Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ በብሔራዊ ባንክ ጣልቃ ገብነት ሊካሄድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ንብ ባንክ፣ አጋጥሞታል በተባለ የእንቅስቃሴ መዳከም ምክንያት፣ የባንኩ የቦርድ አባላት ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ በመግባት የባንኩን ባለአክሲዮኖች ለጠቅላላ ጉባዔ መጥራቱ ታወቀ።

የባንኩ ውስጣዊ ችግርን መነሻ አድርጎ በባንኩ የቦርድ አመራሮች መካከል የተፈጠረ ውዝግብ፣ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ታግዶ መቆየቱን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል። እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተደጋጋሚ ማሳሳቢያ ለንብ ባንክ የሰጠ ቢሆንም፣ የባንኩ ውሳጣዊ ችግሩን ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተፈጻሚ ማድረግ አልቻለም። 

የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ በብሔራዊ ባንክ ጣልቃ ገብነት ሊካሄድ ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የንብ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት

በዚህም ምክንያት ብሔራዊ ባንክ፣ በባንኩ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መገደዱን የጠቀሱት ምንጮቹ፣ በስተመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓርብ ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ፣ ራሱ (ብሔራዊ ባንክ) የሚመራው የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ለታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. መጥራቱን ጠቁመዋል።

ባንኩ አጋጥሞታል የተባለው የውስጥ ችግር፣ በባንኩ የቦርድ አመራሮች መካከል፣ እንዲሁም ባንኩን በሚመሩት የማኔጅመንት አባላት መካከል አለመግባባት መፍጠሩንና ከዚህም የዘለሉ ሌሎች ችግሮች መኖራቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ 

ባንኩ ያለ በቂ ዋስትና ‹‹ደጐሎ›› ለተባለ ድርጅት 27ዐ ሚሊዮን ብር አበድሮ እስካሁን መመለስ አለመቻሉን፣ ብድሩን በተመለከተ በባንኩ የውስጥ አዲት ዕርማት እንዲወሰድ ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ ማኔጅመንቱ ተገቢ ዕርምጃ አለመውሰዱንና በዚህም ምክንያት ብድሩን እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ማስመለስ እንዳልተቻለ ምንጮቹ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አቻ ባንኮች ለካፒታል ዕድገት የአክስዮን ሽያጭ ሲያወጡ፣ ያለ ምንም ችግር ፈጥነው የሚሸጡ ቢሆንም፣ ንብ ባንክ ግን ይህን ሊያሳካ እንዳልቻለ፣ በዚህም ምክንያት ሌሎች ባንኮች ከፍተኛ የካፒታል አቅም ሲፈጥሩ የንብ ባንክ ካፒታል ግን ገና 10 ቢሊዮን ብር እንዳልደረሰ ምንጮቹ ጠቁመዋል።

ባንኩ በሚሰጠው አገልግሎት፣ በሠራተኛ አያያዙ፣ በአይቲ ሲስተም ትግበራውና በሚያሳየው የትርፍ መጠን ከሌሎች የግል ባንኮች ጋር መወዳደር እንዳልቻለ፣ በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል ከግል ባንኮች በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ባንክ በአሁኑ ጊዜ ወደ አሥረኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉን ገልጸዋል፡፡ 

በንብ ባንክ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት በባንኩ የሥራ ሒደት ላይ እክል መፍጠሩን የተገነዘበው ብሔራዊ ባንክ፣ የዕርምት ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ የተለያዩ ውሳኔ እስከ ማሳለፍ ደርሶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በባንኩ ውስጥ የተፈጠረው ጫና በባንኩ የብድር አቅርቦት ላይ ገደብ እንዲጣል ጭምር አድርሷል የሚሉት ምንጮቹ፣ ይህም በባንኩ የሥራ አፈጻጸምና ትርፋማነት ላይ ጉዳት ያሳድራል ተብሎ ተሠግቷል፡፡ 

የ2015 የሒሳብ ዓመት መጠናቀቅን ተከትሎ መካሄድ የነበረበትን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድና በዚህ ጉባዔ የሚመረጡ ዕጩ የቦርድ አባላትን ለማስተዋወቅ ተጀምሮ የነበረው ጥረት፣ በብሔራዊ ባንክ መታገዱንም ምንጮቹ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ዓርብ ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የንብ ባንክ ጠቅላላ ጉባዔና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ በብሔራዊ ባንክ ሰብሳቢነት እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል። በዚህ ውሳኔ መሠረትም የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በብሔራዊ ባንክ ሰብሳቢነት ይካሄዳል።

በቅድሚያም የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ በብሔራዊ ባንክ ተሰብሳቢነት እንደሚካሄድ፣ በመቀጠልም የባንኩን ችግር ለመፍታት ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው አቅጣጫ ተፈጻሚ ያልተደረጉ ውሳኔዎችን በመገምገም ተጨማሪ የማስተካከያ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡  

በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ሆነ ከንብ ባንክ አመራሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች