Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ለመግባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ስለመድረሱ ተነግሯል፡፡ ፋብሪካው ከአዲስ አበባ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ የሚገኝና በኢትዮጵያው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ኩባንያ በጋራ የሚገነባ ነው፡፡ በቀን 150 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ ከአራት ወራት በኋላ ሥራ ይጀምራል፡፡ 

የአገሪቱን የሲሚንቶ አቅርቦትን በ50 በመቶ ያሳድጋል ተብሎም ታምኗል፡፡ በዚህ ፕሮጅክት አጠቃላይ ይዘትና የሥራ አፈጻጸም ብዙ ሊባሉ የሚችሉ መልካም ነገሮች ማስተዋል ችያለሁ፡፡ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ መሆኑ መልካም አፈጻጸም የሚጠቀስም ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ሥራ እንዲጀምር የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ፣ የፕሮጀክቱ ባለድርሻ የሆነው የቻይናው ኩባንያና ኮንትራክተር ጥምረት ሥራው እንዲቀላጠፍ አድርጓል፡፡ እንደተባለው ከወራት በኋላ ሥራ ሲጀምር የሲሚንቶ ገበያን የሚያስተካክል መሆኑም ታምኖበታል፡፡ ምናልባትም ዋጋውን ጭምር ያረጋጋል፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶች አንዱና ዋነኛው ምክንያት የፍላጎቱን ያህል ምርት ባለመቅረቡ ሲሆን፣ በሲሚንቶ ምርት ገበያ ውስጥ ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ በአንድ ጊዜ ማስገባት ከተቻለ ገበያውን ያረጋጋል የሚለውን እምነት ያጠናክራል፡፡ 

ነገር ግን ምርቱ በገፍ መቅረቡ ሳይሆን ዋናው ጉዳይ የግብይት ሥርዓቱን በአግባቡ ማስተዳደር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙ ተስፋ የተደረገባቸው አንዳንድ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን ምርት ለተጠቃሚው ለማድረስ ያልቻሉበት ዋነኛ ምክንያት በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ የነበረው የግብይት ሥርዓት መበላሸት መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡

አዲሱ ፋብሪካም በመልካም የታየለት ተግባሩ ስኬት የሚኖረው ምርቱን በአግባቡ እንዲሠራጭ ከወዲሁ ዝግጅት አድርጎ ሊተገበር ሲችል መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ሌላው ጉዳይ ይህንን ፋብሪካ ዕውን ለማድረግ ሥራውን በሽርክና መሥራት መቻሉ በእጅግ ያገዘው መሆኑን ነው፡፡

የፕሮጀክቱ የሥራ ኃላፊዎች ሲገልጹ እንደተሰማው፣ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከተያዘለት የጊዜ ገደብ ባጠረ ጊዜ ለመጠናቀቁ አንዱ ምክንያት የኢትዮጵያው ኩባንያና ከቻይናው ኩባንያ መካከል በተደረገ ለየት ያለ ስምምነት በጥምረት መሥራት መቻሉ ለውጤት አብቅቷቸዋል፡፡ ጥምረቱ የተፈጠረበት መንገድ የቻይናው ኩባንያ በውጭ ምንዛሪ ባለድርሻ እንዲሆን የአገር ውስጥ ኩባንያ ደግሞ በብር ኢንቨስት በማድረግ ሥራ እንዲሠራ መደረጉ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ግዙፍ ፋብሪካ ለመገንባት አስችሏል፡፡ እንዲህ ያለው ስምምነት በሌሎች ዘርፎች ላይም ሊሠራ የሚችል ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያም ይሆናል፡፡  

በዚህ መንገድ መሠራቱ የቻይናው ኩባንያ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ግዥዎችን በሙሉ ያለ ችግር እንዲፈጸም አስችሏል፡፡ 

እንዲህ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ከመሆናቸው አንፃር፣ እንደ ሌሎች ፕሮጀክቶች በውጭ ምንዛሪ ችግር ሥራው ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል አግዟል፡፡ ይህም በመሆኑ የሽርክና ስምምነት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እጥረትና የገበያ ችግር የነበረበትን ሲሚንቶ በከፍተኛ ደረጃ በማምረት፣ ገበያውን ለማረጋጋት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህ ልምድ በቀላል መታየት የለበትም፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገር ደረጃ ያሉብንን የዋጋ ንረት ለማቃለል እንዲህ ባሉ ስምምነቶች በማካሄድ፣ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን ማካሄድ እንደሚቻል አሳይቷል ማለት ይቻላል፡፡  

እንደ ሲሚንቶ በአገር ውስጥ እጥረት የሚታይባቸውን መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችንም ሆነ በተለያዩ ግብዓቶች ግልጋሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉ ምርቶችን ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው የሚሠሩበት ዕድል ካለ ብዙ ነገሮች ሊቃለሉ ይችላሉ፡፡ እጥረት የሚታይባቸው ምርቶችን በቀላሉ በኢትዮጵያ ማምረት የሚቻልበት ዕድል አማራጭ ዕድል ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ በሚፈለገው መጠን ስለሌለ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ከሚመጡ ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው ሊሠሩ ለሚችሉ ኩባንያዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቢችሉ ብዙ መጠቀም ይቻላል፡፡ 

አሁን ባለንበት ሁኔታ ሌላው ቀርቶ በምርት ላይ የሚገኙ አነስተኛ ፋብሪካዎች ሳይቀሩ ጥሬ ዕቃ ለማስመጣት፣ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለባችውን ፍዳ እያየን ነውና በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና በዌስት ኢንተርናሽናል መካከል የተፈጠረውን ጥምረትና ያስገኘውን ውጤት እንደ ሞዴል በመውሰድ በሌሎች ምርቶች ላይም ተመሳሳይ ሥራ እንዲሠራ የሚመለከተው ሁሉ ቢገፋ የአንዳንድ ምርቶችን እጥረት መቅረፍ የማይቻልበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ 

እንዲህ ያሉ ጥምረቶች በቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚያስገኙት ጠቀሜታም ቀላል አይሆንም፣ አገራዊ ኢኮኖሚውንም ይደግፋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚሰነካከሉ ኢንቨስትመንቶችን ቀና ሊደርጋቸው ይችላል፡፡ የአገራችን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ወደፊትም እንዲህ በቀላሉ የማይፈታ በመሆኑ አንድን ማምረቻ ለማቋቋም ተጨማሪ ሆኖ የሚገባው የውጭ ኩባንያ ለሥራ ሒደት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ጭምር ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ እዚህ ላይ ግን ለሽርክና ስምምነቶቹ በጥንቃቄ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ጨዋ የቢዝነስ ሰው መሆንና ግላዊ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ዕሳቤን ይዞ መሥራትንም የሚጠይቅ ቢሆንም የመንግሥትንም ዕገዛ ይሻል፡፡ ለዚህ ዓይነት ጥምረት የሚሆን ለየት ያለ ሕግም ካስፈለገ ለማውጣት ልንጠቀም እንችላለን፡፡ 

ስለዚህ የሲሚንቶ ፋብሪካ ልምድ በሌሎች ምርቶችም እንዲተገበር ምን መደረግ እንዳለበት ታስቦበት የሚሠራበት መንገድ ቢመቻች በአንዳንድ ምርቶች ላይ ያሉብንን እጥረት ለመቀነስና ዋጋ ማረጋጋት የማይችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ቢያንስ የተወሰኑ የምርት ዓይነቶቻችን ለይቶ ተጨማሪ ኩባንያዎቹን አሳምኖ ማምጣት ይቻላል፡፡ ዘለዓለም ዕቃ አምጥቶ ከመቸርቸር መለስ ብሎ እዚሁ ማምረትን ለመለማመድ አንዱ መንገድ ይህ ነውና ጉዳዩ ጠቀሜታው ታይቶ በቶሎ መተግበር ቢቻል ነገ ተስፋ ይሰጣል፡፡ ኢንዱስትሪያላይዜሽንም ለማስፋፋት ያግዛል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት