Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉእዚያ ድሮን... እዚህ ድሮን...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

ቀን:

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር)

ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ

“በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ ዱቄት ሆኗል” ሲባል፣ “የለም አፈር ልሼ ተነሳሁ” ብሎ እንደ አዲስ ተደራጅቶ መቀሌን በእጁ ያስገባው የትግራይ መከላከያ ኃይል (ቲዲኤፍ) ጦር ተፈጽሞብኛል ባለው ግድያ፣ ጥቃትና ዝርፊያ ሳቢያ “ሒሳብ ለማወራረድ” አጎራባች ክልሎችን ጥሶ ለመግባት ፋታ አልፈጀበትም።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቲዲኤፍን ሱናሚ ሊያመክነውም ሆነ ሊገዳደረው እንደማይችል እርግጠኛ የነበሩት የትግራይ ኃይሎችና ደጋፊዎቻቸው ብቻ አልነበሩም። አጥብቀው የሚኮንኗቸው ተንታኞችም ነበሩበት። የአፄ ኃይለ ሥላሴና የኮሎኔል መንግሥቱ ጦሮችን የሽንፈት አጋጣሚ እየመዘዙ፣ ከደሴና ኮምቦልቻ ስትራቴጂካዊ ከተሞች መያዝ በኋላ አማፂዎቹ አራት ኪሎን ለመቆጣጠር አንዳች ምድራዊ ኃይል እንደማያግዳቸው ተንብየዋል። ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ “የኃይል ሚዛኑ በእጃችን ስለሆነ አዲስ አበባን በቅርብ ጊዜ እንቆጣጠራለን”፣ “ጦርነቱ አልቋል”፣ ወዘተ ማለታቸው የድል አድራጊነታቸው ባሮሜትር ጣራ መንካቱን አመላካች ነበር።

የቲዲኤፍ ሠራዊት የሚቆጣጠራቸውን መሬቶች ባሰፋ ቁጥር በምርኮ እጁ የሚገባው የመሣሪያ ብዛትና ግዝፈት በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ ሄዶ የውጊያ ብቃቱም እየጎለበተ ሄዷል። ሆኖም ሠራዊቱ ከተሞችን ሲቆጣጠር የሚተገብረው የጦርነት አያያዝ (Rules of Engagement) ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት በ1980ዎቹ በሥፍራው ላይ ተግብሮት ከነበረው ፍፁም የተፃረረ ነበረ። እንደ ቀድሞው ለሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሕዝብና ንብረት ትህትናና ክብካቤ በማሳየት ደጋፊውን ለማስደሰትም ሆነ ለማበራከት አልተጨነቀም። ይልቁንም በዓለማችን የሚወገዘውንና ስኮርችድ ኧርዝ (Scorched-Earth Policy) የሚባለውን “ምሕረት የለሽ የጦርነት ሥልት” መተግበሩን የሚያሳዩ ድርጊቶች ተስተዋሉ። የግድያየአስገድዶ መድፈር፣ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን የመዝረፍና የማውደም ዜናዎችና ሪፖርቶች ይጎርፉ ጀመር። መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱ እንደማያስቆማቸው ተረድቶ ሕዝቡ ከመከላከያ ጎን ተሠልፎ ቲዲኤፍን እንዲፋለምና የሚማርከውን መሣሪያ ሁሉ ለግሉ እንዲጠቀም ጥሪ አቀረበ። ይህ ጥሪ ከሕዝቡ ምሬት ጋር ተዳምሮ የአማራ ፋኖና ሚሊሻ ተጋድሎን አጎለበተው። ቲዲኤፍ ሰሜን ሸዋ ሲደርስ እንቢተኝነቱ ወደ ላቀ ደረጃ ለመዳረሱ የእሸቴ ሞገስ ተጋድሎ አንዱ ማሳያ ነው።

ቲዲኤፍ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ሲጠጋ “ጌም ኦቨር” እንዲሉ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ድሉ አይቀሬ ሆኖ ተናኘ። አዲስ አበባ የሚገኙ ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች መስጋታችው ሊሸሽጉ አልቻሉም። በርካቶቹ ከ“ዳግማዊ ግንቦት ሃያ” ክስተት አስቀድመው ሠራተኞቻቸውን ወደ ጎረቤት አገሮች አሸሹ። ዋናው ማምለጥ ነው፣ ለጨርቅና ማቁ ኋላ ይታሰብለታል! 

ይህ በእንዲህ እያለ ድንገት ሌላ ተጨማሪ ተዓምር ተከስቶ የጦርነቱ ማዕበል አቅጣጫ በቅፅበት በ180 ዲግሪ ተቀለበሰ። ቲዲኤፍ በደቡብ አቅጣጫ የመጣበትን ፍጥነት አሻሽሎ በሰሜን አቅጣጫ ወደ ትግራይ ክልል አፈገፈገ። ለአንዳንድ የአማፂያኑ ደጋፊና ተንታኞች ሁኔታውን አምኖ ለመቀበል ተሳናቸው። “በአሜሪካ ትዕዛዝ መሠረት አማፂያኑ ተመለሱ” ብለው ሊያስተባብሉ ሞከሩ። መሬት ላይ የነበረው ሁኔታና የዓለም አቀፍ ሚዲያ “miraculous turnaround” ብለው የገለጹት ክስተት ግን ሌላ ነበር።

የቁርጥ ቀን ደራሿ አቡዳቢ

ከጦርነቱ የአቅጣጫ ቅልበሳ ቀደም ብሎ በቲዲኤፍ ቅፅበታዊ ጉዞ እንቅልፍ ካጡት መሀል ወዳጅ” የአቡዳቢ ባለሥልጣናት ይገኙበታል። የመዲናዋን ዕጣ ፈንታም ሆነ የዶ/ር ዓብይን ሕይወት ለመታደግ ከአየር ኃይላቸው ግምጃ ቤት ክምችት ላይ ቆንጥረው ስድስት ድሮኖችን ከሠለጠነ ባለሙያ ጋር አክለው በወሳኝ ሰዓት አደረሱ። 

ልክ እንደ ወቃማው ንስር ብቸኛ አዳኝ (Solitary Predator) ሆነው ድሮኖቹ የጦር ቀጣናውን ሰማይ ያለከልካይ ተቆጣጠሩት። በውጤቱም የኃይል ሚዛኑን አዛብተው የተጠበቀው ቀርቶ ያልተጠበቀው ተከሰተ። ጄኔራል ፃድቃን ለኒውዮርክ ታይምስ ሲናገሩ በአንድ ጊዜ እስከ አሥር ድሮኖች በሰማዩ ላይ ያንዣብቡ እንደነበር ገለጹ። ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ደግሞ የቲዲኤፍ ግብዓት አቅርቦት (Logistics) ለድሮን ጥቃት ተጋልጦ ከባድ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ይፋ አደረጉ። የአማራ ኃይሎች በዚህ ውጊያ ዕጣ ፈንታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሳይዘነጋ ይህ ጽሑፍ ያተኮረው ግን በድሮኖቹ ዙሪያ ነው።

እዚህ ላይ አንድ የተድበሰበሰ ጉዳይም ነበረ። የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀሌን እንደተቆጣጠረ ለፓርላማም ሆነ ለሚዲያ ድሮን የትግራይ ኃይሎችን ለመበታተን ጥቅም ስለመዋሉ ተገልጾ ነበር። ቆይቶ ጄኔራል ፃድቃንም ከተምቤን በረሃ ከዓረብ አገሮች መጣ ባሉት ድሮን የጦርነት ዳይናሚክሱ እንደተቀየረ መስክረው ነበር። ታዲያ ከዚያ በኋላ ቲዲኤፍ መቀሌን ሲቆጣጠርም ሆነ አልፎ ተርፎ ደብረ ብርሃን አካባቢ እስኪደርስ “ድሮኖቹ የት ገቡ?” ያስብላል። የድሮን ዜና በሚዲያ ላይ በድጋሚ ሕይወት የዘራው ቲዲኤፍ ወደ አዲስ አበባ ከተቃረበ በኋላ ነው።

ታዲያ ቀድሞ የነበሩን ድሮኖች በኢትዮጵያ አልነበሩም ማለት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሆንና ምናልባትም ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው መረጃ ሕወሓት ያቀረበው ክስ ነው። ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው በኅዳር 2013 ዓ.ም. ባሠፈሩት ጽሑፍ፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ አውዳሚ ጦርነት ለማካሄድ ዓብይ (ዶ/ር) አሰብ አየር ቤዝ ከሚገኘው የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ድሮኖች ድጋፍ እንደተጠቀመ ገልጸዋል። በጉዳዩ ጥልቅ ምርመራ ያደረጉ መረጃዎች በደረሱበት ድምዳሜ የሕወሓት ክስ ፍፁም አሳማኝ ነው ማለት ባይቻልም፣ አሰብ የአየር ቤዝ ላይ የተገኘው የሳተላይት መረጃ ክሱ እውነትነት ሊኖረው እንደሚችል አመላካች ነው።

ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል

ተዋጊ ድሮን የኃይል ሚዛንን ያዛባው በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደ ዓውደ ውጊያ ብቻ አይደለም። በሌሎች በርካታ አገሮችም ተተግብሯል። በ1986 ዓ.ም. የሞቃዲሾው የ“ብላክ ሃውክ ዳውን” ክስተት የአሜሪካ መንግሥት 18 ወታደሮቹንና ሁለት ሔሊኮፕተሮቹን በጄኔራል አይዲድ ተዋጊዎች አስበልቶ በወቅቱ ትልቅ ውርደት ተከናንቦ ነበር። ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ተዋጊ ድሮኖችን በመጠቀሙ የኃይል ሚዛኑን ቀየረ። ጂቡቲ ላይ ተቀምጦ የአልሸባብ አባላትን፣ መጓጓዣና ካምፖችን ያላንዳች ገደብ ሶማሌ ውስጥ ተመላልሶ እየገባ በድሮን መረጃ ይሰበስባል፣ ጥቃት ይሰነዝራል

የዩክሬይንና የሩሲያን ጦርነትን ማንሳት ይቻላል። ሩሲያ በ2014 ዓ.ም. ዩክሬይንን ስትወር ጦርነቱን በአሥር ቀናት ለመፈጸም አቅዳ ነበር። ጦርነቱ እንደተጀመረም በርካታ የዩክሬይን ግዛቶችን በቀላሉ ያዘች። ዳሩ ግን የዩይክሬይን መንግሥት፣ ተቋማትና የተቆጩ ዜጎቿ የድሮንን ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመስክ ላይ አበለፀጉት። ድሮኖቹ ወታደራዊ ይዞታን ብቻ አልነበረም ያጠቁት። ወደ ሩሲያ ዕምብርት ዘልቀው እየገቡ የነዳጅ ማጣሪያዎችን፣ ዴፖዎችን፣ ቢዝነስ ሴንተሮችን አጋይተዋል። በውጤቱም የሩሲያን አርሚ ውርደት ውስጥ ከተውት የውጊያ ሞራሉን አንኮታኩተውታል። ዩክሬይን ዓምና ብቻ ከ10,000 በላይ የድሮን አርበኞችን አሠልጥናለች። ከሁለት መቶ በላይ ካምፓኒዎቿ ደግሞ ድሮኖችን በማምረት ላይ እንደተጠመዱ ዘ ኢኮኖሚስት ዘግቧል። 

የአዘርባጃንና የአርሜኒያ ጦርነት ሌላው ሰሞነኛ ዜና ነው። ሁለቱም አገሮች የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አካላት ነበሩ። ሆኖም ግን ሶቪየት ኅብረት በፈራረሰችበት ወቅት አርሜኒያ የአዘባጃን ግዛት የነበረውን ናጋርኖ ካራባህ በጉልበት ቀማች። በመስከረም ወር አዘርባጃን ቱርክ ሠራሽ ድሮኖችን ተጠቅማ የኃይል ሚዛኗን በመቀየር ከ29 ዓመታት በኋላ ግዛቷን አስመልሳለች። 

ድሮን የዓውደ ውጊያ ዕጣ ፈንታን የቀየረው የመንግሥታትን ብቻ አይደለም። ለምሳሌ የሃማስ ቡድን አለ። በጥቅምት መግቢያ በወታደራዊ ቁመናዋ ከፍተኛ በሆነችው እስራኤል ላይ በድንገት ድምበሯን ጥሶ በመግባት 1,400 ገደማ ዜጎችን ሲገድልና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጋዛ ለማገት ችሏል። ይህን ውጤት ለማሳካት ከተጠቀመባቸው መንገዶች አንዱ በድሮኖች አማካይነት በድንበር ላይ የተተከሉትን ካሜራዎችና የመገናኛ አውታሮች በማምከን ነበር።

ሚስጥራዊነቱን ያጣው የድሮኖቹ ሚስጥር

የኢትዮጵያ መንግሥት ተዋጊ ድሮኖች መጠቀሙን ይፋ ቢያደርግም የድሮኖቹን ብዛት፣ ዓይነትና ሥሪት ሚስጥር ለማድረግ ሞክሯል። ሆኖም የውጭ ሚዲያዎች ይህን ሚስጥር ለማወቅ አልተቸገሩም። ድሮኖቹ የተፈበረኩት በቱርክ፣ ኢራንና ቻይና እንደሆነ፣ ለድሮኖቹ የማቴሪያል፣ የሰው ኃይልና የገንዘብ ድጋፍ ደግሞ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እንደተገኘ ይፋ አድርገዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የተዋጊ ድሮኖች መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በሐረር ሜዳ (ቢሾፍቱ)፣ ባህር ዳር፣ ሰመራ፣ አሶሳ መሆናቸውን አሳውቀዋል። 

የሚገርመው ነገር ዋናው የመረጃቸው ምንጫቸው ዝርክርክ የመንግሥት የመረጃ አያያዝ ነበር። በሶሻል ሚዲያ ይፋ የተደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፋር ድሮን መቆጣጠሪያ ጉብኝት ፎቶዎች በሙያው ለተካኑ ተንታኞች ተዝቆ የማያልቅ የመረጃ ፍንጭ “Treasure-Trove of Information” ዘርግፏል። ኮምፒዩተሮቹ ሰሌዳ ላይ የታየው ሎጎ፣ የሶፍትዌር ዓይነት፣ በምልክቶች መሀል ያለው ርቀትና ጥበት፣ ወዘተ. ከድሮን አምራች አገሮች ከተገኙ ፎቶዎች ጋር ተመሳክሮ የሥሪታቸውን ፍንጮች ለመለየት ሞክረዋል። ከተጠርጣሪ ድሮን አምራች አገሮች የሚደረጉ በረራዎችንና የካርጎ ብዛትና ድግግሞሽን ከድሮኖቹ እንቅስቃሴ ጋር እያመሳከሩ መረጃዎቻቸውን አደርጅተዋል። ሌላው ይቅርና በትግራይ ክልል ከሚከሰት የድሮን ጥቃት ሥፍራ ርቀትን በማሥላት በየትኛው የድሮን መቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ ምን ዓይነት ድሮን እንዳለ ተናግረዋል። በተጨማሪ ትግራይ ከሚገኙ የዕርዳታ ሠራተኞች ጋርም እጅና ጓንት ሆነው ሠርተዋል። ከድሮን የተተኮሱትን ቅሪተ አካላት ፎቶዎችን እየሰበሰቡ ለምርመራ እንዲያግዝ (Debris Analysis) ይልኩላቸው ነበር። 

ያፈጠጠ ሁሉ አያይም

ለመደበኛ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ከሰመራ የተለቀቁት ፎቶዎች የሚሰጡት መረጃ ውሱን ነው። በሙያው ለተካነ ደግሞ አንድ ፎቶ አንድ ሺሕ ቃላት ያፈልቃል። በተለይም በስማርት ስልኮች የሚነሱ ፎቶዎች ጠቃሚ አባሪ መረጃዎችን (ሜታ ዳታ) ይይዛሉ። ዋንኛው መረጃ የጂኦ ሎኬሽን (ፎቶው የተነሳበት ኮኦርዲኔት) በመሆኑ የድሮን ጣቢያው በ11.791 ላቲትዩድና በ40.991 ሎንጊቲዩድ የሚገኝ ነው ተባለ። ሥፍራው ደግሞ የሰመራ አውሮፕላን ጣቢያ መሆኑን በቀላሉ አረጋገጡ። የመረጃ አነፍናፊዎቹ በቀጣይ የሰመራ አውሮፕላን ጣቢያ እንቅስቃሴ ላይ የሳተላይት ዓይኖችን በመትከል፣ ድሮኖቹ ከቆሙበት ቦታ በጥቂት ርቀት ፈቀቅ ሲሉ እንኳ ይዘግቡ ጀመር። 

ለስለላ ተግባር ላይ የዋሉት የሳተላይት ምሥሎች መደበኛ ግርድፍ ሪዞሉሽን ያላቸው አልነበሩም። በልዩ ትዕዛዝ የሚቃኙ፣ ዋጋቸው ውድ የሆኑና የምሥል ጥራታቸው ደግሞ የላቁ ኮሜርሻል ሳተላይቶች ተረባርበዋል። ለአብነት Airbus (30 ሴንቲ ሜትር ሪዞሊዩሽን), Planet Sky Satellite (50 ሴንቲ ሜትር ሪዞሊዩሽን), MAXAE Worldview 3 (80 ሴንቲ ሜትር ሪዞሊዩሽን), European Space Image (30 ሴንቲ ሜትር ሪዞሊዩሽን) መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሳተላይቶች በቀጥታ የሚታየውን ይቅርና በሰው ዓይን የማይታየውን መረጃ ፈልቅቀው ማንበብ ይችላሉ። የኢትዮጵያ ድሮኖችን ቁመት፣ ክንፍ ርዝማኔ፣ ውጫዊ ቅርፅ፣ የታጠቁት ሚሳኤል ዓይነት፣ ወዘተ. መረጃዎችን በቀላሉ ለቅመው ከሌሎች ድሮን አምራች መረጃዎች ጋር በማስተያየት ለእውነት የቀረበ ትንበያን አካሂደዋል። 

እ.ኤ.አ. በ1997 የአሜሪካ ኮንግረስ ሪዞሊዩሽናቸው ከፍተኛ የሆኑ (ከሁለት ሜትር በታች) የሳተላይት ምሥሎች ላይ ሕጋዊ ዕገዳ (ሴንሰርሺፕ) ጥሏል። ዓላማው የአገራቸው ሴንሲቲቨ መረጃ ለጥቃት እንዳይጋለጥ ነው። ሆኖም በቴክኖሎጂው ፈጣን ዕድገት ሳቢያ እ.ኤ.አ. በ2020 የዕገዳ መጠኑን ወደ 40 ሴንቲ ሜትር አሻሽለውታል። የሚገርመው ይህ የአሜሪካ ሕግ ለእስራኤልም ከለላ መስጠቱ ነው። እስራኤሎች ጋዛን ጨምሮ አገራቸው ጥራቱ ከፍተኛ በሆነ ሳተላይት እንዲቃኝ አይሹምና። በተቃራኒው ደግሞ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ኮሜርሻል ሳተላይቶች እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ሪዞሊዩሽን ምሥልን ያለ ከልካይ ያነሳሉ፡፡ ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ይቸበችባሉ። የኮሜርሻል ሳተላይቶቹን ድርጊት ለማስቆም አቅም ባይኖር እንኳ የተለያዩ ማስመሰያ ዘዴዎችን (Camouflage) መጠቀም ይቻል ነበር። ሴንሲቲቭ ወታደራዊ መረጃዎችን ከዕይታ መከለልና ማደናገር ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ፀሐይ የሞቀው አሠራር ነበርና። 

ሚስጥርህን በጉያ ፉከራህን በአህያ

በጦርነት ወቅት የወታደራዊ አቅምን አግዝፎ መናገር የወዳጅን ስሜት ያበረታል፣ የጠላትን ልብ ያርዳል። ሆኖም ያለውን መረጃ ሁሉ መዘርገፉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። አንዳንድ መረጃ ይፋ ሲደረግ ከኃያላን ባላንጣዎች ጣጣም ይዞ ሊመጣ ይችላል። በሌለ ነገር በአፍ እላፊ ብቻ እንኳ በጅምላ ጨራሽ መሣሪያ አምራችነት ተጠርጥረው የሳዳም ሁሴን ሕይወትና የአገረ ኢራቅ ዕጣ ፈንታ እንዳልነበር መደረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። “በለፈለፉ ይጠፉ” ይባል የለ?

ኢትዮጵያ ያሏትን ድሮኖች ያላንዳች ከለላ በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች በግላጭ አስጥታቸዋለች። ይህ ደግሞ ድሮኖቹን ለማወቅ የሚደረገውን ጥረት ሙዝ የመላጥን ያህል ያቀለዋል። እንደ አሜሪካ ያሉ ኃያላን አገሮች እንኳ ከምድርም ሆነ ከሰማይ ዕይታ የሚሸሽጓቸው በርካታ ስትራቴጂካዊ መሣሪያዎች አሏቸው። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገዛ ተዋጊ ድሮንን ከዕይታ ለመከለል አለመሞከር ግርምትን ያጭራል። ቢያንስ “ታሪካዊ ጠላቶቻችን” ይህን መረጃ በጥብቅ እንደሚፈልጉት እንዴት ይዘነጋል?

ከሁሉም ተጠርጣሪ የድሮን አምራች አገሮች ትኩረትን የሳበችው ኢራን ናት። በአሜሪካ መንግሥት የንግድ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ስለሆነች። በግልጽ አይነገር እንጂ ሰመራ ላይ ታየ በተባለው በኢራን ሠራሽ ድሮን ምክንያት ኢትዮጵያ በአሜሪካ ጥርስ ውስጥ ገብታ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ነው። ቀደም ብሎ በ1997 ምርጫ ሲጭበረበር፣ ዜጎች በአደባባይ ሲረሸኑና መንግሥት “100 በመቶ ምርጫ አሸነፍኩ” ሲል እንኳ “ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ መንገድ መንግሥቷን መርጣለች” ብለው ሲመሰክሩና ዕርዳታን በገፍ ሲሰጡ ነበር። በትግራዩ ጦርነት ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማባረሯና በርካታ ዕርዳታዎቿን አቋርጣለች። ኢትዮጵያ አጎዋን ታሳቢ አድርጋ ያቀደቻቸው የአሥር ዓመት የኤክስፖርት መር ዕቅድ፣ በቢሊዮኖች ወጪ አድርጋ ማስፋፊያ ያደረገችለት የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የዜጎቿ የሥራ ዕድልና የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት ተመራጭ ሆና መቆየት የምትችልባቸውን ዕድሎች አምክኗል። እንዲሁም የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ለበርካታ ጊዜ ማዕቀብ ለመጣል መሞከሩ የሚነግረን ነገር አንዳንዶች እንደሚሉት “ለትግራይ ኃይሎች በማድላት” ብቻ የተከወነ አይመስልም። 

የዝሆኖቹ ክልሎች የድሮን ድርሻ

ተዋጊ ድሮን በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው በትግራዩ ጦርነት ይሁን እንጂ በጊዜ ሒደት በኦሮሚያና በአማራ ክልል የሚገኙ በርካታ ዜጎችና ንብረቶቻቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል። ድሮንን ጨምሮ የዕለት ተዕለት የግጭት ዜናዎችን በመላው ዓለም ትኩረት ሰጥቶ ከሚከታተሉና መረጃውን ከሚያደረጁ ተቋማት አንዱ “ACLED” ነው። ለእያንዳንዱ ጥቃት ጄኦ ኮርዲኔት፣ ዕለት፣ የሟችና ቁስለኛ ቁጥር፣ የግጭቱ ተዋናዮች ወዘተ. መረጃዎችን ያካትታል። በዚህ ጽሑፍም ከድርጅቱ የተገኘ መረጃን በመንተራስ በኢትዮጵያ ያለውን የድሮን ጥቃት በሥፍራና ጊዜ ፀባይ ለመመርመር ተሞክሯል። 

በአጠቃላይ 125 የድሮን ጥቃቶች በኢትዮጵያ ተመዝግበዋል። ከትግራይ ጦርነት ቀደም ብሎ በተለያዩ ጊዜያት ስምንት የድሮን ጥቃቶች በተለያዩ ሥፍራዎች ተፈጽመዋል። በዚህ ጽሑፍ የቀረበው ጂኦ ስፓሻል ትንታኔም የተመረኮዘው ከትግራይ ጦርነት መባቻ ጀምሮ በተከሰቱ 117 የድሮን ጥቃቶች ሥፍራና ጊዜ መረጃ ላይ ነው። 

በምሥል አንድ እንደሚታየው የትግራይ ክልል 61 የድሮን ጥቃት ሲከሰት አጠቃላይ ቁጥር 52 በመቶ ይይዛል። የጥቃቱ ሥርጭት በዞን ደረጃ ሲታይም ከፍተኛ መበላለጥን ያሳያል። ደቡብ ትግራይ 35፣ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ 14፣ ማዕከላዊ ትግራይ ስድስት፣ ምሥራቅ ትግራይ አምስት የድሮን ጥቃት አስተናግደዋል። የሚገርመው የወልቃይት አካባቢ ነው። ከአማራ ክልል ጋር ባለው የይገባኛል ጥያቈ ሳቢያ በርካታ የምድር ውጊያዎች የተካሄደበት ሥፍራ ሆኖ ሳለ አንዳችም የድሮን ጥቃት አልተመዘገበበትም። የአማራ ክልል 37 የድሮን ጥቃትን አስተናግዷል። ሆኖም ይህ ቁጥር በፋኖ አማፂ ጦር ሰበብ ብቻ የተፈጸመ አይደለም። ቀደም ብሎ ቲዲኤፍ ወደ መሀል አገር ተስፋፍቶ በነበረ ወቅት 23 የድሮን ጥቃቶች በአማራ ክልል ላይ የተፈጸመ በመሆኑ የአማራን ክልል በተለየ ሁኔታ ተደራራቢ የድሮን ተጠቂ አድርጎታል። በዞን ደረጃ ሰሜን ወሎ 15፣ ምዕራብ ጎጃም ሰባት፣ እንዲሁም ሰሜን ሸዋ አምስት የድሮን ጥቃትን አስተናግደዋል። በተያያዥ መገንዘብ የሚቻለው በአማራ ክልል የድሮን ጥቃቶች በርክተው የተፈጸሙት ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በሚጓዘው አውራ ጎዳና ግራና ቀኝ ሥፍራ ነው። በኦሮሚያ ክልል ደግሞ 23 የድሮን ጥቃቶች ሲመዘገቡ ይበልጥ ያተኮሩት የኦነግ ሸኔ በሰፊው ይንቀሳቀስበታል በሚባለው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ነው። በዞን ደረጃ ምዕራብ ወለጋ 15፣ ምዕራብ ሸዋ ስድስት፣ ምሥራቅ ወለጋ አምስት፣ በአማራ ክልል በሚገኘው የኦሮሚያ ልዩ ዞን አምስት ናችው። የኦሮሚያ ክልል የድሮን ጥቃቶችን ከትግራይና ከአማራ ክልሎች የሚለየው የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በበቂ ሽፋን አልዘገቡትም። 

ምሥል ሁለት በጊዜ ሒደት የታየውን የድሮኖች ጥቃት ብዛትን ያሳያል። በ2021 እ.ኤ.አ. 51 ሲሆን በ2022 ደግሞ ወደ 53 ከፍ ብሏል። እ.ኤ.አ. 2023 (ለመጠናቀቅ ገና ከወር በላይ ቢቀረውም) እስካሁን 13 የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል። እ.ኤ.አ. በ2021 የነበረው ጥቃት በትግራይና በአማራ ክልሎች ሲሆን ዒላማው የቲዲኤፍ ኃይል ነበር። እ.ኤ.አ. በ2022 ደግሞ የድሮን ጥቃቱ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች ጎን ለጎን ሲካሄድ የአማራ ክልል መጠነኛ ፋታ አግኝቶ ነበር። እ.ኤ.አ. በ2023 የትግራይም ሆነ የኦሮሚያ ክልሎች ፋታ ሲያገኙ የአማራ ክልል ደግሞ በፋኖ ታጣቂዎች ሳቢያ የድሮኖች ጥቃት ዒላማ ሆኗል።

እዚያ ድሮን... እዚህ ድሮን... | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የድሮን ጥቃት የተከናወነባቸው ሥፍራዎችን ተፈጥሯዊና ማኅበረሰባዊ ምኅዳሮችን ጠለቅ ብለን ስንቃኝ ጥቂት እውነታዎችን ልብ ማለት እንችላለን። አንደኛ መሬቶቻቸው ተራራማና ተዳፋት የሚበዛበት፣ የአፈር ለምነታቸው ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የተሟጠጠ ነው። የተዳፋት መጠኑ ከፍ ማለቱ የወታደራዊ ሜካናይዝድ ጦር እንቅስቃሴና የውጊያ አቅምን በእጅጉ ይወስነዋል። ለመንግሥት ጦር አቋራጭ መፍሔው ደግሞ ድሮን ይሆናል። ሁለተኛ ሥፍራዎቹ የሕዝብ ብዛት የተጫናቸው በመሆናቸው ለእርሻ መሬት ጥበት ችግር የተጋለጡ ናቸው። ሦስተኛ የአካባቢዎቹ የምግብ ዋስትና እጅግ የተመናመነና ለተደጋጋሚ ድርቅና ረሃብ ተጋላጭ ሥፍራ ነው። አራተኛ በተለይም በአማራና ትግራይ ያለው የድሮኖች ጥቃት ሥፍራ ኢትዮጵያ ከውጭ ወራሪም ሆነ የእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ከፍተኛ ጦርነቶችን ለዘመናት ያካሄደችበትና ደም እንደጎርፍ ሲፈስበት የኖረ ሥፍራ ነው። ከብዙ በጥቂቱ የመቅደላ፣ የዓድዋ፣ የሰገሌ፣ የማይጨው፣ የሕወሓት ብለን መጥቀስ እንችላለን። ይህ አልበቃ ብሎ በዚህ አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ከሰማይ የድሮን ዝናብ እየዘነበበት ይገኛል።

በአንፃሩ ደግሞ እስካሁን ባለው ሁኔታ ሰፊው የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍልን የሚሸፍነው ሰማይ ለደመና ማድመኛና ለመንገደኛ አውሮፕላን መተላለፊያ ክፍት ሆኖ እያገለገለ ነው። ይህም አንድ ተስፋ ነው። ልክ ኦሲስ እንደሚባለው በበረሃ መሀል እንደሚገኝ ለምለም ሥፍራ!

ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ

ተዋጊ ድሮኖች በርካታ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም አሉታዊ ጎንም አላችው። ለምሳሌ በተሳሳተ የምሥል ትንታኔና ትርጓሜ ሳቢያ ጉዳዩ ፍፁም የማይመለከታቸው ሰብዓዊና ቁሳዊ ዒላማዎች ሰለባ ይሆናሉ። ድሮኖች ለአንዳንድ አምባገነን መሪዎች እንደ ቀኝ እጅ ሆነው ሕዝባዊ ተቃውሞን ለማፈንና ለማኮላሸት አስችለዋል። እንዲሁም ተጠያቂነት ባልተበጀለት ሁኔታ ድሮኖች ከሕግ አግባብ ውጪ ግድያን (Extrajudicial Assassination) ማካሄድ ያስችላሉ።

የተለያዩ ሚዲያዎች እንደዘገቡት የኢትዮጵያ ድሮኖች ወፍጮ ቤቶችን፣ ተፈናቃይ ዜጎች የተጠለሉበት ሥፍራን፣ የመኖሪያ ቤቶችን፣ የአውቶቡስ ጣቢያን፣ የገበያ ሥፍራን ወዘተ. አጥቅተዋል ተብሎ ወቀሳ ቀርቧል። በዚህም ሳቢያ በርካታ ንፁኃን ዜጎች በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል። ባደጉ አገሮችም የድሮን ጥቃት ተጠያቂነት ቢያወዛግብም በኢትዮጵያ ግን ቃሉም አይነሳም። የተባበሩት መንግሥታትና ኃያላን አገሮች በተደጋጋሚ ድርጊቱን ኮንኑ እንጂ ያመጡት ለውጥ የለም።

ወደ ልማታዊ ድሮን

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ድሮን ለሠርግ ቪዲዮ መቅረጫና ማድመቂያ፣ ውጤታማነቱ በይፋ ባይገለጽም ለመድኃኒት ማድረሻነት፣ እንዲሁም አማፂያንና ይዞታቸውን ለማውደሚያነት እየዋለ ነው። ሆኖም ከተጠቀሱት ተግባራት ባሻገር በርካታ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የድሮን ትሩፋቶች አሉ። ለማሳያ ጥቂቱን እንጥቀስ።

አንደኛ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። እዚህም እዚያም የተለያየ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ ሲፈጠር መረጃ በፍጥነትና በጥራት ማግኘት ግድ ይላል። ድሮኖች የደን ቃጠሎን፣ የጎርፍ አደጋን፣ የአንበጣና የተምች መንጋን፣ ወዘተን ሽፋን በመቃኘትና ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና ለተግባራዊ እንቅስቃሴ አመቺ የሆነ መረጃን ለማቅረብ ያግዛሉ። በውጤቱም የበርካታ ሕይወትና ንብረት መታገድን ያስችላሉ።

ሁለተኛ አርብቶ አደሩ የሚኖርበት አካባቢ ሞቃታማና ደረቃማ ነው። አካባቢው የውኃና መኖ እጥረት ተጋላጭ ነው። አርብቶ አደሩ ቀዬውን ለቆ በግምት ወደ ሌላ ሥፍራ ከመሰደዱ አስቀድሞ ድሮኖች ውኃና ግጦሽ የሚገኝበትን ሥፍራ ቃኝተው ማመላከት ይችላሉ። የሚፈለገውን መረጃ በዋይ ፋይ አማካይነት በየተወሰኑ ርቀቶች በሚቋቋሙ የድሮን ኪዮስኮች ለአርብቶ አደሩ ቢቀርቡለት ጥቅሙ በርካታ ነው።

ሦስተኛ ድሮን ፀጥታና ሰላም ለማስፈን ይረዳል። በአወዛጋቢ የክልልም ሆነ የወረዳ ድንበሮች አካባቢ ስምምነት ቢደረስም በተደጋጋሚ ትንኮሳ እያገረሸ ለማያባራ የግጭት አዙሪት ያጋልጣል። የሰላም ስምምነቱ እስኪፀና ድሮኖች በአወዛጋቢው ሥፍራ መደበኛ ቅኝት ቢያደርጉ ገለልተኛ የሆነ ፈጣን የመረጃ ማቅረብ ይችላሉ። የመረጃ መዛባትን ያመክናሉ፣ አጥፊውን ይለያሉ። ስምምነቱ ዘላቂ እንዲሆን ያግዛሉ።

አራተኛው ያልመከነ ፈንጂን ሥፍራ በመለየት ሞትና የአካል ጉዳትን ያስቀራሉ። ከተለመደው አሠራር ይልቅ ድሮኖች በጥቂት የሰው ኃይል፣ በጀትና ጊዜ ይከውናሉ። ፈንጂዎች ብረታማ ስለሆኑ በፀሐይ ብርሃን ወቅት የሙቀት መጠናቸው ከከበባቸው የአፈር ከፍ ይላል። በአፈሩና በፈንጂዎቹ መሀል ያለውን የሙቀት ልዩነት የድሮኖቹ ተርማል ሴንሰሮች ስለሚለዩት የፈንጂውን ሥፍራ በቀላሉ አመላክቶ ለማምከን ያስችላል።

በመጨረሻምጨዋታው በሰማይሊሆን ነው

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ መንግሥታት ተዋጊ ድሮኖችን ያለ አንዳች ሕጋዊና ሞራላዊ ተጠያቂነት እየተገለገሉበት ነው። በአጭሩ ዓለም ዘጠኝ ሆኖላቸዋል፣ “the New Wild Wild West” እንደሚባለው። ቅጥ አልባ የድሮን አጠቃቀም አንዳንድ መንግሥታትን ሃሺሽ የቀመሱ ‘Governments on Steroids‘ እያስመሰላቸው ነው። ሰማይ ላይ ሆነው የሚፈልጉትን ሲያሳኩ የሰማይ ሰማያቱን አምላክነት ችሎታ የተጎናፀፉ እንዲመስላቸው እያደረገ ነው። በዚህም ሳቢያ ለውይይትም ሆነ ለሰላማዊ መፍትሔ ጆሯቸው ይደፈናል። የኢትዮጵያን የድሮን ስኬት የተመለከቱ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ መንግሥታት ለድሮን ባለቤትነት መሯሯጣቸው አይደንቅም።

ይህ ድሮን አመጣሽ የበላይነት ለረዥም ጊዜ ፀንቶ አይቆይም፣ ሚዛኑ ይቀየራል። ምክንያቱም ተዋጊ ድሮኖች አሸባሪዎችና አማፅያን ቡድኖች እጅ እየገቡ ናቸውና። ለምሳሌ የሊባኖሱ ሄዝቦላ፣ አይሲስ፣ የፓለስታይኑ ሃማስ፣ የናይጄሪያው ቦኮ ሃራም፣ የየመኑ ሃውቲ ቡድን ባለ ድሮኖች ሆነዋል። ተወደደም ተጠላም ሌሎች አማፅያንም ድሮኑን ውለው አድረው እስከ አፍንጫቸው ይታጠቁታል። ገበያ አይደል? ገዥ ካለ ሻጭ አይጠፋም። ዋናው ገንዘብ ነው።

የድሮኖች በአማፅያን ቡድኖች እጅ መግባት በተለይም በአምባገነንነታቸው ለሚታወቁት በርካታ የአፍሪካ መንግሥታት ዱብ ዕዳ እንደሚሆን ነው። ያኔ ታዲያ ጨዋታው በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም ይሆናል። በየጎጡ የሚለኮስ ግጭትም በቀላሉ ከመክስም ይልቅ በቅፅበት ወደ መጠነ ሰፊ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል። በድሮን ጥቃት ወቅት በኮላተራል ዳሜጅ አብሮ የሚወቃው የሰላማዊ ዜጋ ቁጥርም የትየለሌ ይሆናል።

የአይቲ ቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገትም ሌላው ተግዳሮት ነው። ድሮኖች ከምድር መቆጣጠሪያ ጣቢያ ጋር መልዕክት እንዳይለዋወጡ ጃሚንግ ሊያውካቸው ይችላል። በኢንተርኔት ላይ የምናውቀው የሃኪንግ ችግር በድሮን ላይ ሲተገበር ድሮኑ ቀድሞ የተነገረውን ዒላማ ቀልብሶ የራሱን ማዘዣ ጣቢያ ወይም የወገንን ጦር መደምሰስ የሚያስችል አሉታዊ ጎን አለው።

አይቀሬውን የድሮን ወለድ አደጋን ማስቀረት ይቻላል። ሥልጣን የጨበጡ መንግሥታት ከእልህ ነፃ ሆነው የዜጎቻቸውን ልብ ትርታ ማድመጥ ይኖርባቸዋል። የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ከዜጎች የሰላም ዋስትና ጋር አጣምረው ማስፈን ደግሞ ኃላፊነታቸው ነው። አልያማ የግጭት ክብሪቶች እዚህም እዚያም መለኮሳቸው ግድ ነው። ሁሉንም ችግር በድሮን የበላይነት ብቻ ለመፍታት የሚያደርጉት ጉዞ ለትናንት አገልግሏቸዋል፣ ለነገ ተነገ ወዲያ ግን በፍጹም ሊታደጋቸው አይችልም። በዓምና በሬ አይታረስምና፣ በፍጥነት ወደ ቀልባቸው ካልተመለሱ መጥፊያቸው ሊሆን ይችላል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው daniel.kassahun@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...