Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ልዩነትና አገር

ትኩስ ፅሁፎች

አይገባትም ግልጽ ነገር
ምነው መቅለል እንዲህ ማፈር
ሚዛን አልደፋ ብሏት
የምታምነው ገዝፎባት
ያቀብኩትን ትንታኔ
ወረወረችው ወደ እኔ።
የሰነዘርኩት ክርክር
ተናደ እንደ ክምር
እንደ ክር ተፈታ
እንደ ሕፃን ጨዋታ
የእኔ እንደሁ ፈርሶ አልቋል እስቲ የሷን ልስማ
ሳይሻል አይቀርም ቶሎ ብንስማማ።
ተራዋ ደረሰ ሙግቷ ተሰማ
ዝርግፍ አረገችው ምንም ሳታቅማማ።
ታሪኳ  ፍርኃቷ ምኞቷ  ተወራ
በዓይነት በቁመቱ ሁሉንም ደርድራ።
አዬ…
ውኃ አልቋጥር አለኝ ጫፉም አልያያዝ
ዙሪያው ማይገጥም ድብልቅልቅ ድንግዝግዝ
ማሰቢያም የላትም ምን ነካት እቴቱ
ቆጨኝ ያጠፋሁት ጊዜዬን  በከንቱ
በሐሳብ መወራረድ
ስንባባል አንዳንድ
እየተራራቅን
መሠረት ለቀቅን
ከመሠረቱ ላይ መግባባት ከጠፋ
አንድ ላይ ለመኖር የትኛው ነው ተስፋ
የትኛው ነው ውሉ
ብልኃት አመሉ
ልዩነት እያለ
አገር ያስቀጠለ
የትኛው ነው ሕጉ
የትኛው ነው ደንቡ
ተግባብቶ ለመኖር መደገፊያ ግንቡ።
ደግሞስ አየሁ ምድር
እጅጉን የሚያምር
ደግሞስ ሰማሁ ታሪክ
ምናብ የሚማርክ
አዳሜ ባይስማማም
ቆመጥ አይማዘዝም
የገደል ማሚቶ አንድ አዕምሮ የለም
ገበያው ግን አለ ሐሳብ  ለመሸመት
ማስማማት ብቻ ነው ማስገደድ የለበት።
ከሐሳብ ገበያ ከተደረደረው
አንስቶ መግዛት ነው
አማርጦ መውሰድ ነው
ቢያሻህ ይህንን ያዝ ካልሆነም ያንኑ
ኋላቀርነት ነው የእኔን ብቻ እመኑ።
ለካስ
የእኔ ህልም ምኞቴ
ፍላጎት ጉጉቴ
የበላኝ ሕመሜ
ያዛለኝ ድካሜ
የሰው ሁሉ መስሎኝ የግሌ አጀንዳ
የሚስማማኝ ሳጣ ቀረሁኝ ከሜዳ
ከሜዳ መቅረቴ
ያ ሁሉ ልፋቴ
ልፋቴስ ባልከፋ
ሰው ወዴት ጠፋ
ሰውማ እንዳይጠፋ ብቻዬን እንዳልሆን
መሠልጠንን ማወቅ በዚህ ክፍለ ዘመን
ከሰሙኝ አድምጠው አጀንዳዬን ወስደው
እሰየው!  እሰየው!
ሐሳቤን አቅርቤ
ከሰው ፊት ቀርቤ
ካሉኝ ጆሮ ዳባ
ሳይሆን ምንግባባ
አሁንም እሰየው እሰየው እሰየው
ምንም ባንግባባም ለሰው መፍትሔው ሰው።
ለሰው ሀብቱ አገር
ስደተኛ ይናገር
ስደተኛ ይምከር።

– ዳዊት በንቲ፣

(ከሦስት ዓመታት በፊት የተከተበ ግጥም፣ ከማኅበራዊ ትስስር ገጹ የተገኘ)

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች