Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየስኳር ፋብሪካዎች መከላከያ ሠራዊት ተመድቦላቸው  እያመረቱ መሆኑ ተገለጸ

የስኳር ፋብሪካዎች መከላከያ ሠራዊት ተመድቦላቸው  እያመረቱ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ውስጥ ከተካተቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው፣ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሚስተዳድራቸው የስኳር ፋብሪካዎች፣ በፀጥታ ምክንያት ማምረት ባለመቻላቸው፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ተመድቦላቸው ጥበቃ እየተደረገላቸው እያመረቱ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በስኳር ፋብሪካዎች አካባቢ ባለው የፀጥታ ችግር የተነሳ፣ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በአንድ ክፍለ ጦር እየተጠበቀ እንዲያመርት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት፣ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ናቸው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን የ2016 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት፣ ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መከላከያ ሠራዊት ጥበቃ የሚያደርገው ከፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ መሆኑን፣ ይህም ሆኖ አጥፊው ተደብቆ ሥራውን እንደሚሠራ፣ የፋብሪካ መለዋወጫ ከአዲስ አበባ ወደ ፋብሪካው ሲላክ በአጃቢ መሆኑን፣ እንዲሁም ምርት ከፋብሪካዎች ሲወጣም እንዲሁ በአጃቢዎች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በአብዛኛው የስኳር አገዳ እርሻ ልማት ላይ በፍፁም መድረስ አይቻልም ያሉት አቶ ወዮ፣ በዚህም የእርሻና የመስኖ ሥራ ሳይከናወን የአገዳው ምርታማነት ጥያቄ ውስጥ ስለመግባቱ ተናግረዋል፡፡ ይህን ለማስተካከል በየቦታው ቢያንስ በአራት ሥፍራዎች መከላከያ ካምፕ ሠርቶ እርሻዎችን እየጠበቀ ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ  ላጋጠመ የፀጥታ ችግር መከላከያ ተመድቦ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

የከሰም የስኳር ፕሮጀክትም ቆሞ ለሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ ከስኳር ልማት ፈንድ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ በተመሳሳይ ኦሞ አንድና አርጆ ደዴሳ ከሌሎች ፋብሪካዎች በሚገኝ ገቢ ወጪያቸው እየተሸፈነ ነው ብለዋል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካም በ2015 ዓ.ም. በፀጥታ ምክንያት ማምረት ባለመቻሉ፣ ከሌሎች አራትና አምስት ፋብሪካዎች ከተገኘ ገቢ ወጪው ሲሸፍን እንደነበር ገልጸው፣ በፀጥታ ምክንያት ስኳር የማያመርቱ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ማምረት ጀምረው ካቆሙት መካከል ከሰም፣ ተንዳሆ፣ አርጆና መሰል ፋብሪካዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

ነባር ከሚባሉት ፋብሪካዎች መካከል ወንጂ፣ መተሐራ፣ ኦሞ ሦስትና ፊንጫ የተሻሉ የሚባሉና ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ አሁንም ትልቁ ችግራቸው ፀጥታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ፊንጫ ከ19 ሺሕ ሔክታር ወደ 11 ሺሕ ሔክታር መውረዱን፣ አብዛኞቹ ማሽኖች መቃጠላቸውንና አርጆ ከቁጥጥር ውጪ የነበረ ቢሆንም በመንግሥት ጥረት መመለሱን አስረድተዋል፡፡

ከመተሐራ ፋብሪካ 4,800 ሔክታር መሬት አገዳ መጥፋቱን አስታውቀው፣ ፋብሪካዎች የፀጥታ ችግሮች ካልተቀረፈላቸው የተሻለ ስም የነበረው የስኳር ምርት ስሙን ብቻ ይዞ ይቀራል ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ከቋሚ ኮሚቴው ትልቅ ዕገዛ እንፈልጋለን፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መንግሥት የፀጥታ ችግሩን ካላስተካከለ የስኳር ችግርን መፍታት አይችልም ብለዋል፡፡

አንድ ኩንታል ስኳር በ5,780 ብር ከፋብሪካ ተረክበው በ5,800 ብር መንግሥት እየሸጠ መሆኑን የተናገሩት አቶ ወዮ፣ የስኳር ዋጋ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲወዳደር በጣም የወረደ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹ሸራተን ሆቴልን ጭምር እየደጎምን መቀጠል አይቻልም፤›› ብለው፣ ዋጋው በዚህ ዓመት መስተካከል ስላለበት የማስተካከያ ዋጋ የያዘ ዶክመንት ቀርቦ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቢያንስ ፋብሪካዎች ባያመርቱ በተስተካከለ ዋጋ ሌሎችን በተወሰነ ደረጃ በመደገፍ ተሸክሞ መሄድ ይቻላል ብለዋል፡፡

የስኳር ፋብሪካዎች ባላቸው አቅም ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ማምረት እየቻሉ በዚህ ዓመት በተያዘው ዕቅድ በአገዳና በፀጥታ ችግር ምክንያት 300 ሺሕ ኩንታል ብቻ እንደሚያመርቱ የተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ ጣሂር ናቸው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በመሬት ይዞታና በፀጥታ ምክንያት አገዳ ስለማይቀርብ፣ ፋብሪካዎች እየሠሩ ባለመሆናቸው ችግሩ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የተቋማቸውን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርቡ፣ ‹‹የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ሌባ፣ ሽፍታና ወንበዴ ማፅዳት አይደለም፡፡ ሚሊሻ ምን ይሠራል? ከዚያ ካለፈ ፌዴራል ፖሊስ የት ይሄዳል? ይህንን አስተሳሰብ ካላስተካከልነው በየመንደሩ ያለውን የሌባ እንቅስቃሴ መከላከያ መጥቶ ያፅዳ የሚል ፍላጎት እየሰፋ ከሄደ፣ ሠራዊቱ ሥራውን ማከናወን አይችልም፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ የአገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መመከትና ማስቀረት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት አለብን እንጂ፣ የሠራዊቱ ተግባር በየመንደሩ ያለን ሌባ ማሳደድ ባለመሆኑ ይህ መሠረታዊ ችግር መስተካከል አለበት፤›› በማለት ለቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያ አቅርበው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...