Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ ለግብርና ዘርፍ የሚያስከፍለውን የብድር ወለድ በከፍተኛ መጠን ዝቅ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለግብርና ዘርፍ ይጠየቅ የነበረውን የማበደሪያ የወለድ ተመን በከፍተኛ መጠን ዝቅ በመድረግ ባንኮች በተቀማጭ ገንዘብ ላይ ከሚከፍሉት ዝቅተኛ የወለድ መጠን እኩል እንዲሆን አደረገ። በሌሎች ዘርፎች የማበደሪያ ወለድ ላይም መጠነኛ ቅናሽ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የግብርና ዘርፍ ተበዳሪዎች እስካሁን ባንኩ ይጠይቅ የነበረው የብድር ወለድ 11.5 በመቶ ሲሆን፣ አሁን ግን ይህንን ተመን ወደ ሰባት በመቶ ዝቅ እንዲል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 

የብድር ወለድ ተመኑን ዝቅ እንዲል መወሰኑን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የሆነ ያልታረሰ መሬት ሀብት ወደ ሥራ ለማስገባት ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የበለጠ እንደሚበረታቱ ለማድረግ በግብርና ዘርፍ ከአነስተኛ መካከለኛና ኮርፖሬት ፕሮጀክት ብድር ለሚጠይቁ ይጠበቅባቸው የነበረው የ11.5 በመቶ የብድር ወለድ ተመን ወደ ሰባት ዝቅ አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡ 

ለከፍተኛ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ የግብርና ፕሮጀክቶች የተደረገው የማበደሪያ ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ ባንኩ ለዘርፉ ዕድገት ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳየበት መሆኑንም አመልክቷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ባንኩ ለሪፖርተር በሰጠው ማብራሪያ፣ እንዲህ ያለው ዕርምጃ የወሰደው ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንዲሁም በግብርና ምርቶች ላይ የሚታየው እጥረት ለመቀነስ ያግዛል ብሏል።

ሰዎች ወደዚህ ኢንቨስትመንት ገብተው ላለማልማት እንደ ምክንያት የሚያቀርቡትን የብድር ችግር ለማስቀረትም ቢሆን ይህ ውሳኔ አጋዥ እንደሚሆን የባንኩ ማብራሪያ ያመለክተል፡፡ 

‹‹አገር ሊለወጥ የሚችለውም በግብርናው ዘርፍ ሲሠራ ነው፤›› የሚለው የባንክ ማብራሪያ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብም እንዲህ ያሉ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ 

ይህንንም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደ ፖሊሲ ባንክነቱ ለመተግበር በብድር የመጨረሻውን የወለድ ተመን ለዚህ ዘርፍ ሊያቀርብ እንደቻለ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አጠቃላይ ባንኮች አማካይነት የብድር ወለድ ምጣኔያቸው 15 በመቶ መሆኑ እየታወቀ ከአዋጭነት አንፃር በሰባት በመቶ ወለድ ብድር ማቅረብ ይቻላል ወይ? ለሚለው ጥያቄ ባንኩ የፖሊስ ባንክ በመሆኑ እንዲህ ያለውን ነገር ማመቻቸት ስለሚኖርበት ይህንን አድርጓል የሚል ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ መንግሥት ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ ፅኑ ፍላጎት ስላለው በዚሁ መሠረት ተግባራዊ እንደሚደረግም ከባንኩ ያገኘነው ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ 

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለግብርና የሚሰጠው ብድር ወለድ ምጣኔ በዚህን ያህል ደረጃ መቀነሱ ብቻ ሳይሆን ብድሩ ከመካከለኛ ጊዜ እስከ ረዥም ጊዜ (20 ዓመት) ድረስ የሚቆይ ብድር ነው፡፡ 

ብድሩ የሚመለስበትም ወቅት ምርት መገኘት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመሆኑ ባንኩ ለግብርና ኢንቨስትመንት ያመቻቸው ብድርና የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብሎ እንደሚያምን ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ልማት በተሻለ ደረጃ እንዲረጋገጡ አሁን በገበያው ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በተመረጡ ዘርፎች ለተሰማሩና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለሚያነቀሳቅሱ ተበዳሪዎች በሌሎች አገልግሎቶች ላይ መጠነኛ የወለድ ተመን ማሻሻያ መደረጉንም ገልጿል፡፡ 

ባንኩ ሥራ ላይ ያዋለው ይህ ማሻሻያ ዘርፉን ለማሳደግ ያቀደው ስትራቴጂያዊ ሪፎርም አካል ሲሆን፣ መንግሥት የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ እየሠራ ያለውን ሥራ የበለጠ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባንኩ የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉ በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች በጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ምክንያት የነበረባቸውን ዝቅተኛ የማምረት አቅም በማሻሻልና በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ ከመርዳቱም በላይ አገራችን በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ የሚያግዝ መሆኑም ተብራርቷል፡፡

በተጨማሪም የተደረገው የወለድ ተመን ማሻሻያ የምግብና የኢንዱስትሪ ሰብሎች ላይ ያተኮረ ሥራ በኢንቨስተሩ እንዲሠራ የሚያበረታታ ስለመሆኑም ባንኩ ገልጿል፡፡ ከዚህም ሌላ የምግብ ፍላጎትንና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርቶች ከማሟላት ጎን ለጎን፣ የምግብ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ አቅምን ለማሳደግ እንደ መንግሥት እየተሠራ ያለውን ሥራ ያጠናክራል የሚል እምነትም አለው፡፡

ከምሥረታው ጀምሮ ለግብርና ዘርፉን ትኩረት በመስጠት ሲደግፍ የቆየ የፖሊሲ ባንክ መሆኑን የሚጠቅሰው የባንኩ መረጃ ግብርናውን ለማሻሻል መንግሥት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ ማሳካት እንዲቻልና የግብርና ዘርፉን በማነቃቃት በዘርፉ የግል ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና ለመሳብ የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉንም አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ዓመታት ባካሄደው ሪፎርም የነበሩበትን ተግዳሮቶች እየቀረፈና አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞች እያቀረበ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጫው የተመላከተ ሲሆን፣ ይህ የወለድ ተመን ማሻሻያም ወቅቱን የጠበቀና በአገራችን ያለውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ያደረገ ነው ተብሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አብዛኛው የብድር ወለድ ምጣኔው ከዘጠኝ እስከ 12 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ከሌሎች የግል ባንኮች ያነሰ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ደግሞ የተቀራረበ የብድር የወለድ ምጣኔ እንዳለው ያመለክታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች