Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ ኅብረተሰብ ባሉ የቀጥታና የተዘዋዋሪ አስተዋፅኦዎች ይወሰናል፡፡ በአስተናነፃችን ውስጥ እያንዳንዳችን ዕንቢ እሺ የምንለው፣ ወደንና ደስ ብሎን የምናደርገውና የምንታገለውም ነገር ይኖራልንና በሰብዕና ግንባታችን ውስጥ የእያንዳንዳችን ንቁ ተሳትፎ ድርሻ አለው፡፡ በዕድሜና በዕውቀት እያደግን ስንሄድ ሰብዕናችንን የማበልፀግ የነቃ ተሳትፏችንም እያደገ ይመጣል፡፡ በዚህ ውስጥ እንጀራ መብያ ዕውቀትና ሙያችንን ከማዳበር ባሻገር፣ ለማንነታችን መጎልበት ያስፈልጉናል ብለን የምናካሂዳቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ከጊዜ ጊዜ እየተወሳሰበና እየተሳሳረ የመጣው ምድራዊ ኑሯችንም፣ ፈርጀ ብዙ ግንዛቤና የኑሮ ክህሎቶችን እንድናዳብር እየጠየቀን ነው፡፡

አንድ ሰው በግል ባህርይው ራሴን አውቃለሁ/ራሴን መግዛት እችላለሁ ሲል፣ አባባሉ እውነተኛ የሚሆነው፣ በኑሮው ውስጥ ድክመቶቹንና ጥንካሬዎቹን አውቆ ራሱን መግራት ሲችልና አኗኗሩን እንደሚበጅ አድርጎ የመምራት አቅሙን ከጊዜ ጊዜ ሲጨምር ነው፡፡ በዚህ ተግባር ውስጥ፣ ለሥጋዊና ለልቦናዊ ጤናማነት የሚያስፈልጉ ኃይጅናዊ የኑሮ ዘይቤዎችን ማወቅና መለማመድ አለ፡፡ የሆነ ነገር እሳት ላይ ጥዶ የመርሳት ድክመት ያለበት ሰው፣ ድክመቱን ማሸነፊያ መላ ማበጀት መቻል አለበት፡፡ በዝርያ ምክንያት ለአንዳንድ በሽታዎች ተጋላጭነት ያለው መሆኑን ያወቀ ሰው ከአጋላጭ አኗኗር መቆጠብ ይኖርበታል፡፡ ራስን ማወቅና መምራት እንዲህ ያለ ግንዛቤንና የአኗኗር ክህሎትን ይፈልጋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ራስን ማወቅና መምራት በግለኝነት መጣበብ ማለት አይደለም፡፡ የዛሬ ዓለማችን ከአገር ወደ አገር የዓይነተ ብዙ ማኅበረሰቦች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ስብጥር እየጨመረ የመጣበት ከመሆኑም በላይ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባለ ብዙ ማኅበረሰቦች አገሮች ውስጥ ያለው የመኗኗር እውነታ፣ በግለኝነት፣ በራስ ሃይማኖትና ማኅብረሰባዊ ማንነት ውስጥ ታጥሮ ከመኖር ያለፈ ኃላፊነትና ተራክቦን ይጠይቃል፡፡ ከ‹‹ሀ›› ሃይማኖት ውጪ ያሉ ወገኖቻችንን ሃይማኖቶች ለማክበር (ሳናውቅ ላለመዳፈር) በተወሰነ ደረጃ ስለሃይማኖቶቻቸው ምንነት አጠቃላይ ዕውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ የተደጋገፈ ኑሯችን ይህንን ግድ ይለናል፡፡ ስለሃይማኖቶች ብዙ ማወቅ የመከባበር አቅማችንን ይጨምራል፡፡ ስለራሳችን ሃይማኖት ያለን ዕውቀትና እምነት አክባሪነት ማደግና መብሰል ወደ አክራሪነት/ፅንፈኝነት መንሸራተቻ አይደለም፡፡ እንዲያውም ወደ እዚያ ከመንሸራተት ይጠብቀናል፡፡ ፅንፈኝነት የሚመጣው ከተዛባ/ካልበሰለ ግንዛቤና ‹‹የእኔ ዓይነቱ ግንዛቤ ብቻ ልክ›› ከሚል ግትርነት ነው፡፡

በዛሬ የተሳሰረ ኑሯችን ውስጥ፣ ስልል-ጭፍን ያለች ግንዛቤ ይዞ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ አፍሪካዊ ነኝ ማለት፣ የትም የማያደርስ ሆኗል፡፡ ዛሬ ስለኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ተጠይቀን የምንናገረው ብናጣ ራሳችንን ካለማወቅ ቁጥር ነው፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ የአገራችንን ገጸ ብዙ ብዝኃነት ማንነቴ/እኔነቴ ያለ የአዕምሮ ሙሽትና ንቃተ ህሊና ሊጎናፀፍ ይገባዋል፡፡ አፍሪካዊነታችንም አኅጉራዊ ዘመዶቻችን የእኛን ውጣ ውረዳዊ ታሪክና ድል እንደተጋሩ ሁሉ፤ እኛም የእነሱን የታሪክ ውጣ ውረዶች፣ ጥቃቶቻቸውንና ሮሯቸውን፣ ተጋድሏቸውን፣ ድሎችና ኩራቶቻቸውን ሁሉ የእኛ ብለን እንድንጋራ ግድ ይለናል፣ በንቃተ ህሊናም በስሜት ተራክቦም፡፡ ለዚህ ሁሉ፣ ተራ ዜጋን የሚመጥኑ የአጠቃላይ ዕውቀት መጻሕፍት ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ትምህርት ቤቶች፣ ሚዲያዎች፣ የፊልም ጥበብና ሥነ ጽሑፎች ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአፍሪካ ሥነ ጽሑፎችም ለተለያየ የትምህርት ደረጃ በሚመጥኑበትና ለሰፊ ግንዛቤ በሚበጁበት አኳኋን ተመርጠው ቢያንስ በዋናዎቹ የፌዴራል ቋንቋዎች መተርጎማቸው፣ የዘገየን ተግባርን የማሟላት ጉዳይ ነው፡፡

ዛሬ ብዙ ተግባሮች ተደራርበው ሊጫኑን ቢችሉም፣ የትውልድ ቅብብሎሹ አንዴ ከተያያዘና ኅብረተሰባችንን የማስተማሩ ተግባር ጥሩ መሠረት ከያዘ፣ ልጆችን በየፈርጁ የመኮትኮቱ ሥራ ከቤተሰብ አንስቶ የበለጠ የተቃና ይሆናል፡፡ ከአገራችን መልማት ጋር ብዙ ተግባሮች እየቀለሉና የሰብዕና ግንባታችንም ይበልጥ እየበለፀገ ይሄዳል፡፡

የፈረጀ ብዙ ንቃተ ህሊናችን አንዱ አካል ብሔረሰባዊ ማንታችንን የሚመለከት ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ማንነትን (ብሔረሰባዊ ባህልን፣ ቋንቋን፣ ታሪክን፣ ወዘተ) ማወቅና ወድዶ መንከባከብ፣ በብስለት ከያዝነው፣ በራስ ማኅበረሰባዊ ማንነት ውስጥ እንድንጣበብ አያደርገንም፡፡ የበቀልንበት ማኅበረሰብ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ያለፈበትና አሁንም የሚገኝበት የትስስር እውነታ ሌላውንም በዘመድነት የሚያይ ሰፊ ዕይታ እንድንይዝ ይጠይቀናል፡፡ ይህ ግንዛቤ ደግሞ ከአገራዊ ማንነታችን ጋር (ብዝኃነትን ማንነቱ ካደረገ የኢትዮጵያነት ሙሽታችን ጋር) ይሳሳበል፡፡ ማኅበረሰባዊ ዝምድናዎቻችን ከኢትዮጵያ ድንበር አልፈው የሚሄዱ መሆናቸውም የዝምድና ዓይናችንንና ወገናዊነታችንን አፍሪካዊነታችን ድረስ ያስገቡታል፡፡ በቀላል አነጋገር፣ ስለብሔር/ብሔረሰባችን ታሪካዊና አሁናዊ ተዘምዶዎች ግንዛቤያችን በሰፋና በጠለቀ መጠን የምንጠቅመው ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ የህሊና ንቃታችንንና ማኅበራዊ መስተጋብራችንን ነው፡፡

እንዲህ ከኢትዮጵያነትና ከአፍሪካዊነት ንቃተ ህሊናችን ጋር የሚግባባውና የሚጠቃቀመው ብሔረሰባዊ ንቃት፣ ከእነ ኩራቱ፣ ከብሔርተኝነት ጋር መምታታት የለበትም፡፡ ብሔረሰባዊ ንቃትን ከብሔርተኛነት ጋር አሳክሮ ስለራሱ ብሔረሰባዊ ማንነት ቁብ የማይሰጠው ሰው፣ በኢትዮጵያ እውነታ ውስጥ ለመኖር የሚቸገር ይመስለኛል፡፡ ስለበቀለበት ማኅበረሰብ ለማወቅ ደንታ ያጣ ሰው፣ የሌሎች ማኅበረሰቦችን ማንነት ለማክበር ልባዊ ትርታ ይቸግረዋል፡፡ የበቀለበትን ማኅበረሰብ ሀብት ተረድቶ ጣዕሙን ያወቀ ግለሰብ፣ የሌሎችም ማኅበረሰቦች ጣዕምና ዋጋ ይገባዋል፡፡

ብሔረሰባዊ ግንዛቤ በራስ ብሔረሰብ ላይ ሲሽከረከርና በበደል ትርክት ላይ ወደ የተዋቀረ ፖለቲካ ሲያመራ ሌላ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ብሔረሰባዊ ንቃተ ህሊናቸው ያደገና የማንነት ኩራታቸው ያልተጨፈነ ሰዎች፣ ራሳቸውን ከብሔርተኛ የሚለዩበት ስያሜ በማጣት፣ ራሳቸውን ብሔርተኛ ብለው ሲጠሩ አስተውያለሁ፡፡ ‹‹በኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና በእኩልነት የሚያምንና አገሩን የሚወድ ብሔርተኛ መሆን ምን ክፋት አለው?›› ብለው ሲከራከሩም በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ፡፡ እንደ አገር ጠንክሮ በመኖር ውስጥ፣ በማኅበረሰቦች መሃል ዘመዴ/ወገኔ ተባብሎ መተሳሰብ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን የሚያስተጋባና የሚንከባከብ ኅብረተሰባዊ ንቃተ ህሊና መኖርና የፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ለመብቶቻችን መረጋገጥና መጠበቅ ዋስትና ነው፡፡

በዚህ ግንባታ ውስጥ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ብሔርተኛነት ተፈጥሮው አይፈቅድለትም፡፡ ብሔርተኝነት ተገፍቻለሁ/ተበድያለሁ የሚል ትርክትን ንቃተ ህሊናው ስለሚያደርግ፣ አውቆም ሆኖ ሳያውቀው ጥላቻና ቂምን የመዝራት ጥፋት ይሠራል፡፡ መነሻው ላይ በማኅበረሳዊ እንቅስቃሴ ቢጀምርም እንደ ሁኔታው ወደ ብሔርተኛ ትጥቅ ትግልም ሆነ ብሔረሰባዊ ቢጤነትን መሥፈርት ወደ አደረገ የፖለቲካ ቡድንነት መጓዙ የተለመደ ነው፡፡ ብሔረሰባዊ ማንነትን ፖለቲካ በማድረጉ ምክንያትም፣ ወገኔ የሚላቸውን የማኅበረሰቡን ሰዎች፣ በማንነታቸው ብቻ፣ በብሔርተኛ ፖለቲከኛነትና ደጋፊነት ለመጠርጠር ያጋልጣል፡፡ በትግል እንቅስቃሴ ዘመኑም ሆነ ሥልጣን ላይ በወጣ ጊዜ፣ በበደል ትርክቱ መሠረት ‹‹ጠላቴ›› በሚላቸው ላይ በተለያየ መልክ የሚገለጥ ጥቃት ከማድረስ እንደማይፀዳም፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ ታይቷል፡፡ እናም መብቶችን ሊያስከብር ይቅርና የሕዝቦችን አብሮ መኖር እንኳ ለማጠናከር ባህርይው አይፈቅድለትም፡፡ የማኅበራዊና የፖለቲካ ሰላም ረባሽነቱም የማይቀር ነው፡፡

ብሔርተኛ ቡድን ለብሄር/ብሔረሰብ መብት በ‹መታገል› ይታወቅ እንጂ፣ ሥልጣን በያዘባቸው የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች እንደታየው፣ ይዞታዬ በሚለው ግቢ ውስጥ ያሉ ከራሱ ማኅበረሰብ ውጪ የሆኑ ንዑስ ማኅበረሰቦችን ከማክበር ይልቅ ጨፍለቆ መሰልቀጥ አለዚያም በሰበብ አስባብ እያስደነበሩ ማብረር ይቀለዋል፡፡ ብሔርተኛ ፓርቲዎች፣ ግንባሮች በመፍጠር ቢያያዙ እንኳ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ከአድማሳቸው ውጪ ነው፡፡ ብሔርተኛ ቡድኖች በቀረቡበት ምርጫ ውስጥ፣ የሐሳብ ውድድርና እሸነፍ ይሆን የሚል ውድድር አይኖርም፡፡ ይኑር ከተባለ በየብሔረሰቡ ከአንድ የበለጠ ብሔርተኛ ቡድን ማርባትን ይጠይቃል፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ዕርባታው ሲታሰብ፣ ወደ መቶ አርባ ፓርቲ እንደማለት ነው፡፡ እንደዚያም ቢሆን ውድድሩ በየብሔር ብሔረሰብ ይዞታዎች ውስጥ የተሸነሸነ ከመሆን አያመልጥም፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደራሴዎችን መምረጥ ቢመጣም፣ በየብሔር ዝምድና ከየብሔር ፓርቲ የተመረጡ ሰዎችን ከመደመር ውጪ አይሆንም፡፡ አገሪቱን በአያሌው የሸፈኑ ፓርቲዎች በግንባርነትና በአጋርነት ቢጎዳኙም ሽርካነት ከመፍጠራቸው በቀር፣ በየብሔር ፓርቲ ያገኙትን ውጤት ከመደመር ውጪ አይሆኑም፡፡ ይህንን በቅጡ ለመረዳት እንዲቻል አንድ ሰው ያለውን ላስተውስ፡፡ ሰውየው በለውጡ መጀመሪያ ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ብቅ ብሎ የነበር፡፡ ሰውየው በብሔር ፓርቲዎች መካከል የሚካሄድ ‹‹የምርጫ ውድድር›› በየማኅበረሰብ ሠፈሩ ከመሠለፍ እንደማይወጣ ለመግለጽ ‹‹ሐሳቦች የማይወዳደሩበት ምርጫ ምኑን ምርጫ ነው፣ የሕዝብ ቆጠራ እንጂ!›› ይል ነበር፡፡

አባባሉ እውነትን ቁልጭ አድርጎ ከማሳየት በላይ፣ ልብ ውስጥ ተቀብቅቦ አይረሴ የመሆን ጉልበት አለው፡፡ እኔም አስታውሼ እዚህ ጽሑፍ ላይ የተጠቀምኩበት ይህንኑ ጥንካሬውን በማስተዋል ነው፡፡ እኛም ሐሳብ ከሐሳብ የሚፎካከርበት የምርጫ ውድድር የማድረግ ታሪክ ውስጥ ለመግባት ከፈለግንና ሰዎችና መብቶቻቸው የተከበሩበት ዴሞክራሲ ለመገንባት ካቀድን ‹‹ከሕዝብ ቆጠራ›› አባዜ ለመውጣት መቁረጥ ይኖርብናል፡፡

ይህንን የቁርጥ ጉዞ ብልፅግና ፓርቲ ጀማምሮታል፣ የብሔር ቡድኖችን ቀላቅሎ አንድ ወጥ በማድረግ ዕርምጃ፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ያለበት በኅብራዊ (ወጥ) አተያይና በብሔርኛ ክፍልፍይነት መሀል ያለበት መጓተት ሊመለጥ የማይችል ትግል ነው፡፡ ያውም የተገባበት ትግል የአቅም መመጣጠን የሌለበት፣ የአምስት ዓመት ግድም ወጥ የመሆን ጥረት፣ ለ30 ዓመታት ሲደርጅ ከቆየ ብሔርተኛ አስተሳሰብና አወቃቀር ጋር የተጋጠመበት!! ይህንን አዲስ ትግል ልናግዝ የምንችለውና ብዝኃነትን የተቀበለ ወጥ አተያይ የኃይል ሚዛኑን በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክዓ ምድር ውስጥ እንዲቆጣጠር ማድረግ የሚሰምርልን በሁለት መንገድ ነው፡፡ የብሔርተኛ ቡድኖችን መሠረታዊ ችግር ተረድቶ ከብሔርተኛ ቡድንነት እየወጡና ከሌሎች ጋር እየተቀላቀሉ ወጥ ፓርቲ መመሠረት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሌላው መንገድ ደግሞ፣ ብዙኃን ዜጎች በየአካባቢው ብሔርተኛ ቡድኖችን ከመደገፍና ከመምረጥ ይልቅ የትኛውን ሐሳብ የያዘው ፓርቲ ጥቅሜን ያራምዳል ብሎ ወደ ማማረጥ መዞራቸው ነው፡፡

በመጨረሻ ላይ፣ ለሁሉም መሠረት የሆነ አንድ ነጥብ ላንሳ፡፡ ከላይ የነካካናቸው የህሊና ንቃቶቻችን ማለትም ወገንተኝነታችን፣ ኩራታችንና የህሊና ፍርዳችን (ከማኅበረሰብ እስከ አገርና አኅጉራዊ ማንነታችን ድረስ) ጭፍን እንዳይሆን መጠበቂያ ውሉ፣ ሰው መሆናችንን አለመዘንጋት ነው፡፡ ለሰው የመቆርቆር ተፈጥሯዊ ነፍሳችን የነቃ እስከሆነ ድረስ፣ በየትኛውም የማንነታችን ግቢ ውስጥ የምንወስደው የድጋፍና የቅዋሜ አቋም፣የሠለጠነ (ጥፋትን/ፍትሕ አልባነትን ለማገዝ የማይፈቅድ) የመሆን ከፍተኛ ዕድል አለው፡፡

በኢትዮጵያ ኢተንኳሽነት እየኮሩ፣ ከውስጥ መጠማመድ ለመላቀቅ መቸገር!

በኢትዮጵያ መንግሥት አካባቢም ሆነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ፣ ኢትዮጵያ ካልነኳት አለመንካቷ/የትኛውንም ጎረቤት አገር ተንኩሳ ወርራ ስላለማወቋ ተደጋግሞ ይወራል፡፡ በዚህም ታሪኳ ይኮራበታል፡፡ ይህ በጎ ታሪኳ በቅርቡ ተፈትኖም ፈተና አልፏል፡፡

ካለፈው የሰሜን ጦርነት በፊት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ያዳበረች አገር እንደነበረች ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ የሰሜኑ ቀውስ በተከፈተ ጊዜ ግን አጋጣሚውን ከኢትዮጵያ መሬት አለኝ ለሚል ይዞታ የማስፋት ወረራ ተጠቀመችበት፡፡ ኢትዮጵያ ወዲያው የአፀፋ ጦርነት ውስጥ አልገባችም፡፡ ያኔ ወደ ጦርነት ያልገባችው በውስጥ ጦርነት ተጠምዳ ስለነበረ ነው ይባል ይሆናል፤ ነገር ግን የውስጥ ጦርነቷን በሰላም ድርድር ከደመመችው በኋላ በሱዳን ላይ አልዞረችም፡፡ ሱዳን በስተኋላ በሁለት ጄኔራሎች በሚመሩ ሠራዊቶች ውጊያ በተጠመደችበት ጊዜም ብድር ልመልስ አላለችም፡፡ እንዲያውም ሱዳን ከውስጥ ጦርነት ወጥታ ሰላም እንድታገኝ ከጣሩትና አሁንም እየጣሩ ካሉት አገሮች አንዷ ነች፡፡ ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ወይም የመሬት ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ መፈለግ፣ ዛሬም ፅኑ አቋሟ ነው፡፡

በኢትዮጵያ አሁናዊ የውስጥ ሰላም ችግሮች ውስጥ ከርቀት ሥውር እጃቸውን የሰደዱ ነገር ሠሪዎች ዛሬም አይታጡ ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነት ነገረኝነት ኢትዮጵያ በቀላሉ ተበግራ ዘራፍ እንደማትል ግን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ብልህ ዲፕሎማሲዋ እንደተጠበቀ፣ የውስጥ የሰላም ችግሮቿን በውስጣዊ ምክክር/ድርድር እየፈታች ከውጭ ሥውር እጆች ታላቅቃለች ብለንም እንጠብቃለን፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ኢትዮጵያ ከወደብ አልባነትና ከቀይ ባህር ከመገለሏ ጋር ስለተያያዘ ጉዳቷ በማንሳቷ፣ የመስፋፋት ጦርነት እየጎሰመች ስለመሆኗ የተፈጠረው ጫጫታ ሁሉ፣ ኢትዮጵያን የማይገልጽ ነውና መክሰሙ የማይቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ስትራቴጂያዊ ጥቅም፣ በቀጣናዊ የጋራ ጥቅምና የልማት ትስስር ማዕቀፍ ውስጥ ታሳካለች ብለንም እናምናለን፡፡ የዚህ ስኬት ዕውን መሆንም በኩራታችን ላይ ኩራት ይጨምራል፡፡

ከጎረቤት አገሮች ጋር ኢትዮጵያ ያላት መስተጋብር ይህንን ያህል አዎንታዊ ሚና ያለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጎቤቶቿ ጋር ሮጦ ፀብ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ዝምድናና አጋርነት የሚበልጥባት መሆኗንም ታጋሽነቷና የወዳጅ አክብሮቷ እየመሰከረ ነው፡፡ በውጭ ግንኙነት ላይ ይህንን መሳይ አቅም እያለን፣ የውስጥ ሰላምን በማሳካት ላይ እንደምን አቅም አጣን? የውጭ ኃይሎች ሥውር እጅ ኖረም አልኖረም፣ የውስጥ ድክመታችንን አውቀን ለመወጣት ከፈለግን፣ በተቀዳሚ ራሳችንን ተጠያቂ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይገባናል፡፡ ሰበባ ሰበብ ማብዛቱንና አላካኪነቱን ትተን ከሃይማኖት ልሂቃን እስከ ፖለቲካ ልሂቃንና ምሁራን ድረስ አንድ ላይ ተንቀሳቅሰን ለሰላም ዕጦታችን መፍትሔ ለማግኘት ብንቆርጥ፣ መላ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብን ከእኛ ጎን የሚያሠልፍ መፍትሔ እንቸገራለን? ልሂቃን አንድ ላይ ሆነንና ሕዝብን ይዘንስ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ይሳነናል?

በዚህ ጥያቄ ፊት ቆመን ራሳችንን ከመረመርን፣ ዋናው የሰላም ችግር ያለው በእኛው ውስጥ መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ እውነቱን ለማመን ዝግጁ ከሆንንም፣ ዋናው ችግራችን ከእኛ ልሂቃዊ ሽኩቻና መገናተር ይልቅ፣ ከእኛ ፖለቲካዊ ሥሌቶች ይልቅ የሕዝቦች ሰላም መብለጡን አለመቀበላችን ነው፡፡ ሕዝብና አገር ቢበልጥብንማ ኖሮ የሕዝብ ስቃይና ሰቆቃ ሁላችንንም ባብሰከሰከን ነበር፡፡ ከዚህ ሁነኛ ጉዳይ የራቅሁ መስዬ፣ ቁጣና ኩርፊያ  ወደሚያጠቃው ፖለቲካ ነክ የ‹‹ውይይት›› ልማዳችን ልምጣ፡፡ በዚህ ረገድ ያለብንን ገመና ለመረዳት ልሂቃን ሩቅ መሄድ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በየፊናችን በምናደርገው ‹‹ጭውውት›› ውስጥ ከእኛ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ካለው ሰው ጋር ካልሆነ በቀር ተቃራኒ ሐሳብ ሲገጥመን እንዴት እንደምንወራጭ መታዘብ ይበቃናል፡፡ እኔ ራሴ ከማቃቸው ትምህርት ቀመሶች ጋር ሐሳብ ‹‹ስንለዋወጥ›› የሐሳብ ልውውጣችንን በምክንያትና በመረጃ ማሳደግ ከባድ ፈተናችን ነው፡፡ ምክንያቱም ሐሳብን እያፋተጉ የሐሳብ ልውውጡ እንዲያድግ በማድረግ የጋራ ሥራ ውስጥ የመቆየቱ ነገር፣ ዓሳን ከእነ ነፍሱ ይዞ እፍኝ ውስጥ ለማቆየት እንደመሞከር ያስቸግረናል፤ አንዳችን ወይ ሌላችን ተሙለጭልጨን እንወጣና ፈር እናስታለን፡፡ ውይይታችንም ባለበት ሂያጅ ሆኖ ያርፋል፡፡

ለዚህ ችግር ልዩ ልዩ ምክንያቶች ልንደርድር እንችል ይሆናል፡፡ የተለየ ሐሳብን የሚጠቅም ነገር አገኝበታለሁ በሚል ክፍት አዕምሮ ለመስማት አለመፍቀድ፣ ሰውን በትንሽ ፍንጭ የሆነ አቋም ውስጥ ፈርጆ ገና ከመነሻው ውይይትን ጭፍን የግጥሚያ ሜዳ ማድረግ፣ የሐሳብ ስንቅ ማነስ፣ የራስን ሐሳብ ለራስና ለሌላው በማሰማት ፍላጎት ውስጥ ታጥሮ መሽከርከር፣ ሁሉም ወገን አትራፊ የሆነበት የውይይት ልምድ ማጣት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ከየግል ልምዶቻችን ባሻገር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚቀርበው የ‹ሻይ ቡና› መድረክም ገመናችንን የመመልከቻ ጥሩ ሥፍራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በዛሬ የአገራችን እውነታ ውስጥ ቆመን፣ በ‹ሻይ ቡና› መድረክ ላይ ‹‹ሰላም በአገራችን ውስጥ አለ የለም? አንፃራዊ ሰላም አለ የለም? ወዘተ፣ ወዘተ.›› እየተባለ የተደረገውን መጓተትና ልሂቃዊ ‹‹መራቀቅ›› ካስተዋልን፣ ተሳታፊዎቹን በጊዜው ጨምድዶ የያዛቸው ዋና ጉዳይ፣ ሰላምን እንዴት እንጨብጠው የሚል ጥያቄ እንዳልነበር ይገባናል፡፡

አዘጋጁ ሰለሞን ሹምዬ ‹‹የአገራዊ መግባባት ጉዳይ የኮሚሽኑ ብቻ አይደለም፤ እኛም የበኩላችንን ማዋጣት አለብን›› በሚል መሠረተ ሐሳብ ተሳታፊዎች የጋራ መግባባት የሚሹ ብለው ያሙኑባቸውን ጉዳዮች እንዲያስመዘግቡ ከቅርብ ጊዜ በፊት መድረክ ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የታየው ከርዕሰ ጉዳይ የወጣ መባዘን ጆሮ ግንድ የሚያስይዝ ሌላ የገመና ማሳያ ነበር፡፡ ልብ በሉ! የሚያሟግት ጉዳይ ተዘርግቶ በክርክር ተነኮሰከኝ/ጎነጥከኝ የሚሉ ጣጣ በሌለበት፣ ርዕሰ ጉዳዮችን የማዋጣት ሥራን መወጣት ነበር ችግር የሆነው! አንዱ አገራዊ መግባባት ሊደረስ መቻሉን ስለመጠራጠሩ አውርቶ ሲያቆም፣ ሌላው ሌላ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ያትታል፡፡ አወያዩ ታግሶ ሰምቶ አንደገና ዋና ጉዳዩ አጀንዳ ማስያዝ መሆኑን ቢያተውስም፣ መናገር የተፈቀደለት ሰው በዚህ በዚያ ብሎ ሌላ ነገር ሲያወራ ይገኛል፡፡ እኔ በ‹ዩቲዩብ› በተከታተልኩ፣ ቪዲዮ ላይ ያለ ወለም ዘለምታ ነጥቦቻቸውን አንድ ሁለት ብለው ያስያዙ ሰዎች ከአንዱ አራት መብለጣቸውን እጠራጠራለሁ፡፡

በአዎንታዊ ግርምት ያስደመመኝን ሌላ ገጠመኝ ደግሞ ላንሳ፡፡ ምናገኝበት ይሆን በሚል ስሜት ‹አንደበት› የሚል የዝግጅት መጠሪያ ያለውን አንድ ቃለ መጠይቃዊ ሥራ ተከታተልኩ፡፡ የዝግጅቱ እንግዳ ዶ/ር ደቻሳ አበበ የሚባሉ የታሪክ ባለሙያ ነበሩ፡፡ (በነገራችን ላይ ዕድሉ ያላችሁ ሁሉ ‹በዩቲዩብ› የእኚህን ሰው ቃለ መጠይቅ እንድትከታተሉት እመክራለሁ፡፡) ሰውዬው ለመግባባት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችን ከመናገራቸው ባሻገር፣ አጠገባቸው ሌሎች ተወያይ ሰዎች ባልነበሩበት ሁኔታ ውስጥ፣ ንግግራቸው ሊደርሰው የሚችልን የርቀት ሰው ሁሉ ባሰበ ልቦና፣ ጎንታይ ነገር ከአንደበታቸው እንዳይወጣ በቃላት አመራረጥና በሐሳብ አመራረጥ ያደርጉ የነበረው ጥንቃቄ፣ ጥንቃቄ ለማያውቀንና በሾርኒ ወጋ ማድረግ ጉብዝና ለሚመስለን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነበር፣ መማር ለፈቀደ፡፡

ወደ ጀመርኩት ነጥብ አሁን ልመለስ፡፡ ሾርኒም ይጣፍጠን፤ አሁን የሚታዩብን ርዕስ ጠብቆ የመወያየት ችግሮችም እንዳሉ ከእኛው ጋር ይሁኑ፡፡ የሰላም ዕጦትና ሰላምን እንዴት እናምጣው የሚል ጥያቄ ሁላችንንም የሚያንቆራጥጥ የሆድ ቁርጠታችን ቢሆን፣ በውይይት አካሄድ ላይ አሉ የሚባሉ ችግሮችን አልፈን ተደማምጦና በሐሳብ ተጋግዞ መፍትሔ ማበጀትና አንድ ላይ መሥራት ያቅተናል? በበኩሌ አፌን ሞልቼ ፈፅሞ አያቅተንም እላለሁ፡፡ ዋና እንቅፋት የሆነብን፣ ሌላ ሌላ ሥሌቶቻችንንና ፍላጎቶቻችንን ከሰላም ጉዳይ ማብለጣችን ነው የምለውም ለዚህ ነው፡፡

ስለፍልስጤሞች ትግል ህዳሴ

የፍልስጤሞች ትግል ከመካከለኛው ምሥራቅ መረጋጋት ጋር የሚግባባ አዲስ ዕይታ፣ አዲስ የትግል፣ ሥልትና አዲስ ድምፅ ይፈልጋል፡፡

ይህንን መሰሉን ድምዳሜ የማይገፋ የሚያደርገው እስካሁን ትግሉን እንመራለን በሚሉት ቡድኖች በተለይም በሐማስና በአሸባሪነት በተፈረጀ የትግል ሥልቱ፣ የፍልስጤሞች ጥያቄና ሕዝቡ ይበልጥ እየተጎዱ፣ የትግላቸው ግብ ከዓይናቸው እየራቀ፣ የመሬት ይዞታቸው እያነሰ፣ ተሰሚነታቸው እየደከመ ደጋፊዎቻቸው እየሳሱና ይበልጥ እየተከፋፈሉ መሄዳቸው ነው፡፡

ይህ የተሰሚነትና የድጋፍ ቅዝቀዜ በሙስሊም/ዓረብ አገሮች አካባባቢም በአውሮፓ አካባቢና በቀሪው ዓለምም ያለውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፡፡ በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ ከፋም ለማም ለፍልስጤሞች በጎ አቋም የነበረው የፖለቲካ መስመር ዛሬ የሌለ ያህል ሆኗል፡፡ በአንፃሩ በየመተነኳኮሉ ዕርምጃ የእስራኤልና የአሜሪካ ኢፍትሐዊ አቋም፣ ማናለብኝ ባይነትና ቅጣት አድጓል፡፡ እንደ ማደጉም በዓለማችን የሚደርስበት ውግዘትና ተቃውሞ አብሮ አልሰፋም፣ አላደገም፡፡ ከመቃወም ይበልጥ ባይተዋርነትን የመረጡት/ ቅር ቢሰኙም ከግልምጫና ከመጠመድ ለመራቅ ዝም የሚሉት አገረ መንግሥታት በርክተዋል፡፡ ይህ ግንዛቤ፣ በሌጣ ማስተዋል ደረጃ ብዙ ሰው ሊጋራው የሚችል ግንዛቤ ይመስለኛል፡፡

በአሁኑ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሐማስ ተንኩሶ ያስጀመረውን መራራ የእስራኤል ጥቃት በመቃወም ረገድ በዓረብ አገሮች አካባቢና ከዚያ ውጪ ባሉ አገሮችም ሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እያደር የጨመረው ተቆርቋሪነት፣ የዝምታና የቸልታ ጊዜ መለወጥ መጀማመሩን የሚናገር ሳይሆን፣ ፍልስጤሞች ላይ ከጨቅሎች እስከ አረጋውያን በአጭር ጊዜ የደረሰው የሟቾች፣ የቁስለኞችና የተፈናቃዮች ብዛት፣ እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው መደረማመስ ህሊና ከሚታገሰው በላይ ሆኖ በውድም በግድ አውጋዦች እንዲበዙ በማድረጉ ነው፡፡

እንደዚያም ሆኖ፣ በእስራኤል-አሜሪካ-አውሮፓ ኅብረት አሸባሪ የሚባለው ሐማስ ሕዝብን ጋሻ በማድረግና ለወታደራዊ ምሽግነት መዋል የማይገባቸውን ሲቪል ተቋማት በመጠቀም መታማቱ ለአሜሪካና ለእስራኤል የጨከነ ቅጣት ጥሩ ማማሃኛ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የፍልስጤሞች ጥቃትና ጉዳት ወሰን እንዲያጣ አድርጓል፡፡ አልፎም፣ በእስራኤልና በአሜሪካ ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ላይ ሊንር ይችል የነበረውን ውግዘት ብዙ አጉድሏል፡፡ በዚህ የአጉዳይነት ሚና ውስጥ የየመን ሁቲዎችና የሂዝቦላህ ጀብደኞችም አስተዋፅኦ አለበት፡፡

ሐማስ፣ አል ሽፋ ሆስፒታልን በሥውር ስለመጠቀሙ የማያጠራጥር ማስረጃ አልቀረበም፡፡ ወደ ተደረመሰው ሆስፒታል ገብተው እንዲያዩ ከተፈቀደላቸው የጋዜጠኛ ቡድኖች አንዱ የነበረው ቢቢሲ ራሱ አስተማማኝ መረጃ መስጠት አልቻለም፡፡ ሐሰት ስለመሆኑም በአጥጋቢ መረጃ ያጋለጠ እስካሁን የለም፡፡ ሐሜቱ እውነት ሆነም አልሆነ፣ እስከዛሬ ባለን ልምድ የ‹ነፃ አውጪ› ባህርይ ያለው ቡድን ለዚህ ዓይነት ሐሜት ምቹ መሆኑ (ሕዝብን ጋሻ ከማድረግና ለወታደራዊ ሥራና ምሽግነት ፈፅሞ መዋል የለባቸውም የሚባሉ ሥፍራዎችን በሚስጥር ከመጠቀም እንደማይፀዳ፣ ያለ መፅዳቱም ምክንያት አጥቂውን በሕዝብና በዓለም ዘንድ የማስወገዝ ግብና ለገዛ ደኅንነትም በቀላሉ የማይደፈር መደበቂያ መፈለግ ሊሆን እንደሚችል) ይታወቃል፡፡

የፍልስጤሞች የጋዛ ሰርጥና የ‹ዌስት ባንክ› ኑሮ እንቆቅልሻዊ (ከ‹አይ› እና ከ‹አዎ› የተሠራ) ነው፡፡ ሁለቱ ሥፍራዎች ዕውቅና ያላቸው የፍልስጤማውያን ይዞታ የመምሰላቸውን ያህል፣ በአየርም በየብስም ነፃ ህልውናቸው ያልተረጋገጠ (በእስራኤል መዳፍ ውስጥ ያሉ/በተለያየ ሰበብ የሚደፈሩ) ናቸው፡፡ እስራኤልን እንደ አገረ መንግሥት ለማወቅ አንድም ቀዳዳ የሌላቸው እንደ ሐማስ ያሉ ቡድኖችም ለእስራኤል ተኝተውላት አያውቁም፡፡ የጋዛና የዌስት ባንክ አስተዳደር ከፍልስጤሞች ነፃ አገረ መንግሥትነት ጋር ገና ያልተገጣጠመ መሆኑም የእነ ሐማስን መንግሥትነት ከነፃ አውጪነት ባህርይ ጋር እንዲዳበል አድርጎታል፡፡ ይህ ደባል ባህርይ እስከቀጠለ ድረስም የፍልስጤሞች ኑሮና ይዞታ የተረጋጋ አይሆንም፡፡ እንደ ሐማስ ያሉ ቡድኖች መንግሥት እየመሩም ቢሆን ሕዝብና ሲቪል ተቋማት ውስጥ በሚሹለከለክ የትግል ሥልት መታማታቸውና ለእስራኤል-አሜሪካ መረን የወጣ ጥቃት ማሳበቢያ መሆናቸው ይቀጥላል፡፡

ይሁን እንጂ፣ በአሜሪካ የሚታገዘው የእስራኤል ጥቃት ማሳበቢያ ስላገኘ፣ ሆስፒታልንና ቤተ እምነትን ለወታደራዊ ተግባር እነ ሐማስ ስለማዋላቸው የማያወላዳ ማስረጃ ቢገኝ እንኳ፣ እስራኤል በሲቪሎች ሕይወትና ኑሮ ላይ በጋዛና ከጋዛ ውጪ እያደረሰች የቆየችው ልክ ያጣ ቅጣት የግፍ ደረጃው አይቀልም፡፡ አሁን የአሜሪካን አባሪነት ይዛ እስራኤል ያካሄደችው መጠነ ሰፊ ጥቃት የሀማስን የማጥቃት ኃይል ከማጠናቀቅ ባሻገር፣ የፍልስጤሞችን ትግል ተስፋ ወደ ቆረጠ የመጨረሻ አቅመ ቢስነት ደረጃ የማውረድም ድርብ ዓላማ ያለው ይመስላል፡፡ አሜሪካ የበላይ የሆነችበት ሥርዓት እስከቀጠለ ድረስም፣ አሁን ያለውን የትግል ሥልት ለመደቆስ የማያቅማማው በትር የሚረግብ አይመስልም፡፡ የአሜሪካን የበላይነት የሚገዳደርና የፍልስጤሞችን በደል ለማዳመጥ የተሻለ ጆሮ ያለው የኃይል ሚዛን በቅርብ ስለመፈጠሩም እርግጠኛ ለመሆን አይቻልም፡፡

እንዲያውም፣ ፍልስጤሞች እየገረረ ከመጣው የጥቃት አዙሪት እንዲወጡና የአሜሪካን ጉልበተኛነት የሚገዳደር/የሚቃረን ሌላ ልዕለ ኃያላዊ ጎራ የመውጣቱ ሒደት እንዲፋጠን ከተፈለገ፣ የፍልስጤሞች አቋምና ትግል ያለመሳቀቅ የብዙ አገሮችንና የዓለም አያሌ ሕዝቦችን ድጋፍ ሊያገኝ የሚችልበትን አዲስ ትርታ መጨበጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ትርታ የእስራኤልን ህልውና ከማወቅ ጋር የፍልስጤሞችን የነፃ ህልውናና የይዞታ ጥያቄዎች አዛምዶና አቻችሎ በሚያመጣና የጠላትነትና የመጠቃቃት ታሪክን በሚደመድም ድርድርና ዕርቅ መካከለኛው ምሥራቅ ተከባብሮ የሚኖርበትን ግብ ከመፈለግ መስመር የራቀ አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት መስመር ያለው የፍልስጤሞች የእንቅስቃሴ ድምፅ (በተለይ የሶሪያን፣ የሊባነን-ሂዝቦላህንና የኢራንን ድጋፍ ይዞ) ዓለም ላይ ብቅ ቢል፣ አገሮች ከትንሽ እስከ ትልቅ (‹ብሪክስ›ን ጨምሮ) በሰፊውና በአዲስ ንቃት የሚደግፉት፣ ችግሮችን በፍትሐዊነት ለዘለቄታ የመፍታት ዓለማዊ ልቦና ካሸለበበት የሚነቃ ይመስለኛል፡፡

ይህንን መሰል የአቋም ለውጥ ጋዛና ዌስት ባንክ ውስጥ ከሚደረግ የቡድኖች/የብዙኃን ይፋ ስብሰባ ይገኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጣ ዕርዳታንና መሣሪያን ተቆጣጥሮ መኖርን የለመዱና ከቀጣናው መደማማት የሚያተርፉ ኃይሎች እንዲህ ያለውን ድምፅ  ‹‹የፍልስጤሞችን ትግል የካደ/ለእስራኤል የተንበረከከ አቋም›› እያሉ ከመቅጨት እንደማይመለሱ ይገመታል፡፡ እናም፣ የዚህ ዓይነቱ የትግል ሐሳብ ምሁራዊ አቅም ካላቸው የፍልስጤሞች ተቆርቋሪዎች አካባቢ፣ የፍልስጤሞች የእስከ ዛሬ ትግል የተጓዘበትን ታሪክ ከእነ ትርፍና ኪሳራው ብትንትን አድርጎ ባቀረበ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ቢመጣ፣ በፍልስጤሞች ዘንድ አዲስ የትግል ጥንስስ  እንዲፈጠር ጥሩና ፈጣን መንደርደሪያ የመሆን ዕድል ሳይኖረው አይቀርም፡፡ እነ ሊባነን፣ ሶሪያና ኢራንም የፍልስጤሞችንና የራሳቸውን ፈርጀ ብዙ ጥቅም  የሚያስተውሉ ከሆነ፣ የዚህ ዓይነቱን እንቅስቃሴ መፈጠርና መጎልበት እንዲያግዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአዲሱ ድምፅ ላይ እነሱም ከተጨመሩበት፣ የአሜሪካ መከታ ያላት እስራኤል ቀይ መስመር አበጅታ ጥቅም በማቻቻል ላይ ገታራ ብትሆን እንኳ፣ ከእነ መከታዋ ብዙ የድጋፍ መራቆት ፈተና ይገጥማታል፡፡ ይህም እየዋለ ሲያድር ከበድ ያለ ጫና እየወለደ መምጣቱ አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...