Sunday, March 3, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለጥቃት ተጋላጮች አስተማማኝ ከለላ ይሰጥ!

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የተከሰቱ መጠነ ሰፊና አሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ያወጣው መግለጫ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ኮሚሽኑ በሦስቱ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ዓውድ ውስጥና ከግጭት ዓውድ ውጪ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በእጅጉ አሳሳቢነቱ መቀጠሉን ነው ያስታወቀው። በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተስፋፍተው በቀጠሉ ግጭቶች ዓውድ ውስጥ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዕገታዎችና ዘረፋዎች የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት እጅግ የከፋ ማድረጋቸውን መግለጫው ያትታል፡፡ መግለጫው እስከ ወጣበት ረቡዕ ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በእነዚህ አካባቢዎች የደረሱ ተጨማሪ ጥቃቶችን በተመለከተ ለኮሚሽኑ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን ገልጾ፣ የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራውን መቀጠሉን አስታውቋል። እንዲሁም በአጋጠሙ ክስተቶች ላይ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ፣ ዝርዝር መረጃዎችና ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያደርገውን ጥረት እቀጥላለሁ ብሏል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣  ‹‹በዚህ የግጭት ዓውድ እየደረሰ ያለው እጅግ አሰቃቂ ጉዳት ከዚህ የበለጠ ከመባባሱና የበለጠ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግሥት ተገቢውን ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖችና መንግሥት ሰብዓዊ የተኩስ ማቆም አድርገው ወደ ውይይት እንዲያመሩ፣ መንግሥት በተለይ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎችና ነዋሪዎች በሙሉ የተሟላ ጥበቃና ደኅንነት እንዲያረጋግጥ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ የጥፋተኞችን ተጠያቂነትና ፍትሕ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፣ መንግሥትና ሌሎች አጋር አካላት በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች  በቂ የሆነ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ልብ ሰባሪ መግለጫ ሲወጣ ኢትዮጵያውያን ደንገጥ ማለት አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ መንግሥት በቀረበለት ማሳሰቢያ መሠረት ግጭቶች እንዲቆሙ ተነሳሽነቱን መውሰድ ሲገባው፣ በግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትም ለሰላም መስፈን የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ ሥፍራዎች በታጣቂዎች በተሰነዘሩ ብሔር ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች ሳቢያ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው፣ አካላቸው መጉደሉና ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በብዛት መሰደዳቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡ በተለይ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞችና አረጋዎች የጥቃቶቹ ሰለባ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ቤታቸው ውስጥና ከቤታቸው ውጪ አሠልፎ በመረሸን ታጣቂዎቹ ነውረኛ ጭካኔ ማሳየታቸው የመግለጫው አንድ አካል ነው፡፡ በቤተ እምነት ጸሎት ላይ የነበሩ ወገኖች ሳይቀሩ መገደላቸው ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም እርሻዎቻቸውና የመኖሪያ ቤቶቻቸው ተቃጥለው የወደሙባቸው፣ እንስሳቶቻቸው የተገደሉባቸውና የተዘረፉባቸው በርካቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ጭካኔዎች በንፁኃን ላይ እስከ መቼ ነው የሚቀጥሉት የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሲሆን፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ዓላማ ምን እንደሆነ ሲታሰብ ግራ ያጋባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየተለመደ የመጣው ነውረኛ ጭካኔ ሊቆም የሚችለው፣ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በትብብር መሥራት ሲችል ብቻ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከመግለጫው ለመረዳት እንደተሞከረውም የሚፈለገው ይኸው ነው፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ባወጣቸው በርካታ መግለጫዎች ሲያሳስብ የነበረው፣ መንግሥት ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሰላማዊ ሰዎችን የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት ነው፡፡ በተጨማሪ ለችግሮች ሕጋዊና ፖለቲካዊ መፍትሔዎች እንዲፈለጉ በማሳሰብ፣ የግጭት ተሳታፊ አካላት በሙሉ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም በማድረግ ለውይይትና ለድርድር እንዲቀመጡም ጥሪ ሲያደርግ ነበር፡፡ ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብና ፍትሕ ማስፈን ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሲሆን፣ መንግሥት ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በግጭቶች ምክንያት የሚፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ነበር፡፡ በአሁኑ መግለጫም  በግጭቶቹ ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲባል፣ ከመንግሥት በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጭካኔ ድርጊቶችን ከመቃወም በዘለለ ለዘለቄታዊ መፍትሔ በአንድነት መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ መሀሉ ዳር እስኪሆን ድረስ ዝምታ አይበጅም፡፡ ለአገር ህልውና ሲባል ልዩነትንና የሚሳሱለትን ክብር ገታ አድርጎ መነጋገር ይገባል፡፡ ማዶ ለማዶ ሆኖ የጎሪጥ ከመተያየት ተቀራርቦ በመነጋገር ልዩነትን ፈር ማስያዝ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ያስፈልጋታል ሲባል ለአባባል ያህል የሚነገር ተራ ጉዳይ አይደለም፡፡ ያለ ጥፋታቸው እየተቀጡ ያሉ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞችና ሌሎች ሰላማዊ ወገኖች ሰቆቃ በቀጠለ ቁጥር ለአገር ህልውና ይዞት የሚመጣው ዳፋ ከባድ ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ተዋንያን ከዚህ ዓይነቱ አደገኛ የጥፋት አዙሪት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ በመረዳት፣ ለዘለቄታዊ ሰላም መስፈን የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት መወጣት ግዴታቸው ነው፡፡ ልዩነትን ይዞ በሠለጠነ መንገድ መነጋገርና መደራደር እየተቻለ በሰላማዊ ወገኖች ደም የሚወራረድ ሒሳብ ማንንም የትም አያደርስም፡፡ ለሰላም የሚደረግ እያንዳንዱ ጥረት አድካሚ ቢሆንም ፍሬ እንደሚያፈራ በመገንዘብ፣ ከፓርቲና ከግለሰብ ተክለሰባዊ ግንባታ በላይ ለአገርና ለሕዝብ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞች ባልተሰማሙ ቁጥር ንፁኃን የሚያልቁበት የፖለቲካ ቁማር መገታት አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ቁማር አጥፊ ነው፡፡ በሕዝብ ዕንባና ደም በመነገድ ወይም በመቆመር የሚገኝ ሥልጣንና ጥቅም ዕርባና ቢስ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የተጓዙ ያተረፉት ውርደት ነው፡፡

በየአካባቢው በሚፈጸሙ ጥቃቶችና የመብት ጥሰቶች ምክንያት በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቃቶቹና የመብት ጥሰቶቹ በአሳሳቢነት ቀጥለዋል ብሎ መግለጫ ሲያወጣ፣ መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ግብረ መልሳቸው ፈጣን መሆን አለበት፡፡ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች ያለ ጥፋታቸው ሰለባ መሆናቸው ሲቀጥል፣ በአገር ህልውና ላይ የሚያስከትለው መዘዝ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የማይኖርባቸው በርካታ ግጭቶችና ጥቃቶች በሰላማዊ ወገኖች ላይ ያደረሱት ጥፋት፣ ዕልቂት፣ መፈናቀል፣ መራብ፣ መጠማት፣ ውድመት፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ናቸው፡፡ ከግጭቶቹ አካባቢዎች ርቀው ጥፋቶችን የሚያበረታቱ በጀብደኝነት ለንፁኃን ሰቆቃዎችን ሲያመርቱ፣ አንድም ቀን ለሰላምና ለመረጋጋት የሚረዳ አስተዋፅኦ ለማበርከት ፈቃደኝነታቸውን አሳይተው አያውቁም፡፡ በዚህ መሀል ግን ሕዝባችን ያለ ኃጢያቱ የመከራ ዶፍ እየወረደበት ነው፡፡ ከሞት የተረፉ ወገኖች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተሰደው የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ሲንከራተቱ፣ በስማቸው የሚነግዱባቸው ግን ምንም ዓይነት ርኅራኄ ሊያሳዩዋቸው አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ነው ለጥቃት ተጋላጮች አስተማማኝ ከለላ መሰጠት ያለበት!       

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...