Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየትምህርት ሚኒስቴር አዲሱ መመርያ የሴቶችን የመማር መብትና የሕፃናትን ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ

የትምህርት ሚኒስቴር አዲሱ መመርያ የሴቶችን የመማር መብትና የሕፃናትን ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ

ቀን:

በራቤል ደሳለኝ

የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ያደረገው የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎች ምዘናና የክፍል ዝውውር ረቂቅ መመርያ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ አምስት፣ አንድ ተማሪ በወሊድ ምክንያት 15 ተከታታይ የትምህርት ቀናት ካረፈች በኋላ ትምህርቷን መቀጠል ትችላለች። ሆኖም 16 ቀናትና ከዚያ በላይ ከትምህርት ገበታዋ ከቀረች ከዘመኑ ትምህርት ትታገዳለች፤›› የሚል ድንጋጌ ማካተቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የሴቶች መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ረቂቅ ድንጋጌውን ከሴቶች የመማር መብትና ከሕፃናት መብቶች አንፃር በድጋሚ እንዲያጤነው እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

የረቂቅ መመርያውን ይዘት ከመመልከታችን በፊት በዝግጅት ሒደቱ ላይ የሚከተሉትን ጉዳዮች መመልከት ይኖርብናል፡፡ ለድንጋጌው መነሻ እንዲሆን የትምህርት ቤቶችን ዓውድ፣ እንዲሁም የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊና አሁናዊ ሁኔታ የሚዳስስ ተገቢ የሆነ የዳሰሳ ጥናት ተሠርቶ ነበር? በተጨማሪም የተቀመጠው የ15 ቀናት ተከታታይ የወሊድ ዕረፍት የሴቶችና የሕፃናት መብቶችን የሚያከብር፣ የሚያስከብርና የሚያሟላ ስለመሆኑ የተደረጉ ዳሰሳዎች ነበሩ? 15 ተከታታይ ቀናት ዕረፍት የሚለውን ቁጥር ለማስቀመጥ መነሻ ምክንያትና ታሳቢ የተደረጉ ነገሮች ምንድናቸው? ምክንያቱም ረቂቅ መመርያው ሴቶች ከወለዱ በኋላ የሚያስተናግዷቸውን አካላዊ፣ አዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ማገናዘብ፣ እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ እናት የሚሆኑ ሴቶችን ልዩ ፍላጎት ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ በተመሳሳይ ከወለደች ከ15 ቀናት በኋላ ወደ ትምህርት ለምትመለስ እናት ተማሪ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ትምህርት ቤቶች ያላቸው አቅምና ዝግጁነትም ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሌላ በኩል ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሴት ተማሪዎች ከወሊድ በኋላ ወደ ትምህርት የመመለስ መመርያ ያላቸው ሲሆን፣ ይህም መመርያ ከአጠቃላዩ የተማሪዎች ወደ ትምህርት የመመለስ መመርያ የተለየ ነው፡፡ በመሆኑም በረቂቅ መመርያው ዝግጅት ወቅት በተለይ የሌሎች አፍሪካ አገሮችን ልምድ ለመመልከት ዕድሉ ነበረ ወይ የሚለው ሌላኛው የዝግጅት ሒደቱን የሚመለከት ጥያቄ ነው። እንዲሁም በረቂቅ መመርያው ላይ የሕፃናትና የሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ በተለይ የሴቶችን የመማር መብት ዕውን ለማድረግ መንግሥትን የሚያግዙ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች በጥናት፣ በምርምርና በውትወታ ሥራዎች ለሴቶችና ሕፃናት መብቶች የሚሟገቱ ማኅበራትና ግለሰቦች ግብዓት እንዲሰጡበት ዕድሉ ተመቻችቶ ነበር? በተለይ ድንጋጌው በዋነኝነት የሴቶችን የመማር መብትና የወሊድ ፈቃድ የማግኘት መብትን የሚመለከት ቢሆንም፣ ጉዳዩ የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትና አገልግሎቶች ተደራሽነት፣ እንዲሁም የሥርዓተ ፆታ እኩልነትንም ይመለከታል፡፡ በመሆኑም የጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በረቂቅ መመርያው ላይ የመሳተፍ ዕድሉ ነበራቸው? የሚሉት ጥያቄዎች የድንጋጌውን ተቀባይነት ይመዝናሉ፡፡

የረቂቅ መመርያውን ይዘት ስንመለከት መነሻችን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ስምምነቶች፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ግቦች (Sustainable Development Goals/SDG) ናቸው፡፡ የመማር መብት ከሰው ልጆች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው ያለ ምንም አድልዎ የመማር መብት አለው። የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት በዋነኝነት ለመማር መብት መነሻ መርሆች ናቸው፡፡ የተደራሽነት መርህ የትምህርት ቤቶች በበቂ መጠን በአካባቢው ማኅበረሰብ አቅራቢያ መገኘት፣ አካላዊና ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት፣ እንዲሁም ማንኛውም ሰው ያለ ምንም አድሎና መድልዎ ትምህርት ማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በራሱ መሠረታዊ መብት ከመሆኑ በተጨማሪ የመማር መብት ሌሎች ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር በጣም አስፈላጊ ዘዴ በመሆኑ ለምሳሌ ሰዎች የሥራ፣ ንብረት የማፍራትና የማስተዳደር መብቶች፣ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ፍትሕ የማግኘት፣ ከጥቃት ነፃ መሆን፣ ወሲባዊና የሥነ ተዋልዶ ጤና መብቶችን ተጠቃሚ እንዲሆኑና እንዲጠይቁ ለማድረግ መሠረታዊ መብት ነው።

ትምህርት ሰብዓዊ መብቶችን በማስተዋወቅ፣ እንዲሁም ሴቶችንና ሕፃናትን በማብቃት ከአደገኛ የጉልበትና የፆታ ብዝበዛ በመጠበቅ ረገድ ወሳኝ ሚና አለው። የመማር መብት እንደ ማናቸውም ሰብዓዊ መብቶች ሦስት ዓይነት ግዴታዎችን በመንግሥት ላይ ይጥላል። እነዚህም የማክበር፣ የማስከበር/የመጠበቅና የማሟላት ግዴታዎች ናችው። የማሟላት ግዴታው የመማር መብትን ማስተዋወቅ፣ መብቶቹ ዕውን እንዲሆኑ ማመቻቸትና የማቅረብ ግዴታን ጨምሮ ሌሎች አዎንታዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ ያጠቃልላል።

በዚህ መሠረት መንግሥት የሴቶችን እኩልነት በትምህርት ዘርፍ ለማረጋገጥ፣ ያለውን የፆታ ልዩነት ለማጥበብና በተራማጅነት ለማስቀረት አዎንታዊ ዕርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡ ከእነዚህ አዎንታዊ ዕርምጃዎች መካከል ለሴቶች ትምህርት ማቋረጥ ዋነኛ ተግዳሮት የሆነውን ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከል፣ የቤተሰብ ምጣኔን፣ መረጃንና ትምህርትን ጨምሮ የፆታና የሥነ ተዋልዶ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን ሁለንተናዊ ተደራሽነት ማረጋገጥ (SDG 3.7) ዋነኛ ናቸው፡፡ እነዚህ ዕርምጃዎች በሴት ተማሪዎች ዘንድ ያልታቀደ እርግዝናና ወሊድን ለመከላከል ቁልፍ ናቸው።

ከመከላከል በተጨማሪ መንግሥት በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ እንደሰፈረው የሥርዓተ ፆታ ልዩነቶችን በማስቀረት የትምህርትና የሙያ ሥልጠና ደረጃዎችን ለሴቶችና ለወንዶች እኩል ተደራሽ ማድረግ (SDG 4.5)፣ በትምህርትና በሌሎች መስኮች የፆታ እኩልነትን ማሳካትና ሁሉንም ሴቶችና ልጆች ማብቃት (SDG 5) አለበት፡፡ እነዚህን ግቦች ለመድረስ ትምህርት ቤት የገባች አንዲትም ሴት ወደኋላ እንዳትቀር መንግሥት በራሱና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመሆን የድጋፍ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ መሠረት ምንም እንኳን ልጅ ለመውለድ ሁለቱም ፆታ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም፣ ልጅ መውለድ የሴት ልጅ ተፈጥሮአዊ ግዴታ በመሆኑ ከልጁ አባት አንፃር በሴቷ ሕይወት ላይ ያልተመጣጠነ ተፅዕኖ ስለሚኖረው፣ በወሊድ ምክንያት ትምህርቷን እንዳታቋርጥ የሚያግዙ ዕርምጃዎችን በመውሰድ መንግሥት ወንዶችም ሴቶችም በእኩል ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፡፡

በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎች ምዘናና የክፍል ዝውውር ረቂቅ መመርያ ከላይ የተገለጹትን ዕሳቤዎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች፣ የልማት ግቦችና የመንግሥት ግዴታዎች ጋር የሚጣጣም እንዲሆን ለማድረግ በወሊድ ምክንያት ከ16 ቀናት በላይ ከትምህርት ገበታ ከቀረች ከትምህርት ዘመኑ ትታገዳለች የሚል ድንጋጌ ከማስቀመጥ ውጪ ሌሎች አማራጮችን መመልከት ይኖርበታል፡፡ የወሊድ ዕረፍት ከእርግዝና፣ ልጅ ከመውለድና ጡት ከማጥባት ጋር የተያያዙ የእናትየውንና የሕፃኑን አካላዊና ሥነ ልቦናዊ፣ እንዲሁም ሌሎች የጤና ጉዳዮችን በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚያስችል መብት ነው፡፡ እንዲሁም እናትየው የዕረፍት ጊዜዋን ስትጨርስ ከመውለዷ በፊት ወደ ነበረችበት ሕይወት (ሥራ ወይም ትምህርት) እንድትመለስ ዋስትና ይሰጣል። ረቂቅ መመርያው አሁን ባለበት ሁኔታ ለእናትየው በቂ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ የማገገሚያ ጊዜ የማይሰጥና ሕፃኑ በቂ እንክብካቤ እንዲያገኝ የማያስችል ሲሆን፣ ይህም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች በተቃራኒ የሕፃኑን ጥቅም በቀዳሚነት ከግምት ውስጥ ያላስገባና በሕይወት የመኖርና የማደግ መብቱን የሚፃረር ነው።

መመርያው በተጨማሪ የትምህርት ሥርዓቱ የሴቶችንና የሕፃናትን ልዩ ፍላጎትና መብቶች አካታች ያልሆነና ያገለለ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ በተለይ ደግሞ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከመኖሪያ አካባቢ ያላቸውን ርቀት፣ የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት አለመኖርና እጥረት፣ መፀዳጃ ቤትን ጨምሮ ለእናቶች አመቺ የሆነ የመሠረት ልማት በሌለበት፣ እንዲሁም የሥነ ልቦና ማማከር፣ የልጆች ማቆያና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶች ተደራሽነት ውስንነቶች ባሉበት ሁኔታ ከ15 ቀናት ዕረፍት በኋላ ወደ ትምህርት ቤት እንድትመለስ ማስገደድ እናትየውን ለሌላ የጤና ጉዳትና እንግልት የሚዳርግ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ምቹ ባልሆኑበት፣ ሌሎች አማራጮችም ባልተቀመጡበት ሁኔታ መመርያው ሕፃን ልጇን በ16ኛው ቀን እንድትተውና ትምህርት ቤት እንድትመለስ ሲያስገድዳት፣ በውጤቱ ወደ ትምህርት ቤት መመለስን እንዳትመርጥ እያደረጋት ነው፡፡

እንዲሁም ረቂቅ መመርያው ተማሪዋ በ16ኛው ቀን ወደ ትምህርት ካልተመለሰች ከትምህርት ዘመኑ የሚያግዳት በመሆኑ፣ ይህ ድንጋጌ መሠረታዊ የመማር መብትን የማይነፍግና የሴቶች የትምህርት መብትን ወደኋላ የሚመልስ ዕርምጃ (Retrogressive Measure) አለመሆኑን መንግሥት ማስረዳት ይጠበቅበታል። መንግሥት ያለውን ከፍተኛ የሀብት መጠን በመጠቀምና ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትምህርትና በሌሎች መስኮች የፆታ እኩልነትን ማሳካትና ሁሉንም ሴቶችና ልጆች ለማብቃት በተራማጅነት (Progressively) የመሥራት ግዴታ አለበት።

በመሆኑም ይህ ረቂቅ መመርያ ሁሉንም ሌሎች አማራጮች በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ፣ የሰብዓዊ መብቶችን በማጣቀስ የሴቶችንና የሕፃናትን መብት በማይጥስ፣ በማያጠብና በማይነፍግ መንገድ የተቀረፀና ወደኋላ የሚመልስ ዕርምጃ አለመሆኑን ለማረጋገጥ የትምህርት ሚኒስቴር መመርያውን እንደገና ማጤን ይኖርበታል እላለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል desalegnrabel@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...