Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያስጠናቸው ጥናቶች ተግባራዊነትና ሒደት እስከ ምን?

የፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያስጠናቸው ጥናቶች ተግባራዊነትና ሒደት እስከ ምን?

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከዓመት በፊት ጥናት አስጠንቶ ለክለቦችና ለተለያዩ የስፖርት ባለድርሻ አካላት ማድረሱ ይታወሳል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ‹‹ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናትና የልማት ፍኖተ ካርታ›› በሚል ርዕስ በአሜሪካ ታውሰን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የፌስ ኮርነር አማካሪ ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) አማካይነት ካስጠናቸው መካከል ቅድሚያ ሊተገበሩ ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች ወደ ተግባር ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመሩም ተገልጾ ነበር፡፡

 ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ ሊግ አክሲዮን ማኅበርና በብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል ያለው ግንኙነት፣ የክለብ ይዞታነት፣ የተጫዋቾች የደመወዝ አከፋፈል ሥርዓት፣ እንዲሁም የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ (ላይሰንስ) ይገኙበታል፡፡

በጥናቱ መሠረት አክሲዮን ማኅበሩ ከፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት መፈራረሙን ይታወቃል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሁለቱ ተቋማት መካከል ሲነሳ የነበረው የሥራ ድርሻና የኃላፊነት ወሰን በግልጽ ተለይቶ በጋራ የሚሠሩበት ጉዳዮችን በተመለከተ ስምምነት አስረዋል፡፡

በሌላ በኩል በጥናቱ ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር ሲሆን፣ ይህም የደመወዝ ጣሪያ በይፋ ለማስቀመጥ ውይይት እየተደረገ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በሚቀመጠው የደመወዝ ጣሪያ አማካይነት የሚከፈላቸው ሲሆን፣ ምን ያህል መጠን እንደተቀመጠ ይፋ የሆነ ነገር የለም፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጫዋቾች ክፍያ ቅጥ ያጣ በመሆኑ፣ ክለቦችንና ከተማ አስተዳደሮችን፣ ሊጉን፣ እንዲሁም የአገሪቱ እግር ኳስ ወደ ኋላ እንዲቀር ምክንያት መሆኑ ይነሳል፡፡

በሊጉ እየተካፈሉ የሚገኙ ክለቦች በዓመት የሚያወጡት በጀት ከፍተኛውን የሚይዘው የተጫዋቾች ደመወዝ መሆኑን ተከትሎ፣ የአክሲዮን ማኅበሩ የተጫዋቾች ደመወዝ ክፍያ ጣሪያ እንዲያስቀምጥ ሐሳብ ሲቀርብለት ነበር፡፡

በዚህም መሠረት አክሲዮን ማኅበሩ ከመደበኛው ጥናት በዘለለ ተጨማሪ ጥናት በማድረግና ከክለቦች ጋር ውይይት ሲያደርግ መክረሙ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያ መጠን ለማስቀመጥ ከውሳኔ መድረሱ ተጠቁሟል፡፡

የደመወዝ ጣሪያው ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ በፕሪሚየር ሊጉ እየተካፈሉ የሚገኙ ክለቦች፣ እንዲሁም ተጫዋቾች ይፋ ለሚደረገው የክፍያ አስተደደር ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዓመት በፊት ይፋ በሆነው ጥናት መሠረት የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደርን ለመገምገም አራት የመረጃና የማስረጃ ምንጭ ግልጋሎት ላይ መዋላቸውን ተጠቅሶ ነበር፡፡

እነዚህም የእግር ኳስ ገዥ ሕጋዊ ሰነዶች ግምገማ፣ የአገሮች ተሞክሮዎች ፍተሻ የሳይንሳዊ ጥናት ጽሑፎችና ከሊጉ የባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገ ቆይታ ይገኙበታል፡፡ የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር የተሞክሮ ዳሰሳ መካከል የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት የገንዘብ አወጣጥ ጨዋነት መመርያ (ፋይናንስ ፌር ፕሌይ) በአውሮፓ የሚተገበር የክለቦች የገንዘብ አወጣጥ መመዘኛና መቆጣጠሪያ መንገድ አንዱ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡

በአውሮፓ ሊጎች ውስጥ የሚሳተፉ የእግር ኳስ ክለቦች ከሚያገኙት ገንዘብ በላይ እያወጡ እንዳልሆነ ለመቆጣጠር ዩኤፍኤ የሚጠቀምበትን አሠራር ሥርዓት እንደሚከተል ያስቀምጣል፡፡

በአንፃሩም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ክለቦች ከሚያገኙት ገቢ በላይ እንዳያወጡ፣ እንዲሁም ክለቦች እንደ አቅማቸው መኖር የሚያስችላቸው ስትራቴጂ እንደሚቀረፅ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ለተጫዋቾች የሁለት ዓመት ቆይታ ከስድስት ሚሊዮን እስከ 13 ሚሊዮን ብር ድረስ እየከፈሉ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡

በዚህም መሠረት አንድ ተጫዋቾች እስከ 600 ሺሕ ብር ወርኃዊ ደመወዝ እየተከፈለው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል አክሲዮን ማኅበሩ በጥናት ካካተቷቸው ጉዳዮች መካከል ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ የተጠቆመ ሲሆን፣ የመውጫ ዕቅድ ተሰናድቶ እንዴት መተግበር እንዳለበት እየመከረበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በመውጫ ዕቅዱ መሠረት በተለይ በመንግሥት ይዞታነት የሚተዳደሩ ክለቦች እንዴት ከመንግሥት ይዞታነት ይላቀቁ የሚለው፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙ ክለቦች እየተከተሉበት ከሚገኘው መንገድ እንዴት መላቀቅ አለባቸው የሚለው ትኩረት አግኝቷል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ እየተሳተፉ ከሚገኙ 16 ክለቦች ውስጥ 13ቱ ክለቦች በመንግሥት ይዞታነት የሚተዳደሩ ናቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...