Sunday, March 3, 2024

የዕቅድና የትግበራ ተቃርኖ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዜጎችን ‹‹በቀን ሦስት ጊዜ ማብላት ነው ዕቅዴ›› የሚሉ መሪዎችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታለች፡፡ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግርና ጠላት ‹‹ድህነት ነው›› ብለው ለፀረ ድህነት ትግል ክተት ያወጁ ፖለቲከኞችንም ኢትዮጵያ ተመልክታለች፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከድንቁርና፣ ከችጋር፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት በማላቀቅ ወደ ሥልጣኔ ማማ የማሸጋገር ግብ እንዳላቸው የተናገሩ መሪዎች በየዘመናቱ መጥተው ሄደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ድህነት ግን ዛሬም በቦታው እንዳለ ይገኛል፡፡ አገሪቱን ከችግር አረንቋ ለማውጣት በሚል በየዘመናቱ ብዙ ቢታቀድም ሆነ ፀረ ድህነት አዋጅ እየታወጀ የክተት ዘመቻ ቢካሄድም፣ ይህችን አገር ከችግርም ሆነ ከችጋር ቅርቃር ፈልቅቆ የሚያወጣ ዘዴና ብልኃት ዛሬም ድረስ አለመገኘቱ በሰፊው የሚተች ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ባለህበት እርገጥ በሆነ ዕድገትና ለውጥ ላይ የቆመችው ተረግማ ይሆን እንዴ የሚል መለኮታዊ ክርክር ቢነሳም፣ በብዙዎቹ ቤተ እምነቶች ‹‹ፈጣሪ የባረካት አገር›› የመሆኗ ጉዳይ ሚዛን በሚደፋ ሁኔታ በስፋት ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከመለኮታዊ ክርክር በመለስ ኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት ልትወጣ ስለምትችልባቸው ሁኔታዎች ሳይንሳዊ መላምት የሚሰጡ ወገኖች አቅዶ የመሥራትን ጉዳይ መሠረታዊ አገራዊ ችግር መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ሌሎች አገሮች ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ በፍጥነት ከችግር አረንቋ የወጡት በጥሞና በማቀድ ብቻ ሳይሆን፣ በዕቅድ የተለሙትንም በአግባቡ በተግባር መተርጎም በመቻላቸው እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

በ1955 ዓ.ም. ይፋ በሆነው ሁለተኛው የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ የመግቢያ አንቀጽ ያሠፈሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ‹‹ይህን መሰሉ መሻሻል ተፈጻሚነት አግኝቶ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው፣ በረጅም ዘመን ፕሮግራም በየደረጃው ቀስ በቀስ ሥራ ላይ እንዲውል ሲደረግ ነው፡፡ ለአንድ አገር ሕዝብ የማያቋርጥ እውነተኛ የመሻሻል ዕድገትን ያገኘ መሆኑን መረዳት የሚቻለው በሥራ ተፈጽሞ በሚታይ ነገር እንጂ፣ በሚደነቁ ወይም በሚጋነኑ ዲስኩሮች በመግለጽ ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛ የምናምንበት መሻሻል በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባውን እንጂ በሚንሸራተት አሸዋ ላይ ያለውን አይደለም፡፡ ዘመናዊ የኢኮኖሚ የማኅበራዊ ኑሮና የአስተዳደር ማሻሻያ ዘዴዎች ከአገራችን ጥንታዊ ባህልና ታሪክ ጋር ተስማሚነት ኖሯቸው እንዲሠራባቸው እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ባዕድና ከሕዝባችን አቅም በላይ የሆኑ ማናቸውም ጊዜ የፈጠራቸው ፈሊጦች በአገራችን ላይ እንዲሰርፁ የምንፈልገውና የምንመኘው አይደለም፤›› በማለትም ነው የከተቡት፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሴ ይህን ቢሉም ከአምስት ዓመት ቀደም ብሎ ወደ ሥራ ያስገቡት የመጀመሪያው የአምስት ዓመት ዕቅድ፣ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና እንኳን ማረጋገጥ እንዳልቻለ በመግቢያ አንቀጻቸው ወረድ ብለው ያምናሉ፡፡ የሕዝብ ቁጥር በመጨመሩና የምግብ ፍላጎት በማደጉ አገሪቱ 45 ሺሕ ቶን እህል ከውጭ ለማምጣት መገደዷን በግልጽ አሥፍረዋል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ተተገበሩ የሚባሉት ሦስቱ ተከታታይ የአምስት ዓመታት የልማት ዕቅዶች የኢትዮጵያን የዕድገት ሁኔታ መቀየራቸው በሰፊው ይነገራል፡፡ አንዳንዶች እነዚህን የልማት ዕቅዶች መሠረት በማድረግ የንጉሡ መንግሥት ኢትዮጵያን በተጠናና ትልም ባለው መንገድ ለመምራት ያደረገውን ጥረት ለማድነቅ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡

ይሁን እንጂ በአገራዊ ዕቅዶች ላይ ረጅም ጊዜ የሠሩና በደርግ ዘመነ መንግሥት፣ ከፕላን ሚኒስትርነት እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ድረስ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሠሩት የኢኮኖሚ ምሁሩ አቶ ፋሲካ ሲደልል ይህን አይጋሩም፡፡

‹‹ሲጀመር ዕቅድ በራሱ ምትኃት አይደለም፣ ትልቁ ነገር ምንድነው ያቀድከው የሚለው ነው፡፡ አንድ አገር ትርጉም ባለው መንገድ እንዲያድግ ከተፈለገ ኢኮኖሚው በማያቋርጥ ሁኔታ ለአሥርት ዓመታት በአማካይ ከስምንት እስከ አሥር በመቶና ከዚያ በላይ በሆነ ጥቅል የኢኮኖሚ ገቢ (ጂዲፒ) አኃዝ ማደግ መቻል አለበት፡፡ ከዴንግ ዣኦ ፒንግ መሪነት በኋላ የቻይና ኢኮኖሚ ለ30 ዓመታት በሁለት አኃዝ ነበር ያደገው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም አንድ አገር ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ በዓመት በአማካይ የጂዲፒውን ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚያህል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማግኘት አለበት፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ተነስተውም የጂዲፒን አንድ ሦስተኛ የሚያህል ተጨማሪ የልማት ኢንቨስትመንት ማግኘት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

በንጉሡ ዘመን ታቀደ እንዲሁም መጣ ስለሚባለው ለውጥ በማንሳት እሳቸው በአመራርነት ከሠሩበት የደርግ አስተዳደር ጋር ያነፃፀሩት አቶ ፋሲካ፣ የንጉሡ ዘመን እንደሚነገርለት አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹የጃንሆይ ዘመን ኢኮኖሚ ትንሽ ኢኮኖሚ ነበር፡፡ ኢንቨስትመንቱ ያደገው የጂዲፒውን 15 በመቶ ያክል ነበር፡፡ በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅዳቸው ላይ ካልሆነ በስተቀር ትርጉም ያለው ለውጥ አላመጣም፡፡ የመጀመሪያው የንጉሡ የአምስት ዓመት ዕቅድ የተማረ የሰው ኃይል እጥረትም የገጠመው ነበር፡፡ በአማካይ በ3.7 በመቶ ብቻ ነው የአገሪቱን ኢኮኖሚ አሳደገ የሚባለው፡፡ የነፍስ ወከፍ ገቢ ቢጨምርም በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ አልመጣም፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

ሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ትግበራ ዘመን ላይ ግን ትርጉም ያለው ዕድገት መመዝገቡን የሚናገሩት አቶ ፋሲካ፣ በዓመት አምስት በመቶ የጂዲፒ ዕድገት በአማካይ መመዝገቡን ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከዜሮም የተነሳ ስለነበር ብዙ ለውጥ እንደታየበት ያወሳሉ፡፡

ሦስተኛው የአምስት ዓመት ልማት ዕቅድ ላይ ኢኮኖሚው ቀድመው ያልታዩ ችግሮች እንደገጠሙት ነው አቶ ፋሲካ የሚናገሩት፡፡ ‹‹ከ1960/61 ዓ.ም. ጀምሮ የኢኮኖሚ ዕድገቱ እያሽቆለቆለ ሄደ፡፡ የመሬት ፖሊሲው ባለመለወጡ፣ አነስተኛው አርሶ አደር ትኩረት ስላልተሰጠው፣ የጭሰኛውና ገባሩ የመሬት ፖሊሲ በመቀጠሉ፣ ግብርናው መነቃነቅ አቃተው፡፡ የጃንሆይ የዕድገት ዕቅዶች ኢኮኖሚው ትንሽ ስለነበር ትልቅ ግምትም የሚሰጣቸው ለውጦች ቢያመጡም ነገር ግን ሥር ነቀል በሆነ ሁኔታ ኢኮኖሚውን አልቀየሩም፤›› ይላሉ፡፡  

‹‹በእኛ ጊዜ ለዕድገት አመቺ የሆኑ ነገሮች ባይኖሩም ለልማት ሥራዎች ብዙ ትኩረት ተሰጥቶ ነበር፡፡ የሶማሌ ጦርነት፣ ድርቅና ረሃብ፣ እንዲሁም ጦርነት መቀጠሉ ዕድገቱን ቢጎትተውም ለልማት የነበረን ቁርጠኝነት ግን እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ በሒደት የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ካምፑ መዳከም፣ አገሪቱ ዕርዳታና ብድር እንዳታገኝ ይደረግ የነበረው ዕቀባና ጫና መጨመር እንዲሁም የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ገበያ መር ዕድገትን አለመፈቀዱ ሁሉ፤›› የታሰበውን የልማት ዕቅድ ለመተግበር እንዳገደ ነው አቶ ፋሲካ ከኖሩበትና በቅርበት ከሚያውቁት በመነሳት ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት፡፡

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድና ሁለት እየተባለ በሚታቀድበት የኢሕአዴግ ዘመን፣ ይህን ግብታዊ ዕቅድ በምን መንገድ ልታስፈጽሙት ነው የሚል ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይሰነዘሩ ነበር፡፡

የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ ‹‹ያነሰ እንጂ ትልቅ መመኘትና ማለም ለምን ሲባል ይጠላል?›› ብለው ተከራክረው ነበር፡፡ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው በመጠቀም ይህን ተለጠጠ የተባለ ዕቅድ ለማስፈጸምና ከግብ ለማድረስ መንግሥታቸው በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ቃል ገብተውም ነበር፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባትን ጨምሮ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ማመንጨት አቅም ከ2‚000 ሜጋ ዋት በአንዴ ወደ 10‚000 ሜጋ ዋት ማድረስ፣ ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለኤክስፖርት የሚትረፈረፍ ስኳር የሚያመርቱ አሥር ግዙፍ የስኳር ፋብሪካዎችን መገንባት፣ የወጪ ንግድ ገቢ ግኝትን  በአመት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማሻገር፣ በቴሌኮም፣ በዲጂታል፣ እንዲሁም በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች ሥር ነቀል ዕድገት ማስመዝገብ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ገንብቶ የራስን ፍጆታ በራስ አቅም መሸፈን፣ ወዘተ እየተባለ የታቀደው አገራዊ ትልም ሁሉ ቀስ በቀስ እንደማይሳካ ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡

በዚህ ጊዜ በመለስ እግር ተተክተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያቀዳችሁት የት ደረሰ ከሚል ጥያቄ ጋር ተፋጠጡ፡፡ ጂቲፒ አንድ ጂቲፒ ሁለት ስትሉ የነበረው ምን ላይ ደረሰ? አገራዊ ዕቅዶቻችሁ ግባቸውን አልመቱም ተብለው በተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ሲጠየቁ ታየ፡፡

ይህን ጊዜ መንግሥታቸውንና ዕቅድ ትግበራውን መከላከል የመረጡት አቶ ኃይለ ማርያም ዕቅዶቻቸው የተለጠጡ እንደነበረ ቀድሞውን እንደሚያውቁ፣ አንዳንዶቹን መቶ በመቶ ማሳካት ይቻላል ብለው እንዳልጀመሯቸው መናገር መረጡ፡፡ ‹‹በእኛ እምነት ተጀምረው ከነበሩ ስኳር ፋብሪካዎች ብዙዎቹ 70 እና 80 ከመቶ አፈጻጸም ላይ መድረሳቸው በራሱ ዕቅዳችንን የተሳካ አድርገን እንድንቆጥር ያስችለናል፤›› በማለትም ተከራከሩ፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ይህን ሲናገሩ ግን የአገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ብዙዎቹ ዳዋ ለብሰው ሜዳ ላይ ቀርተው እንደነበር፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽንና የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርቶች ሲመዘግቡ ነበር፡፡ አገሪቱ በውጭና በአገር ውስጥ ብድር ዕዳ ተቸግራ የምትገነባቸው የኃይል ማመንጫ፣ የመስኖ አውታሮች፣ ስኳርና ማዳበሪያ ፋብሪካዎችም ሆነ ሌሎች አገር ይቀይራሉ የተባሉ የልማት ውጥኖች በምዝበራና በዝርፊያ ለብክነትና ለኪሳራ መዳረጋቸው ብዙም ሳይዘገይ መጋለጥ ጀመረ፡፡

 በኢንቨስተሮች ይለማሉ የተባሉት የጋምቤላን ጥብቅ ደን ያስመነጠሩ እጅግ ከፍተኛ የመንግሥት ብድር የተወሰደባቸው ሰፋፊ እርሻ ፕሮጀክቶችም ሳይሳኩ ቀሩ፡፡ በሠራዊቱ ሥር እንዲደራጁ የተደረጉ የአገሪቱን ኢንዱስትሪ ሽግግር ያፋጥናሉ የተባሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሳይሆኑ ባክነው ቀሩ፡፡ የጊዜው መንግሥት ሌላው ቀርቶ ከሕዝብ በሚመነጭ ቁጠባና ሀብት የሚሠሩ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችንም በታሰበው ልክ ማስፈጸም ሲያቅተው ነው የታየው፡፡ ከሁሉ በላይ የመላው ኢትዮጵያውያንን ትኩረት ያረፈበት በሞራልም በገንዘብም ብዙኃኑ ዜጋ የሚደግፈው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በብልሹ አስተዳደርና በምዝበራ ለመጓተት ተዳረገ መባሉ፣ ሁሉንም አንገት ያስደፋ ብሔራዊ ክብርና ኩራት ላይ ጭምር ጥላ ያጠላ መጥፎ ዕጣ ሆኖ የታየ እንደነበር በርካቶች እስካሁን ይናገራሉ፡፡

ይህን መሰሉ ዕቅድ አለመተግበር ያስከተለው አገራዊ ክስረት በተፈጠረ ማግሥት ፖለቲካዊ ለውጥ በሕዝቡ ግፊት መጣ፡፡ ኢሕአዴግ ከሥልጣን ተወግዶ የለውጡ አመራር (የአሁኑ ብልፅግና) በቦታው ተተካ፡፡ የማንፈጽመውን አናቅድም፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ ሰጥቶ ዳር ማድረስ እንጂ አገራዊ ኪሳራና ዕዳ ያሸከሙን ጅምር ሥራዎችን ሳናገባድድ የተለጠጡ ዕቅዶችን አናቀርብም የሚል አስተዳደር ወደ ሥልጣን መጣ፡፡ አዲስ የመሠረት ድንጋይ ልንጥል ቀርቶ በየቦታው የተጣሉ የመሠረት ድንጋዮችን ለቅመን አንጨርስም በማለትም ሰፊ ድጋፍ ያስገኘ ቅስቀሳ አደረገ፡፡

አዲሱ መንግሥት ግን ብዙም ሳይዘገይ ኢትዮጵያን ማበልፀግ ነው ግቤ ብሎ ተነሳ፡፡ ኢትዮጵያን ለማበልፀግ ደግሞ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ያስፈልጋል አለ፡፡ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ አዘጋጅቶም ይፋ አደረገ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለአገር፣ አረንጓዴ አሻራ (ግሪን ሌጋሲ)፣ የበጋ መስኖ ልማት፣ የሌማቱ ትሩፋት፣ ወዘተ. እየተባሉ እጅግ ትልልቅ አገራዊ የልማት ውጥኖች መከታተል ጀመሩ፡፡

በብልፅግና ዘመን ተቋማዊ ባለቤት ኖሯቸው ይፋ ከሚደረጉ አገራዊ የልማት ዕቅዶች በተጨማሪ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጪነት የተጀመሩ እየተባለ በርካታ የልማት ንቅናቄዎች ሲጀመሩ መታየቱ አዲስ ባህል እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፡፡

የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ዋና ግቡ መሆኑን የሚናገረው አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ በእነዚህ የልማት ውጥኖች በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጦች እያመጣ መሆኑን ይከራከራል፡፡ ዕቅድ ማስፈጸሙ ላይ ከኢሕአዴግም ሆነ ከቀደሙት መንግሥታት የተሻለ ስለመሆኑ የሚናገረው መንግሥት የተጋነነ በሚል ክርክር የሚነሳባቸው የስኬት ማሳያ አኃዛዊ ሪፖርቶችን ይፋ ከማድረግም ተቆጥቦ አያውቅም፡፡

አዲሱ መንግሥት ‹ኢትዮጵያን በማበልፀግ ከታላላቅ አገሮች ተርታ አሠልፋለሁ›፣ እንዲሁም ‹ከብልፅግና ጎዳና የሚያስቆመን የለም› የሚሉ ተስፋዎች ከመመገብ ወደኋላ ብሎም አያውቅም፡፡ ከዚህ ቀደም ‹ኢትዮጵያን ከዝቅተኛ ወደ ባለመካከለኛ ገቢ አገርነት እናሸጋግራለን› ተብሎ የአጭርና የረዥም ጊዜ አገራዊ ዕቅዶችን እንተገብራለን ቢባልም፣ በአገሪቱ ትርጉም ያለው ለውጥ አለመምጣቱ ይወሳል፡፡ ብዙዎች ከዚህ ተነስተው የብልፅግና ዕቅድና ውጥን ካለፉት በምን የተለየ ነው ሲሉ ጥያቄ ያነሱበታል፡፡

በሥራ ፈጠራና በንግድ ክህሎት ላይ ያተኮረ ‹‹መነገጃ›› የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ የጻፉትና ለረጅም ጊዜ በላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ በግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያነት የሠሩት አቶ ጌታቸው ጳውሎስ፣ በኢትዮጵያ ዕቅድ አወጣጥና አተገባበር ላይ እንቅፋት የሚያጋጥመው በዕውቀት የሚሠራ ሥራ ባለመኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

አገሪቱ የምታወጣቸው ዕቅዶች በመሠረታዊነት አገሪቱን ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ሀብቶች ጠንቅቀው የለዩ አለመሆናቸውን አቶ ጌታቸው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ተነፃፃሪ ጥቅም (ኮምፓራቲቭ አድቫንቴጅ)ን መለየት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ለሚሠሩ ሥራዎች ስኬት ወሳኝ መሠረት ነው፡፡ ፖሊሲ ስትቀርፅ እነዚህን በዓለም ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ሀብቶች ግምት ውስጥ መክተት አለብህ፡፡ ለምሳሌ ስዊድን ማዕድን በተለይም ብረትና የእንጨት ሀብት በሰፊው አላት፡፡ አገሪቱ በብረት ሀብቷ ተጠቅማ እንደ ቮልቮ ያሉ ምርቶችን፣ ትልልቅ ማሽነሪዎችና በርካታ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ታመርታለች፡፡ በሌላ በኩልም ከካርቶንና ከወረቀት ጀምሮ የእንጨት ውጤቶችን በማምረትም ጠንካራ ተወዳዳሪ ነች፡፡ ልክ እንደ ስዊድን ሁሉ የእኛ ኢኮኖሚ በዓለም ተፎካካሪ የሚሆንባቸውን የዕድገት መሠረቶችን መለየት አስፈላጊ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱ የዕድገት አካሄድ አለመለመዱን የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፣ በዘፈቀደና ከዕውቀት ነፃ በሆነ ሁኔታ ግብታዊ ዕርምጃዎች መለማመዳቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህ አንፃራዊ የመወዳደሪያ ሀብቶቻችንን ለይቶ ያለማወቅ ጉዳይ ደግሞ እንደ አገር አቅጣጫችንን ለመለየት ፈተና እንደሆነም ያሰምሩበታል፡፡

‹‹ሌላኛው ችግር ከዕቅድ አወጣጥ ጀምሮ እስከ ማስፈጸም እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥር ድረስ ባለው የሥራ እርከን ከሙያተኞች ይልቅ በፖለቲካ ሹመኞች መመራቱ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ይህን አሳሳቢ ከሆነው የዋጋ ግሽበት መፍትሔ ጋር አያይዘው ለማንሳት የሚሞክሩት አቶ ጌታቸው፣ ቲማቲም ላይ የገጠማቸውን በቅርበት የሚያውቁትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡

የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ በሚሠሩ ወቅት የቲማቲም ጁስ መጠጣት እንደለመዱና ይህን ልማድ አሁንም እንደሚያዘወትሩ ያስረዱት አቶ ጌታቸው፣ በቅርብ ጊዜ ቲማቲም ጁስ ገበያ ውስጥ እንዳጡ ይናገራሉ፡፡ ምርቱን የሚያቀርቡ አምራቾች ዘንድ በመደወል የእጥረቱን ምክንያት ለመጠየቅ መሞከራቸውንም ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ‹‹አራት ኪሎ ቲማቲም ፈጭተንና አቀነባብረን አንዲት ጣሳ ቲማቲም ጁስ ከምናመርት ይልቅ፣ አንድ ኪሎ ቲማቲም በጥሬው ብንሸጥ እኮ ያዋጣናል፤›› የሚል መልስ ማግኘታቸውን በአግራሞት ይናገራሉ፡፡

‹‹አገሪቱ ሥር የሰደደ የምርት እጥረት እያለባት ሁለንተናዊ የልማት ግብና አቅጣጫን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ አተኩሮ መረባረብ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ የዋጋ ግሽበትና መፍትሔዎቹ እየተባለ ብዙ ችግር ተኮር ያልሆነ ዕቅድ በኢትዮጵያ መታቀዱ የተለመደ ነው፤›› በማለትም ዕቅድና አገራዊ ችግሮች የተገላቢጦሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ‹‹ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ዕርምጃዎችና አማራጮቻቸው በኢትዮጵያ፣ ቅጽ ሁለት የኢኮኖሚ ጉዳዮች›› በተባለው ዕትሙ በኢትዮጵያ ስለሚካሄዱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የታላላቅ ኢኮኖሚስቶችን ምልከታ አጋርቶበታል፡፡ በዚህ ጥናታዊ ዕትም ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ዓብይ ኢኮኖሚ (ማክሮ ኢኮኖሚ) ሁኔታና መንግሥት ወደፊት በኢኮኖሚው ውስጥ ሊኖረው የሚገባ ሚና›› በሚል ርዕስ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር)፣ ከፍተኛ ዕድገት አመጣ የሚባለውን የኢሕአዴግ ዘመንን አገራዊ የኢኮኖሚ አመራር ውጤታማነት በሰፊው ፈትሸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ መናጋት የገጠማት›› አገር እንደሆነች ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ያስቀመጡት ባለሙያው መንግሥቱንም፣ ‹‹የጠራ የንድፈ ሐሳብ መሠረት የሌለው ልማታዊ መንግሥት›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ የአገሪቱ የመዋዕለ ንዋይ ዕቅድ፣ የአገሪቱ የምግብ አቅርቦት፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በመሠረታዊነት ችግር እንደገጠማቸው በመጥቀስ ዜጎች ሊሸከሙት የሚከብድ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ኢኮኖሚውን እየፈተነው መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ብር ከማተም በተጨማሪ የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ (በተለይ የምግብ አቅርቦት) አጠቃላዩ የአገሪቱ ዕድገት በሚጠይቀው መጠን ካለማደጉ ጋር ተዳምሮ፣ የኢኮኖሚውን ጤናማነት እንዳቃወሱት ባለሙያው ያብራራሉ፡፡

ከዚህ በመነሳት፣ ‹‹የጠራ የልማታዊ መንግሥት ንድፈ ሐሳብና ከእሱም ተፈልቅቀው የወጡ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ቢከተል ኖሮ አሁን የገባንበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግር ውስት በዚህ መጠን ባልገባን ነበር፤›› በማለት ያስቀምጣሉ፡፡ ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) በኢትዮጵያ መጣ የሚባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ‹‹መዋቅራዊ ለውጥ ያላመጣ›› መሆኑን ነው የሚደመድሙት፡፡

ከአሥር ዓመታት በላይ ተመዘገበ ተብሎ ሲነገርለት የቆየው የኢትዮጵያ ዕድገት በተጨባጭ የኅብረተሰቡን ሕይወት ትርጉም ባለው መንገድ አለመቀየሩን፣ ምሁሩ በተለያዩ መመዘኛዎች ያቀርባሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2002 በኢትዮጵያ በቀን ከ1.25 ዶላር በታች የሆነ ገቢ እያገኘ የሚኖረው 51 በመቶ ሕዝብ እንደነበር፣ ተመዘገበ የሚባለው ዕድገት ይህን አኃዝ ከ47 በመቶ በታች አለማውረዱን ነው የገለጹት፡፡ ይህን ከእነ ቻይና፣ ኮሪያና ታይዋን የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ጋር ያነፃፀሩት ዓለማየሁ (ዶ/ር) እነዚህ አገሮች እ.ኤ.አ. በ1981 የነበራቸውን 77 በመቶ ከድህነት ወለል በታች የነበረ ሕዝብ በ2018 ግን ከ13 በመቶ በታች እንዳወረዱት ያስቀምጣሉ፡፡ ምሁሩ የማክሮ ኢኮኖሚ መናጋት ችግር በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ መቀጠሉንም በግልጽ ያብራራሉ፡፡

ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ተገዥነት ነፃ በውጡባቸው እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ዓመታት እንደ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሆንግ ኮንግና ታይዋን ካሉ አገሮች ጋር ተነፃፃሪ የሆነ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ነበሩ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያም ቢሆን በተመሳሳይ የዕድገት ሁኔታ ላይ ነበረች ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ አራቱ የእስያ አገሮች በዕድገት ሽምጥ እየጋለቡ ‹‹የእስያ ነብሮች›› በሚል ተቀፅላ ተሰጥቷቸው ከፍተኛ ለውጥ ሲያስመዘግቡ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ግን ባሉበት እየረገጡ በድህነትና ኋላቀርነት ተዘፍቀው እንደቀሩ ብዙ ተቺዎች ይናገራሉ፡፡

ከእስያ ነብሮች አንዷ የሆነችው ሲንጋፖር የእንግሊዝ ዋና ከተማ የለንደንን ግማሽ የምታህል ብትሆንም፣ በውኃ የተከበበችና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለቤት እንደነበረች ታሪክ ከትቦታል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት የሚባል ነገር የሌላት ደሃዋ ሲንጋፖር እ.ኤ.አ. በ1959 ነፃ ስትወጣ ብቻዋን እንደ አገር መቆም ከብዷት ከማሌዢያ ጋር ተቀላቀለች፡፡ ደሃን አስጠግቶ የችግር ጎተራ መሆን ያልፈለጉ በርካታ የማሌዥያ ፖለቲከኞች የሲንጋፖርን መቀላቀል ተቃወሙ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ የማሌዥያ ፓርላማ ሲንጋፖር እንድትወጣና ብቻዋን አገር እንድትሆን በአብላጫ ድምፅ ወሰነ፡፡

አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመሩት ሊ ኩዋን ዩ ሲንጋፖር በዓለም ታሪክ አስደናቂ የሚባል ዕድገት እንድታስመዘግብ ሥር ነቀል ዕርምጃዎች መውሰድ ጀመሩ፡፡ የህንድ፣ የቻይና ወይም የማሌዥያ የዘር ግንድ አለኝ እያለ በዘር ሽኩቻ ውስጥ የወደቀ፣ ትንሽ መሬት ላይ ተጨናንቆ የሠፈረ ሕዝብን የተፈጥሮ ሀብት የሌለው ደሴትን በፍጥነት የሚያሳድግ ዕቅድ አወጡ፡፡ አገሪቱ ያላትን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የንግድ መተላለፊያ ወደብን ያማከለ ልማት ጀመሩ፡፡ እስያን ከቀሪው ዓለም ጋር ለማገናኘት ወሳኝ የንግድ መተላለፊያ ወደብ የሆነችው ሲንጋፖር በአንዴ መለወጥ ጀመረች፡፡

በሲንጋፖር ያለ ውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዕድገት የማይታሰብ ነበር፡፡ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የታክስ አሠራር ተዘረጋ፡፡ ሙስናና ምዝበራን መቅረፍ፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲን መታገልም ትኩረት ተሰጠው፡፡ ዛሬ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚፈስባት አገር የሆነችው ሲንጋፖር በዚህ ዕቅድ ትልቅ ለውጥ አምጥታለች ይባላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 አሜሪካ 351 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማግኘት ዓለምን ስትመራ ቻይና 155 ቢሊዮን ዶላር አግኝታ ሁለተኛ ነበረች፡፡ ሲንጋፖር ደግሞ በ105 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም ሦስተኛ ተብላ ነበር፡፡

ሲንጋፖር ከቅኝ ተገዥነት ነፃ ስትወጣ ዓመታዊ ጥቅል ኢኮኖሚ ገቢዋ 700 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የሊ ኩዋን ዩ መንግሥት በወደብና በንግድ አውታሮች ላይ ሰፊ ልማት አደረገ፡፡ በዓለም ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው ወደቦች አንዱን ገነባ፡፡ ከዓለም ተፎካካሪ አየር መንገዶች አንዱን መገንባቱም ይነገራል፡፡ ለዜጎች ጥቂት ካሳ በመክፈል አስደናቂ የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት በማካሄድ ተሳካለት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የአገሪቱን ጥቅል ገቢ ከ320 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ ቻለ፡፡ የዓለም ቁልፍ የሎጂስቲክስ መዲናና የረቀቁ (High Tech) ምርቶች ምንጭ የሆነች አገር የፈጠረው የሊ መንግሥት ዛሬ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ65 ሺሕ ዶላር በላይ አድርሷል ይባላል፡፡

ሲንጋፖር አቻዎቿ ደቡብ ኮሪያ፣ ሆንግ ኮንግና ታይዋን በተጠናና በታቀደ መንገድ ፈጣን ትርፍ (ልማት) በሚያመጡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ በመረባረባቸው የዜጎቻቸውን ሕይወት የሚቀይር ሥር ነቀል ዕድገት ማስመዝገባቸውን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -