Sunday, March 3, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው ቀርቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ፋታ ከሚነሷት ችግሮች ውስጥ የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት እንደሆኑ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ደግሞ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆን፣ የሶማሊያ መረጋጋት አለመቻል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሱዳን የገባችበት አደገኛ ጦርነት፣ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ደፍረስ ማለትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤልና በሐማስ መካከል የሚካሄደው ጦርነት መቋጫ አለማግኘቱ፣ በዚህም ምክንያት በቀይ ባህር አካባቢ የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት መቃጣቱና ምላሹ ከበድ እንደሚል መጠበቁ ሊፈጥር የሚችለው ሥጋት አሳሳቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ ባለበት ቀጣና ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሯን የምትፈታባቸው በርካታ አማራጮች ቢኖሩም፣ በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፉ ኃይሎች ከግትር አቋማቸው ለመላቀቅ ፈቃደኛ የሆኑ አይመስሉም፡፡ ግትርነት ለማንም እንደማይበጅ ግን ይታወቃል፡፡

በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ የሰው ኃይል፣ በርካታ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ለማድረግ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ሌሎች ፀጋዎችን መጎናፀፍ የምትችለው ኢትዮጵያ ትኩረቷ በሙሉ ልማት ላይ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ሰላም ሰፍኖ ከአሳፋሪው የድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጥረት መታገዝ ያለበት በሠለጠነ የሰው ኃይልና ተቋማዊ አደረጃጀቱ ጠንካራ በሆነ አፈጻጸም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት አሠራር በሕጉ መሠረት ግልጽ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት መሆን ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋም በሕግ በተሰጠው ኃላፊነትና ተጠያቂነት መሠረት ሥራውን ማከናወን ይኖርበታል፡፡ ጠንካራ ግለሰቦች ሲመሩት መኖሩ የሚታወቅ ተቋም፣ እነሱ ዞር ሲሉ እንደሌለ የሚቆጠርባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ተቋማትን በሚፈለገው መጠን መገንባት አለመቻል ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ችግር መጋለጥን ነው ያስከተለው፡፡ በዚህም ምክንያት ሥራ በአግባቡ ሳይሠራ ሪፖርቶች በአስደንጋጭ ቁጥሮች ተኳኩለው እየቀረቡ ያደናግራሉ፡፡ ጉዳቱ ግን ለአገርና ለሕዝብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች ሲበራከቱ አስፈላጊውን የመፍትሔ ዕርምጃ ለመውሰድ ቆራጥነት ያስፈልጋል፡፡ ዙሪያውንና በቅርብ ርቀት የውጭ ተፅዕኖዎች ሲበዙ ቆም ብሎ ሁኔታዎችን ማጤን ይገባል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው አስተማማኝ ሰላም ሲሰፍን እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን በሚረብሽ ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚው ለማደግ እጅግ በጣም ብዙ ተስፋ ሰጪ ዕምቅ አቅሞች አሉት፡፡ እነዚህን አቅሞች አውጥቶ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ግን ሰላም ለማስፈን የሚረዱ ተግባራት መኖር አለባቸው፡፡ መንግሥት ከማንም በላይ ትልቅ ኃላፊነት ስላለበት ለሰላም መስፈን የሚረዱ ዕርምጃዎች ላይ ማትኮር ይጠበቅበታል፡፡ በአንድ በኩል በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሕግ እያስከበረ፣ በሌላ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ንግግርና ድርድር እንዲመጡ ማድረግ አለበት፡፡ ሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ከሌብነትና ከዝርፊያ ፀድተው ሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት ያግኝ፡፡ በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ዕጦት የሚነሱ ቅሬታዎችን ያስወግድ፡፡ ሥልጣናቸውን ያላግባብ የሚገለገሉበትን በሕግ አደብ ያስገዛ፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት መረጃቸው ለሕዝብ ግልጽ ይደረግ፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ለሕዝብ ቅሬታና ተቃውሞ መነሳት ምክንያት የሆኑ ብልሹ አሠራሮች መወገድ አለባቸው፡፡ ከታች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ትልቅ ተቋም ድረስ የተሰማሩ ሠራተኞችም ሆኑ አመራሮች፣ ለብሶትና ለተቃውሞ መነሻ ከሚሆኑ ድርጊቶች ሲታቀቡ ለሰላም መስፈን ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ዜጎች ለአገራቸው ሰላም አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችሉት በእኩልነት የሚያኖራቸው አሠራር ባህል ሲሆን ነው፡፡ በየደረሱበት ቦታ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሲከበሩ፣ አድሎአዊና አግላይ ድርጊቶች ገለል ሲደረጉና በሁሉም አገራዊ ጉዳዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳተፋቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የሚስተናገዱ ዜጎች ሕግ አክባሪ፣ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ የሆኑ፣ ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት የሚመሩ ይሆናሉ፡፡ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ የሚመሩ ተቋማት በብዛት ሲኖሩ ዜጎች ለእንግልት አይዳረጉም፡፡ በሥልጣናቸው የሚባልጉ ሹማምንትም አይኖሩም፡፡ ለፀብና ለግብግብ የሚዳርጉ ምክንያቶች ስለማይኖሩ ሰላም አስተማማኝ ይሆናል፡፡ ኢኮኖሚያዊም ሆኑ ማኅበራዊ ችግሮች በጋራ ጥረት ይቃለላሉ፡፡ ውስጣዊ አንድነት ስለሚጠናከር ከውጭ ሥጋት ሊፈጥሩ የሚሞክሩ በጭራሽ እንዳያስቡት ይገደዳሉ፡፡

ውስጣዊ አንድነት እየተዳከመ ቅራኔው በየአቅጣጫው ሲበራከት ግን ለታሪካዊ ጠላቶች በቀላሉ ተጋላጭ እንደሚኮን ነጋሪ አያሻም፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ሳቢያ ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና አይዘነጋም፡፡ ይህ ፈተና ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ገባሮች ላይ ምንም ዓይነት የተጠቃሚነት መብት እንዳይኖራት ስለሚፈለግ፣ በህዳሴ ግድብ ሰበብ እየተደረገ ጫናውና ግፊቱ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ በሰሜንም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች እንዳይበርዱ የሚፈለገው፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እየተበላሉ በመጨካከን በጋራ የአገራቸውን ጥቅም እንዳያስከብሩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ገላጋይ መስለው የሚገቡ ኃይሎች የራሳቸውን ጥቅም ከግምት ሲያስገቡ፣ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ሸሪክ ከሆኗቸው አገሮች ጋር ያላቸውን ዝምድና እያሰቡ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአንዱ አውዳሚ ጦርነት ወደ ሌላው እንደ ዘበት ሲሸጋገሩና ሲተላለቁ፣ ዳር ሆነው በማሾፍ ከንፈር የሚመጡም ሆኑ ‹እሰይ ስለቴ ሰመረ› የሚሉት ጭምር የኢትዮጵያን መዳከም ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ መሀል ግን ‹በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ…› እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን አገራቸውን እየጎዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በዚህ ጊዜ የሚያዋጣቸው ከአገራቸው ማንኛውም አካባቢ የጠመንጃ ልሳን እንዲዘጋ የሚረዱ መፍትሔዎች ላይ መረባረብ ነው፡፡ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች ለግጭት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮች እንዲፈቱ ድምፃቸውን ማሰማት አለባቸው፡፡ ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አካላት፣ ለተፈጠሩ ችግሮች በመጀመሪያ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝ ዕድል መስጠት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ፀንታ እንድትቆም ማድረግ የሚቻለው፣ ሁሉም ተቀናቃኝ ኃይሎች ለልዩነቶቻቸው ዕውቅና ሰጥተው ለመነጋገር የፈቃደኝነት ምልክት ሲያሳዩ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ለድርድር የሚሆኑ መደላድሎችን ማመቻቸት አያቅትም፡፡ ተቀናቃኝ ኃይሎች ከፈለጉ በአገር በቀል የችግር መፍቻ ዘዴዎች፣ ካልፈለጉ ደግሞ በውጭ አደራዳሪዎች አማካይነት ተገናኝተው ቢነጋገሩ ተጠቃሚው የችግሩ ሰለባ የሆነው ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ላይ እየደረሰ ካለው የግጭት ጉዳትና ውድመት በተጨማሪ፣ በኑሮ ውድነት ምክንያት የድህነት ሕይወቱን መግፋት እየተሳነው ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ የአገሩ ህልውና ጉዳይ ጭንቀት ውስጥ እየከተተው ነው፡፡ ስለዚህ ለአገርና ለሕዝብ ደኅንነት ትኩረት ይሰጥ! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...