Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትወደ ፓሪስ ኦሊምፒክ ለማቅናት የተፋጠጡት የማራቶን አትሌቶች

ወደ ፓሪስ ኦሊምፒክ ለማቅናት የተፋጠጡት የማራቶን አትሌቶች

ቀን:

ዋና ዋና የማራቶን ውድድሮችን ጨምሮ በርካታ የጎዳና ሩጫዎች በ2023 ተከናውነዋል፡፡ በውድድሮቹ ከአዋቂ አትሌቶች አንስቶ በርቀቱ ለመጀመርያ ጊዜ መካፈል የቻሉ አትሌቶችም ተስተውለዋል፡፡ በአብዛኛው ውድድር ከምንጊዜውም በላይ አዳዲስ ሰዓቶች የተመዘገቡበት ነበር፡፡

የ2023 ሊገባደድ ከአንድ ወር ያነሰ ዕድሜ ቀርቶታል፡፡ አብዛኛው አትሌት ትኩረቱን ለፓሪሱ ኦሊምፒክ አድርጓል፡፡ ከቀናት በፊት በቫሌንሺያ የተደረገው የማራቶን ውድድር ለተወሰኑ የማራቶን አትሌቶች ከወዲሁ ወደ ፓሪስ ሊያመሩ የሚችሉበት ዕድል የሰጠ ሆኖላቸዋል፡፡

ከፍተኛ ግምት አግኝቶ በነበረው የቫሌንሺያው ማራቶን፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በወንዶች ውድድር የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ድል ሲያደርጉ፣ በሴቶች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አትሌቶች በቫሌንሺያው ማራቶን ከማሸነፍ ባሻገር፣ የኦሊምፒክ የቅድመ ማጣሪያ ሰዓት አምጥተው ወደ ፓሪስ ለመጓዝ የሚያስችላቸውን አቅም ለመፍጠር ዝግጅት ሲያደርጉ መክረማቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ውድድሩንም ከሚያሸንፉ አትሌቶች ይልቅ የኦሊምፒክ ቅድመ ማሟያ ሰዓት ማምጣት የሚችሉ አትሌቶች ትኩረት ስበው ነበር፡፡

የኦሊምፒክ የሦስት ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ፣ የ5 ሺሕ እና 10 ሺሕ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ ዑጋንዳዊው ጆሹዋ ችፕቴጊ እና የ2021 የለንደን ማራቶን አሸናፊው ሲሳይ ለማ ተካፍለውበታል፡፡

ከውድድሩ አስቀድሞ የምንጊዜም የረዥም ርቀት ድንቅ አትሌት ቀነኒሳ ወደ ፓሪስ ኦሊምፒክ ማምራት እንደሚፈልግ መጥቀሱን ተከትሎ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ነበር፡፡

በትራክ እንዲሁም በአገር አቋራጭ ውድድሮች በስሙ የታሪክ አሻራ ማኖር የቻለው ቀነኒሳ፣ በማራቶን ተመሳሳይ የታሪክ አሻራ ለመጻፍ ፍላጎት ቢኖረውም፣ በጉዳት ምክንያት በፈለገው መጠን ሊያሳካው እንዳልቻለ ሲናገር ተደምጧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 የበርሊን ማራቶን 2፡03፡03 ምርጥ ሰዓት፣ ከዚያም በ2019 2፡01፡41 የገባበት ፈጣን ማስመዝገብ የቻለው ቀነኒሳ፣ በአመሻሹም ቢሆን በማራቶን የኦሊምፒክ ተሳትፎ እንዲኖረው አጠብቆ የፈለገ ይመስላል፡፡

ቀነኒሳ እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በቫሌንሺያ ማራቶን ከሦስት ወራት የጉዳት ቆይታ በኋላ መካፈል የቻለ ሲሆን፣ በዕድሜ የአንጋፋ አትሌቶች ክብረ ወሰን ባለቤት በመሆን ሌላ አዲስ ታሪክ በስሙ ማጻፍ ችሏል፡፡ ቀነኒሳ በቫሌንሺያ ማራቶንን 2፡04፡19 በሆነ ሰዓት አራተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው፡፡

የ41 ዓመቱ ቀነኒሳ በስፔንዋ ከተማ ሲሮጥ በጎዳና ዳርቻ የነበሩ ተመልካቾች ድጋፋቸውን ሲቸሩት ተስተውሏል፡፡ የፓሪስ ኦሊምፒክ ግቡ አድርጎ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ቀነኒሳ፣ ለቀጣይ ማራቶን ጠንካራ ዝግጅት አድርጎ በኦሊምፒክ መሳተፍ እንደሚፈልግ አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡

‹‹ቀነኒሳ ከሩጫው ዓለም ይሰናበታል›› የሚል አስተያየት እየተሰጠው ቢገኝም፣ እሱ አሁንም በሩጫ መቀጠል እንደሚፈልግና በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ማንኛውንም ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡

‹‹ውድድሩን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በበላይነት ማሸነፋቸው በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌቶች ነበሩ፡፡ እኔም ከሦስት ወራት በኋላ በጤንነት ተመልሼ ያገኘሁት ውጤት አስደሳች ነው፤› በማለት ቀነኒሳ በቀለ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ወደ ፓሪስ ኦሊምፒክ ማቅናት እንደሚፈልግ የገለጸው ቀነኒሳ፣ በቀጣይ በሚካፈለው ማራቶን፣ የተሻለ ውጤት በማምጣት አገሩን ወክሎ የመሳተፍ ዕቅድ እንዳለው ጠቁሟል፡፡

‹‹በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ በዚህ ውጤት ብቻ አይገደብም፡፡ በቀጣይ የሚደረገው ውድድር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ወደ ፓሪስ ኦሊምፒክ ለማቅናት ዕድል አለ፡፡ በቀጣይ ውድድር ጥሩ ሰዓት አምጥቼ አገሬን በኦሊምፒክ ለመወከል የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤›› ሲል ቀነኒሳ አክሏል፡፡

በሌላ በኩል በቫሌንሺያ ማራቶን ውድድር የቦታውን ሰዓት ጭምር በማሻሻል ያሸነፈው ሲሳይ ለማ፣ የኦሊምፒክ ተሳትፎውን ዕውን ለማድረግ የመጀመሪያውን ምዕራፍ አገባዷል፡፡

ሲሳይ የቫሌንሺያ ማራቶን 2፡01፡48 በማጠናቀቅ የቦታውን ክብረ ወሰን ማሻሻል የቻለ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በመቀጠል ሁለተኛው የፈጣን ሰዓት ባለቤት ሆኗል፡፡ በርቀቱ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዳዊት ወልዴ 2፡03፡48 ሦስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ውድድሩን በፍጥነት የመራው ኬንያዊው አሯሯጭ ሂላሪ ኪፕኮች ሲሆን፣ እስከ 30 ኪሎ ሜትር ድረስ የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን የሚሰበርበት ሰዓት ፍጥነት ውስጥ ይዟቸው ሲጓዝ ነበር፡፡

ኬንያዊው አሯሯጭ ውድድሩን እስከ 30 ኪሎ ሜትር በፍጥነት ከመራው በኋላ ውድድሩን ለአትሌቶቹ አስረክቦ ቢወጣም፣ አትሌቶቹ በዚያው ፍጥነት ሊጓዙ አልቻሉም፡፡

በውድድሩ ከቀነኒሳ በመቀጠል ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረውና የመጀመሪያው የማራቶን ተሳትፎውን ያደረገው ዑጋንዳዊው ጆሽዋ ችብቼጌ 2፡08፡59 በሆነ ሰዓት 37ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

አትሌቱ በትራክ ላይ በተለይ በ10 ሺሕ 5 ሺሕ ሜትሮች የነበረውን የበላይነት በማራቶን ማሳካት አልቻለም፡፡ ውድድሩን 37ኛ ደረጃን ይዞ ከማጠናቀቁ በላይ ውድድሩን ሲያጠናቅቅ ራሱን መቆጠጠር ተስኖት ተደግፎ ሲወጣ ጭምር ተስተውሏል፡፡

የቫሌንሺያውን ውድድር ያሸነፈው ሲሳይ በርካታ ታዋቂ ውጤታማ አትሌቶች የተሳተፉበትን ውድድር ማሸነፍ መቻሉ እንዳስደሰተው ገልጾ፣ በቀጣይ ወደ ኦሊምፒክ ለማቅናት የሚያስፈልገውን በቂ ዝግጅት ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጿል፡፡

‹‹በውድድሩ ብዙ ታላላቅ አትሌቶች የውድድር ቦታውን ክብረ ወሰን ይሰብራሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን የተጠበቀው ሳይሆን ያልተጠበቀ ሆኖ እኔ የቦታውን ክብረ ወሰን በመጨበጥ አሸንፌያለሁ፤›› በማለት ሲሳይ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ሲሳይ በፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመሮጥ አንድ ዕድል እንደቀረው ገልጾ፣ ለቀሪው ውድድር በቂ ዝግጅት እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡

ሌላው ኢትዮጵያዊው ዳዊት ወልዴ ውድድሩ ፈታኝ እንደነበር ጠቅሶ፣ በውድድሩ ያልተጠበቀ ውጤት እንደሚመዘገብ ግምት እንደነበረው አብራርቷል፡፡ አትሌቱ ወደ ኦሊምፒክ ለመሻገር የመጨረሻውን ውድድር ጥሩ ሰዓት ለማምጣት ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ ማቀዱን ተናግሯል፡፡

በሴቶች ውድድር ምንም እንኳን የቦታውን ክብረ ወሰን ማሻሻል ባይቻልም፣ ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ደገፋ፣ የሪዮ ኦሊምፒክ 10 ሺሕ ሜትር ሻምፒዮናዋ አልማዝ አያና እና ሕይወት ገብረ ኪዳን ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ በመያዝ በበላይነት ማጠናቀቅ ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ወርቅነሽ 2፡15፡51 በሆነ ሰዓት አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ አልማዝ አያና 2፡16፡22 ሁለተኛ፣ እንዲሁም ሕይወት ገብረ ኪዳን 2፡17፡59 ሦስተኛ በመሆን በበላይነት አጠናቀዋል፡፡

በቅርቡ ከወሊድ የተነሳችው ወርቅነሽ በሴቶች ማራቶን የምንጊዜም ሰባተኛ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ሦስቱም እንስቶች ወደ ኦሊምፒክ ለማቅናት ዕቅድ እንዳላቸው የገለጹ ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ውድድሮች ፈጣን ሰዓት አምጥተው አገራቸውን ለመወከል ግብ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ሕይወት ገብረ ኪዳን በቫሌንሺያ የግሏን ምርጥ ሰዓት ማምጣቷ እንዳስደሰታት ገልጻለች፡፡

ከዓመታት በፊት የዓለም አትሌቲክስ ይፋ ባደረገው የፓሪስ ኦሊምፒክ የመግቢያ መሥፈርት መሠረት፣ 50 በመቶ ማሟያ ሰዓት ማምጣት፣ እንዲሁም ቀሪ 50 በመቶ የዓለም አቀፍ ደረጃ በዋነኛነት ተቀምጧል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በጋራ በመሆን ለወንዶች ከ2፡11፡30 በታች፣ እንዲሁም ለሴቶች ከ2፡29፡30 በታች የሆነ ሰዓት ማምጣት የቻሉ አትሌቶች ወደ ፓሪስ ለማቅናት እንደሚያስችላቸው አስቀምጧል፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያውያን በፓሪስ ኦሊምፒክ ሊወክሉ የሚችሉ ተፈላጊውን ሰዓት ማሟላት የቻሉ በርካታ አትሌቶች ከወዲሁ ብቅ ብቅ ያሉ ሲሆን፣ በቀሪ ውድድሮች ላይ የሚያመጡት ሰዓት ወደ ፓሪስ ለማቅናት ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...