Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን...

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሲሆን፣ ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በፍሬንድሺፕ ሆቴል ውይይት በተካሄደበት ወቅት ‹‹ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴት እየተሸረሸረ በመሆኑ›› ደንቡ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በቢሮው የቱሪዝም አገልግሎት ደረጃ ምደባና አቅም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ዓምደማርያም ማሞ፣ ‹‹ቢሮው በአዋጅ ቁጥር 74/2014 አንቀፅ 22 ቁጥር 6-13 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ ኢትዮጵያዊ ባህልና ዕሴት እየተሸረሸረ በመሆኑ የደንብ ረቂቅ አውጥቷል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ደንብ በካቢኔው ሲፀድቅ በተለያዩ ሆቴሎች፣ ባሮች፣ ሥጋ ቤቶች እንዲሁም መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ የሚታየው ከኢትዮጵያ ባህልና እሴት ያፈነገጠ የአለባበስ እንዲሁም ጌጣጌጥ አጠቃቀም እንዲስተካከል እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው ቱሪዝም ዓለም አቀፋዊ ውድድር መሆኑን ገልጸው፣ ሆቴሎች በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሠረት መሥራት ስለሚገባቸው፣ እንዲሁም በአገሪቱ ወግ፣ ባህልና እሴት መሠረት ማገልገል ስለሚጠበቅባቸው ይህ ደንብና መመሪያ እንዲወጣ ግድ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ከዚህ አንፃር በአገራችን የሚገኙ ሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የግንዛቤ ችግር አለባቸው›› ያሉት ዶ/ር ሒሩት፣ ‹‹እነዚህ ተቋማት ዓለም አቀፍ መደበኛ አሠራር፣ ፕሮቶኮል (ድሬሲንግ ኮድ) ባለመረዳታቸው ልቅ የሆነ ዘመናዊነትን አልፎ ተርፎም የፋሽን ማሳያ እስኪመስሉ ድረስ ተቀይረዋል፤›› ያሉ ሲሆን ይህ ደንብ ፀድቆ ተግባራዊ ሲሆን እነዚህንና የመሳሰሉ ችግሮችን እንደሚቀርፍ እምነታቸውን መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹‹ይህንን ደንብ በማውጣት ሒደት ውስጥ ብዙ ተዋናዮች ተሳትፈውበታል›› ያሉት ኃላፊዋ፣ ከሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋም አስተማሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም የሕግ አካላት እንደተሳተፉበት ጠቅሰዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ሃፍታይ ገብረ እግዚአብሔር ስለ ደንቡ አስፈላጊነት ሲያስረዱ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ያሉ ሆቴልና መሰል ተቋማት ወጥ የሆነ ሥርዓት እንዲሰፍን ከማገዙም በላይ፣ ባህልና ወጉን ያልጠበቀ የአለባበስ ሥነ ሥርዓትን በመቆጣጠር ኢትዮጵያዊ አለባበስና መስተንግዶ ሥርዓትን ለማስከበር እንዲሁም ባለሙያዎች የሚደርስባቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጫናን ለማስቀረት ይረዳል›› ሲሉ ተደምጠዋል።

ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች የተካተቱበት ረቂቅ ደንቡ በቢሮው ቀደም ተብሎ ሊሠራ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ቶሎ እንዳይወጣና ወደ ሥራ እንዳይገባ ግን የተለያዩ ምክንያቶች ማነቆ እንደነበሩ አቶ ሃፍታይ ጠቅሰው፣ ከእነዚህም ውስጥ በዋነኝነት የአመራሮች መለዋወጥ፣ የግብዓት ማነስና በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች አንድ ላይ ሆነው ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው ጉዳዩ እንዲንከባለል አድርጎታል ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ደንብ በሚፀድቅ ጊዜ ተቋማት አይተገብሩትም ብዬ አላስብም›› ያሉት አቶ ሃፍታይ፣ ተቋማቱ የዚህ ሕገ ደንብ ደጋፊ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።

‹‹በወጣው ረቂቅ መሠረት በተዋረድ ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተማና ወረዳ ድረስ በባለሙያዎች ክትትልና ቁጥጥር መመሪያው የሚፈጸም ይሆናል፤›› ያሉት ደግሞ አቶ ዓምደማርያም ማሞ፣ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ ባለሙያዎች የመንግሥት የሥራ ሰዓትን መሠረት በማድረግ በክትትል የሚያረጋግጡ ሲሆን፣ የተለየ ጥቆማ ከደረሰ ግን ቢሮው ባልተጠበቀ ሰዓት በመፈተሽ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ጠቅሰዋል።

አክለውም በክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መሠረት ደንቡን ጥሶ የተገኘ አካል በደንቡ መሠረት የሚጠየቅ ሲሆን፣ የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው በኋላ ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ቅጣቱ እስከመታሸግ ሊደርስ እንደሚችል ገልጸው፣ በዚህ አካሄድ አቤቱታ ያለው ተቋም ወይም ወገን በፍትሐብሔር ሕግ መሠረት አቤቱታውን የማቅረብ መብት እንዳለውም ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢሮው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ያወጣውን ደንብ ከፍትሕ ተቋማት ጋር ሙሉ በሙሉ የማስፈጸም መብት እንዳለው አስገንዝበዋል።

በደንቡ ከተጠቃለሉት ውስጥ አንዱ ክፍል የሆነው የቅጣት አሰጣጥ ሁኔታን የሚደነግግ ሲሆን ይህም ደረጃ ሀ፣ለ፣ሐ በመባል ተከፍሏል።

ደረጃ ‹ሀ› አሥር ለቅጣት የሚዳርጉ ድርጊቶችን የሚገልፅ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ የደረት ክፍልን ያልሸፈነ/ች፣ ከአንገት በታች የሚሸፍን ሸሚዝ ያለበሰ/ች፣ ሴቶች ጉርድ ቀሚስ ከለበሱ ቁመትና ቅዱ ከጉልበት በታች ካልሆነ፣ ወንድ ጆሮ ጌጥ ካደረገና የመሳሰሉት ድርጊቶች በዚህ ቅጣት ደረጃ ተጠቃለዋል።

ደረጃ ‹ለ› አራ ስድስት ለቅጣት የሚዳርጉ ድርጊቶችን የሚገልፅ ሲሆን፣ ከነሱም መሀል የወንድ ባለሙያ ፀጉሩን በአጭሩ ያልተቆረጠና ያላበጠረ፣ ፂሙን ያልተቆረጠ፣ የአንገት ሀብል ያልሸፈነ/ች፣ ከጋብቻ ቀለበት ውጪሌላ ቀለበት ያደረገ/ች እና የመሳሰሉት በዚህ ቅጣት ደረጃ ተጠቃለዋል።

ደረጃ ‘ሐ’ ሁለት ለቅጣት የሚዳርጉ ድርጊቶች የተቀመጡበት ሲሆን፣ እነዚህም ወንድ በጆሮው ፊት ለፊት ያለው ፂም ከጆሮው እኩሌታ ካለፈና የገነነ ሽታ ያለው ሽቶ፣ ሎሽን፣ ዶድራንት የተጠቀመ በዚህ ቅጣት ደረጃ ተጠቃለዋል።

ደንቡ ከፀደቀ በኋላ የተጠቀሱትን ክልክል ድርጊቶች ሲያደርግ ተገኝቶ እነዚህን ነገሮች በቁጥጥር ባለሙያዎች እንዲያስተካክል ታዞ፣ በአሥራ አምስት ቀን ሳያስተካክል የተገኘ ተቋም፣ ሃምሳ ሺሕ ብር ቅጣት ያለው ሲሆን፣ ያጠፋው ግለሰብም አንድ ሺ ብር ያስቀጣዋል።

ይህንንም ክፍያ እንዲከፍሉ ከታዘዙበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ካልከፈሉ ድርጀቱ እንደሚታሸግ ደንቡ ይደነግጋል፡፡

በውይይቱ ላይ የቢሮው የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መስተንግዶ ማኅበር፣ የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር፣ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋምና የአዲስ አበባ ሆቴሎች ሥራ አስኪያጅ ማኅበር አባላት ተገኝተዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም ‹‹በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ ከከተማችን ማኅበረሰብ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ስለነበር ደንብና መመሪያው አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...