Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርዕውን ለምክክር ዝግጁ ነን?

ዕውን ለምክክር ዝግጁ ነን?

ቀን:

በንጉሡ አክሊሉ (ዶ/ር)

ሰሞኑን ከተወሰኑ ወዳጆቼ ጋር ስለአገራችን የፖለቲካ ጉዳይ የልብ የልባችንን ለመጫወት ዕድል አግኝተን ነበር፡፡ ለአገራችን ሰላምና ደኅንነት እጅግ የሚያስቡና ዕለት ተዕለት የሚጨነቁ አልፎም የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ ጭምት አልሞት ባይ ተጋዳዮች ናቸው:: ጨዋታችን እዚህና እዚያ ሲረግጥ ቆይቶ በመጨረሻ ምክክር (ዲያሎግ) ላይ አተኮረ፡፡ ይህችን ጽሑፍ የማዘጋጀት ሐሳብም በዚያን ጊዜ በልቤ ተፀነሰ::

ከተወሰኑ ዓመታት ጀምሮ የአገራችን ፖለቲካ ፅኑ ሕመም ፈውስ የሚያገኘው እስካሁን በመጣንበት የአስተሳሰብ ቅኝት ሳይሆን፣ ከራሳችን ባህላዊ ፀጋዎችና ከሌሎች አገሮች ከምናገኘው መልካም ተሞክሮ መሆኑን ተረድተን ይህ የምክክር ሐሳብና መንፈስ በመሪዎቻችን ልብ ውስጥ ሰርፆ እንዲገባ ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር የዳገት ሩጫ እየሮጥን እንገኛለን:: በዚህ ቀጥ ያለ ዳገት ላይ በምናደርገው ሩጫ ያለውን ከባድ ድካምና ውጥረት የሚያረግቡልንና ኃይላችንን የሚያድሱልን መልካምና ጣፋጭ ገጠመኞችና ድሎች አጋጥመውን ያውቃሉ:: እነዚህን ድሎች በስስት እያጣጣምን እንደገና ያንን የዳገት ሩጫ እያጧጧፍን እስካሁን ቀጥለናል:: ግባችን በመንገድ ላይ ድሎች መርካት ሳይሆን፣ አገራችን ከዕልቂት አዙሪት ወጥታ ሰላም፣ ደኅንነትና የኢኮኖሚ ዕድገት እየተሻሻለ ሄዶ ለመጪው ትውልድ ይህ መልካም ዘር መተላለፍ እንዲችል ማገዝ ነው::

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዛሬ በመንግሥት አመራርም ይሁን በተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት እንዲሁም በሌላ ዓይነት ሲቪክ አመራር ላይ የምንገኝ ልሂቃን አገራችን የገጠማትን ፈርጀብዙ እንቆቅልሽ ለመፍታት ግንባር ቀደሙ ኃላፊነት የእኛ እንደሆነ ተገንዝበን የምክክር (ዲያሎግ) ሐሳብና መንፈስን በቅጡ እየተረዳን መሄድ ጠቃሚ ይመስለኛል:: አሁን ባለኝ ልምድና ትዝብት እንዲሁም ከበርካታ ወዳጆቼ ጋር በማደርገው የሐሳብ ልውውጥ የምክክርን ትርጉምና መንፈስ በቅጡ ተረድተነዋል ብዬ ለመደምደም ይሳነኛል፡፡ ቃሉ በአንደበታችን ስለበረከተ የሚመጣ ለውጥ በፍጹም የለም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ ቃላትና ጽንሰ ሐሳቦች በሚገባ ሳናመነዥግና ሳንውጣቸው ከውስጣችንም ጋር ተዋህደው ጥቅም ሳይለግሱን በአንደበታችን ብቻ ስናላምጣቸውና ስናሽሞነሙናቸው ሰንብተን እዚያው አፋችን ውስጥ ሞተው ተቀብረዋል፡፡ ዲያሎግም ይህ ክፉ ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስበት የሁላችንንም በተለይም የልሂቃንን ኃላፊነትና መሰጠት ይፈልጋል፡፡

ስለአገራችን ልሂቃን የምክክር ባህል ሳስብ አንድ የጓደኛችን እውነተኛ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለትምህርት አውሮፓ የሚገኝ አንድ አገር ሄዳ ሕመም ይገጥማታል:: በዚያ አገር አለ የተባለ ሐኪም ጋ ለመቅረብ ዕድል ታገኝና በቀጠሮዋ ቀን ትቀርባለች፡፡ ሐኪሙ ገና እየመረመራት ሳለ እሷ አነበብኩት ያለችውን መጽሐፍ እየጠቀሰች የሕመሟን መንስዔና ስያሜ ማብራራት ትጀምራለች፡፡ ትንሽ ሊያወራ ሲሞክርም እያቋረጠችው ልታስረዳውና ልታርመው ትሞክራለች:: ልጅቱ አላቆም ብትለው ለማዳመጥ ዝግጁ አለመሆኗን አስተውሎ ሐኪሙ ዝምታን መረጠ፡፡ ከቆይታ በኋላ ‘ምነው ዝም አልህ?’ ብላ ስትጠይቀው ‘አይ አንቺ የተሻለ ታውቂያለሽ’ ብዬ ነው ብሎ መለሰላት፡፡ በምላሹ ድንገት ድንጋጤ የገባት ጓደኛችን ይቅርታ ጠይቃው ያነበበችውን መጽሐፍ ጠቅሳ ንባቧ እጅግ እንደጠቀማት የምታወራውም ያንን ተመርኩዛ እንደሆነ ስትነግረው፣ አሁንም ትንሽ ዝም ብሎ ሰማትና ‘በነገራችን ላይ ያንን ያልሽውን መጽሐፍ የጻፍኩት እኔ ነኝ’ ብሎ መለሰላት፡፡ የጓደኛችን ድንጋጤ አሻቅቦ በድጋሚ ይቅርታ ጠይቃ ሕክምናዋን በትህትናና በጨዋነት መከታተል ቀጠለች፡፡

ዛሬም ስለአገራችን ፅኑ ሕመምና ስለምክክር ጅማሮ ሳሰላስል በዚህ ጉዳይ ከልሂቃኖቻችን ማንም አዋቂ ወይም ሐኪም እንደሌለ ይልቁንም ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ድጋፍና ፈውስ የሚያስፈልገን ሕመምተኞች እንደሆንን ማወቅ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት በርካታ ዝግ ምክክሮችን በማካሄድና በመምራት በተለያየ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ አያሌ ልሂቃን መሪዎቻችን ጋር ለመገናኘትና ለማገልገል ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ባሉበት መስክ አንቱታን ያተረፉ እጅግ የማከብራቸው መሪዎች ናቸው፡፡ ይሁንና በእነዚሁ ከፍተኛ ምክክሮች ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ሁላችንም በምክክር ጉዳይ ገና ድጋፍ የሚያስፈልገን ተማሪዎች እንደሆንን ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች ሕመማቸውን ተገንዝበው ለምክክር የተሻለ የልብ ፈቃደኝነት እንዳላቸው ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ ሌሎች ደግሞ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ሕመማቸውን በፍጹም አልተገነዘቡም፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አለመገንዘባቸውንም ካለማወቃቸውም በላይ አልፎ አልፎ ሐሳቡን ሁሉ ሲያናንቁትና የትም እንደማያደርሰን ሲናገሩ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡

ይህ ሕመማችን ከምን መጣ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መፈለግ እንደሚገባ ተረድቻለሁ፡፡ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብል ሁላችንንም የሚያስማማን ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም ችግሮች ሲፈጠሩ የኃይል አማራጭ መጠቀም በታሪካችን የለመድነው ጉዳይ ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣንና ጉልበት ያለው አካል ፈላጭ ቆራጭ ብቻ ሳይሆን ሁሉን አዋቂ ሐኪም ሆኖ ትንታኔን እየሰጠና የሌላውን ሐሳብ እያጥላላና እያቃለለ የራሱን መድኃኒት አዝዞ በግድ ‘ሕመምተኛውን’ እየጋተ ለማከም ሲሞክር ቆይቷል:: ትንሽ ቆይቶ ያ በግድ የተጋተ መድኃኒት ፈውስ አላመጣ ሲል ችግሩ መካሪውን ‘ሐኪም’ ሳይቀር ከሥፍራው እያሳደደና እያዋረደ የቀደሙትን አዋቂዎች በሌሎች አዋቂዎች ተክቶ ሲቀጥል በተደጋጋሚ አስተውለናል፡፡ ይህ ችግር አገርና ሕዝብ ላይ የከሰተውን የማያባራ የግጭትና የእንቆቅልሽ አዙሪትም በሚገባ ታዝበናል፡፡ ይህ እጅግ አሳሳቢ የሆነ የጋራ ሕመማችን ነው፡፡ እንደ አገር ሕመምተኝነታችንን ካልተረዳን ያሰብነው ምክክር ረብ የለሽ ሆኖ ይቀራል የሚል ፍርኃት አለኝ፡፡ ባለኝ ልምድና ትዝብት ይህ ምክክር ጠል በሽታችን በሕክምና ቋንቋ ሥር የሰደደ (Chronic) እና ተላላፊ ወረርሽኝ (Epidemic) ደረጃ የደረሰ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ለምክክር የተዘጋጀን እንድንሆን እስቀድመን ራሳችንን ብንመረምር መልካም ይመስለኛል:: ለዚህም ይረዳን ዘንድ ከዚህ ቀጥዬ ሦስት ዋና ዋና የምክክር ባህሪያት አሳይቼ ለማብራራት እሞክራለሁ::

ዲያሎግ (ምክክር) ሦስት ዋነኛ ባህሪያት አሉት:: እነዚህን ማድረግ ስንፈቅድና ስንችል ምክክር ገብቶናል፡፡ ተዘጋጅተናል ማለት እንችላለን፡፡ እነዚህ ነገሮች በአንድ ጀምበር የሚዋሀዱን እንዳልሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል:: ይሁንና ቀስ በቀስ ልማዳችን ሆነው እስኪዋሀዱን ድረስ እየደጋገምን ስህተታችንን እያረምን ብንተገብራቸው  ይጠቅሙናል፣ እየተሻሻልንም እንሄዳለን፡፡ በየጊዜው ቆም እያልን እነዚህን የዲያሎግ መሠረታዊ ባህሪያት ማሰላሰል ብንችል ያለንበትን ሁኔታ በቅጡ እየተረዳን እንሄዳለን::

ታዲያ እነዚህን ሦስት የዲያሎግ ባህሪያት ምንድናቸው?

ዲያሎግ የትኩረቱ ርዕስ ምንም ይሁን ምን ሐሳብን በነፃነት በማንሸራሸርና በማሸጋገር እርስ በርስ አንዳችን ሌላውን በሚገባ ለመረዳትና ለማወቅ የምናደርገው ሒደት ሲሆን በዋናነት እኩልነት፣ ማዳመጥና ነፃነት ተብለው የሚጠሩ ሦስት ጽንሰ ሐሳቦችን በውስጡ ይይዛል:: እነዚህን ሦስት ነገሮች የማይፈቅድ ውይይት ዲያሎግ ተብሎ ሊጠራ አይችልም:: እነዚህን ሦስት ነገሮች በውይይት ጊዜ የማይፈቅድ ሰው ደግሞ ለምክክር ገና አልተዘጋጀምና ራሱን ለምክክር ሒደት ማስተካከል ይጠበቅበታል:: በተስተካከለ አስተሳሰብና ቅኝት በምንወያይ ጊዜ ሰዎች የመደመጥና የመከበር ስሜት ይሰማቸዋል:: ይህ ደግሞ እነሱም በተራቸው እኛን እንዲያዳምጡን፣ አክብሮትን እንዲቸሩንና የእኛን ሐሳብ እንዲረዱን ያደርጋቸዋል:: እኩልነት፣ ማዳመጥና ነፃነት በሌለበት መከባበር የለም፡፡ መከባበር በሌለበት ሁኔታ ሰዎች የተዋረዱ፣ የተናቁና የተገፉ ስለሚመስላቸው በዚህ ጊዜ የችግሮቻችን መፍትሔ ላም አለኝ በሰማይ ሊሆንብን ይችላል:: ቀጥዬ እነዚህን ሦስት ፅንሰ ሐሳቦች ማለትም እኩልነት፣ ማዳመጥና ነፃነት በምሳሌ እያስደገፍኩ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ ከማብራሪያዎችም በኋላ እያንዳንዳችን ያለንበትን ሁኔታ መገምገም እንድንችል የተወሰኑ ጥያቄዎችን እሰነዝራለሁ፡፡  

  1. ዲያሎግ እኩልነት ይፈልጋልእርስዎ በውይይት ጊዜ እኩልነትን ይፈቅዳሉን?

በውይይት ጊዜ ሁሉም ተሳታፊዎች አንዱን ከአንዱ ያለ ማበላለጥ እኩል ተደርገው ሊቆጠሩ ይገባል፡፡ ከዲያሎግ ውጪ ባሉ ኹነቶች ምናልባት የደረጃ ቅደም ተከተል አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ በዲያሎግ ጊዜ ግን ያለምንም ልዩነት እኩልነት ሊሰፍን ይገባል፡፡ ይህም ማለት ማንም ሐሳቡን ሌላው ላይ በጉልበት ሳይጭን የሰዎች ሁሉ ሐሳብ እኩል መከበሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዚህ ጊዜ የአንድን ቡድን ወይም ሐሳብ የበላይነት በሌሎች ላይ መጫን አይገባም፡፡ በአንድ ሐኪምና ታካሚ መካከል በሚኖር ግንኙነት የሐኪም ጫና አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ዕርዳታ ፈላጊው ታካሚው እንጂ ሐኪሙ አይደለም፡፡ ይሁንና በምክክር ጊዜ የሐኪምና የታካሚ ዓይነት ግንኙነት ሊኖር አይገባም፡፡ በምክክር ጊዜ ሁሉም ተሳታፊ ታካሚ ተደርጎ መቆጠር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ይህ የእኩልነት ፍላጎት በባለሥልጣናትና ከፍተኛ ማዕረግ ባላቸው ተሳታፊዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖና የሚጭነው ኃላፊነት አለ፡፡ ይህም የሌሎችን ሐሳብ ሳይንቁ የማዳመጥ ኃላፊነት ነው፡፡ እውነት እኛ ዘንድ ብቻ እንደሚገኝ እርግጠኛ ብንሆን እንኳን የሌሎችን ሐሳብ በትህትና ስናዳምጥ እውነት በአንድ ሰው ዘንድ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ውስጥ ሊገኝ እንደችል ማስተዋል ይሆንልናል::

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ የተከሰተ የሁለት ሴቶች አስደናቂ ታሪክ ላካፍላችሁ፡፡ በናዚ መኮንኖች ልጆችና በናዚ በተጎዱ ቤተሰቦች ልጆች መካከል የተዘጋጀ ምክክር ነበር፡፡ ሴቶቹ ልጆች ዜላና ሄልጋ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዜላ በናዚ ጦር 75 የቤተሰብ አባላት ተገድለውባታል፡፡ አባቷ 13 የሥቃይ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ሲዘዋወሩ ቆይተው ሕይወታቸው በተዓምር ከተረፈ በኋላ ለልጆቻቸው በየዕለቱ ‘ሂትለር በአይሁድ ላይ ያደረሰውን ግፍ በፍጹም እንዳትዘነጉ’ እያሉ ይመክሯቸው ነበር:: በዚህ መረጃ ምክንያት ዜላ ከደረሰባት የሥነ ልቦና ጉዳት የተነሳ ከስቃይዋ ለማገገም ለዓመታት ሕክምና መከታተል ተገድዳ ነበር:: በአጠቃላይ በቤተሰቦቿ ላይ ለደረሰው ዕልቂትና ስቃይ ጀርመናውያንን በሙሉ ትኮንን ስለነበር ከማንም ጀርመናዊ ጋር በፍጹም መገናኘት አትፈልግም ነበር፡፡

በሌላ በኩል ሄልጋ የናዚ ወታደር የነበረው አባቷ ዘወትር እንዴት መልካም ሰው እንደነበረና አንድ ተራ ወታደር ሆኖ በበጎነቱ የብዙዎችን ሕይወት እንዳዳነ ከቤተሰቦቿ እየሰማች ነበር ያደገችው:: ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በድንገት የሥነ ልቦና ችግር አጋጥሟት ሐኪም ዘንድ ስትሄድ በህልሟ የሰዎችን አስከሬንና አፅም እያየች በፍርኃት እንደተሞላች ለሐኪሟ በነገረችው ጊዜ፣ ሐኪሟ አባቷ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የነበረውን ሚና በሚገባ እንድትመረምር ምክር ይለግሳታል:: ከአድካሚ ጥረትና ምርምር  በኋላ አባቷ ኤስኤስ ተብሎ ይጠራ የነበረው የናዚ የደኅንነት ክንፍ አባል እንደነበረና በቀድሞው የሶቪየት ኅብረት ቤላሩስ ግዛት የደኅንነት ኃላፊ ሆኖ በማገልገል ቁጥራቸው ከአርባ ሺሕ በላይ ለሚደርስ ንፁኃን ሰዎች ግድያ ዋነኛ ተሳታፊና ተጠያቂ እንደነበረ ማወቅ ቻለች፡፡ ሄልጋ ይህ አስደንጋጭ ዜና ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ስብራት ስለፈጠረባት እስከ ሞት ድረስ በሚደርስ ፍርኃት ተውጣ የሟቾች ቤተሰቦች የሚያሳድዷት እየመሰላት ለሳምንታት ከቤት መውጣት አቅቷት ሰነበተች፡፡ ከረጅም ጊዜ የሕክምና ክትትል በኋላ ጤንነቷ መሻሻልን ማሳየት ጀመረ፡፡ ከሚሰማት ከፍተኛ የኩነኔ ስሜት የተነሳ ወደ ቤላሩስ ሄዳ የሟች ቤተሰቦች እሷን ገድለው አባቷን እንዲበቀሉም ዘወትር ትመኝ ነበር፡፡

እነዚህ ሁለት ልጆች በዚህ ዓይነት ሥቃይ ውስጥ ሳሉ የተጎጂዎችና የጎጂዎችን ልጆች የሚያገናኝ አንድ ድርጅት እንዳለ በተለያየ አጋጣሚ ሰምተው እ.ኤ.አ. በ1992 በአሜሪካ ለመገናኘት ቻሉ፡፡ በዝግጅቱ በአጠቃላይ 23 ልጆች ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም ታሪካቸውን እንዲያጋሩ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር:: በዚህም ሒደት ዜላ በተለይ የሄልጋን ታሪክ ስትሰማ በቅንነቷና በእውነተኛነቷ ተረትታ እንዲህ አለቻት፡፡ ‘ሂትለርን ባገኘው እንዲህ ልለው እፈልጋለሁ፡፡ ሄልጋን እንድጠላት ያደረግኸው ነገር በሙሉ ከአሁን በኋላ ለዘለዓለም አይሳካልህም፡፡’ ከአምስት ቀናት አብሮ ቆይታ በኋላ ተዓምር በሚባል ሁኔታ ዜላና ሄልጋ ተቀራርበው ባደረጉት ምክክር የዓመታት ሕክምና ያልፈወሰው ቁስል በዚህ ሒደት መፍትሔ አገኘ፡፡: በኋላም የዜላ እናት ለሄልጋ እንዲህ አለቻት፣ ‘አባትሽ ለፈጸመው ስህተት አንቺን መወንጀልና መጥላት በፍጹም አልፈልግም፡፡’

ይህ እውነተኛ ታሪክ ምክክር የወለደው እኩል መደማመጥ እንዴት ወደ ፈውስ፣ ወዳጅነትና ፍቅር ሊመራ እንደሚችል ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የተጎጂዎች ልጆች የተጎዳነው እኛ ብቻ ነንና እኛን ብቻ ስሙን ቢሉ ኖሮ የጎጂ ልጆች መናገር ሳይችሉ ከሥቃያቸው ሳይፈወሱ፣ ለሌላውም ፈውስ ሳያመጡ ቂምና በቀል ለትውልድ ይተላለፍ ነበር፡፡ የተጎጂ ልጅ የነበረችው ዜላ በኋላ ስትመሰክር፣ ‘የአጥፊዎችም ልጆች ከሂትለር ሥርዓት የተነሳ ልክ እንደኛ ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚያሳልፉ ማወቅ ለእኔ በጣም አስገራሚና አስደንጋጭ ነገር ነበር’ ብላ ነበር፡፡

እርስዎስ በአስቸጋሪ ታሪክ-ነክና ፖለቲካዊ ውይይቶች ላይ ሌሎችን ተሳታፊዎች እኩል የመቁጠር ልምድ አለዎት? ባይስማሙበት እንኳን አንድን ሐሳብ ማንም ያቅርበው ማን ያከብራሉን? በውይይቶች ጊዜ ለሌሎች የመናገርን ዕድል ይሰጣሉ? ወይስ የራስዎን ዕውቀትና ሐሳብ በሌሎች ላይ መጫን ይቀናዎታል? የተለየ ሐሳብ የሚያቀርቡ ሰዎችን እንደ አላዋቂና ቂል የመቁጠር ልምድ አለዎት? በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እርስዎ የማይደግፉት ሐሳብ እንዳይቀርብ ከቀረበም ሌሎች እንዳይደግፉት የመጫን ፈተና አለብዎት? በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሌሎች ያቀረቡትን ከእርስዎ የተለየ ሐሳብ የማንቋሸሽና የማሳነስ አዝማሚያስ ያሳያሉ?

  1. ዲያሎግ ማዳመጥን ይሻልእርስዎስ የማዳመጥ ፈቃደኝነትና ልማድ አለዎት?

በውይይት ጊዜ ሁለት የማዳመጥ ዓይነቶች ይስተዋላሉ፡፡ አንደኛው ከሚነሱ ሐሳቦች ስህተትን በመፈለግ ምላሽ ለመስጠት ሲባል የምናዳምጠው ማዳመጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሌሎችን ሐሳብ ለመረዳትና ያሉበትን ሁኔታ በሚገባ ለመገንዘብ የሚደረግ ማዳመጥ ነው:: እውነተኛ ማዳመጥ ሁለቱን ጆሮዎቻችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንን፣ የፊታችንን ገጽና መላ ሰውነታችንን ይጠይቃል፡፡ እውነተኛ ማዳመጥ የሰዎችን ሐሳብ እግሮቻችንን ጫማቸው ውስጥ በማጥለቅ ስሜቶቻቸውን፣ ፍርኃታቸውን፣ ሥጋታቸውን፣ ጭንቀታቸውን፣ ብሶታቸውን በሚገባ እንድንረዳ ይረዳናል፡፡ በሕክምና ሳይንስ የሕመምተኛው ታሪክ ዘገባ የሕክምናው ሒደት ዋነኛ ሥራ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ነው ሐኪም ዘንድ ስንቀርብ ልባችን ውልቅ እስኪል ድረስ የሚያናዝዙን::

ፍሬዓለም ሽባባው ‘ላስብበት’ በሚል ርዕስ ባስነበበችን መጽሐፍ ውስጥ የከተበችው አንድ ታሪክ አለ፡፡ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ዘወትር በምሳ ሰዓት አንድ ልጅ የምሳ ዕቃውን ይዞ ከሰዎች ተለይቶ ይሮጥና ለብቻው ቆይቶ ይመለሳል:: ይህ ነገር በተደጋጋሚ መከሰቱን ያስተዋሉ ሰዎች ለልጁ የተለያየ ቅፅል ስም ያወጡለት ነበር፡፡ ስስታም፣ ግለኛ፣ የመሳሰሉ ስሞች:: ይሁንና የሆኑ ሰዎች አንድ ቀን ቀስ ብለው ሲከታተሉት ከተደበቀበት ቦታ የምሳ ዕቃውን ሳይከፍት በትምህርት ሰዓት ሲመለስ ያስተውላሉ፡፡ ቀስ ብለው ጠርተው ሲያናግሩትና ሲያዳምጡት ታሪኩ ሌላ ነበር:: ለካስ በየዕለቱ የሚሸከመው ምሳ ዕቃ በቤታቸው ድህነት የተነሳ ባዶ ነበር:: የምሳ ዕቃው ባዶነት መታወቅ የራስን ብያኔ ወደ ጎን አድርጎ የማዳመጥ ውጤት ነበር:: ከዚህ የተነሳ ፍሬዓለም የትምህርት ቤት ምገባ እንዲጀመር ራዕይ እንደፀነሰች፣ ይህም ታሪክ ቀስ ብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ጆሮና ልብ አግኝቶ የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም እንዲስፋፋ አስችሏል::

ዛሬ በአገራችን የፖለቲካ ጡዘት ከሰዎች ባህሪይና ንግግር ጀርባ ያሉትን የስሜት ስብራቶችና ቁስሎች መፈወስ የሚቻለው ለሰዎች ጆሮዎቻችንን ከልባችን ጋር በመስጠት ነው:: ማዳመጥ የሰዎችን ቁስል የመፈወስ ታላቅ ጉልበት አለው:: ሰዎችን ሳናዳምጥ በቀረን ቁጥር የተሳሳቱ የራሳችን ግምቶች አዕምሮአችንን ይሞሉትና ፀብን ያባብሳሉ:: ስለዚህ በማዳመጥ ቅድመ ብያኔአችንና ወደ አንድ ያደላ አመለካከታችንን ማረቅ እንችላለን:: ምክንያቱም ሰዎች መደመጣቸውን ሲያውቁ በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ዘክዝከው ለመናገር ድፍረት ያገኛሉና ነው:: በተለያዩ የምናዘጋጃቸው ምክክሮች ላይ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመንና የምንሰማው አቤቱታ የመደመጥ እጥረት ነው::

ጆን ፖል ሌደራክ የሚባሉ ታዋቂ የሰላም ተመራማሪና አስተማሪ እ.ኤ.አ. በ1995 በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ ያሰፈሩት ነገር እስከ ዛሬ ያስገርመኛል:: የሁለት አገሮችን አባባሎች እያነፃፀሩ ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር:: በኤስዋቲኒ (ስዋዚላንድ) ‘የችግር መፍትሔ ያለው በብርቱ ንግግር ውስጥ ነው’ የሚል አባባል አለ:: በኢትዮጵያ ደግሞ ‘ጉልበት ሲደክም ምላስ ይረዝማል’ የሚል አባባል እንዳለ አንድ ትልቅ የፖለቲካ መሪ ነግሮኝ ነበር ይላሉ፡፡ ይህም የኢትዮዽያውያን አባባል ውይይት የብርቱዎች ሳይሆን የደካሞች መሣሪያ ነው የሚል መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ያሰምሩበታል፡፡ በእውነት ይህ ድካማችን በዚህ ደረጃ መታወቁን የኚህን ጎምቱ ምሁር ትንተና ስሰማ በጣም አዘንኩ:: በእውነተኛ የጋራ ጥረታችን ይህንን አባባል ‘ጉልበት ሲበረታ ጆሮ ይረዝማል’ በሚል አባባል የምንቀይርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ያም ቀን ይናፍቀኛል፡፡

አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል “ዳኛው ማነው?” በሚል ርዕስ ባስነበቡን መጽሐፍ አንድ በጣም ያስገረመኝ ታሪክ አለ፡፡ ወቅቱ በ1957 ዓ.ም. ሲሆን የመሬት ይዞታ ሥርዓት እንዲሻሻል ለፓርላማ የቀረበ አንድ ረቂቅ ሐሳብ ነበረ፡፡ በዚሁም ረቂቅ ላይ የመሬት ሥሪቱን ለማሻሻል የቀረበው አንድ ሐሳብ እያንዳንዱ ከፍተኛ የመሬት ባለቤት ከያዘው መሬት ከ90 ጋሻ በላይ የሆነውን ቢመልስ፣ ያለውን ጥያቄ ሊመልስ ይችላል የሚል ነበር (በነገራችን ላይ አንድ ጋሻ መሬት 4‚000 ካሬ ሜትር ገደማ ማለት ነው)፡፡ ይህንን ሐሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በድጋፍ ቢያሳልፈውም ታላላቅ ባላባቶችና የመሬት ባለቤቶች ይገኙበት የነበረው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በቅጡ ሳያዳምጥ ውድቅ ስላደረገው ሳይተገበር ቀርቷል:: ይህ መልካም ምክርን አለማዳመጥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በፈነዳው አብዮት ቀድሞ የቀረበውን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኝነታቸውን ቢገልጹም፣ የዘገየ ምላሽ ስለነበረ በርካታ ባላባቶችን መሬታቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በአገሪቱ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ እያገረሹ መከራ ያበዙብንን ችግሮች ቀፍቅፎ አልፏል:: ስለዚህ ዛሬ የሚሰነዘሩ የመፍትሔ ሐሳቦችን በቅጡ አዳምጠን ካልተጠቀምንባቸው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያረጁና ረብ የለሽ ሊሆኑብን ይችላሉ፡፡

እርስዎስ የተለየ ወይም የማይስማሙበት ሐሳብ በውይይት ወቅት ሲነሳ የሚያዳምጡበት መንፈስ እንዴት ነው? ስብሰባ ጠርተው አብዛኛውን ጊዜ የሚቀናዎት የእርስዎን እውነት ማስረዳት ነው ወይስ ጊዜ ሰጥቶ በአክብሮት ማዳመጥ? የማይደግፉት ሐሳብ ሲሰሙ በትዕግሥት ያዳምጣሉ ወይስ ንዴትዎን መቆጣጠር ይሳንዎታል? ወደ ውይይት በሚሄዱበት ጊዜ ይበልጥ ዝግጅት የሚያደርጉት ለማዳመጥ ነው ወይስ ለማስረዳት? በሌሎች ዘንድ የእውነት ቅንጣት እንዳለ ያውቃሉ ወይስ እውነት እርስዎ ዘንድ ብቻ እንደምትገኝ ሆኖ ይሰማዎታል? ሰዎች በፍጹም ሊረዱኝ አልቻሉም ይላሉ? ወይስ እርስዎም ሰዎችን ለመረዳት ጥረት ያደርጋሉ?

  1. ዲያሎግ ነፃነትን ይፈልጋልእርስዎስ ለሌሎች በነፃነት የመናገር ዕድል ይሰጣሉን?

በውይይቶች ወቅት ሰዎች ውስጣቸው ያለውን ነገር ዘርግፈው እንዳያወጡና ብሶታቸውን አፍነው እንዲመለሱ የሚያደርጋቸው ዋነኛ ጉዳይ የነፃነት መንፈስ ጉድለት ነው፡፡ በውይይት ወቅት ሰዎች ውስጣቸው ያለውን ነገር በመተንፈሳቸው ችግርና መዘዝ ያስከትልብናል የሚል ሥጋት ካደረባቸው ሐሳቡን ሳይተነፍሱት በውስጣቸው እንደታመቀ ይመለሳሉ፡፡ በግልጽና በድፍረት ሳይነገርና ሳይተነፈስ የቆየ ጉዳይ ደግሞ ልክ ተከድኖ እሳት እንደጠገበ ድስት ነው፡፡ እሳት ላይ ተከድኖ የተጣደ ድስት ሳይተነፍስ ቆይቶ ልክ የተከፈተ ጊዜ ሲገነፍል ራሱንም አካባቢውንም እንደሚያቆሽሽ ያልተተነፈሰ ሐሳብም እንዲሁ ነው፡፡ አንድ ቀን ራስንም ሌሎችንም የሚጎዳ ኃይል የተቀላቀለበት ዕርምጃ ሊወልድ ይችላል፡፡ የፖለቲካ ውይይቶች ነፃ የሆነ ንግግርን ግድ ይላሉ፡፡ የታመቀው ሐሳብ እንዲተነፍስ ሲፈቀድለት አስታራቂ መላ ለመዘየድም ዕድል ይሰጣል፡፡

አይሪን ሎር የምትባል አንዲት ፈረንሣዊት ፖለቲከኛ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመን ፈረንሣይን ለተወሰነ ጊዜ በተቆጣጠረች ወቅት፣ የጀርመን ወታደሮች በርካታ ጓደኞቿን ገድለው በጅምላ ከመቅበራቸውም በላይ የገዛ ልጇን ብዙ ሥቃይ አድርሰውበት ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ አይሪን ለጀርመን ከፍተኛ ጥላቻ ስላሳደረች፣ ጀርመን በአንድነቱ ኃይል የቦምብ ናዳ ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ በብርቱ ትመኝ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በስዊዘርላንድ አንድ የውይይት ማዕከል ተገኝታ በነበረ ጊዜ ጀርመናውያን በስብሰባው ላይ ስለነበሩ እነሱን ላለማነጋገር ስትል ሥፍራውን ለቅቃ ወደ አገሯ ልትመለስ በማኮብኮብ ላይ ሳለች፣ በአንድ ሰው ጉትጎታ ሐሳቧን ቀይራ መሳተፏን ቀጠለች፡፡ ታዲያ በአጋጣሚ በምሳ ሰዓት አንድ ክላሪታ የምትባል ጀርመናዊት ሴት አግኝታ አይሪን ውስጧ የነበረውን ምሬት፣ ጥላቻና ፍርኃት በሙሉ በፊቷ አፈነዳችው፡፡ ጀርመናዊቷ ክላሪታ ምንም መልስ ሳትሰጥ በፀጥታ ስታዳምጣት ከቆየች በኋላ በተራዋ፣ ‘ባሌ አዳም ይባል ነበር፣ እ.ኤ.አ. በሐምሌ 1944 የተወሰኑ ጀርመናውያን ሂትለርን ለመግደል ያልተሳካ ሙከራ ባደረጉ ጊዜ ባሌ የዚያ ሚስጥራዊ ውጥን አባል ነበር፡፡ ሙከራው ሲከሽፍ ባሌ በሂትለር ተገድሎብኛል፡፡ እርግጥ ነው እኛ ጀርመናውያን ሂትለርን በበቂ ሁኔታ መቃወም ሲገባን አልተቃወምንም፡፡ ምላሻችንም በጣም ዘግይቷል:: በዚህ ምክንያት በእናንተና በእኛ በራሳችንም ላይ ዘግናኝ ግፍና ዕልቂት ተፈጽሞብናል:: ለዚህ ሁሉ ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ’ ብላ ተናገረች::

በክላሪታ ታሪክና ይቅርታ ልቧ በጣም የተነካው አይሪን ከምሳ በኋላ አብረው እንዲጸልዩ ጠይቃት ከጸሎቱ በኋላ በመካከላቸው አንድ ድልድይ እንደተገነባ ተሰማት፡፡ ከዚህ በኋላ አይሪን ከምሳ በኋላ በነበረው ቀጣይ ውይይት ላይ ሐሳብ ለማካፈል ጥያቄ አቀረበች፡፡ በዚህ ጊዜ አዘጋጆቹ ምን ልትል ፈልጋ ይሆን ብለው በጣም እየተጨነቁ ፈቀዱላት፡፡ አይሪንም ተነስታ፣ ‘ጀርመንን በጣም ከመጥላቴ የተነሳ ከአውሮፓ ካርታ ላይ ፈጽሞ እንድትደመሰስ እንኳን እፈልግ ነበር፡፡ አሁን ግን ጥላቻዬ ስህተት እንደሆነ ስለተረዳሁ ሁላችሁንም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ’ አለች፡፡ በሥፍራው የነበሩ ጀርመናውያን በአይሪን ንግግር በጣም ደነገጡ:: ይህንንም ተከትሎ በሥፍራው ተገኝቶ ይህንን ያዳምጥ የነበረ አንድ ወጣት ጀርመናዊ የፓርላማ አባል፣ ‹‹አኛም ጀርመናውያን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገር ካሳ መክፈል የሚገባን ነገሮች አሉ፤›› ብሎ የተሰማውን ስሜት ገለጸ፡፡ ጀርመናውያኑም ተሰብስበው ወደ አይሪን ዘንድ በመሄድ የተሰማቸውን መሪር ሐዘንና ኃፍረት ገልጸው ከሁን በኋላ ዳግም እንዲህ ዓይነት ግፍ እንዳይከሰት ሕይወታቸውን እንኳን አሳልፈው እንደሚሰጡ ቃል ገቡላት፡፡ በእነዚህ ተፅዕኖ አምጪ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው መልካም ግንኙነት በጀርመናውያንና በፈረንሣውያን መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የሥነ ልቦና ግድግዳ ለመደርመስ ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ተመራማሪዎች በኋላ ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ የክላሪታና የአይሪን በነፃነት ለመደማመጥ መፍቀድ ቅድመ ብያኔና የራስን አስተያየት ወደ ጎን በመተው በሙሉ ትኩረት የተከናወነ ስለነበረ፣ ውጤቱ ከግለሰቦች ፈውስ አልፎ በአገሮች ግንኙነት ላይ መልካም ተፅዕኖ ማምጣት ችሏል፡፡ 

በቅርቡ በሁለት የተቀያየሙ ቡድኖች መካከል ምክክር ስናካሂድ አንድ ሰው መጥተው እንዲህ አሉኝ፡፡ ‘እኔ ብዙ ስብሰባዎች ላይ እናገራለሁ ብዬ እየተሳተፍኩ ምንም ነገር ሳልተነፍስ እመለስ ነበር፡፡ አሁን ግን በልቤ ምንም ሳላስቀር ሁሉንም ነገር ዘረገፍኩት፡፡ ምን ተዓምር እንዳደረጋችሁ አላውቅም’፡፡ በእውነቱ እኛ ያደረግነው ነገር የሰዎችን ጆሮና ልብ በተለያዩ ዘዴዎች ማዘጋጀትና ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበት ሁኔታ ማመቻቸት ነበር፡፡ እኚህ ሰው ቀጥሎ ያሉኝ ነገር ግን በጣም ግርምታን ሊጭርብኝ ችሏል፡፡ ‘ከዚህ ውይይት በኋላ እንደተረዳሁት እኛም ብንሆን ብፁዓን አይደለንም’ ነበር ያሉኝ፡፡ እውነተኛ ምክክር በሌለበት ሁኔታ ሁሉም ራሱን አፅድቆ ሌላውን ግን ኮንኖ ነው የሚመለሰው፡፡ ምክክሩ ያለ ፍርኃት ሐሳብ በነፃነት በሁሉም አቅጣጫ እንዲንሸራሸር ካስቻለ ግን በሰዎች ዘንድ እውነተኛ መደማመጥን ከመፍጠሩም በላይ፣ እስካሁን ያላስተዋልነውን የሰዎችን ፅድቅና የራሳችንን ስህተት እንድናይ ዓይኖቻችንን ይከፍትልናል፡፡ ይህም ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ዕርምጃ ነው፡፡ በዲያሎግ ጊዜ ይህንን ሐሳብን ያለ ፍርኃት ለመግለጽ የሚያስችለው አንዱ ዋነኛ ነገር የተወያዮች የልብ ክፍትነትና ልበ ሰፊነት ነው፡፡ ይህም በሰውነታችን አቋምና ቋንቋ፣ በፊታችን ገጽታ፣ እንዲሁም በንግግራችን አቀራረብና ይዘት የሚገለጽ በመሆኑ የሰዎችን ዝግጁነት በቀላሉ ማወቅ እንችላለን፡፡

እርስዎስ በውይይት ጊዜ ያለ ምንም ፍርኃት የልብዎን ለመግለጽ ፈቃደኛ ነዎት? ለሌሎችስ በእውነት ያለምንም ፍርኃትና ሰቀቀን ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ይፈቅዳሉ? ያበረታታሉ? በሌሎች የሚሰነዘረው ሐሳብ የእርስዎን ሐሳብ ከመቃወም አልፎ ውሸት እንደሆነ ቢያውቁ እንኳን በትዕግሥት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነዎት? ለሚሰነዘሩ ሐሳቦች አስተያየት ሰጪው ላይ ሳይሆን ሐሳቡ ላይ ብቻ አተኩረው የራስዎን ሐሳብ መሰንዘር ይችላሉ? እርስዎን በግል የሚቃወም ሐሳብ በሕዝብ ፊት በይፋ ቢሰነዘርብዎ ቂም ሳይቋጥሩ ምላሽ መስጠትና መቀጠል ይችላሉን? በእንዲህ ዓይነት ውይይቶች ምን ያህል ልበ ሰፊ ነዎት?

ጽሑፌን ለማጠቃለል ይህችን ጥያቄ ልጠይቅ፡፡ ለመሆኑ በእነዚህ ሦስት የምክክር መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች መነጽር ዝግጁነትዎን ሲገመግሙ ራስዎን የት አገኙት? ለምክክር ዝግጁ ነኝ ብለው ያስባሉ? ከላይ እንደተብራራው በእኩልነት፣ በማዳመጥና በነፃነት በሚገባ ያምናሉ?

ምክክር የአገራዊ ችግሮቻችንን መፍቻ ብቸኛ መፍትሔ አይደለም፡፡ ይሁንና ሥር የሰደዱ የተሳሳቱ ግምቶች፣ ብያኔዎችና ጥርጣሬዎቻችንን ይቀንስልናል፡፡ የተበላሹ ግንኙነቶቻችንን ያድስልናል፡፡ የተሸረሸረውን እርስ በርስ መተማመን ይመልስልናል፡፡ በዚህ የተሻሻለ መሠረት ላይ ቆመን በጋራ ለምናፈላልገው መፍትሔ መንገዱን ቀለል ያደርግልናል፡፡ በኋላም የተሻለ የጋራ ፈውስ ያመጣልናል፡፡ ፈውሱ የጋራ ሲሆን ደግሞ የተሻለ ዘላቂነት ይኖረዋል፡፡

አንድ እጅግ የማከብራቸው ጎምቱ የፖለቲካ መሪ በተወሰኑ የምክክር ሒደቶች ላይ ከተሳተፉ በኋላ በአንድ ወቅት፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ማዳመጥና መነጋገር ብንችል ኖሮ ችግሮቻችንን በቀላሉ መፍታት እንችል ነበር፤›› ብለው የተናገሩት ልቤን በእጅጉ የነካው አባባል ነበር፡፡ በትክክል መነጋገርና መደማመጥ ስንችል መፍትሔው ይቀላል፡፡ በእውነት በተለያዩ አገሮች ያሉ ሕዝቦች ከአስከፊ የእርስ በርስ ፍጅት በኋላ በመነጋገርና በመደማመጥ ወደፊት መራመድ ከቻሉ እኛም በሚገባ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ መንፈስ ለምክክር ራሳችንን በእውነት እናዘጋጅ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዴስቲኒ ኢትዮጵያ መሥራችና አስተባባሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው negusumb@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...