Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል ለሰማይ ለምድር ሲል፣ በየወንዙም በየአጋጣሚም ሲማማል፣ በየዓመቱም በየአሥሩም በእዮቤልዩም የሰብዓዊ መብቶችን በዓል ሲያከብር፣ እኛም እንደ አገር፣ እንደ መንግሥት የዚሁ ዓለም ማኅበር መሥራች፣ የጥንት የጠዋት አባልና በሥራውም አባሪ ተባባሪ ሆነን ስለሰብዓዊ መብቶች አደራና ግዳጅ ስናወራና ስንናገር እነሆ ዛሬ በዚህ ሳምንትና በዚሁ ቀን 75 ዓመት ሞላን፡፡ ሰባ አምስት ዓመት የሞላው፣ አሁንም አስረግጦ ለመናገር የዓለም የሰብዓዊ መብቶች ‹‹ንቅናቄ›› እና ሰነድ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም አባል፣ አካል ሆና የተሳተፈችበት ተግባርና እዚያው በቦታውና በወቅቱ የፈረመችበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው፡፡ ያኔም ከ75 ዓመት በፊት፣ የሰብዓዊ መብቶች ዩኒቨርሳል ዲክላሬሽኑን በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ እንደተባለውና ከዚያም በኋላ በየዓመቱና በየጊዜው እንደሚነገረው፣ የዓለም አቀፋዊ ሰብዓዊ መብቶች ብሎ ነገር ወይም ሐሳብ መነሻ የሆነው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ የደረሰው ጥፋት፣ ዕልቂትና አረመኔያዊነት ነው፡፡

ይህንን ኢትዮጵያ የምታውቀው ዝም ብሎ ታሪክ ውስጥ፣ ታሪክ ትምህርት ውስጥ ወይም የሩቅ ተመልካች ሆና አይደለም፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ መግቢያ የሆነው የጀርመን ናዚ መንግሥት እ.ኤ.አ. ሜይ 8 ቀን 1945 ሲሸነፍና በዕለቱም (ሚያዝያ 30 ቀን 1937 ዓ.ም.) የአውሮፓ ድል በዓል ሲከበር፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከቤተ መንግሥታቸው ለሕዝብ ባደረጉት ንግግር ከሌሎች መካከል በአይሁዶችና በሶቪየቶች ላይ የደረሰውን ግዙፍ ዕልቂት ጠቅሰው ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዛሬ 75 ዓመት የፀደቀውና እኛም እዚያው በቦታው ያፀደቅነው ዩኒቨርሳል ዲክላሬሽን ኦፍ ሒዩማን ራይትስ መግቢያም፣ በተለይም የመግቢያው የመጀመሪያዎቹ ሦስት አንቀጾች (ፓራግራፎች) የሚሉትም፣ የሚያብራሩትም ይህንኑ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተናገሩት ነው፡፡ ይህም የመብቶች ሰነድ (UDHR) እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 10 ቀን 1948 (ታኅሳስ 1 ቀን 1941 ዓ.ም.) ከመፅደቁ በፊት ገና ሚያዝያ 30 ቀን 1937 ዓ.ም. ነው፡፡ ገና የሳንፍራንሲስኮው ጉባዔ ተመድን ሳይመሠርት ወይም በመመሥረት ላይ እያለ ነው፡፡ ‹‹ስለዓለም ሰላም በሳንፍራንሲስኮ የተሰበስበውም ጉባዔ ጥበቡን እንዲገልጽለት፣ የሥራውም ፍሬ ተስፋ ሁሉንም የሚያስተካክል እንዲሆን አምላክን እንለምናለን›› ብለው ሲናገሩ ነው፡፡ በዚህ ንግግራቸው ከላይ እንደተገለጸው፣ ‹‹የሰላም ድል ካልተጨመረበት በቀር የጦር ድል ብቻ የሚሰጠው ጥቅም ታላቅ ሊሆን አይችልም፡፡ የሰላም ድል ሊባል የሚቻለውም ጦርነትን በኃይል ለማስቀረት መቻል ብቻ አይደለም፣ የአንዱ መብት በመነካት ወይም በመጉደል የመሣሪያ ወይም የመንፈስ ጦርነት እንዲቀር ለሚመጣው ዘመን የጦርነት ሥራውና ስሙ ከሰው አንደበትና ህሊና በፍፁም እንዲፋቅ ለማድረግ የሚቻልበት መጠንቀቂያ በተፈጸመ ጊዜ ነው›› ያሉት፣ የ‹‹UDHR›› መግቢያ የአማርኛ ወይም የኢትዮጵያ አቋም ትርጉምና ማብራሪያ ነው፡፡

መላው ዓለም የሰብዓዊ መብቶችን የአልማዝ እዮቤልዩ ከወር በላይ ለዘለቀ ጊዜ በሚያከብርበት በዚህ ወቅት፣ የመጀመሪያው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያፀደቀው የሰብዓዊ መብት ስምምነት የጄኖሳይድ ኮንቬንሽም 75ኛ ዓመትም የሚከበረውና የሚውለው በዚሁ ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ እንዲያውም ዲሴምበር 9 የጄኖሳይድን የመከላከልና የዚያ ሰለባ የሆኑን ሰማዕታት መዘከሪያ ቀን ጭምር ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የተደራረበ፣ ተደራርቦ የሚውል ክብረ በዓል የማንገሥ አደራም ዕዳም የመወጣት ግዳጅ ውስጥ ያለነው ደግሞ፣ ራሱ ከተመድ መፈጠር ጋርና እንዲያውም ከራሱ ከተመድ ውሳኔ ውስጥ የመጣና የወጣ፣ ሰባ አምስት ዓመት የሞላው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራሱ በይፋ (ኦፌሴል) የፍልስጤም (The Question of Palestine) ጥያቄ ብሎ የሚያውቀው የዓለም ሰላም ደዌ ሆኖ የቆየው ችግር ጋዛ የአረመኔያዊ ወንጀል ማሳ፣ የጅምላ መቃብር ባደረገበት ግፍ፣ መከራና ሥቃይ ከሞላ ጎደል በቀጥታ ሥርጭት በቴሌቪዥን መተላለፍ በቻለበት ወቅት ነው፡፡

ሰብዓዊ መብቶች ሥልጣኔ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጥ የሚባል ወይም ፈረንጆች ‹‹ጎልድ ስታንዳርድ›› የሚሉት መሥፈሪያ/መለኪያ አላቸው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ወርቃማ መለኪያ የሚባሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረቻ ሰነዶችም ጭምር የሚባሉት ሁለት ዶክመንቶች ናቸው፡፡ የተመድ ቻርተርና ዲክላሬሽኑ (UDHR) ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር በአንድ ቃል፣ ኑረምበርግ ችሎት/ፍርድ ቤት ላይ የመጨረሻውና ከሁሉም በላይ የከፋ የሆነው ዓለም አቀፋዊ ወንጀል ተብሎ ከተበየነው ከወረራ/ከአግሬሽን ወንጀል ይጠብቀናል፣ ከዚህ የሚጠብቅ የሕግ መተማመኛ ይሰጠናል፡፡ ወረራን ወይም አግሬሽንን እንዲህ የተለየ፣ የከፋና የጦር ወንጀሎች ሁሉ አናት የሚያደርገው ሌሎች ግትልትል ወንጀሎችና እኩይ ጥፋቶች በሙሉ ስለሚያካትት ነው፡፡ እና በቻርተሩ አንቀጽ 2 (4) መሠረት አንድ አገር በሌላው አገር የፖለቲካ ነፃነትና የግዛት አንድነት ላይ ኃይል መጠቀምን (The Threat or Use of Force) ይከላከላል፡፡ ይህ ግን በተግባር የተረሳ፣ እርግፍ ተደርጎ የተተወ ከሆነ ቆይቷል፣ ለአሜሪካ አይሠራም፡፡ የሚሠራው ለሩሲያና ለሳዳም ሁሴን ሲሆን ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ‹‹ትርጉም›› የሚያገኙት ከጉልበተኞቹ አገሮች ጥቅምና ፍላጎት ጋር ተገናዝበው እንደሆነ፣ በየፊናችንና በየተራችን ዓይተናል፡፡ ልዕለ ኃያላዊ ማናለብኝነታቸውን ‹‹ሽብር›› በመከላከል ትግሉ ውስጥ ሲጋለጥ፣ በሰብዓዊ መብት ረገጣ ራሳቸው ሲቆሽሹ ዓይተናል፡፡ እ.ኤ.አ. ሜይ 2023 አንድ መቶ ዓመታቸውን ደፍነው አሁን ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም (በጦር ወንጀለኝነት ቁም ስቅል ካሳዩት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት) ትልቅ ስምና ሥርጭት ባገኘ መጽሐፍ ውስጥ ‹‹ለፍርድ የቀረቡት››) ኪሲንጀር የምንነጋገርበት ጉዳይ ትልቅ ምስክር ናቸው፡፡ ለፍርድ የቀረቡበት መጽሐፍ ሳይሆን ዊኪሊክስ በ2011 ዓ.ም. ከ36 ዓመት በኋላ አጋልጦ ያወጣባቸው ንግግራቸው/ደባቸው የእሳቸውን ‹‹ውስልትና›› ብቻ ሳይሆን፣ የአድራጊ ፈጣሪ የአሜሪካን ደባ፣ የውሸት መርህና የሕግ የበላይነት አክባሪነት ቀልድ የሚያመላክት ነው (ቱርክ ቆጵሮስን ወረረች ተብሎ የአሜሪካ ምክር ቤት ዕቀባ ያደርግባታል፡፡ አንካራ ላይ በአሜሪካና በቱርክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል በተደረገ ስብሰባ ላይ ኪሲንጀር የኒክሰን አስተዳደር ቱርክን ለመሰለ ወዳጅና አጋር፣ የኔቶ አባልማ ‹‹ዘዴ›› ፈልገን ባይሆን በሌላ ወዳጅ አገር አማካይነት ዕርዳታውን እንሰጣለን ይላሉ፡፡ ቱርክ ያለው የአሜሪካ አምባሳደር እሱማ ሕገወጥ ነው ይላል፡፡ ይህንን ጊዜ ነው ኪሲንጀር ‹ሕገወጡን ወዲያው፣ ሕገ መንግሥት የሚፃረረውን ቀስ እየተባለ እንፈጽመዋለን› እንደ ቀልድና እንደ ዋዛ የተናገሩት)፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያከብራቸው፣ አባል አገሮችም እንዲያከብራቸው በጥብቅ አደራ ብሎ የቤት ሥራ አድርጎ የሚሰጣቸው በርካታ በዓላት አሉ፡፡ በአጠቃላይ ዓመቱ በሙሉ በ‹‹ዓለም አቀፋዊ ቀን›› የተገጠገጠ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል፣ የተለይም ከምንነጋገርበት ጉዳይ ጋር በተያያዙት ዋና ዋናዎቹ 24 ኦክቶበርና 10 ዲሴምበር ናቸው፡፡ ሃያ አራት ኦክቶበር የተመድ ቻርተርና የድርጅቱ ፍርድ ቤት (ኢንተርናሽናል ኮርት ኦፍ ጀስቲስ) ደንብ ወይም ‹‹ስታቲዩት›› በአባል አገሮች ተፈርሞ በየአገሮቹም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት ፀድቆ፣ የማፅደቂያውም ሰነድ የቻርተሩ አንቀጽ 110 እንደሚደነግገው የተሟላ ቁጥር ላይ ሲደርስ ነው፡፡ በአጭሩ የተመድ ቻርተር አንቀጽ 110 እንደሚከተለው ይወስናል፡፡ አንደኛ ይህ ቻርተር በፈራሚ አገሮች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት ‹‹ራቲፋይ›› ይደረጋል፣ ወይም ይፀድቃል፡፡ ሁለተኛ ቻርተሩ የሚፀናው/ሥራ ላይ የሚውለው ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ሶቪየት ኅብረት፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ አሜሪካና አብዛኛዎቹ ፈራሚ አገሮች ያፀደቁበትን ሰነድ ገቢ ካደረጉበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ እንዲሁም ቻርተሩን የፈረሙትና ቻርተሩ ከፀና በኋላ ያፀደቁት አገሮችም የየራሳቸውን የማፅደቂያ ሰነድ ገቢ ካደረጉበት ቀን ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች/ኦርጅናል አባል ይሆናሉ ይላል፡፡ ይህ የቻርተሩ አንቀጽ 110 የሚደነግገው ተሟልቶ ቻርተሩ ጁን 26 ተፈርሞ በተባሉት ዋና ዋና አገሮችና በተፈላጊው አገሮች ቁጥር ልክ ‹‹ሪቲፋይ›› የተደረገው ኦክቶበር 24 ነው (ኢትዮጵያ ቻርተሩን በዕለቱ ብትፈርምም ያፀደቀችበትን ሰነድ ገቢ ያደረገችው ግን ኖቬምበር 13 ወይም ኅዳር 4 ቀን 1938 ዓ.ም. ነው)፡፡

ሃያ አራት ኦክቶበር ወይም ጥቅምት 14 የተመድ ቀን ሆኖ እንዲከበር የተወሰነው እ.ኤ.አ. በ1947 ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በ1971 ደግሞ የሕዝብ በዓል እንዲሆን ተመድ ጥብቅ አደራ የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ያገኘነውን፣ የተገለጠልንና የምናውቀውን ያህል የአገራችንን አንዳንድ መረጃዎች ማካፈል ወደኋላ የምናነሳውን ጥያቄ ለማገላበጥ ያግዛል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ

ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች ጠቅላላ ጉባዔ በኅዳር 20 ቀን 1940 ዓ.ም. ባደረገው ውሳኔ የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች ኪዳን እንዲከበር ይተባበሩት ዘንድ፣ የተባበሩትም ነፃ ሕዝቦች ማኅበር አባሎች ስለጠየቀና እኛም የተባባሩት ነፃ ሕዝቦች ሥራና የሥራቸውም ፍሬ በሕዝባችን ዘንድ የታወቀ እንዲሆን ምኞታችን ስለሆነ ቀጥሎ ያለውን አውጀናል፡፡

  1. ይህ አዋጅ የ1941 ዓ.ም. የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች በዓል አዋጅ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፣
  2. የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች በዓል በጥቅምት 19 ቀን 1941 ዓ.ም. እንዲውልና እንዲከበር በዚህ ታውጀዋል፡፡

ይህ ‹‹አዋጅ›› እውነት በአገር የሕግ አወጣጥ ማዕቀፍ ውስጥ የወጣ ሕግ ነው ወይ? ብለን የምንጠይቀው ከእውነት፣ ከሀቅ ወይም ከታሪክ አኳያ የሚያጠራጥር ነገር ስላለ አይደለም፡፡ ዛሬ እንኳን በተደረበበት የዕድገት ደረጃ አንፃር ገና ተፈልጎ መገኘት ያልቻለ ‹‹ሚዛን›› ይዘን/ተውሰን የትናንትናዋን/የጥንቷን የ40ዎቹን ኢትዮጵያ እንለካለን ወይ ካልተባለ በቀር፣ ከላይ የተገለጸው ጥቅምት 14 የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች በዓል አድርጎ ያወጀው ሕግ ‹‹ችግር›› የሚታይ ይመስለኛል፡፡ የምንነጋገረው ጥቅምት 1941 ዓ.ም ስለወጣ ሕግ ነው፡፡ በዚያ ወቅት እንዲያውም ከዚያም በፊት ከየካቲት 1934 ዓ.ም. ጀምሮ አገራችን ‹‹ነጋሪት ጋዜጣ›› የሚባል የቆመባት አገር ነች፡፡ የመንግሥት የኦፊሴል መናገሪያም፣ መነጋገሪያም ይኼው ብቻ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በዚህ ነጋሪት ጋዜጣ የወጣውን አላውቅም፣ አልሰማሁም፣ ማንም አልነገረኝም ማለት መከራከሪያም መከላከያም አይደለም፡፡ ይህ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሌላ አሠራርን፣ ሥርዓትን የሚመለከት ነገር አለ፡፡ ከፍ ሲል እንዳለ ያወጣነው ጥቅምት 14ን የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች በዓል አድርጎ ያወጀው/አወጀ የተባለው ሕግ በወጣበት ወቅት ፀንቶ ሥራ ላይ ያለ የሕዝብ በዓላት አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 9/1934) አለ፡፡ ይህ ሕግ በ1948 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 151 እስኪተካ ድረስ የአገር ሕግ ሆኖ ኖሯል፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ ቁጥር 17/1967 የ1948 የአገር የሕዝብ በዓላት ሕግ የተካና አሁን ፀንቶ የሚገኘው የአገር ሕግ ነው፡፡ የአንድ አገር የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀናት የትኞቹ ናቸው? (የዚህስ የሕግ ማዕቀፍ የትኛው ነው?›) ብሎ የመጠየቁ ነገር የጠቅላላ ዕውቀት ወይም አገር ጎብኚ ማወቅ የሚፈልገው፣ ወይም የ‹‹ባህል ልውውጥ›› ሰው ደንታ ብቻ አይደለም፡፡ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የሰው ኃይል፣ ወዘተ ጉዳይ ነው፡፡ በ1967 ዓ.ም. የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት መሰናበት፣ መወገድ ተከትሎ የወጣ የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን ሕግ ዛሬም በተለይም ከ1983 ዓ.ም. ለወጥ በኋላ የመጣውን አዲስ ነገር፣ የተከተለውን ለውጥ ማስተናገድ አቅቶት ከ30 ዓመታት በላይ ‹‹ባለቤት›› አጥቶ እያየን የ1941 ዓ.ም. የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች የጥቅምት 14 በዓል አዋጅ/ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ አልወጣም የምንለው ሥርዓት፣ አሠራር ይህንን ሁሉ ከቁጥር ማስገባት፣ የዚህ ሁሉ ባለቤት አበጁልኝ ስለሚል ነው፡፡

ኦክቶበር 24 ወይም ጥቅምት 14 የተመድ ቀን ወይም የተባበሩት ነፃ ሕዝቦች ቀን ሆኖ የሚከበረው (ኢትዮጵያ ያኔ በ1941 ዓ.ም በመንግሥቱ አማካይነት እንደፈቀደቸው፣ እንደ ሕዝብ በዓል ባይሆንም) ቻርተሩ የፀደቀበት፣ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ የዋለበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ቻርተሩ እንዴት ሆኖ እንደሚፈረም፣ እንደሚፀድቅ የቻርተሩ አንቀጽ 110 ይወስናል፡፡ ‹‹The present Charter shall be ratified by signatory states in accordance with their respective constitutional processes.›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያ በዕለቱ 26 ጁን ሳንፍራንሲስኮ ላይ የፈረመችውን ቻርተር በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቷ እንደተደነገገው አፅድቃ፣ የማፅደቂያ ሰነዱን ገቢ ያደረገችው 13 ኖቬምበር 1945 ነው (ኅዳር 4 ቀን 1938 ዓ.ም.)፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ ደግሞ ኢትዮጵያ የዓለም ማኅበርን ቻርተር በፈረመችበት፣ ባፀደቀችበት ወቅት የነበራት ሕገ መንግሥታዊ ሒደት (ፕሮሰስ) የትኛው ነው የሚለው ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በወቅቱ የነበረውን የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አግባብ ያላቸው ክፍሎች፣ በተለይም ሁለት ምዕራፎች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ወይም መጀመሪያ የምንመለከተው የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ምዕራፍ የ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት አማካሪዎች››ን የሚያቋቁመው ምዕራፍ አራት ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ በዋነኛነት የተደነገገው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትና የሕግ መመርያ ምክር ቤት አማካሪዎች እንደሚኖሩ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አማካሪዎችን የሚመርጣቸው ንጉሠ ነገሥቱ ራሱ እንደሆነ፣ የሚመረጡትም በመሣፍንትነትና በሚኒስትርነት፣ በዳኝነትና በጦር አለቅነት መንግሥታቸውን ብዙ ዘመን ካገለሉ መኳንንቶች ወገን እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ሌላውን የሕግ መመርያ ምክር ቤት አባላትን ደግሞ ‹‹ለጊዜው ሕዝብ መምረጥ እስኪችል እስከተወሰነው ዘመን ድረስ መኳንንቶችና ሹሞች›› እንደሚመርጧቸው ይደነግጋል፡፡ ይህ ምዕራፍ ሌሎች ዝርዝር ድንጋጌዎች ቢኖሩትም የትኛውም ‹‹የተመከረበት›› ጉዳይ ንጉሠ ነገሥቱ ወዶ ሳይቀበለው ሕግ ሆኖ ሊቆም የሚችል ነገር የለም፡፡ የዓለም መንግሥታት ሳንፍራንሲስኮ ላይ በተሰባሰቡበት ከ25 አፕሪል እስከ 26 ጁን ማለትም ከሚያዝያ 17 እስከ ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም. ድረስ፣ ቸርተሩ ሥራ ላይ በዋለበት ጥምቀት 14 ቀን 1938 ዓ.ም. ሥራ ላይ ባለው፣ የአገር ሕግ ሆኖ ፀንቶ በኖረው የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መሠረት እንዴትና ምን ቻርተሩ ተመክሮበትና ተዘክሮበት ፀደቀ? ይህንን ማዕቀፍ ከማሳየት ከፍ ያለ ሌላ መረጃ የለኝም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በዚያው ወቅት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ጥቅምት 23 ቀን 1938 ዓ.ም. በፓርላማ ባደረጉት የዙፋን ቃል፣  

‹‹ኢትዮጵያ ድል ተገኝቶ ይህ ጦርነት ባለቀበት ጊዜያት አንድነት የተባበሩት መንግሥታት ሰላምን ለመጠበቅና ለማደራጀት ያሰቡትን አዲስ የመንግሥታት ማኅበር መተዳደሪያ ወደ ሳንፍራንሲስኮ በላክናቸው መልዕክተኞች አማካይነት አብራ ሠርታለች፡፡

እኛም ይህንን የመንግሥታት ማኅበር ማስተዳደሪያ አሁን በቅርቡ ከዚህ በተሰበሰባችሁ መማክርት ፊት ቀርቦ እንድትስማሙበት ከተደረገ በኋላ አፀደቅነው፡፡ ኢትዮጵያም ለዚህ ለተባበሩት መንግሥታት ማኅበር መሥራች አባል ሆነች፡፡ አሁንም በዚህ በምንነግራችሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በዚሁ እጅግ ታላቅ በሆነው በመንግሥታት አንድነት ማኅበርና እንደዚሁም በሌሎች የዓለም መንግሥታት ሥራ በሚከናወንባቸው ማኅበሮች የሥራ ተካፋይ ሆና ሥራዋን ጀምራለች፡፡ ነገር ግን መጀመር ብቻ በቂ አይደለም››

ብለው መናገራቸውን ፍሬከናፍር ቁጥር 1 ይነግረናል፡፡

ሌላው ትልቅ ክብረ በዓል ዛሬ በአጠቃላይ በዚህ ሳምንት ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ወሩ ሁሉና ከዚያም በፊት የነበሩት ወራት በአገራችን ጭምር በተለያዩ ስብሰባዎች ያከበሩትና የሚያከብሩት በዓል ‹‹UDHR›› የፀደቀበት ዕለት ነው፡፡ ዲሴምበር 10 ቀን 1948 ወይም ታኅሳስ 1 ቀን 1941 ዓ.ም.፡፡ እዚህም ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ይህ ሰነድ በፀደቀበት በፓሪስ ስብሰባና አዳራሽ ላይ ባደረገቸው ‹‹ተሳትፎ›› ንጉሡ በንግግራቸው እንዳሉት የሥራ ተካፋይ ሆና ሥራዋን ጀምራለች፡፡ ‹‹ነገር ግን መጀመር ብቻ በቂ አይደለም›› እንዳሉት ከአደባባይ ሠልፍ አኳያ፣ የአባልነት ወጉን ከማድረስ አንፃር ብዙ የጎደለንም ሆነ ያሳጣን ነገር አናይም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የመሠረታዊ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን ድንጋጌ የተቀበልነው የአገራችም የሕግ ሥርዓት የዓይን ብርሃን፣ የእግር መንገድ ይሁን ብለን የተፈጠምነው ምን መሠረት፣ ምን መሰናዶ፣ ምን ጉዝጓዝ ላይ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው (እግረ መንገዳችንን ቻርተሩንና ዲክላሬሽኑን የመቀበልና የማፀደቅ ጉዳይ የተለያየ አሠራር እንዳለው ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ዲክላሬሽኑ እንደ ቻርተሩ ስምምነት ወይም ቲሪቲ አይደለም)፡፡

አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡ አንቀጽ 9 (4) በዚሁ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩ መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ተፈጻሚነትና አተረጓጎም ደግሞ፣ ከእነዚህ ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ጋር መጣጣም አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊ የአካባቢያዊ (ሪጅናል) የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች የወቅቱ ዝርዝር እንደሚያመላክተው ደግሞ ብዙ የሚያሳስብ፣ አገርን ባለ ዕዳ ያደረገ አይደለም፡፡ ገና መቀበልና ማፅደቅ አለብን የምንላቸው ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እንዳሉ ሁሉ፣ ያንኑ ያህልም አዳዲስ ሕጎችን ማውጣት፣ ነባር ሕጎችን ማሻሻል የሚፈልጉና የሚጠይቁ የማስተካከል/ሪፎርም የማድረግ ውዝፍም፣ ያለማቋረጥ መካሄድ ያለበትም ቋሚ ሥራ ነው (ለምሳሌ በዚህ ዓመት 2023/2016 ኢትዮጵያ የዓለም የሥራ ድርጅት አባል የሆነችበትን 100ኛ፣ አዎ አንድ መቶኛ ዓመት በይፋ፣ በአደባባይ ስብሰባ ያከበረችበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ የማሰላሰል፣ የማብሰልሰል፣ ‹‹ትርፍና ኪሳራ›› የመተሳሰቢያ ወቅት ኢትዮጵያ የትኞቹን የአይኤልኦ ኮንቬንሽን ሳታፀድቅ ቀረች? የትኛውን አፅድቃለች? እና ለምን አታፀድቅም? ተብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው፣ ተጠይቋልም፡፡ ሕመማችን ግን ኋላ የቀረንበት፣ ያላፀደቅነው ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ያፀደቅናቸው፣ የኢትዮጵያ ሕግ አካል ያደረግናቸው የአይኤልኦ (ILO) ኮንቬንሽኖች ራሳቸው መኗኗሪያችን ሆነዋል ወይ? ማኅበር የማደራጀት መሠረታዊ መብት ራሱ ከስም ጌጥ ከፍ ያለ ዋጋ አግኝቷል ወይ? ሩቅ ሳንሄድ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 42 (የሠራተኞቹ መብት ንዑስ ቁጥር 1/ሐ/ የተጠቀሰው ሕግ እነሆ እስከ ዛሬ አልወጣም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህንን ካዛዘ ግን 29 ዓመቱ ነው)፡፡ ዋናው ችግራችን ግን ይህና ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የምናወጣቸውንና የተቀበልናቸውን ሕጎች፣ የመብትና የነፃነት ድንጋጌዎች ግዘፍ ሰጥቶ፣ ሥጋ አልብሶ፣ ነፍስ ዘርቶ፣ አቅፎና ደግፎ መኗኗሪያችን እንዲሆኑ ማድረግ ያስቻለ መሰናዶ አለን ወይ? በዚህ ላይ የተመሠረተ ግንባታና ዕድገት አድርገናል ወይ ነው? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ስንሆን፣ ከዚያም በኋላ የዛሬ 75 ዓመት ዓለም አቀፋዊውን ዲክላሬሽን እጃችንን አውጥተን ስናፀድቅ (እጃቸውን አውጥተው ድምፀ ተዓቅቦ ካደረጉ ስምንት አገሮች ስንለይ)፣ ይህንን የአደባባይ አቋማችንና ሠልፋችንን የሚሰማ፣ የሚያውቅ ፍጥርጥርና መሰናዶ አለን ወይ? ያኔም፣ ከዚያ በኋላም ለብዙ ጊዜ፣ ዛሬም፣ በተለይም አሁን ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ዴሞክራሲ እንሄዳለን፣ ሕግ ገዥ ወደ ሆነበት ሥርዓት እንገነባለን ብለን ከተነሳን በኋላ የሁላችንንም ርብርብ ያገኘ የጋራ ሥራ አልሆነም፡፡

እ.ኤ.አ. በ1948 ዓ.ም. ፓሪስ ላይ በመልዕክተኛችን አማካይነት የተቀበልናቸው የመብትና የነፃነት ድንጋጌዎችን አሜን፣ አሚን/ይሁን ብለን ይዘን መጥተን የዘራናቸውና ብቀሉ ያልናቸው የገባር ጭሰኛ ሥርዓቱና መሣፍንታዊና መኳንንታዊ ጌትነቱ በተንሠራፋበት ምድር፣ አፈር፣ አየርና ከባቢ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ለሕዝብ ስለፈቀዳቸው መብቶችና ሕዝብ ለመፈጸም ግዴታ ስለሆነባቸው ነገሮች›› የሚለው የ1923 ሕገ መንግሥት የምዕራፍ ሦስት ርዕስ ራሱ ሥራችንንን ሁሉ የእንቧይ ካብ መሆኑን ያሳያል፡፡ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንኳን አይገልጸውም፡፡ በ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ላይ በንጉሡ ዘመን የተደረጉ የሕግ ለውጦች እንኳን ያው ልፋታችንን ‹‹ውኃ ወቀጣ›› ነው ያደረጉት፡፡ የኤርትራ በፌዴሬሽን የኢትዮጵያ አካል መሆን በ1945 ዓ.ም. በፌዴራል አዋጁ አማካይነት የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በጣም የተሻሻለ ‹‹ይዘት›› ሰጥቶታል፡፡ ከዚያም በኋላ የማይናቁ የሕግ ማሻሻዎች ተደርገዋል፡፡ በ1948 የተሻሻለውን ሕገ መንግሥት አምጦ የወለደውም ከ1945 ዓ.ም. ማሻሻያ የጀመረው እንድርድሮሽ ነው፡፡

ሰባ አምስት ዓመት የሞላው ይህ ሰነድና ንቅናቄ በዓለም ዙሪያ የበርካታ አገሮችን ሕገ መንግሥቶች መግራት (በእነሱ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ) ከመቻሉም በላይ (ከሞላ ጎደል)፣ ሁሉም ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ተፈልቅቀውና ተዘርዝረው የወጡት ከዚሁ ነው፡፡ የእኛም አገር ታሪክና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፏችንን የመዘገበው አካሄድ፣ አማረማመዳችን እንደሚያሳየው የዲክላሬሽኑ ድንጋጌዎች በተለያየ መልክና ልክ፣ በተለይም ከ1945 የመስከረም 1 ቀን የፌዴራል አዋጅ ወዲህ የኢትዮጵያ የሕግ አካል ሆነዋል፡፡ ምን ያህል ተዋህደውን፣ ተቀላቅለውን፣ ወይም ተዋህደናቸውና ተቀላቀልናቸው ኖርን ሌላውና ዋናው ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች የመላው የሰው ልጅ በመላው ዓለም በተፈጥሮ ያገኛቸው ቢሆኑም፣ ለኑሮ ሥርዓታችን ግን ‹‹ባዕድ መጥ›› ተክሎች ነበሩ፡፡ ሐሳቦቹን፣ እምነቶቹን፣ ጆሯችንና ዓይናችን ብቻ ሳይሆን ልባችንና አንጀታችን ውስጥ ቦታ አግኝተው እንዲጎዘጎዙ የሚያደርግ መሰናዶና መደላድል አላበጀንም፣ አላደራጀንም፡፡ ይልቁንም በወቅቱ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግንኙነታችን ፓሪስ ላይ እጅ አውጥተን እሺ ይሁን፣ አሜን/አሚን ያልናቸውን ወደ ሕግ ለውጡን የሚሉ ሐሳቦች መስማት የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ‹‹ለካስ እሜቴም እንደ እኛ ሰው ነበሩ?›› ያልነው እኮ ገና በ1967 ዓ.ም. ነው፡፡ ተደጋግሞ እንተገለጸና እንደሚታወቀው ጨዋታዎችን ማወዳደር ራሱ ቅድሚያ መሰናዶ ይፈልጋል፡፡ የተስተካከለ የሜዳ ዝግጅትን (Level Playing Field) የሚባል ቁም ነገር የመጣው ከጨዋታ ነው) ይጠይቃል፡፡ ራሱ ጨዋታው በብቃትና በሥነ ምግባር በታነፁ ሰዎች የተሞላ ተቋማዊ አቅም ይፈልጋል፡፡ ፍትሐዊ የጨዋታ መርሐ ግብር አዘጋጁ ይላል፡፡ ኢአድሏዊ ዳኝነት፣ የፀጥታ አስከባሪዎችን ለጨዋታው ጀርባ ሰጥቶ በሥራ ላይ የማተኮር ንቁነትን የመሰለ ‹‹የሚገርም›› ባህርይ፣ አቤቱታዎችን ያለ አድልኦ መርምሮ ትክክለኛ ውሳኔ የሚሰጥ አካልን ይሻል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት አገር ማበጀት፣ ማደራጀትም (የዴሞክራሲ ግንባታም) ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሳይንስና ጥበብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የጎደላት አስቀድሞ በዚህ ላይ መረባረብ ነው፡፡ ከፓርቲ፣ ከየትኛውም ወገንተኛነት ነፃ ሆነው የታነፁ የመንግሥት ዓምዶችን ማጣት ነው፡፡

ሕግ ማውጣት፣ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን እየመከሩ መቀበል አስፈላጊና ወሳኝ ቢሆንም፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች የሕግ መተማመኛ ስለተሰጠባቸው ብቻ መኗኗሪያችን ይሆናሉ፣ አብረውን አሉ ካሉት አይደለም፡፡ በደርግ (በኢሕዲሪ) ሕገ መንግሥት እኮ በመብቶችና በነፃነቶች ዝርዝር ውስጥ ለመብትና ለነፃነት፣ ለፀረ ዘረኝነት፣ ለዴሞክራሲና ለሰላም በሚያደርጉት ትግል ምክንያት ጥቃት ለሚደርስባቸው የውጭ አገር ዜጎች ጥገኝነት የመስጠት መብት/ግዴታ የሚያቋቁም ድንጋጌ ነበር፡፡ ሕግ ከስም ጌጥ የበለጠ፣ ከአደባባይ ሠልፍ ማሳመሪያ የተሻገረ፣ የአገርና የሕዝብ እስትንፋስ የሚሆነው የዴሞክራሲን መደላድል አስቀድመን ስንደለድል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...