Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

ቀን:

በያሲን ባህሩ

 የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ በእነዚህ ወቅቶች በጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት፣ በአሸናፊና በተሸናፊ ፍልሚያ ውስጥ የኖሩ የአገሪቱ ሕዝብ ኢፍትሐዊነት፣ ፀረ ዴሞክራሲና ድህነትን የመሳሰሉ ፅልመቶችን ተከናንበው እንዲኖሩ ሆነዋል፡፡ ከሦስት አሥርት ዓመታት ወዲህ ወደ ሥልጣን የመጣው ፓርቲ ኢሕአዴግም ቢሆን ለዘመናት በሕዝብ ውስጥ ሲብሰከሰኩ የኖሩ ችግሮችን በጋራና በሚዛናዊነት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣  የራሱን ችግር ሲቀፈቅፍ ከርሞ ነው ከሥልጣን ፈቀቅ ያለው ሊባል ይችላል፡፡

ኢሕአዴግ አሁን ለምንገኝበት ቀውስ ካድሬዎቹንና ከፊል የአገዛዝ ጥበቦቹን ብቻ ሳይሆን ያስተላለፈው ቂምና ቁርሾን፣ ያልተፈቱ የወሰን፣ የማንነትና የፖለቲካ ውዝግቦችን፣ እንዲሁም ፅንፈኛ የፖለቲካ ዕይታዎችን ጭምር ነው የሚሉ ብዝዎች ናቸው፡፡ በዚህም የሕዝብን የተከማቹ ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ መመለስ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የአገር ባላንጣዎች፣ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ፅንፈኛ ሴራቸውን እንደ ምቹ አጋጣሚ የተጠቀሙበት ኃይሎች በፈጠሯቸው ተደጋጋሚ ቀውሶች የአገር ህልውናን ከመፈታተን ጀምሮ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን ሁሉ እናውቀዋለን።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እነሆ የኢሕአዴግ ወራሹ ብልፅግና ወደ ሥልጣን ከመጣ ያለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በአገር ደረጃ ከፍተኛ ግጭት፣ ስደት፣ መፈናቀልና የአገር ሀብት ውድመት እየተባባሰ የቀጠለውም ለዚህ ነው፡፡ በሰከነ የፖለቲካ መስተጋብርና የሰጥቶ መቀበል መርህ አገረ መንግሥትን በሥልጡን መንገድ ከማስቀጠል ይልቅ፣ ሁሉም በየፊናው ነፍጥ አንስቶ በጉልበት የበላይነቱን ለማሳየትና ሕዝብን ለመከራ ለመዳረግ የበቃውም በተንጋደደ የፖለቲካ መንገድ በመንጎዱ ነው፡፡

በእርግጥም ትናንት በትግራይና በኦሮሚያ፣ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ከሞላ ጎደል  ወደ ሙሉ ጦርነት ያደገ ውጊያ እየተካሄደ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ልጆች እየተላለቁ ነው፡፡ ንፁኃን በድሮንና በከባድ መሣሪያ ሳይቀር እየረገፉ ይገኛሉ፡፡ የመንግሥት ተሿሚ በመሆናቸው ብቻ በደፈጣ የሚገደሉ የቤተሰብ ኃላፊዎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ የእምነት ተቋማትና መሪዎቻቸው ይፈርሳሉ፣ ይገደላሉ፡፡ የደሃ አገር ሀብት እሳት እንደነካው ቡቃያ በየሜዳውና በየሸንተረሩ ወደ አመድነት ይቀየራል፡፡ በዚህም እንኳን ዕድገት ሊታይ ድህነትና ኑሮ ውድነት እየተባባሱ መጪውን ወቅት የመከራ ዘመን እንዳያደርጉት በእጅጉ ተፈርቷል፡፡ ግን እስከ መቼ፡፡

በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ የዴሞክራሲ ንፍቀ ክበቡም ካለፉት ወቅቶች በበሳ ደረጃ መጥበቡ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አለመፈታታቸው የችግሩ መባባስ ተጨማሪ ምክንያት ሆነዋል የሚሉ ጥቂት አይደሉም፡፡ በየደረጃው የመንግሥት አሠራርን ለሕዝብ ግልጽ ከማድረግ ይልቅ እውነታውን መደበቅና መሬት ላይ የሚታየውን መካድ የሥርዓቱ መገለጫ ሆኗል፡፡ በአንዳንድ ዘርፎች/ሴክተሮች በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የተጠያቂነት አሠራር መጣሱ ብቻ ሳይሆን፣ የሕግ የበላይነት መለስ ቀለስ ሲል መታየቱ ብልፅግና ብቻውን የሚያቆመው አገር እንደሌለ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል የሚሉ በርክተዋል፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን እንዳልተወገዘ ሁሉ አሁንም አንዳንድ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝብን ንቀውና በማናለብኝት ተወጥረው መዋል ማደራቸው የሚያሳዘን ክስተት ነው፡፡ እውነት ለመናገር በቀውስ ውስጥ እንዳለ መንግሥት ቅድሚያ ለሰላምና መነጋገር መስጠት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ብልፅግና ባሳለፍናቸው አምስት ዓመታት በኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተነሱ ዋና ዋና ድክመቶችን እንኳን ለማረም አለመቻሉ የውድቀቱ ማሳያ ነው፡፡

በጦርነትና በአለመግባባትም ውስጥ ሆኖ ቢሆን በአንዳንድ ሜጋ ፕሮጀክቶች (ቅድሚያ ሊሰጣቸው የማይገቡ የቱሪስት መስህቦች ይባዘሉ ቢባልም) እንደ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሉጂ ዘርፎች፣ የማንነት ጥያቄዎችና መሰል ጉዳዮች ላይ ተስፋ ሰጪ ዕርምጃዎችን መውሰዱ የማይካደው ብልፅግና በዋናነት ግን ሰላምና አንፃራዊ አገራዊ ደኅንነትን ማረጋገጥ አለመቻሉ በቀውስ አዙሪት እንዲመላለስ አድርጎታል፡፡ ዓለም አቀፍ ሁኔታውም ተጨምሮበት የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ሕዘቡን ክፉኛ እያራደው የሚገኘውም፣ የአገር ውስጥ ምርቶች ጭምር በሰላም ዕጦት ምክንያት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ነው፡፡

መንግሥት ቅድሚያ የውስጥ ችግሩን በድፍረት ለይቶ በመታገል ሌሎችን ወደ መታገልና መነጋገር መግባት ባለመቻሉ፣ አልፎ ተርፎም ከሕግ ውጪ የፓርቲና የመንግሥት ሥራን በመቀላቀል ሕገወጥ ድርጊቶች መፈጸምን በቅቡልነት አስቀጥሏል (በቅርቡ ድርጊቱን አውግዞ መግለጫ ቢያወጣም ጆሮ ዳባ ልበስ ነው የተባለው)፡፡ በብሔርና በጥቅም የተሰባሰቡ አንዳንድ መርህ የለሾች በኔትወርክ በመቧደን የአገር ሀብት ያለ ቅጥ መዝረፋቸው እየተሰማ መሆኑ፣ የግዥና የጨረታ ሕጎችን እየጣሱ ራስንና ቢጤዎቻቸውን የሚያበለፅጉ ስለመኖራቸው መነገሩ ብልፅግና ከኢሕአዴግ በምን ተሻለ እያስባለ ነው፡፡

ቀላል ቁጥር የሌላቸው የቢሮክራሲው ሰዎች በተለይ በከተሞች መብታቸውን ለማስከበርና አገልግሎት ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ማንገላታታቸውና ጉቦ በይፋ እስከ መጠየቅ መድፈራቸው የፖለቲካ ውድቀት ነው፡፡ እንዲሁም ይህንኑ በማረም የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስና የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እስከ ሕዝቡ ድረስ የወረደ ጥልቅ ውይይትና መተማመን ከማድረግ ይልቅ፣ ግልጽነት በሌላቸውና ፓርቲው ብቻ የወሰናቸው የወሰን፣ የማንነት ወይም የልማት ዕቅዶች በዱብ ዕዳ መወርወራቸው ቅሬታ እየፈጠሩ ነው።

ትናንትም ሆነ ዛሬ የአገሪቱ ልማት ባለቤት ሕዝብ መሆን ሲገባው፣ በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትና አመራሮች በጭፍን ሲወስዱት የሚታየው የመረረ ዕርምጃ ቀውስ እየፈጠረ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለሕግ አልገዛም የሚሉና ፀረ ሰላም ድርጊት ውስጥ የመግባት አካሄድ የሚከተሉ አካላትን በጠንካራ ፖለቲካና የሕዝብ ግንኙነት ከሕዝብ ነጥሎ መታገል ሲቻል፣ ኃይልና ጉልበትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መዝመት ያልተጠበቀ ውድ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ፈጥኖ ካልተነቃበትም አገርን የሚያዳክመው ይኸው አካሄድ ብቻ ነው፡፡

ትናንት ሕዝብና መንግሥትን ያጋጩ በርካታ ጉዳዮችም በአጭር የሥራ ዘመን መፍትሔ ያገኛሉ ማለት አይቻልም፡፡ ቢያንስ ግን ጥያቄዎች የሚመለሱባቸው ምልክቶች፣ የጋራ ችግሮች የሚቀረፉባቸው አቅጣጫዎች፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጭላንጭሎች መታየት ነበረባቸው፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ ሕዝብ ለመንግሥት ያቀረባቸው በርካታ ጥያቄዎች በተቻለ መጠን በውይይት፣ በሕግና በሥርዓት መመለስ ሲገባቸው በማናለብኝነት የአንዱን መልሶ ሌላውን ማሳደር ወይም የእኔ ጊዜ ነው ብሎ ሌላውን መግፋት ከጦርነት ውስጥ አያወጣም፣ ሰላምም አያረጋግጥም፡፡

ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር መነጋገር ይቅርና ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነው ሊደማመጡ ባለመቻላቸው የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፣ እየተቀጠፈም ነው፡፡ በርካቶች ለአካልና ለሥነ ልቦነ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፣ እስካሁንም አልቆመም፡፡ የአገርና የሕዝብ ህልውና ለአደጋ ተጋልጦ የነበረ መሆኑም የማይዘነጋ ሲሆን፣ ገና ያልጠገገ ሥጋት እንዳረበበ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስከትለው ጥፋት ብቻ ነው፡፡

በእርግጥ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመደማመጥና ቀውስ ምክንያት በአምስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ስድስት ጊዜ ያህል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ችግሮችን ማርገብ ባያስችልም፣ በርካታ አገራዊ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ቆይቷል። ያም ሆኖ ግን ዘላቂ ሰላም የሚሹ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር ሁነኛ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ መደበኛ ሕጎችን እየሻሩ አገር ለመምራት መሞከር፣ ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ ሲያጋልጥ ታይቷል፡፡ የአገር ገጽታንም ሲያጨልም ነው የቆየው፡፡ እናም አሁንም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይልቅ ፈጥኖ ለድርድር የሚበጅ ንግግር መጀመር ነው የሚሻለው፡፡

እናም ከአሁን በኋላም ያለፈው አልፏል ብሎ ከእያንዳንዱ አኩራፊና ሸማቂ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚናቸው የማይናቅና ምናልባትም ከገዥው ፓርቲ ተገዳዳሪ ፓርቲዎች ጋር መነጋገርና መደራደር መጀመር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የታሰሩ ተለቀው፣ የተሰደዱ ተመልሰው፣ የተኳረፉና የተጠላለፉ ይቅር ተባብለው በዕርቅና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመግባባት መሰናዳት ይገባል፡፡

እንደ አገር ባለፉት 30 ዓመታት በሰላማዊ ፖለቲካዊ ምኅዳር ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶች የታለፉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ ከዜሮ በታች የነበረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከማጥ ውስጥ ተነስቶ በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችንም አሳይቶ እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ በተለይ በመሠረተ ልማት፣ ከእነ ጉድለቱም ቢሆን በትምህርትና በጤና ዘርፎች፣ እንዲሁም በኢንዱስትሪና በወጪ ንግድ አመርቂ ሥራዎችም ሲከናወኑ ነበር፡፡

ነገር ግን ሕዝብ በገዛ አገሩ የባይተዋርነት ስሜት እየተሰማው፣ ተንቀሳቅሶ መሥራትና መኖር ተስኖት፣ ሰላምና ደኅንነት አጥቶ መኖሩና በኑሮ ውድነት መደቆሱ የከፋ ጉዳት ነው፡፡ በማንነትና በእምነት ምክንያት መጠቃቃቱ፣ ዘረፋና ዕገታው፣ ሞትና ስደቱ ተባብሶ በሰቆቃ መኖርም ካለመኖር የሚሻል አይደለም፡፡ በእነዚህና በተመሳሳይ ሳንካዎች ምክንያት የሚታየው የምጣኔ ሀብት መታወክ፣ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እየደቆሰው መገኘቱም ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ለመውጣት ግን ሆደ ሰፊ ሆኖ መነጋገሩ ነው መፍትሔ የሚያመጣው፡፡  ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል ሰላምና መረጋጋት ዕውን መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቱ የመንግሥት ወይም የገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የፖለቲካ ተዋንያንና የሕዝቡ ጭምር ነው፡፡ በተለይ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎችን ግንባር ቀደም ተሳትፎም ይሻል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ እንደ ሱቅ በደረቴ መሥርቶ አለሁ በማለት የተበታተነ ትግል ከመምራት ይልቅ፣ በርዕዮተ ዓለምና በዓላማ እንግባባለን የሚሉ ተሰባስበው ጠንካራ ድርጅት መፍጠር ይገባቸው ዘንድ ሕዝብ ይወክለኛል በሚለው ላይ ሁሉ ግፊት ማድረግ ይገባዋል፡፡

በጉልበት ሥልጣን ለመንጠቅ የሚሹና በብሔራዊም ሆነ በኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ውስጥ ሆነው በምርጫ ጊዜ ብቻ ከያሉበት እየተጠራሩ በመምጣት፣ “ምኅዳሩ ጠበበብን” የሚሉትን አጣባቢዎች ሕዝባችን በቃችሁ ሊላቸው ይገባል። የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ደካማው ዘገባ እንደሚያመለክተው ተስፋ የተጣለበት በአገራዊ ምክክር የምክክር ኮሚሽን እንደሚመራ የሚጠበቀውን መድረክ ለማኮላሸት፣ በመንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ያሉ ጥገኞች እያንዣበቡ ነው፡፡

በመሠረቱ ለማንም ሆነ ለምንም ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመደራደርም ሆነ ለመፎካከር የሚቻለው፣ ከብዛት ይልቅ ጥራት ሲኖርና ለዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ክፍት መሆን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የሕግ ተገዥነትና ለአገር ህልውና ተቆርቋሪነትም ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብን ሳይወክሉ በተናጠል እንደ ቁማር በፖለቲካ ውስጥ ለማትረፍ ብቻ ለመመላለስ መፍጨርጨር ከንቱ ምኞት ነው፣ የሚበጅም አይደለም፡፡

በግለሰቦች ተክለ ሰውነት ሥር የተከለሉ፣ አባላቶቻቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው የማይታወቁ መናኛ ፓርቲዎች ለአገር የሚፈይዱት ምንም ነገር የለም፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋርም አይሄዱም፡፡ በድርድር የማመቻመቻ መድረኮቹም የታየው ይህና ከላይ በተመለከተው ዓይነት ተደራጅተው የተለመደ አሰልቺ ሁኔታ ውስጥ ለመዘፈቅ የሚባትሉ ኃይሎች ናቸው (ተበታትኖና በመንደር ተደራጅቶ በጎበዝ አለቃ በመመራት ጠንካራ የፖለቲካ ትግል ማድረግና ተፅዕኖ መፍጠርም ስለማይቻል መሰባሰቡና መደራጀቱ ነው የሚበጀው)፡፡

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚታየው የፖለቲካ ስብስቦች የትግል ሥልታቸው  ኋላቀር፣ ከሥልጣኔ ጋር የማይተዋወቅ፣ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ቦታ የማይሰጥ፣ በጭፍን ጥላቻ የተዋጠ፣ ከውይይትና ከድርድር ይልቅ እልህና ጉልበት የሚበረታበት፣ በሸፍጥና በሴራ የተተበተበና ቡድንተኝነት የሚያጠቃው ነው። ግትርነቱና ያገኘሁትን ዕድል ካልሞትኩ አሳልፌ አልሰጥም ባይነትም አገር ይበትናል እንጂ አዋጭ አይደለም፡፡

ወይ ጠቅልሎ የመውሰድ አለበለዚያም በዜሮ የመውጣት አባዜ የተጠናወተው የአገራችን ፖለቲከኞችን (የመስቀል ወፍ ፖለቲካም እንኳ ቢሆን) ያለፈ ታሪክ ስንመረምር ዴሞክራሲ የሚል ታፔላ ቢለጠፉም፣ ውስጣቸው ግን ፀረ ዴሞክራሲያዊ መሆኑን መገንዘብ አያቅትም፡፡ እንዲህ ዓይነት ፖለቲካ ደግሞ ትውልዱን የማይመጥንና ዳግመኛ ዕድል ሊሰጠው የማይገባ ነውና መንግሥትም ሆነ መላ ፖለቲከኞች ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል።

እነዚህ ኃይሎች ዴሞክራሲ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ትርጉሙ ግራ እስከሚያጋባ ድረስ ፈሩን እንዲስት ማድረጋቸው፣ ይልቁንም ፅንፈኝነትና ጭፍንነት የበላይነት እንዲያገኙና ሰላም እንዲደፈርስ ምክንያት መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ እነዚህ ሕገወጥነት ስለተፀናወታቸው ለሕግ የበላይነት ክብር ነፍገዋል፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ላይ ታፔላ በመለጠፍ ድምፃቸው እንዲታፈን አድርገዋል፡፡ ሕግ ባለበት አገር ሕገወጥነት እንዲሰፍንና ከላይ እንደተመለከተውም ውጤቱ አስከፊ እንዲሆን ምክንያት የነበሩ መሆናቸውን ሕዝብ ተገንዝቦ በጥብቅ ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ሃይ ማለትም አለብን፡፡ በአፋጣኝ መጀመር ያለበት የብልፅግና፣ የሸማቂዎችና የመላው ይመለከተኛል ባይ ፖለቲከኛ ውይይትና ድርድር ብልሹውን የፖለቲካ ባህል እንዲያስወግድ ከተፈለገ፣ ሰከን ያለና የሠለጠነ ግንኙነት እንጂ የኖርንበት የቡድንተኝነትና የድርቅና ፖለቲካ አያስፈልገንም፡፡ ዴሞክራሲ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት፣ የማያስማሙ ጉዳዮችን እያቻቻሉ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ የሚግባቡበት፣ ከኃይል ይልቅ ውይይትን የሚያስቀድሙበትና ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ የሚሆኑበት ነፃ መድረክ እንጂ ጉልበተኞች የሚፈነጩበትና አላዋቂዎች የሚቀልዱበት አይደለም፡፡ እናም በየትኛውም አገር ያለ የአገር ሰው ለዚህ እውነታ በድፍረትና በሀቅ መቆም አለበት፡፡

በየትኛውም የአገራዊ ምክክር አጀንዳ ወይም የፖለቲካ ውይይት የድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ፓርቲዎች/ተፋላሚዎች እርስ በርስ ዕውቅና መሰጣጣትና ለሰጥቶ መቀበል መርህ ተገዥ ሊሆኑ የግድ ነው፡፡ ይህ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚንፀባረቅ ፍላጎት መሬት ላይ ወርዶ በተግባር እንዲታይ፣ እነዚህ ኃይሎች መጀመሪያ ለሕግ የበላይነት መገዛት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ በሕግ የበላይነት ሥር የሚመራ መንግሥታዊ ሥርዓት ነውና (በቅርቡ በኦነግ ሸኔና በመንግሥት መካከል የተደረገውና ያልተጨበጠ ዓይነት ድርድር አገር እንደማያቆም ልብ ይሏል)፡፡

መቼም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ውይይትም ሆነ ድርድር ለማድረግ መሰናዳት ያለባቸው ወገኖች፣ ለሕዝብ የሚጠቅሙት ያለፉትን ቂምና ቁርሾዎች ወደ ጎን በማድረግና ለአገርና ለሕዝብ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ከልብ በማመን መንቀሳቀስ ሲችሉ ነው፡፡ አዲሱን ጉዞ በሠለጠነ መንገድ ላይ በመጓዝ ሲጀምሩት እንጂ አንዱ በሌላው ጫማ ላይ ሳይቆምና ባለመተሳሰብ ሕዝብን ያላማከሉ ጩኸቶችን በማሰማት አይደለም (እዚህ ላይ ሕወሓት፣ የአማራ ፖለቲከኞችና የፌዴራል ኃይሎች በጥብቅ ሊያስቡበት ይገባል)፡፡ ጎበዝ እንንቃ፡፡ ከፖለቲካ ፍጆታነት የማይዘሉ አጓጉል ድርጊቶችን በማስወገድ የዜጎችን አንገት ሲያስደፋ የኖረውን አስከፊ የፖለቲካ ባህል መለወጥ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ድርድሩም ሆነ ውይይቱ በቀና መንፈስ እንዲጀመር ሲፈለግ በቅድመ ሁኔታዎች እያመካኙ ምክንያት መደርደር ሊቆም ይገባል፡፡ ድርድሩም ሆነ ውይይቱ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ክፍት ከሆነ ቀዳሚው ጉዳይ የአገርና የሕዝብ ጥቅም ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁርጠኛ መሆን ግዴታ ነው፡፡ የመንግሥትም ዋነኛ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...