Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጎህ ባንክ በ2015 ሒሳብ ዓመት ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የቤት ብድር አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ሞርጌጅ ባንክ በመሆን የባንክ ኢንደስትሪውን የተቀላቀለው ጎህ ቤቶች ባንክ፣ በሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ከሰጠው አጠቀላይ ብድር ውስጥ 50 በመቶው የረዥም ጊዜ የሞርጌጅ (የቤት) ብድር መሆኑን አስታወቀ። በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ የ1.5 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አሳይቷል።

ባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ሪፖርት እንደጠቀሰው፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ለሞርጌጅና ለሌሎች የንግድ ሥራዎች የሰጠው አጠቃላይ ብድር 1.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ጎህ ባንክ በ2015 ሒሳብ ዓመት ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የቤት ብድር አቀረበ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጎህ ቤቶች ባንክ ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት

በሒሳብ ዓመቱ መጀመርያ ላይ የባንኩ የብድር ክምችት 298.3 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሰጠውን ብድር ወደ 1.3 ቢሊዮን ብር ከፍ አድርጓል። በዚህም መሠረት በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የነበረው የባንኩ የብድር አቅርቦት፣ አገልግሎቱን አንድ ብሎ ከጀመረበት ከ2014 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ342 በመቶ ብልጫ እንዳለው የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አስታውቋል፡፡ 

የጎህ ቤቶች ባንክ ዳይሬክተቶች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ናና ባቀረቡት ሪፖርትም፣ በሒሳብ ዓመቱ ካቀረበው አጠቃላይ ብድር ውስጥ ወደ ግማሽ የተጠጋው ወይም 49.2 በመቶ የሚሆነው የረዥም ጊዜ የሞርጌጅ ብድር መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም መሠረት ወደ 50 በመቶ የሚጠጋው ብድር ለቤት ግዥ፣ ለቤት ግንባታና ዕድሳት፣ እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያያዥነት ላላቸው የብድር ጥያቄዎች የቀረበ ነው።

ጎህ ቤቶች ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ካቀረበው ብድር በተጨማሪ፣ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድ ያስመዘገበው ውጤት ከቀዳሚው ዓመት የ255.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ያስረዳል። የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ2014 ከነበረው 256.6 ሚሊዮን ብር ወደ 911.8 ሚሊዮን ብር ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ ተቀማጭ ሒሳብ የከፈቱ የባንኩ ደንበኞች ብዛትም ከ5,023 ወደ 21,932 ማደጉን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ 

ከተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 70.2 በመቶው ከሞርጌጅ ቁጠባ መገኘቱ ባንኩ የተመሠረተበት ዓላማ ተስፋ ሰጪ መሆኑን እንደሚያመላክት የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ጌታሁን አስታውቀዋል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃርም ባንኩ በተጠናቀቀው የሐሳብ ዓመት ሦስት ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱ ታውቋል። ይህም ከቀዳሚው ዓመት ከነበረው 162 ሺሕ ዶላር ጋር ሲነፃፀር የ2.8 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አለው፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩ በዚህ ጉዳይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ጎህ ባንክ በዋናነት በሞርጌጅ አገልግሎት ላይ የተሰማራ ቢሆንም፣ ከታወቁ ዓለም አቀፍ ባንኮችና የገንዘብ አስተላላፊዎች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ በመሥራቱ ጠቃሚ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማመንጨት እንደቻለ ገልጸዋል።

በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 212.6 ሚሊዮን ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በቀደመው ዓመት ከነበረው ከ121.7 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀርም የ74.7 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ለዚህም ከብድር የተገኘው የወለድ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ እንዳበረከተ ሪፖርቱ ይጠቁማል።

የባንኩ አጠቃላይ ወጪ በIFRS አሠራር የተደረጉ ማስተካከያዎችን ጨምሮ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 206.2 ሚሊዮን ብር ሆኖ የተመዘገበ በመሆኑ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲነፃፀር የ81 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በቀደመው ዓመት ጠቅላላ ወጪው 113.8 ሚሊዮን ብር እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 2.63 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በ2014 የሒሳብ ዓመት ደርሶበት ከነበረው 1.21 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ117.4 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

የጎህ ቤቶች ባንክ የተፈረመ ካፒታል 1.99 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ ካፒታሉም የተከፈለ ካፒታልን፣ የተለያዩ መጠባበቂያ ሒሳቦችንና ያልተከፋፈለ ትርፍን ጨምሮ 1.55 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው መጠን ጋር ሲነፃፀር የ757.8 ሚሊዮን ብር ወይም የ96.2 በመቶ ዕድገት አለው። የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ባለፈው ዓመት ከነበረበት 780 ሚሊዮን ብር 69.3 በመቶ በማደግ 1.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 

ባንኩ በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር በመቅረፍ ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት በጀመረው ጥረት ከተለያዩ ሪል ስቴት አልሚዎች ጋር በትብብር መሥራት መጀመሩን አቶ ጌታሁን ተናግረዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ባንኩ ከፊል የባለቤትነት ድርሻ የያዘበት ጎህ የቤቶች ልማትና ገበያ አ.ማ. የተሰኘ የሪል ስቴት ኩባንያ ጋር በመተባበር የቤት ግንባታዎችን እንደጀመረ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን በሪል ስቴት ኩባንያው በኩል በማስገንባትና ለተጠቀሚዎች ለማስተላለፍ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም ገልጸዋል። ባንኩ ከዚህ ኩባንያ በተጨማሪ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል ከሚጥሩ ሌሎች መሰል ድርጅቶችም ጋር በቅርበት እንደሚሠራ የቦርድ ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጌታሁን ባቀረቡት ሪፖርት በቀጣዮቹ ዓመታት ተግዳሮቶችን የዳሰሱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ያለችበት የፀጥታ ችግርና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ከዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ጋር ተዳምሮ በ2016 የሒሳብ ዓመትም ለታዳጊ ባንካቸው ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የገንዘብ ፖሊሲ የባንኮች የብድር አቅርቦት ላይ ገደብ መጣሉ፣ የጎህ ባንክን ዕድገት ወሳኝ በሆነ መልኩ እንደሚነካ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሞርጌጅ ባንክ ሥራን በተገቢው ሁኔታ ለመሥራት የሚያስችል ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ በየጊዜው መናር፣ ለአጭርም ሆነ ረዥም ጊዜ የሚቆይ ገንዘብ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ማሰባሰብ አስቸጋሪ መሆን የዘረዘሯቸው ሌሎች ተግዳሮቶች ናቸው። ከዚህም ተጨማሪም ከዓለም አቀፍ የውጭ ባንኮች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ መሥራት አለመቻልና የቴክኖሎጂ ግዥ ዋጋ ውድ መሆን፣ ባንካቸውን እየፈተኑ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።

ጎህ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት በተለያዩ አፈጻጸሞች ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ ቢሆንም፣ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ግን ከቀዳሚው ዓመት በ19 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ያልተጣራ ትርፍ 6.38 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ካገኘው ያልተጣራ 7.9 ሚሊዮን ብር ትርፍ ጋር ሲነፃፀር የ1.5 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አለው፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ለታየው ቅናሽ ምክንያት ከሆኑት መካከል ለአዳዲስ ቅርንጫፎች ማስፋፊያ የቢሮ ኪራይና አላቂ ቁሳቁሶች ለማሟላት፣ የሠራተኞች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የመጣው የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም መጠን ማደግ፣ በዋጋ መናር ምክንያት የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ ከካፒታል ዕቃዎችና ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የዕርጅና ቅናሽ መጠን ከፍ ማለት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብሏል፡፡

ጎህ ባንክ ከሌሎች የንግድ ባንኮች ለየት ባለ መልኩ በሞርጌጅ ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሠራ ባንክ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባንኩ ቤቶች በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ የቋሚ ሠራተኞች ቁጥር 156 ደርሷል፡፡ ጎህ ባንክ እንደ ንግድ ባንኮች ብዙ ቅርንጫፎችን በመክፈት የማይስፋፋ ቢሆንም፣ የባንኩን የአገልግሎት አሰጣጥ ያማከለ የቅርንጫፎች ሥርጭት በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች እንደሚኖሩት በሒሳብ ዓመቱ አምስት ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት ቁጥራቸውን ዘጠኝ እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች