Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመን ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት የተጣራ 1.8 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘመን ባንክ በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት የ22.8 በመቶ ብልጫ ያለው 1.81 ቢሊዮን ብር የተጣር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

ዘመን ባንክ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙ ያስመዘገበው የተጣራ ትርፍ የባንኩ አማካይ የተከፈለ ካፒታል መሠረት በማድረግ ለባለአክሲዮኖች በአንድ አክሲዮን 31.1 በመቶ የትርፍ ድርሻ ማስገኘቱ ታውቋል። 

የባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ገቢም ከቀዳሚው ዓመት የ37.7 በመቶ ዕድገት በማሳየት 5.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በሒሳብ ዓመቱ ለገቢው ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያበረከተው ከወለድ የተገኘው ገቢ ሲሆን፣ ይህም አራት ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የወለድ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ39.1 በመቶ ወይም የ1.5 ቢሊዮን ብር ዕድገት የተመዘገበበት ሆኗል፡፡ 

ከዓለም አቀፍና ተዛማጅ የባንክ አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ 1.74 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ4.1 በመቶ ወይም የ68 ሚሊዮን ብር ዕድገት የተመዘገበበት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም  ከዕቅዱ አንፃር የ357 ሚሊዮን ወይም በ17 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን፣ ለዚህም በዋናነት የብር የመግዛት አቅም መዳከም ከውጭ ምንዛሪ ግዥና ሽያጭ የተገኘው ገቢ ከዕቅድ በታች እንዲሆን ማድረጉን አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል።

በሌላ በኩልም ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ በተቀመጠው መመርያ መሠረት፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ 262.5 ሚሊዮን ዶላር ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጉ ታውቋል፡፡ ይህ ገንዘብ በባንኩ በኩል ሥራ ላይ ቢውል ኖሮ ሌሎች ተጓዳኝ ጥቅሞች ሳይጨመሩበት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ባንኩ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ያስችል እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ 

ዘመን ባንክ በ2015 ሒሳብ ዓመት በገቢና በወጪ ንግድ፣ እንዲሁም በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት፣ ኢንቨስትመንትና በሌሎች የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ደንበኞች ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ 527.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል። ይህም ግኝት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ25.5 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ5.1 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ 

ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰጠው የብድር ክምችት ወደ 31.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ10.3 ቢሊዮን ብር ወይም የ48.6 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም የ37.2 በመቶ ወይም የ10 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 36.9 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡ 

የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ የባንኩን ብድሮች ጤናማነት ለማረጋገጥ በተሠራው ተከታታይ ሥራ የተበላሸ ብድር መጠኑ በ2014 ሒሳብ ዓመት ከነበረበት 1.51 በመቶ ወደ በ2015 የሒሳብ ዓመት ወደ 1.09 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ይህ የተበላሸ የብድር መጠን የብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ጣራም ሆነ፣ በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ካለው የተበላሸ ብድር መጠን ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

አቶ ኤርሚያስ በበኩላቸው፣ የአንድን ባንክ ጤናማነት ከሚያረጋግጡት ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ የብድር ጤናማነት በመሆኑ፣ በተለይም የምጣኔ ሀብት ዕድገት መቀዛቀዝ በሚያጋጥም ጊዜ የተበላሹ ብድሮች ሊጨምሩ የሚችሉበት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ፣ በቀጣይ ቦርዱ የባንኩ ብድሮችን ጤናማነት፣ እንዲሁም የተበላሹ ብድሮች በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው ይሆናል ብለዋል፡፡

የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት በ2015 መጨረሻ ላይ 47.8 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ36.2 በመቶ ወይም በ12.7 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል፡፡ 

ባንኩ ካፒታሉን ከአምስት ቢሊዮን ብር ወደ 15 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያሰለፈውን ውሳኔ ተከትሎ አሥር ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አዲስ አክሲዮኖችን ለነባር ባለክሲዮኖች ያቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው አክሲዮን የግዥ ማረጋገጫ ማግኘቱን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ገልጸዋል።

አቶ ኤርሚያስ አክለውም፣ ‹‹የባንካችን ባለአክሲዮኖች የባንካችንን ካፒታል ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆን በወሰናችሁት መሠረት እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጨማሪ 9.2 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈርመው ተጠናቀዋል፤›› ብለዋል፡፡

ይህም የተፈረመ ካፒታሉን ወደ 14 ቢሊዮን ብር እንዳሳደገው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች