Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት ኢንዱስትሪው ውስጥ የገቡ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የኅትመት ቴክኖሎጂን ለምን አናሳድግም? ችግሮችን ለምን አንፈታም? በተለይ በትምህርት ዘርፍ ያሉብንን ችግሮች ለምን አንቀርፍም? ለምን የአገራችንን ፍላጎት በአገራችን አንሸፍንም?›› በሚል መነሻ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር፣ የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ ይዞ የተመሠረተው በ1996 ዓ.ም. ነበር፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተ 20 ዓመታት ቢያስቆጥርም ዘርፉ አሁንም በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ዘውዱ ጥላሁን የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር የኅትመት ኢንዱስትሪውን በአጠቃላይ፣ እንዲሁም ከትምህርት መጻሕፍት ኅትመት ጋር የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ያደረገችው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩን ከመሠረታችሁ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዓላማችሁ በኅትመት ኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት የኅትመት ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሰበት ማድረስ ባይቻል እንኳን፣ የአፍሪካ አገሮች የደረሱበት ደረጃ በሒደት ለማሳደግና ለማድረስ እንደሆነ ትገልጻላችሁ፡፡ አሁን ከ20 ዓመታት በኋላ ዕድገታችሁን እንዴት ታዩታላችሁ?

አቶ ዘውዱ፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ በኋላ የኅትመት ኢንዱስትሪው ያለበትንና ወደኋላ የቀረበትን ሁኔታ ለማየት ጥረናል፡፡ ከአጋር ድርጅቶችና ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን ጥናቶችን አድርገናል፡፡ በጥናቱ መሠረት በዋናነት ለኅትመት ኢንዱስትሪው በአገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት አለመሰጠቱን ዓይተናል፡፡ ከመጀመሪያውም የማኅበር አለመኖር እንደ ድክመት የታየ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች የኅትመት ኢንዱስትሪ ማኅበር ቀድመው በመመሥረታቸው ችግራቸውን መፍታትና ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ችለዋል፡፡ ኅትመት በመሠረቱ በእኛ አገር በቂ ጥናትና ምርምር አልተደረገበትም፡፡ ኅትመት አምራች ወይስ አገልግሎት ሰጪ ነው የሚለው በመንግሥት ፖሊሲ አልተወሰነም፡፡ እንዲሁም የኅትመት ድርጅቶች አቅምና ደረጃም በጥናት አልተለየም፡፡ ይህ ማለት በተለይ የኅትመት ኢንዱስትሪው አምራች መሆኑ ተለይቶ ከተቀመጠ ልዩ ልዩ ማበረታቻ ለማግኘት ያስችላል፣ ለግብዓት አቅርቦት የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ሊያሰጥ ይችላል፣ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ሥልጠናና ተሞክሮ ድጋፍ፣ ወዘተ ሊደረግለት ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የኅትመት ኢንዱስትሪው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር አዝጋሚነትና ውስንነት እንዳለበት ታይቷል፡፡ ለዚህም የኢንዱስትሪው ዕድገት ፈጣንና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና ተለዋዋጭ መሆኑ ታይቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የግብዓት አቅርቦትና ሰንሰለት በእጅጉ ውስንነት የሚታይበት፣ ተደራራቢ ቀረጥና ታክስ የሚከፈልበት፣ በተለይም እንደ አገልግሎት ስለሚቆጠር የሚፈቀድለት የውጭ ምንዛሪ እጅግ በጣም አናሳና በወቅቱ የማያገኝ፣ እንዲያውም ጨርሶ የማይፈቀድበት ሁኔታ አለ፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን የኅትመት ኢንዱስትሪው የሚፈጥረው እሴትና የሚቀጥረው የሰው ኃይል ከሌላው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢበልጥ እንጂ የማያንስ ሆኖ ሳለ፣ በግብርና በቀረጥ የሚያስገኘው ገቢ ከፍተኛ ሆኖ እያለ፣ ይህ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ አይገባም፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረትን ሊቀርፍ የሚችል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አለመኖር፣ በሌላ በኩል የወረቀት አምራች አለመሆናችንና ሁለት የወረቀት ፋብሪካዎች ብቻ መኖራቸውና እነሱም የጥራት ጉድለት የሚነሳባቸው ናቸው፡፡ እጅግ አነስተኛ የሚባል ከአንድ በመቶ በታች በጣት የሚቆጠሩ ምርቶችን የሚያመርቱ መሆናቸው፣ የኅትመት ኢንዱስትሪው ዋና ዋና ችግሮች ሆነው ታይተዋል፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ ማኅበሩ ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ችግሩ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ሥራ እያጣ የመጣውን የኅትመት ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር እየተነጋገርንና የኅትመት ኢንዱስትሪው እንዲያድግ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ ያሉ የኅትመት ኢንዱስትሪዎች ባላቸው አቅም እየሠሩ እንዳልሆነ፣ ትልቁን ሥራ የሚሰጠው መንግሥት ቢሆንም በርካታ የኅትመት ሥራዎች ለውጭ ኩባንያዎች መሰጠታቸው፣ ለምሳሌ የትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች መጻሕፍት ኅትመት ለአብነት ሊነሳ እንደሚችል በስፋት ይነገራል፡፡ አቅማችሁ ውስን ነው የሚባለውን በተመለከተ እናንተ ምን ትላላችሁ?

አቶ ዘውዱ፡- በማኅበር ደረጃ የአቅም ውስንነት አለባቸው የሚባለውን አንቀበለውም፡፡ የኅትመት ገበያውን ከሚፈጥሩልን ድርጅቶች አንፃር በተለይ ከትምህርት መጻሕፍት ኅትመት አንፃር ስንመለከት ሁኔታውን ያላገናዘበ ውሳኔ ነው የተሰጠው፡፡ እንደ ባለድርሻ አካላት ጨረታዎች ከመውጣታቸው በፊት አላማከሩንም፡፡ በአጭር ጊዜ ጨረታ አውጥተው በአጭር ጊዜ እንዲሠራ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መንግሥት ቀደም ብለው አሳውቀውና ጊዜ ሰጥተው በአገር ውስጥ ከፍተኛ አቅም ላላቸው፣ ከውጭ በማይተናነስ ጥራትና ጊዜ ሊሠሩ ለሚችሉ ሥራውን መስጠት ይችሉ ነበር፡፡ በአገር ውስጥ ያለው የኅትመት ኢንዱስትሪ በርካታ ሚሊዮን ብሮች የፈሰሰበት ኢንቨስትመንት ሲሆን፣ በርካታ ሠራተኞች የያዘና ማንኛውንም ሥራ ሊሠራ የሚችል ነው፡፡ ሁሉንም የኅትመት ጨረታዎች ባንችል እንኳን የመስክ ጉብኝት ተደርጎና አቅማችን ታይቶ በሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) ሌሎች አገሮችም እንደሚያደርጉት፣ የአገር ውስጥ አቅም ተጠቅመንና በቂ ጊዜ ተሰጥቶን እስከ 60 በመቶ የውጭ ኅትመትን አገር ውስጥ ማስቀረት ይቻላል፡፡ አነስተኛ አቅም ላላቸው የኅትመት ተቋማት ሌሎች የኅትመት ሥራዎችን እንዲሠሩ ዕድል መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ከትልቁ የኅትመት ሥራ ላይም በአውትሶርሲንግ አቅማቸው በሚፈቅደውን መጠን ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል፡፡ ትልቁን ሥራ የሚያሠራው ትምህርት ሚኒስቴር ከእኛ ጋር በመነጋገርና በመተባበር በጋራ ቢሠራ፣ አሁን የሚታየው የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት በተወሰነ ደረጃ ይቀረፍ ነበር፡፡ መጻሕፍቱ ጥቅም ላይ ከመዋላቸው ከስድስት ወራት በፊት ተዘጋጅተውና ጨረታ ወጥቶ ቢሆን ኖሮ የአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪዎች ተሳታፊ መሆን ይችሉ ነበር፡፡

በርካታ አታሚዎች ሥራ አጥተው ቁጭ ብለው ትምህርት ሊጀመር ወር ሲቀር ጨረታ ይወጣል፡፡ ከሚሰጠው ጊዜና ከሚጠየቀው የመጻሕፍት ብዛት አኳያ አብዛኛው የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ደፍሮ ለመውሰድ ይቸገራል፡፡ በዚህም ሳቢያ የኅትመት ሥራው ወደ ውጭ ይወጣል፡፡ በዚህን ጊዜ አቅም የላቸውም እንባላለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ጨረታ ሲወጣ የወረቀት ፋብሪካ ስለሌለን ለዚህ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ማግኘት ፈታኝ ነው፡፡ ይህንንም ቢሆን በጋራ ተመካክረን ልንፈታው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ያለበለዚያ በጋራ አቅም ፈጥረን ካልሠራንና የኅትመት ኢንዱስትሪውን ካላሳደግን ወደፊትም ችግሩ ይቀጥላል፡፡  እኛ የምንለው ቀደም ብለው ሥራውን ቢሰጡን ማተሚያ ቤቶችን አስተባብረን አገር ውስጥ መሥራት እንችላለን ነው፡፡ ሁሉም አታሚ ሥራ ያገኛል፣ ብዙ ሠራተኛ ይቀጥራል፣ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፣ መንግሥትም ግብር ይሰበስባል፡፡ አቅም የላቸውም የሚባለው ነገር አይገባንም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የሚሰጡ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በአካል የመስክ ጉብኝት አድርገውና አቅማችንን ዓይተው፣ ወይም አስጠንተውና መክረው አያውቁም፡፡ አገር ውስጥ ያለውን አቅም ያየና ጥናት ያደረገም የለም፡፡ በርካታ ዘመናዊ የኅትመት ማሽኖች አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ እኛ እነዚህን አስተባብሮ ለማሠራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ኅብረት ፈጥረናል፣ ተነጋግረናል፡፡ ይህ መቼ ወደ ተግባር እንደሚለወጥ አናውቅም፡፡ መታወቅ ያለበት ግን አቅሙ አለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሺዎች የሚቆጠሩ አታሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ ይሰማል፡፡ ነገር ግን ደረጃቸውና አቅማቸው አይታወቅም፡፡ ትልልቅ የኅትመት ሥራዎችን ለመሥራት ጥሩ አቅም አላቸው የሚባሉት አታሚዎች ምን ያህል ናቸው?

አቶ ዘውዱ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሺሕ በላይ የኅትመት ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ይገመታል፡፡ የማኅበራችን አባላት የመንግሥትና የግል የኅትመት ኢንዱስትሪዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ100 በላይ አባላቶቻችን ናቸው፣ ጥሩ አቅም ያላቸው፡፡ የተለያዩ ኅትመቶችን በጥራትና በብቃት መሥራት ይችላሉ የሚባሉት ከ150 እስከ 200 ይደርሳሉ፡፡ እነዚህ በአቅማቸው መጠን መሥራት የሚችሉ ናቸው፡፡ ትልልቅ የመንግሥት ኅትመቶች ሲኖሩ ብንመካከር ተከፋፍለን መሥራት እንችላለን፡፡ ከመንግሥት ብርሃንና ሰላም፣ የትምህርት መሣሪያዎች ማደራጃ፣ ከግሉ ዘርፍ ደግሞ እጅግ በጣም ዘመናዊ የኅትመት ማሽኖች ያሏቸውና ልምድ ያካበቱ ትልልቅ የማተሚያ ድርጅቶች አሉ፡፡ የኅትመት ሥራው ወደ ውጭ ከሚወጣ ይልቅ ለአገር ውስጥ ቢሰጥ በዕውቀቱ የሚሠራው በዕውቀቱ፣ በጉልበቱ የሚሠራው በጉልበቱ ይሠራል፡፡ ኢንዱስትሪውም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ሥራውን ውጭ አገር በመላክ ኢትዮጵያ የምወታጣውን የውጭ ምንዛሪ አገር ውስጥ ማስቀረት ይቻላል፡፡ አንድ ትንሽ ማተሚያ ቤት ሲከፈት በትንሹ ከ30 እስከ 50 ሠራተኞች ይቀጥራል፡፡ ከመቅጠር ጀምሮ ለአገር ያለው አበርክቶም ቀላል አይደለም፡፡ ማተሚያ ቤቶች እንደ ሌላው ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂን የሚደግፉና ፈጠራ የታከለባቸው ቢሆኑም ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በችግራችሁ ላይ ተወያይታችሁ ነበር፡፡ ምን ዓይነት ውጤት ተገኘ?

አቶ ዘውዱ፡- የኅትመት ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ባሉት ችግሮች ዙሪያ ግንዛቤ ፈጥረናል፡፡ ዘርፉ ከ40 እስከ 50 በመቶ እሴት ስለሚጨምር፣ በርካታ የሰው ኃይል ስለሚቀጥር፣ ታክስና ቀረጥ ስለሚከፍል፣ ከውጭ በሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ታክስ ይነሳ የሚለውን ማኅበሩ ጠይቆ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጥቅል ወረቀት ላይ የታክስና የቀረጥ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ይህንን የታክስ ማሻሻያ የምንደግፍ ቢሆንም በጣት የሚቆጠሩ ጥቅል ወረቀት በዌቭ ኦፍሴት የሚያትሙትን ማተሚያ ቤቶች ጨምሮ ሁሉም ማተሚያ ቤቶች መቶ በመቶ ዝርግ ወረቀት ነው የሚጠቀሙት፡፡ ይሁንና ማሻሻያው ለጥቅል ወረቀት ትኩረት በመስጠት የቀረጥና የታክስ ማሻሻያው አምስት በመቶ እንዲሆን ወስኗል፡፡ በሪም የሚመጣውን የዝርግ ወረቀት ሳያካትት ይባስ ብሎ እስከ ዛሬ ያልታየ 15 በመቶ መሆኑ አግባብነት የሌለው መሆኑን ለገንዘብ ሚኒስቴር አስረድተን መተማመን ላይ ደርሰን፣ የቀረጥና የታክስ ማሻሻያው በዝርግ ወረቀት ላይ ማለትም በኢትዮጵያ ስታንዳርድም ተቀባይነት ባለው 61cm × 86cm፣ እንዲሁም 70cm × 100cm እንደገና ታይቶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲልና ሌሎችም ለኅትመት ግብዓት ብቻ የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የታክስና ቀረጥ ማሻሻያ እንዲደረግ፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ኮሚቴ ተቋቁሞ አብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡

የሰው ልጅ ዕውቀት የሚቀረፅበት የመጻሕፍት ኅትመት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የኅትመት ዋጋው ውድ ስለሆነ ማሳተም የሚፈልጉ የሚያዙት ከአምስት ሺሕ የማይበልጥ ነው፡፡ ዋጋው የተወደደው ተደራራቢ ታክስ ስለምንከፍል ነው፡፡ ዕውቀት የሚጨምሩና መረጃን ተደራሽ የሚያደርጉ ኅትመቶች ታክሳቸው እንዲቀንስ መደረግ አለበት፡፡ መንግሥት ይህንን እንዲያይልን እንፈልጋለን፡፡ ኢንዱስትሪው ተኪ ምርት ላይ የሚሠራ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ግብር እንከፍላለን፡፡ መጽሐፍ ከውጭ ሲገባ ታክስ አይደረግም፡፡ እኛ አገር ውስጥ አትመን ስንሸጥ ታክስ እንደረጋለን፡፡ ለምን ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪው ቀረጥ አይነሳለትም? በዚህ ሁኔታስ እንዴት ከውጮቹ ጋር ተወዳዳሪ መሆን ይቻላል? ዘርፉ በተጠና መንገድ ተወዳዳሪ እንዲሆን መደረግ አለበት፡፡ አገር ውስጥ መሥራት እየቻልንስ ሥራው ለምን ውጭ ይወጣል? መንግሥት ይህንን ዓይቶ ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡ ለአገር ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ብድርን በተመለከተም በረዥም ጊዜ ለሚከፈል ብድር ከምናገኘው ውጪ ለማሽን መግዣ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቦታ ቅድሚያ አይሰጠንም፡፡ ማኅበሩ ይህ እንዲስተካከልና ቴክኖሎጂው እንዲያድግ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይፈልጋል፣ ቁርጠኝነቱ ካለም ማሳካት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ ለሚገቡና ለኅትመት አገልግሎት ለሚውሉ ግብዓቶች ግብር እንዲስተካከል ወይም እንዲቀር እንቅስቃሴ ጀምራችኋል፡፡ ከምን ደረሰ?

አቶ ዘውዱ፡- በአገር ውስጥ ያሉት ሁለት የወረቀት ፋብሪካዎች አሁን የኅትመት ሥራ ለደረሰበት ቴክኖሎጂ የሚመጥን አቅርቦት የላቸውም፡፡ እጅግ ዝቅተኛ ጥራት ያለው ምርት በጥቂቱ ያቀርባሉ፡፡ ለመጻሕፍት ኅትመት የሚውል ወረቀት ለምሳሌ አርት ወረቀት አያመርቱም፡፡ እኛ ዕድሉ ቢሰጠን አቅሙ አለን፡፡ ነገር ግን ተወስነናል፡፡ በህንድ ለምሳሌ ከወረቀት ማምረት ጀምሮ ወደ ውጭ ለሚላኩ የኅትመት ሥራዎች የመንግሥት ድጋፍ አለ፡፡ እኛ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዘን ለኅብረተሰቡ የኅትመት ውጤቶችን ማድረስ፣ ከአገር ወጥተን ለጎረቤት አገሮች ለጂቡቲ፣ ለሶማሌላንድና ለደቡብ ሱዳን የኅትመት ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ተወስነናል፡፡ እኛ ዘንድ በጎና ቅን አመለካከት ይጎድላል፡፡ የአገርን ምርት አለማድነቅ አለ፡፡ ሁልጊዜ ጥገኛ እንሆናለን፡፡ መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች በጥራት አምርተው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማበረታቻ ያደርጋል፡፡ ለኀትመት ኢንዱስትሪውስ ለምን አያደርግም? እኛም ድጋፍ ቢሰጠን እንችላለን፡፡ ሠርተንም አስመስክረናል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከክልል ትምህርት ቢሮዎች የተሰጡ በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኅትመት ሥራዎችን በጥራትና በተባለው ጊዜ ያስረከቡ ድርጅቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአቅም ውስንነት ያለባቸውን ድርጅቶች ሳያጠኑና ሳይፈትሹ ባልተገባ ጨረታ ሒደት አሸናፊ አድርገው ሥራውን ከሰጡ በኋላ ውጤቱ ሳያምር ሲቀር፣ ሁላችሁም በአንድ ላይ አቅም የላችሁም ተብሎ ይደመደማል፡፡ የኢንዱስትሪ ቦታዎችን ዞሮ መጎብኘትና መገምገም፣ ካሉት ውስጥ ማን ሊጫረት ይችላል የሚለውን ማየትና መለየት ይገባል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር የተመካከርነውም ችግሩን ዓይቶ ውሳኔ እንዲሰጠን ነው፡፡ ለኅትመት ብቻ የሚያገለግሉና ከውጭ አገር የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የተጣለው ቀረጥ ቅናሽ እንዲደረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረናል፡፡ በቅርቡ በዝርግ ወረቀት ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግ ተስፋ አለን፡፡ ይህ ሲቀነስ በዋናነት የመጻሕፍት ዋጋና የሌሎች የኅትመት ምርቶች ዋጋ እንዲቀንስ ያግዛል፡፡ መንግሥት ለአገር ውስጥ ኅትመት ኢንዱስትሪው ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ገዥ አካል ነው፡፡ ለኅትመት ኢንዱስትሪው የሚበጅ ሥራ መሥራትና ገበያ መፍጠር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በአገልግሎት ሰጪ ዘርፍ መካተታችሁ ምን ችግር አስከተለ?

አቶ ዘውዱ፡- ለኅትመት ግብዓቶችና ለመለዋወጫ ዕቃዎች ግዥ የውጭ ምንዛሪ አናገኝም፡፡ አልፎ አልፎ ቢፈቀድልንም ከጠየቅነው በታች እጅግ ያነሰ ለዚያውም የዘገየ ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሥልጠና ዕድል የለንም፣ ድጋፍ አይደረግልንም፡፡ ማኅበሩ በፋይናንስ ረገድ የአቅም ውስንነት አለበት፡፡ በተለይ የኅትመት ኢንዱስትሪውን የሚመለከቱ፣ ለፖሊሲ ውሳኔ የሚረዱና የሚቀርቡ ደረጃቸውን የጠበቁ ልዩ ልዩ ጥናቶችን ለማካሄድ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል፡፡ ኅትመትን የሚመለከቱ ሌሎች ድጋፎችን ለማግኘት ጥያቄ ስናቀርብ እንደ ኢንዱስትሪና ተኪ ምርት አምራች ስለማንቆጠር ዕገዛ አይደረግልንም፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት መጻሕፍት ማተም ያልቻላችሁት ለምንድነው?

አቶ ዘውዱ፡- ሥራው ሲታሰብ ገና ለውጭ የመስጠት ሐሳብ ተይዞ ነው የሚጀመረው፡፡ ጨረታ ወጥቶ ሒደቱ እስኪጠናቀቅ ሁለትና ሦስት ወራት የሚፈጅበት የመንግሥት ተቋም በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍትን በሁለት ወራት ውስጥ አትሙ ይላል፡፡ ነገር ግን እነሱ የጨረታውን ሒደት ጨርሰው አሸናፊውን ለማሳወቅ በሚወስድባቸው የወራት ጊዜ ውስጥ ከግብዓት አቅርቦትና ከዋጋ አንፃር ብዙ ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የትምህርት ሚኒስቴር 40 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የትምህርት መጻሕፍት አሳትሟል፡፡ ነገር ግን የ40 ሚሊዮን ዶላር ምርት ለማምረት በግብዓትነት በግርድፉ ከ24 ሚሊዮን እስከ 28 ሚሊዮን ብር (60 በመቶና 70 በመቶ) የጥሬ ዋጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ያህል ዋጋ ያለው ግብዓት ምንም የወረቀት ፋብሪካ ለሌላት አገርና ሦስት ወራት ለተሰጠው የማስረከቢያ ጊዜ ጥሬ ዕቃውን አጓጉዞና አምርቶ እንዴት ይቻላል? ነገር ግን ይህን ማድረግ የሚቻለው ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ከአሳታሚው ድርጅት ጋር ቀድሞ በመምከርና በመወያየት፣ በአገር ውስጥ እንዲታተም ፅኑ ፍላጎት ካለ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ  ለውጭ የተሰጡት የትምህርት መጻሕፍትም እስካሁን ድረስ ተጠቃለው አለመግባታቸው የችግራችን ግዙፍነት የሚያሳይ ነው፡፡ የውጭ አታሚ ድርጅቶችም እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ጨረታዎችን የሚሠሩት በአገራቸው ካሉ ማተሚያ ቤቶች ጋር በሽርክና ሲሆን፣ መንግሥትም በቀረጥና በታክስ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ ስለሆነም የአገራችን አሳታሚዎች ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው፡፡ ይህ እውነት እያለ ለምንድነው የአገር ውስጥ ኅትመት ኢንዱስትሪውን የማይሞክሩት? ለተለያዩ የአገር ውስጥ አታሚዎች ሁለትና ሦስት የትምህርት ዓይነቶች አከፋፍለው ሰጥተው ለምንድነው የማያሠሩት? ከፋፍለው ለምን አይሰጡም? አገር ውስጥ ያለው እንደማይችል ተቆጥሮ ሥራው ለውጭ ተሰጠ፡፡ በተባለው ጊዜም ለተማሪዎች አልደረሰም፡፡ አገር ውስጥ ያለውን አቅም አያውቁትም፡፡ኢንዱስትሪው የአገር ሀብት ነው፡፡ ተስማምቶና ተነጋግሮ መሥራት እየተቻለ ይህ አይደረግም፡፡

ሌላው ቢቀር 100 ዓመታት ያስቆጠረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እንኳን አልተሰጠውም፡፡ ለምሳሌ ከላይ እንደገለጽኩት ከአንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በተጨማሪ አቅም ያላቸው ትልልቅ አታሚ ድርጅቶች አሉን፡፡ በማኅበራችን አማካይነት ተከፋፍሎ ቢሰጣቸው እነሱ ሥራውን ሊሠሩ ለሚችሉ ማተሚያ ቤቶች እንደ አቅማቸውና እንደ ችሎታቸው አከፋፍለው የተወሰኑ ሥራዎችን መሥራት ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር እንደ አገር ማሰብ ነው፡፡ ይህንን መንገድ እንኳን መከተል አልተፈለገም፡፡ ሥራ ተቀብለው ችግር የሚፈጥሩ ድርጅቶች የሉም አንልም፣ ችግሩ በብዛት ያለው ግን መንግሥት ዘንድ ነው፡፡ ማኅበራችን ራሱ ከጥራት ጀምሮ ኃላፊነት ወስዶና ተቆጣጥሮ ማሠራት ይችላል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከማኅበሩ ጋር በመሆን የኢንዱስትሪውን አቅም ቢያጠኑ፣ ለኅትመት ተብሎ ለውጭ ኩባንያዎች የሚወጣውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ማስቀረት እንችላለን፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ለኅትመት ኢንዱስትሪው ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂና አቅም ይዘው እየመጡ ነው፡፡ መጻሕፍትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኅትመቶችንም መሥራት የሚችሉ ናቸው፡፡ ማኅበሩ ደግሞ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ የቴክኒክ ችግር ካጋጠመ እርስ በርስ የዕውቀት ሽግግር እያደረጉ ችግሮችን እንዲቀረፉ ይሠራል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የኅትመት ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ከመፍጠርና በተለይ የኅትመት ኢንዱስትሪው እየዘመነ ከመሄዱ አኳያ ዘርፉ ተግዳሮት አልገጠመውም?

አቶ ዘውዱ፡- ኅትመት የአንድ ሰው ሥራ ሳይሆን በቡድን የሚሠራ ነው፡፡ የኅትመት ሥራ በሚሊዮን ብር የሚቆጠሩ ዋጋ ያላቸውን የግምትና የፕሮግራም ሶፍትዌሮችን ጨምሮ በቅድመ ኅትመት በኅትመትና በማጠናቀቅ የሥራ ሒደት ውስብስብ ሥራዎች የሚካሄድበት፣ በእያንዳንዱ ክንዋኔ ጥልቅ ዕሳቤና ፈጠራ የሚታከልበት ነው፡፡ በኅትመት ምርቶች እንደ የደንበኛው ፍላጎት ተለዋዋጭ ነው፡፡ ስለዚህ የኅትመት ሥራዎች ሁሌም አዲስ ናቸው፡፡ ለዚህ ዓይነት ውስብስብ ሥራ እሴት የሚጨምር ሙያተኛ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም የሠለጠነ የኅትመት ባለሙያ ማግኘት ቀላል ነው ማለት አይቻልም፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በሚፈለገው ደረጃ የሚያሠለጥን የኅትመት ማሠልጠኛ ተቋም እጥረት አለ፡፡ ስለዚህ ብቁ የኅትመት ባለሙያ እጥረት እንዳለ አንክድም፡፡ ስለሆነም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከመንግሥትና ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራን ነው፡፡ መሠረታዊ የሆኑ የኅትመት ዕውቀቶችን ለማስጨበጥ አርቲስቲክና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅቶች ማሠልጠኛ ተቋም ከፍተው ሥልጠና እየሰጡ  ነው፡፡ ይህ ብቻውን በቂ ነው ብለን አናምንም፡፡ ይህ ጉዳይ የኅትመት ኢንዱስትሪው ዋነኛ ተግዳሮት በመሆኑ መንግሥት፣ ማኅበራችንና ማተሚያ ቤቶች፣ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለኅትመት ሥራ የምትሰጡት ዋጋ ውድ ነው ይባላል፡፡ ይህ ለምን ሆነ?

አቶ ዘውዱ፡- ይህ ጉዳይ ከውጭ ምንዛሪና ከአቅርቦት ውስንነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለኅትመት ግብዓቶች የውጭ ምንዛሪ አይገኝም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተፈቅዶላቸው ለራሳቸው ፍላጎት የሚያውሉ ማተሚያ ቤቶች ዋጋ፣ በግል የውጭ ምንዛሪ አግኝተው ከሚያስመጡና ከዘርፉ ውጪ ከሆኑ አቅራቢዎች ጋር ሲነፃፀር ዋጋው እጅግ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው የማኅበራችን አባላት ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ይህንን ውስንነት ዓይቶ ቀደም ሲል የኅትመት ወረቀቶችንና ሌሎች ግብዓቶችን፣ እንደ ጅንአድ ያሉ ድርጅቶችን ተጠቅሞ ግብዓቶችን ለማስመጣትና ክፍተቱን ለመሙላት ፍላጎት አላሳየም፡፡ በሌላ በኩል እስካሁን በዚህ ረገድ የኅትመት ዋጋ እንዲቀንስ የሚደረጉ ማበረታቻዎች እዚህ ግባ የሚባሉ ባለመሆናቸው፣ አንዳንዴም የቴክኖሎጂው አለመዘመን፣ እንዲሁም በአሳታሚዎች ትዕዛዝ ከአቅም ጋር ተያይዞ አነስተኛ መሆን ዋጋውን ውድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ዞሮ ዞሮ የኅትመት ዋጋ ውድ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ልዩ ልዩ የማበረታቻ ዘዴዎችን፣ የፋይናንስ አቅምን፣ የቴክኖሎጂ ዕድገትንና የሰው ኃይል ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ውድነትን መቀነስ ይቻላል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ወረቀት አምጥተው እጥረቱን እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው ከትርፍ ህዳግ በላይ ጨምረው ይሸጣሉ፡፡ ይህም በኅትመት ዋጋውን ያንረዋል፡፡ ተወዳዳሪ ዋጋ እንድንሰጥ ቀጥታ በኅትመት ኢንዱስትሪው ውስጥ ላሉና አቅሙ ላላቸው ድርጅቶች ግብዓት እንዲያመጡ ቢፈቀድ፣ ተወዳዳሪ መሆንና መጻሕፍትንም በተመጣጣኝ ዋጋ ማተም እንችል ነበር፡፡ ስለዚህ አታሚ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበት አሠራር መከፈት አለበት፡፡ ይህ በዋጋም ተወዳዳሪ ያደርገናል፡፡ አገር ውስጥ ላለማሳተም የሚሰጠው አንዱ ሰበብ ዋጋው ውድ ነው የሚል ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ቢፈቅድልን ይህንን መቅረፍ ይቻላል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ ለኅትመት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ተደራራቢ ታክስ ከፍለን እናመጣለን፡፡ ወረቀት ደግሞ በውድ ዋጋ አገር ውስጥ እንገዛለን፡፡ እነዚህ ሲደራረቡ የኅትመት ዋጋ ከፍ ማለቱ ግልጽ ነው፡፡

ስለዚህ የኅትመት ኢንዱስትሪው እንደ አቅሙ ለሥራው ብቻ ለሚያውለው ግብዓት ታክስ ሊነሳለትም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአገር ውስጥ ብዙ ዕድሎች እያሉ አንጠቀምም፡፡ መንግሥት ታክስ ሙሉ ለሙሉ ቀንሶ መኖር እንደማይችል ይገባናል፡፡ በፊት በነበረው በሪም ለምንገዛቸው ወረቀቶች አምስት በመቶ ታክስ የምንከፍለው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወረቀት ስንገዛ 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት እንከፍላለን፡፡ ነገር ግን ከውጭ የሚገባ መጽሐፍ 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ አይከፈልበትም፡፡ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመጻሕፍት ነፃ ተደርጓል ከተባለ ለሁሉም መሆን አለበት፡፡ 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ከተነሳ የውጭዎቹ ከሚሰጡት ዋጋ ያነሰ ለመስጠት የሚያግደን ነገር አይኖርም፡፡ አሁን የታክስ ጉዳይ አለ፣ ግብዓት ከአትራፊ እንገዛለን፡፡ የትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ አገር ውስጥ በብር መክፈል እየተቻለ በውጭ ምንዛሪ በውጭ ተቋማት ከሚያሠሩ፣ ተነጋግረው በአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ችግር መፍታት አለባቸው፡፡ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ይህ አካሄድ አገርን ከጥገኝነት አያወጣም፡፡ የመጻሕፍት ኅትመትን በአገር ውስጥ በተኪ ምርት ማሠራት እየተቻለ ወደ ውጭ በመላኩ፣ አገር ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጣባቸው የኅትመት ማሽኖች ሥራ እንዲያጡ አድርጓል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ሥራ አለ ብለው ዘመናዊ ማሽኖች አምጥተው ሲጠባበቁ ሥራው ወደ ውጭ መውጣቱ ዘርፉን እየጎዳው ነው፡፡ አንዳንዶች እየዘጉ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ብዙ ስንሠራ ስለኖርን ኅትመት አይቻልም የምንለው ነገር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የደኅንነት ጉዳይ ያለባቸው ፓስፖርት፣ ቼክና ገንዘብ ውጭ አገር ነው የሚታተሙት፡፡ አገር ውስጥ ማተም ለምን አዳጋች ሆነ?

አቶ ዘውዱ፡- የኅትመት የደኅንነት አሠራር ፕሮሲጀርና ስታንዳርድ አለ፣ የውጭ አገር ተሞክሮ መቅሰም ይቻላል፡፡ እንዲሁም ለሚስጥራዊ ሥራ የምንጠቀምባቸውን የኅትመት መሣሪያዎችና ግብዓቶች ማበረታቻ ተደርጎላቸው ከውጭ በማስገባት አገራችን ውስጥ መሥራት ይቻላል፡፡ ሥራውንም ለተመረጡ ማተሚያ ቤቶች መስጠት ይቻላል፡፡ ከአፍሪካ አገሮች ከእኛ ያነሰ ሕዝብና ኢኮኖሚ ይዘው የአገራቸውን ገንዘብ የሚያትሙ አሉ፡፡ እኛም እንችላለን፣ ነገር ግን እኛ ለምን ይህንን አናደርግም? ቼክ በፊት አገር ውስጥ ይታተም ነበር፡፡ አሁን ለውጭ ተሰጥቷል፣ ለምን? የደኅንነት ማስጠበቂያ አሠራሮችን መዘርጋት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ፓስፖርትም ማተም ይቻላል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪ አለኝ ተብሎ አጀንዳ፣ የግድግዳና የጠረጴዛ ካላንደር፣ እስክሪብቶ ላይ ለሚታተም የኅትመት ሥራ ውጭ ድረስ የሚኬድበት አሠራር ነው በኢትዮጵያ ያለው፡፡ ነገር ግን የግልም ሆነ የመንግሥት ማተሚያ ቤቶች ዕድሉ ከተሰጣቸው ማተም ይችላሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች በአገራችን ውስጥ በስፋት የሚገኙትን ያህል ከእነሱ በኅትመት ዘርፍ የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ መለወጥ ይገባናል፡፡ በግሉም ሆነ በመንግሥት የኅትመት ኢንዱስትሪው የሚሰጠው ጠቀሜታ በሚገባ ተጠንቶ አገር ልትጠቀም ይገባል እንላለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለኢትዮጵያ የሚበጀው ኮስተር ብሎ የባህር በር ጥያቄውን መግፋት ብቻ ነው›› ብሩክ ኃይሉ (ፕሮፌሰር)፣ አንጋፋ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ባለሙያ

ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፈረንሣይና በአሜሪካ ተመድበው በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡ ዳያስፖራው በ‹‹ኖ ሞር›› ንቅናቄ ሲያደርግ በማስተባበር ተሳትፈዋል፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራው ለአንድ...

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...