Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተለያዩ አገልግሎቶች በተቆፈሩ ጉድጓዶች ገብተው የሚሞቱ ታዳጊዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

ለተለያዩ አገልግሎቶች በተቆፈሩ ጉድጓዶች ገብተው የሚሞቱ ታዳጊዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ለማዕድን ማውጣትና ለመንገድ ሥራ ተብለው ተቆፍረው በተተውና ውኃ በያዙ (ባቆሩ) ጉድጓዶች ውስጥ ለመዋኘት ሲሉ ገብተው የሚሞቱ የታዳጊዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ከመስከረም እስከ ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ብቻ አራት ሰዎች ለተለያዩ አገልግሎት ተብለው ተቆፍረው የተተውና ውኃ የያዙ ጉድጓዶች ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ተቆፍረው ክፍቱን በተተውና ውኃ ባቆሩ ጉድጓዶች ውስጥ ዋና ለመዋኘት በሚል ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው ጨምረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. ብቻ የ23 ዓመት ወጣትና የአሥር ዓመት ታዳጊ፣ በኅዳር ወር ደግሞ የ19 ዓመት ወጣት፣ የ12 ዓመትና የስምንት ዓመት ታዳጊዎች በጉድጓዶች ውስጥ ለመዋኘት ገብተው ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

አደጋዎቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 እና 13 ጨምሮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማርያምና ዱላ ማርያም በሚባሉ አካባቢዎች ችግሮቹ በስፋት እንደሚታዩ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ንጋቱ ገለጻ፣ ይህ መረጃ ኮሚሽኑ አገልግሎት ተጠይቆ ምላሽ የሰጠባቸው ብቻ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ለኮሚሽኑ ጥሪ ሳይደርስ የደረሱ አደጋዎች መረጃ አልተካተቱም፡፡

የኮሚሽኑ ሥራ በዋናነት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ለይቶ ለኅብረተሰቡና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማሳወቅ መሆኑን፣ ከዚያ ውጪ የተጠያቂነት ሥራ የተቋሙ ኃላፊነት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

አደጋ እያደረሱ የሚገኙት ጉድጓዶች ለመንገድ ግንባታ የሚሆኑ ድንጋይ ለማውጣት፣ ለመስኖና ለመንገድ ዝርጋታ በሚል የተቆፈሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው ዳሰሳ ለሥጋት ተጋላጭ ብሎ የለያቸው 25 የተቆፈሩ ጉድጓዶች መኖራቸውን፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች ችግሮቹ በስፋት የሚታይባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ፣ በባለሥልጣኑ ለማዕድን ማውጣት ለ222 ተቋማት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ፈቃድ ከተሰጣቸው ውስጥ 54 የሚሆኑት በሸገር ከተማ የተከለለ መሆኑን ጠቁመው፣ ስድስት የሚሆኑት ባለቤት የሌላቸውና የተፈጥሮ ኃይቅ የሚመስሉ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ትልልቆቹ ጉድጓዶች ባለሥልጣኑ ከመቋቋሙ በፊት የነበሩ መሆናቸውን፣ አሁን ባሉበት ከቀጠሉ የሰው ሕይወት የሚቀጥፉ ናቸው ብለዋል፡፡

አደጋ እንደሚያስከትል እያወቁ በአግባቡና በጥንቃቄ የማያለሙት ዕቅድ ያላቸው ተቋማት ተለይተው ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው አቶ ዲዳ ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት የተያዙ መሆናቸውን፣ ከካሳ፣ ከድንበርና ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ እንደልባቸው ጉድጓዶቹን ለመድፈን እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ችግር በመነጋገር ከዚህ የበለጠ አደጋ ሳይከሰት መፍትሔ ለመስጠትና ጉድጓዶቹን ለመድፈን እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይ ባለቤት የሌላቸው ጉድጓዶች በእርሻ ማሳ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን፣ ከዚህ ውስጥ ውኃ በቦቴ የሚቀዳባቸው፣ ከብቶች የሚጠጡበት፣ አሸዋ የሚታጠብባቸውና ለመስኖ ጭምር አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህ ጉድጓዶች የሚሰጡትንና የሚያስከትሉትን ጉዳዮች በመለየት ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግና መልሶ ልማት ላይ ለማዋል መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶቹ የተቆፈሩ ጉድጓዶች መልሶ ለመድፈን አስቸጋሪ መሆናቸውን፣ ባለሥልጣኑ ይህን ለማድረግ የአካባቢው ማኅበረሰብ ፈቃደኛ አለመሆኑ ሌላኛው ችግር ነው ብለዋል፡፡

በተለይ ወጣቶች ሕይወታቸውን ያጡባቸው ጉድጓዶች በሥራ ላይ የሚገኙ መሆናቸው፣ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ሥር እንደሚገኙና ቦታውን አደጋ እንዳያደርስ መከላከል እንዳይቻል ከድንበርና ከካሳ ጋር ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በባለሥልጣኑ ፈቃድ የሚሰጣቸው ተቋማት በዋናነት የድንጋይ ጠጠር፣ ጥቁር ድንጋይ ለቤትና ለመንግድ ግንባታ የሚውል ምርት ቆፍረው ለሚያወጡ ድርጅቶች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ክፍት በተተውና ውኃ በአቆሩ ጉድጓዶች ውስጥ ገብተው የሞቱ በ2013 ዓ.ም. አሥር፣ በ2014 ዓ.ም. ስምንት፣ በ2015 ደግሞ ሰባት የሚሆኑና ዕድሜያቸው ደግሞ ከአሥር እስከ 21 መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአካባቢው ዕድሜያቸው ከፍ ያሉት በዚያው አካባቢ የቀን ሥራ የተሰማሩ እንደሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...