Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን ያሳሰበው የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት

ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን ያሳሰበው የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት

ቀን:

በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ወቅት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የነበረው አለመግባባት ገለልተኛ ሆኖ ለመዳኘት ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሁለቱንም ተቋማት ጋብዞ ነበር፡፡

ባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በተገኙበት ውይይት ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተናጠል ሁለቱንም ተቋማት ከሦስት ሰዓታት ላልተናነሰ ጊዜያት እንዳነጋገረ ጠቅሶ፣ ነገር ግን ምንም ጭብጥ እንዳላገኘ ማብራራቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በውይይቱ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች መኖራቸውን አቶ ቀጄላ አውስተው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሁለቱም ተቋማት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ያላት ተሳትፎ የደመቀ መሆኑንና ሁለቱም ተቋማት አገርን ማስቀደም እንደሚገባቸው አቅጣጫ ተሰጥቶ ነበር፡፡

በሌላ በኩል በሁለቱም አካላት መካከል ያለው የግለሰቦች እልህ መጋባት መቆም እንደሚገባውና ችግሮች ቢኖሩም በውይይት እንዲፈቱ የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአንፃሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኅዳር 15 እስከ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ በተከናወነው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በ2024 በፓሪስ ከሚሰናዳው የኦሊምፒክ ጨዋታ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ያለው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ ተነስቷል፡፡

የመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን መዝጊያ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) ኦሊምፒክን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጊዜው ዕቅድ እንዲያቀርብ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥያቄ ቢቀርብለትም በቂ ምላሽ አልሰጠም ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ በጊዜው ዕቅድ እንዲያስገባ ጥያቄ ቢቀርብለትም በቂ ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም፡፡ ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የክልል ቢሮ ኃላፊዎችን ብቻ ነጥሎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በማግለል ከአዲስ አበባ እስከ ፓሪስ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፤›› በማለት መስፍን (አምባሳደር) አስረድተዋል፡፡

እንደ መስፍን (አምባሳደር) ማብራሪያ፣ እንቅስቃሴውና አካሄዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነትና ሥልጣንን ያላካተተ ተገቢነት የሌለው ነው ብሏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኦሊምፒክ ኮሚቴው ጋር ያለው ግንኙነት በዚህ ከቀጠለ፣ በ2020 ኦሊምፒክ ወቅት ያጋጠመው አለመግባባትና ውዝግብ በፓሪስም ሊገጥም ይችላል የሚል አስተያየት ከሚኒስቴሩ ተሰንዝሯል፡፡

‹‹መንግሥት ያስቀመጠውን ፖሊሲ አስፈጻሚ ተቋም ያገለለ ማንኛውም ተግባር ተቀባይነት የለውም፡፡ በዚህም ምክንያት ኦሊምፒክ ኮሚቴውም ሆነ አብሮ በጋራ እየሠራ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከወዲሁ በጉዳዩ ላይ ግልጽ አቅጣጫ ይዞ እንዲጓዝ ግልጽ ማድረግ እንፈልጋለን፤›› ሲሉ መስፍን (አምባሳደር) አብራርተዋል፡፡

እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማብራሪያ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ መንግሥት በአዋጅ በሰጠው ሥልጣን መሠረት አገር አቀፍ የስፖርት መመርያዎችን አክብሮ እየሠራ እንደሚገኝና ጥሩ ግንኙነት እንዳለው መስፍን (አምባሳደር) አብራርተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የገቢ ምንጩን ለማሳደግ በማርኬቲንግ ቡድን አማካይነት እየተንቀሳቀሰ ያለበት ሒደት በመልካም ጎኑ ተነስቷል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኢትዮጵያ የስፖርት እንቅስቃሴ ለማከናወን የማዘውተሪያ ሥፍራ ማነቆ ሆኖ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዓመታት በፊት ዕድሳት እየተደረገለት የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም የትራክ ጥገና እንደ አዲስ ለማከናወን ከተቋራጭ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ የተነሳ ሲሆን፣ ለኦሊምፒክ ዝግጅት ለማድረስ አስፈላጊ ጥረት ይደረጋል ተብሏል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ በኋላ የመጡትን ውጤቶች የበለጠ ለማስጠበቅ ጠንክሮ መሥራት፣ በየርቀቱ አስቀድሞ ብሔራዊ አሠልጣኞችና ብሔራዊ አትሌቶችን ከማሰናዳትና ውጪ፣ በአግባቡ መጠቀም ኢትዮጵያ ካለችበት የሀብት አቅም ሁኔታ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶች በተለይ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚያገኙትን ገቢ እንዲያሳውቅ ጥያቄና አቅጣጫ ቢሰጥም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ምላሽ አለመስጠቱ ተነስቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማ መንገዶችና ልምድ መካፈል የሚፈልጉ በርካታ አገሮች ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ቢጠቅስም፣ ፌዴሬሽኑ ግን ብዙ ሊጓዝበት እንዳልቻለ ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተቃረቡበት ወቅት በአሠልጣኞች፣ በማናጀሮች፣ እንዲሁም አትሌቶች መካከል አላስፈላጊ መግባባቶች እየተለመዱ መምጣታቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥርዓት ማስያዝ ይኖርበታል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በአጭር ርቀት፣ እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ላይ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉ አትሌቶች ቢኖራትም፣ በርቀቶቹ ላይ ደፈር ብሎ አትሌቶችን ማፍራት አለመቻሏ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም በቀጣይ በርቀቱ በደንብ መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የተገኙ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር የነበረው ቁርሾ ወደ ሰላም መመለሱን አስረድተው፣ ዓምና የነበረው ስህተት እንዳይደገም በጋራ እየሠሩ  መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ገዛኸኝ ማብራሪያ፣ የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ዝግጅት ቀድሞ መጀመሩና በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ለመሥራት እንቅስቃሴውን መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፓሪስ ትንሽ ወጣ ብላ በምትገኝ አንቶኒ ከተማ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከኦሊምፒክ ጨዋታው ቀድሞ ልምምዱን እንዲያደርግ ስምምነት ላይ መድረሱ ተጠቅሷል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤቱ ተወካይ አስተያየት፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን፣ በተለይ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ተቀራርቦ እየሠራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ከዚያም ባሻገር ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከክልሎች ጋር በመነጋገር የኦሊምፒክ ችቦ በክልሎች ለማዘዋወርና ከወዲህ ለማነቃቃት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ደኤታው በመዝጊያ ንግግራቸው የመንግሥት አቅጣጫዎች፣ የመንግሥት ስፖርት ልማት ዕቅድ፣ ከፖሊሲና ከአሥር ዓመቱ ዕቅድ የሚያያዙ መሆናቸው ተነስቷል። ከዚህም ባሻገር  በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በክትትልና ድጋፍ ወቅት የሚታዩ ክፍተቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባና በግብዓት ተወስደው፣ ግብረ መልስ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሚኒስትር ደኤታው አብራርተዋል።

አትሌቲክስ ስፖርት የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በዓለም አቀፍ መድረክ አጉልቶ ከሚያሳይ ስፖርት መካከል ብቸኛው እንደሆነ ተነስቷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በኋላ ጠንክሮ በመሥራት ውጤታማ መሆን መቻሉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአንፃሩ ፌዴሬሽኑ ካስቀመጠው ግብ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአትሌቲክሱ የሚጠብቀውን ውጤት ያላሳካበትን ምክንያት በጥልቀት መገምገም እንደሚገባው ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ አሳስቦታል፡፡

ከዚህም አንፃር የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ የእርስ በእርስ ግንኙነት ምን ይመስላል? እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ከተቋማት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ሕጋዊና ሰላማዊ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባው ተጠቅሷል።

በውድድር ዝግጅት ወቅት በአትሌቶች እንዲሁም አሠልጣኞች  ምርጫ ውሳኔን በተመለከተ፣ በሥራ አስፈጻሚና ቴክኒካል ባለሙያዎች መካከል ያለው የሥራ መደራረብና አንዳንድ ጊዜ የሚገጥሙ አላስፈላጊ ሁኔታዎች ጠለቅ ያለ ውይይት እንደሚሹ ተጠቅሷል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ አባላትና የባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግልጽና ጠቃሚ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግና ለመጪው የፓሪስ ኦሊምፒክ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...