Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ዝርፊያና ዘራፊዎች ሲበራከቱ ጠንቀቅ ከማለት ጀምሮ በጋራ ምን ማድረግ እንዳለብን መነጋገር የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ እኔ ላይ ካልደረሰ ስለሌላው ግድ አይሰጠኝም ማለት የጠቀመው ዘራፊዎችን ብቻ ነው፡፡ የእኔም መነሻ ይህ የቆየ ችግራችን ነው፡፡ በፊት ‹ቁጭ በሉ› ከሚባሉ አጭበርባሪዎች ጀምሮ እስከ ኪስ አውላቂዎች በርካታ ገጠመኞችን እንደምናውቅ አልጠራጠርም፡፡ በበኩሌ ከሁሉም የማይረሳኝ ፒያሳ ውስጥ የዛሬ 15 ዓመት የተፈጸመ ድርጊት ነው፡፡ ሰውየው በሙሉ ልብስ ከከረባት ጋር ተውቦ ዘ ኬቭ የሚባለው ካፌ ግድግዳ ተደግፎ ያለቅሳል፡፡ ይኼን የመሰለ ዘንካታ ሰው ምን ሆኖ ነው እየተንሰቀሰቀ የሚያለቅሰው በማለት ጠጋ አልኩት፡፡ እንደ ሕፃን ልጅ ፊቱ በዕንባ ታጥቦ ዓይኖቹ ድልህ ይመስላሉ፡፡ ለማንኛውም አረጋግቼ ለማነጋገር ስጠጋው ሰዎች ከበብ ማድረግ ጀመሩ፡፡

‹‹ወንድሜ ምን ገጠመህ?›› በማለት የመጀመሪያውን ጥያቄ ስወረውርለት፣ ‹‹ወገኖቼ ተዘረፍኩ፣ በቁሜ ተዘረፍኩ…›› እያለ እዬዬ አለ፡፡ እኔና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ሰውዬውን ከከበባው ውስጥ አውጥተን ትሪያኖ ካፌ ወስደን አረጋግተን ማነጋገር ጀመርን፡፡ ሰውዬው እንደሚለው በእጅ በሚያዝ አነስተኛ ቦርሳ 40 ሺሕ ብር ይዞ ባንክ ለማስገባት ደጎል አደባባይ ከታክሲ ሲወርድ፣ ሁለት ከገጠር የመጡ የሚመስሉ ሰዎች ሰላምታ ያቀርቡለታል፡፡ እሱ እንደሚለው እነዚህ የገጠር ሰዎች የተባሉት ወንድና ሴት ናቸው፡፡ ወንድየው በሃምሳ፣ ሴትየዋ ደግሞ በአርባ ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ይገመታሉ ነበር ያለን፡፡

ሁለቱ ገጠር ተብዬዎች በገጠር የአነጋገር ዘዬ ሎተሪ ደርሷቸው ከገጠር እንደመጡ፣ ነገር ግን እንዴት ገንዘባቸውን እንደሚቀበሉ ስለማያውቁ እሱ እንዲያወጣላቸው እየተለማመጡ እየጠየቁት ሳለ ሁለት ሎተሪ አዟሪዎች ይመጣሉ፡፡ ሰዎቹም ይኼው የደረሰንን ዕጣ እይ ብለው የሎተሪ ቲኬታቸውን አውጥተው ያሳዩታል፡፡ በእርግጥም የአንደኛ ዕጣ አሸናፊ ቁጥርና የሎተሪው ቁጥር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰውየው በሐሳባቸው ተስማምቶ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በር ድረስ አብሯቸው ይሄዳል፡፡ እነሱም መታወቂያ ስለሌላቸው ገብቶ እንዲያወጣላቸው በገጠር አነጋገር ይለምኑታል፡፡ እሱም ምንም ሳይጠረጥር ተስማምቶ ሊያወጣላቸው ሲገባ ሴትየዋ ቦርሳውን ትቀበለዋለች፡፡ ‹‹ምን እንደነካኝ አላወቅኩም፣ 40 ሺሕ ብር የያዘውን ቦርሳዬን ሳልጠራጠር ሰጥቻት ገባሁ፡፡ የሚመለከተው ኃላፊ ዘንድ ደርሼ ሎተሪውን ሰጠሁት፡፡ ገልበጥ ገልበጥ አድርጎ ካየው በኋላ አንገቱን እየነቀነቀ ‹ሎተሪው ያንተ ነው?› ሲለኝ አይደለም አልኩት፡፡ ‹በል ወዳጄ ንብረት ወይም ገንዘብ ሰጥተህ ከሆነ ፍጠን› ሲለኝ በቁሜ ደረቅኩ፡፡ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ግቢ ወጥቼ ወዲያ ወዲህ ብል ማንም የለም፡፡ በቃ ለዓመታት የለፋሁበትን ጥሪቴን በደቂቃዎች ውስጥ አዘረፍኩ፡፡ እኔማ መሞት ነው ያለብኝ…” ብሎ እዬዬውን ሲያቀልጠው ያስደነግጥ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሰውየውን ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስደን ቃሉን እንዲሰጥ አደረግን፡፡ አንድ በጣም ታዋቂ ልምድ ያለው መርማሪ ፖሊስ በዓይን እንተዋወቅ ስለነበር በጣም አዝኖ፣ ‹‹የእኛ ሰው በተደጋጋሚ ሲነገረው አይሰማም፡፡ በሎተሪ የተነሳ በፖሊስ ሬዲዮና ጋዜጣ ብዙ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡ ነገር ግን በየቀኑ የሚዘረፈው ሰው ብዙ ነው፡፡ ትንሽ ጥቅም ለማግኘት ወይም በአጉል አዛኝነት ሕዝቡ እየተዘረፈ ነው፡፡ ይኼንን መጥፎ ድርጊት ለማስቆም አንድ አገር አቀፍ ዘመቻ ያስፈልገናል…›› ብሎኝ ተለያየን፡፡ የዚያ ቅስሙ የተሰበረ ሰው ሁኔታ ግን አሁንም ፈጽሞ አይረሳኝም፡፡ ለዓመታት ያለ ዕረፍት እየሠራ በዕቁብ ያገኘውን ገንዘብ ነበር በገጠር መሳይ ወንበዴዎች የተዘረፈው፡፡ አሁንም የረቀቁ በርካታ ዝርፊያዎች በዙሪያችን አሉ፡፡ የአንድ ወቅት ገጠመኜ ደግሞ ይህንን ይመስላል፡፡

የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ነው ከፒያሳ ይዞኝ የመጣው ታክሲ ሚሊኒየም አዳራሽ ፊት ለፊት የድሮው ቦሌ ሚኒ ካፌ አጠገብ ያወርደኛል፡፡ መንገዱን ተሻግሬ እንደጨረስኩ ሚሊኒየም አዳራሽ በራፍ አጠገብ አንዲት በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ሴት እሪ ትላለች፡፡ ጠጋ ብዬ ምን እንዳጋጠማት አንዱን ስጠይቅ ከዓረብ አገር እንደገባች መዘረፏን ይነግረኛል፡፡ ሚሊኒየም አዳራሽ ጥበቃ ላይ ያሉት የፖሊስ ባልደረቦች እያፅናኑዋት ድርጊቱ እንዴት እንደተፈጸመ ይጠይቋታል፡፡ ልጅቷ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ስትደርስ ሻንጣዎቿንና የእጅ ቦርሳዋን ይዛ ታክሲ ታፈላልጋለች፡፡ በዚህ መሀል ሁለት ሰዎች እንደሚረዷት ይነግሯትና በመኪና ይዘዋት ይወጣሉ፡፡ ሚሊኒየም አዳራሽ ጋ ሲደርሱ እሷ ለዘመዶቿ ስልክ እንድትደውልና የሚሞላ ፎርም እንድትሞላ በማለት ከመኪና እንድትወርድ አድርገው፣ ሳታስበው በፍጥነት ተፈትልከው ይጠፋሉ፡፡

ለዓመታት ዓረብ አገር ለፍታ ያገኘችው ገንዘብ፣ ወርቅና ሌሎች ጌጣጌጦች፣ የሞባይል ስልኮች፣ አልባሳት፣ መጫሚያዎችና የመሳሰሉትን ንብረቶች ሰዎቹ ዘርፈዋት በመሄዳቸው ባዶ እጇን ቀርታለች፡፡ በእውነቱ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ግፍ ነው የተፈጸመባት፡፡ ይህች ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተሰዳ በዓረብ አገር በሥቃይ ያሳለፈች ሴት አገሯ ስትገባ የወንበዴዎች ሰለባ መሆኗ ቅዠት ሆኖባታል፡፡ የገጠማትን እየተናገረች በመሀል እሪሪ ስትል አዕምሮዋን የሳተች ትመስላለች፡፡ በእርግጥም አዕምሮዋን ብትስት አይገርምም፡፡ የለፋችበትን ገንዘብና ንብረት በደቂቃዎች ውስጥ ተዘርፋ ባዶዋን ቀርታለች፡፡ መሄጃ የላትም፡፡ በአንድ ጊዜ የቀኑ ብርሃን ጨለማ ሆኖባታል፡፡ በበኩሌ ዕንባዬን መቆጣጠር ነበር ያቃተኝ፡፡ ሰው በወገኑ ላይ ይኼን ያህል እንዴት ይጨክናል? በሊቢያ በረሃ ያ ሁሉ አረመኔያዊ ግፍ ተፈጽሞባቸው የተጨፈጨፉት ወገኖቻችንን ለሚያስብ ማንም ዜጋ፣ ይኼ በአገራችን ወንበዴዎች የተፈጸመ የዝርፊያ ተግባር ከዚያ አይተናነስም፡፡

የዚህ ዓይነት ድርጊት ከዚህ በፊት ተፈጽሞ እንደሆነ ለማጣራት አንድ የማውቀው ሰው ዘንድ ወደ ቦሌ ድልድይ አካባቢ አመራሁ፡፡ እሱ እንደነገረኝ ከዓረብ የሚመጡ በርካታ ሴቶች በተለያዩ ጊዜያት ተዘርፈዋል፡፡ አንዳንዶቹ በታክሲ እየታፈኑ ተወስደውም ይደፈራሉ፡፡ ገንዘባቸው፣ ጌጣ ጌጦቻቸውና አልባሳቶቻቸው ተዘርፈው በቦሌ መንገድ ላይ እንደ ዕብድ የሚሮጡ ብዙ ጊዜ ታይተዋል አለኝ፡፡ ሕግ ባለበት አገር እንዴት እንዲህ ዓይነት ተግባር በአደባባይ ይፈጸማል? እንዲህ ዓይነቶቹ ሰብዓዊነት የሚጎድላቸው ዘራፊዎች ከኤርፖርት እስከ ውጪ ድረስ ያላቸው የግንኙነት ሰንሰለት እንዴት አይታወቅም? እነሱስ ማን ናቸው? ፖሊስ ይህንን ጉዳይ በጥብቅ ተከታትሎ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡ በዚህ ደግሞ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከበቂ በላይ ነው፡፡

እንግዲህ ከላይ የገለጽኩላችሁ ችግር የቆየ ቢመስልም አሁንም እንደሚኖር አልጠራጠርም፡፡ በቀደም ዕለት ቦሌ መድኃኔዓለም ተሳልሜ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ ለመሄድ መንገዱን ማቋረጥ ነበረብኝ፡፡ መንገዱን አቋርጬ በእግረኛው ጎዳና ላይ ስራመድ አንድ ወንድና ሴት ፈረንጅ አልፈውኝ ሲሄዱ ድንገት ሁለት ጎረምሶች ከፊታቸው ተገተሩ፡፡ ፈረንጆቹ በሁኔታው ተደናግረው ግራና ቀኝ እያዩ ሲቆሙ አንደኛው ማስቲካ ወይም ናፕኪን የያዘበትን ሱቅ በደረቴ ፊታቸው ሲያስጠጋ፣ ሌላው በፍጥነት ወደ ወንዱ ፈረንጅ የጃኬት ኪስ እጁን ሰዶ የሆነ ነገር ለማውጣት ሲጣደፍ ፈረንጁ እጁን ግጥም አድርጎ ያዘው፡፡ ይኼን ጊዜ ባለሱቅ በደረቴው ሰውየውን በአንድ እጁ በቦክስ ሲማታ ሴቷ ፈረንጅ ከኋላው በጠረባ ስትመታው ወደቀ፡፡ እጁ የተያዘው የጓደኛውን መውደቅ ሲያይ መንጭቆ በሩጫ ተፈተለከ፡፡

እኔና አንድ ሰው በድንገተኛው አጋጣሚ ተደናግጠን ስለነበር ወደ ፈረንጆቹ ዘግይተን ስንንደረደር፣ እነሱ የእኛን የዘገየ ዕርዳታ ሰጪነት ባለመፈለግ በቆምንበት ጥለውን መንገዳቸውን ሲቀጥሉ ባለሱቅ በደረቴ መሳዩ ሌባም ከወደቀበት ተነስቶ እሱም ሸሸ፡፡ እዚያ ጋ ሚዛን ይዘው የሚቆሙ ሁለት ታዳጊዎችና አንዲት ሕፃን የያዘች የእኔ ቢጤ ስንጠይቃቸው የተለመደ ድርጊት መሆኑን ነገሩን፡፡ በቅርብ ርቀት ላይ ያለው መብራት አካባቢ ፖሊሶች ሲኖሩ ሌቦቹ ድርሽ እንደማይሉ፣ ሳይኖሩ ሲቀሩ ግን ብቅ እንደሚሉ ተነገረን፡፡ የሚመለከታቸው ልብ ይሉት ዘንድ አሳስባለሁ፡፡ 

(ዓብይ አለማየሁ፣ ከቦሌ ሆምስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...