ ያ ባለሥልጣን ግን ከቀረበለት አማራጮችና አስተያየቶች ረጋ ብሎ አስቦ መምረጥ፣ ከሕጉና ከአሠራሩ ጋር አጣጥሞ መወሰድ የራሱ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እንደ ምሁር ለአገርህም ለሕዝብም የሚጠበቅብህን፣ የምታውቀውንና የሚሰማህን ማሰማት አለብህ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የውኃ ሀብት መሐንዲስ ነዎት፡፡ ከዚህ በፊት የዘርፍ ተማራማሪዎች ከዚሁ የውኃ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ከከሰም፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የውኃ ምንጮች ጋር በተገናኘ ለመንግሥት ምክረ ሐሳቦች አቅርበው ተፈጻሚ ሳይሆኑ የቀሩ ስለመኖራቸው ይነሳል፡፡ እርስዎ በዚህ ዘርፍ ምን አበረከቱ? ለመንግሥት ያቀረቡት ምክረ ሐሳብ ነበር ወይ?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- ከመነሻው አገሪቱ የውኃ ማማ ነች ሲባል ከሌላ አገር አንፃር እውነት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በውኃ መኖርና በውኃ መጠቀም ይለያያሉ፡፡ በውኃ ለመጠቀም ያለውን የዝናብ ውኃ በተገቢው አጠራቅሞ፣ አክሞና ተቆጣጥሮ ለተጠቃሚዎች በሚፈለገው ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ካልተደረገ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ እውነት ለመናገር አሁን አዲስ አበባ ያለው የውኃ አቅርቦት ሊኖር ከሚገባው 50 በመቶ ገደማ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ተመችቶህ የውኃ ችግርን ሳታነሳ ጤናህ ተስተካክሎ ለመኖር የሚያስችል የውኃ አቅም አለ፡፡ ከዚህ በፊት ሲቢሉ የተሰኘ ጫንጮ አካባቢ የሚገኝና በጥናቱ የተሳተፍኩበትና የኮሚቴ አባል የነበርኩበት የውኃ ግድብ ነበር፡፡ ይህ ግድብ ለአዲስ አበባ የውኃ ችግር በጣም ትልቅ እረፍት ሊሰጥ የሚችልና የከተማውን የውኃ ፍላጎት ለብዙ ዓመት ሊያራምድ የሚችል ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ አስበነው የነበረው ፕሮጀክት ተቀይሮ ኋላ ላይ አዲሱ ፕሮጀክት በ50 በመቶ አቅሙ ተቀንሶ ነው ለመገንባት የታሰበው፡፡ ሌላው የነበረው ዕቅድ በግፊት ሳይሆን የእንጦጦ ተራራን በስቶ ውኃውን ውስጥ ለውስጥ በማሳለፍ ሸጎሌ አካባቢ የውኃ ማጣሪያ ተሠርቶለት ለአገልግሎት እንዲውል ነበር፡፡ የአሁኑ የተቀየረ ዕቅድ ግፊቱን ወደ ላይ 30 ሜትር ከፍ አድርጎ 30 ኪሎ ሜትር ቧንቧ ዘርግቶ በግማሽ አቅም ለማምጣት  ነው፡፡ በአጠቃላይ ለመንግሥት ተቋማት ያቀረብኩት ወይም የተጠራሁት ባይኖርም እኔ ሁሌም ዝግጁ ነኝ፡፡ አገልግሎቴንም በነፃ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱውኃ አጠቃቀም በተመለከተ ለመንግሥት ያለዎት መልዕክት ምንድነው?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- በመስኖና በኃይል ማመንጨት ረገድ ጥሩ እየሄደ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ለመሥራት ከተነሳሽነት በላይ የሀብት እጥረት ይወስናል፡፡ ነገር ግን አጠንክሬ መናገር የምፈልገው በአትክልት ልማትና በኮንስትራክሽን የሚባክነው ውኃ ከከተሞች አቅርቦት ላይ ተቀንሶ መዋሉ መቆም አለበት፡፡ ምክንያቱም በከተሞች ካለው የውኃ አቅርቦት ውስንነት ላይ ቀንሶ ለካሮት፣ ለአትክልትና ለኮንስትራክሽን ከማዋል ይልቅ የዝናብ ውኃ ማጠራቀምና በጣሪያ የውኃ ማስወገጃ ቧንቧ ወደ ማጠራቀሚያ በመውሰድና በማከማቸት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድርግ ቁርጠኛ የሆነ አቋም ሊኖር ይገባል፡፡ የመጠጥ ውኃን ለመቆጠብ የሚያስችሉ ማናቸውም ዓይነት ሳይንሳዊ ድጋፎች ለማድረግ እኔም ዝግጁ መሆኔን በዚሁ እገልጻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ምሁራን የምታቀርቧቸውን ሐሳቦች ለመቀበል ፈቃደኝነት ይታይበታል ወይ?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- መንግሥት ላይቀበለው ይችላል፣ ላያውቅም ይችላል፡፡ በሩን በጣም መቆርቆር ይፈልጋል፣ ማንኳኳት ይጠይቃል፡፡ ግን መንግሥት ፎረም መፍጠር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ለበጎ ፈቃደኞች ጥሪ በማድረግና በማሰባሰብ ለማዳመጥ ፈቃዱን ሰጥቶ ሐሳባቸውን መቀበል አለበት፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያውያን ባህል ሳትጣራ መሄድ ያስቸግራል፣ ተጠርተህ መቅረት ደግሞ ይጨንቅሃል፡፡ ስለዚህ መንግሥት መጥራት አለበት፡፡ ለምሳሌ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሼ የገባሁት በአንድ አጋጣሚ ነው፡፡ ስዊድን እየኖርኩ በነበረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ ከትምህርት ሚኒስትሩ ጋር ምሁራንን ሰብስበው ሲያነጋግሩ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩት ምሁራን በመንግሥት ስህተት ነው፣ መንግሥት ተሳስቷልና የሚችሉ ካሉ መጥተው ወደ ድሮ ቦታቸው ተመልሰው ቢሠሩና ቢያገለግሉ የሚል ጥሪ አቀረቡ፡፡ እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ስንባረር ሥልጣን ላይ ባይኖሩም እንደ መንግሥት ከአገር እንድንወጣ መደረጋችንን መቀበላቸው፣ ሁለተኛ ደግሞ ቀጥተኛ ጥያቄ መቅረቡና ኑ ዕገዛ አድርጉ ስንባል እኔ ያደረግኩት በነሐሴ አጋማሽ ጥሪውን ሰምቼ በጳጉሜ እዚህ መጥቼ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ይህንን ጥሪ ስሰማ ላፕቶፔን ዘግቼ ነው የመጣሁት፡፡

ሪፖርተር፡- በስደት ከነበሩበት ስዊድን ወደ አገርዎ ሲመለሱ ምን ተሰማዎት?

ፕሮፌሰር አድማሱ፡- በመምጣቴ አልተቆጨሁም፡፡ ከበፊቱም ከአገር መውጣት አልፈልግም ነበር፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ሥራ መውጣት አልፈልግም ነበር፡፡ በሕገወጥ መንገድ በጉልበት ነው የወጣነው፡፡ እና ይህንን ቂም የሚያሽርልኝ ነገር ሳገኝ ደስ ብሎኝ  መጣሁ፡፡ በእርግጥ ውጭ አገኝ የነበረው ገቢ በጣም ብዙ ነው፡፡ ከቤተሰብ ተለይቼ ቢሆንም ለአገር የምከፍለው ዕዳ አለብኝ፡፡ ዕዳዬን እንዳልከፍል ተጥሎብኝ የነበረው ማዕቀብ ሲነሳ ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ማገልገል ጀመርኩ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...