Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዘመኑን ያልዋጁ ልኳንዳ ቤቶች

ዘመኑን ያልዋጁ ልኳንዳ ቤቶች

ቀን:

አዲስ አበባ ውስጥ በማኅበረሰቡ ዘንድ ለምግብነት ያልተለመደ የአህያ ሥጋ እየቀረበ ነው ተብሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ እየተናፈሰ ነው፡፡ ይህም በልኳንዳ ነጋዴዎችና በተጠቃሚው ዘንድ ውዥንብር ፈጥሯል፡፡

ዘመኑን ያልዋጁ ልኳንዳ ቤቶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ማኅበረሰቡ ለውዥንብር የተዳረገውም የአህያ ሥጋውን ከመደበኛው ሥጋ ጋር ተቀላቅሎ ይሸጣል የሚል መረጃ በመኖሩ ባደረበት ፍራቻ ነው፡፡ በዚህም ልኳንዳ ቤቶች ገበያቸው መቀዛቀዙን ይገልጻሉ፡፡ ለሽያጭ ያዘጋጁት መደበኛ ሥጋ ከገና ፆም በፊት እንደ ወትሮው ገዢ በማጣቱ ለኪሣራ ዳርጎናል ይላሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ አየለ ሳህሌ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የሚናፈሰው ወሬ በማስረጃ ያልተደገፈ ነው፡፡

የማኅበሩ አባል የሆኑ ልኳንዳ ነጋዴዎች በችርቻሮና በብልት የሚሸጡት ጥራቱና ጤንነቱ የተጠበቀ የበሬ፣ የበግና የፍየል ሥጋ መሆኑን ገልጸው፣ ለሽያጭ የሚያቀርብላቸውም የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ ለእርድ አገልግሎት የሚቀርቡለትን እንስሳት መጀመሪያ በቁሙ፣ ሲቀጥል ደግሞ ከእርድ በኋላ የጤንነት ምርመራ እንደሚያደርግላቸው፣ በሁለቱም ዓይነት ምርመራ የጤና እክል ያልተገኘባቸውን የሥጋ ምርት ለየልኳንዳ ቤቶች እያጓጓዘ እንደሚያቀርብ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ወጣ ባለ ወይም ባፈነገጠ መንገድ በማኅበረሰቡ ዘንድ ለምግብነት ያልተለመደ የአህያ ሥጋ የማኅበሩ አባል በሆኑ ልኳንዳ ቤቶች እንዳልቀረበ፣ ለማቅረብ በሚሞክሩ ልኳንዳ ቤቶች ካሉ ማኅበሩ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና የደንብ አገልግሎት ቢሮዎች ተገቢውን ዕርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይሉ ገልጸዋል፡፡

ልኳንዳ ቤቶቹ አዲስ አበባ በአሁኑ ጊዜ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የማይመጥኑና ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ሲያያዝ ከመጣው ባህላዊ የሽያጭ ሥርዓት ያልተላቀቁ ወይም ያልዘመኑ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የልኳንዳ ቤቶችን አደረጃጀትና የሽያጭ ሥርዓት ለማሻሻል ማኅበሩ ብዙ ጥረቶችን አድርጓል ብለዋል፡፡

ካደረጓቸውም ጥረቶች መካከል ከዩኤስአይዲ በመጡ ባለሙያዎች በመታገዝ የልኳንዳ ቤቶች አደረጃጀት ላይ ያተኮረ ሥልጠና መሰጠቱ ለአብነት ያህል እንደሚጠቀስ፣ ሆኖም ሥልጠናው በተለያዩ ምክንያቶች አለመቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡

ልኳንዳ ነጋዴዎቹ ለሽያጭ የሚያቀርቡትን የሥጋ ምርት ቀዝቃዛ አየር ባለበት ቤት ወይም ፍሪጅ ውስጥ ማስገባት ሲገባቸው በየበራፉና በየመስኮቱ ፊት ለፊት ሲያንጠለጥሉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ሸማቹ ወይም ተጠቃሚው ፍሪጅ ውሰጥ የገባን ሥጋ ለቁርጥ የመግዛት ፍላጎት የለውም፡፡

በዚህም የተነሳ ነጋዴው ሥጋውን በባህላዊ መንገድ የማቅረብ ፍላጎቱ የፀና እንደሚሆን፣ ተጠቃሚውም ባህላዊውን ንግድ የሚፈልገው መሆኑ አሠራሩ ፀንቶ እንዲቆይ አስተዋጽኦ ማድረጉን ከግንዛቤ ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የተንጠለጠለውም ሥጋ ለብክለት መንስዔ ለሆኑ ብናኝና አቧራ እንደሚጋለጥ፣ በገበያ ዕጦት የተነሳ ውሎ ሲያድር ደግሞ ጠውልጎ እንደሚጠቁር፣ ይህም ለጤንነት ሥጋት ከመፍጠሩ ባሻገር ነጋዴውን ለኪሣራ እንደሚዳርግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡፡

አንድ ልኳንዳ ቤት ከመቋቋሙ አስቀድሞ የሚቋቋምበት ቦታና አካባቢ ምቹነት የውኃ አቅርቦት፣ ፍሪጅና የንፅህና መጠበቂያ ክፍል ያለው መሆኑንና በአጠቃላይ ዘመኑን የዋጀ ወይም አዲስ አበባ አሁን የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን ሆኖ መገኘቱ በቅድሚያ መረጋገጥ እንዳለበት፣ ይህንንም ማረጋገጥ ያለበት ፈቃድ ሰጪው አካል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን ያለው አሠራር አንድ ጠበብ ያለ ቤት ቀለም ተቀብቶና የሥጋ መደርደሪያ ተዘርግቶ ከታየ ወዲያውኑ ፈቃድ የመስጠት ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትና የድርጅቱ ቅርንጫፍ በሆነው በአቃቂ ቄራ የሚገለገሉና በአጠቃላይ 1,500 አባለት ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር የተቋቋመው በ1959 ዓ.ም. መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸው፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ በለገዳዲ፣ በቡራዮና በሰበታ ቄራዎች የሚገለገሉ ሌሎች ልኳንዳ ነጋዴዎች በማኅበሩ ለመታቀፍ ከፈለጉ በሩ ክፍት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...