Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከ25 በመቶ በላይ ሠራተኞቹ የለቀቁበት ፀረ ሙስና ኮሚሽን መፍትሔ ይሰጠኝ አለ

ከ25 በመቶ በላይ ሠራተኞቹ የለቀቁበት ፀረ ሙስና ኮሚሽን መፍትሔ ይሰጠኝ አለ

ቀን:

‹‹ከ20 ዓመታት በላይ አገልግዬ ደመወዜ አንድ ኩንታል ጤፍ መግዛት አይችልም››

የኮሚሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ

በኑሮ ውድነት ምክንያት የሚከፈላቸው ደመወዝ አላኖር ያላቸው ከ25 መቶ በላይ ሠራተኞቹ በአንድ ዓመት ውስጥ ሥራቸውን መልቀቃቸውን ጠቅሶ መፍትሔ ይሰጠኝ ሲል፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለፓርላማ ጥያቄ አቀረበ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኮሚሽኑ የ2016 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሐሙስ ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያቀርብ፣ ለፀረ ሙስና ትግሉ እንዲያግዙት የቀጠራቸው ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ሊያኖራቸው ባለመቻሉ ሥራቸውን ለቀው እየወጡ ሥራዬን አዳጋች አድርጎብኛል ብሏል።

የኮሚሽኑ የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ ከ2016 ዓ.ም. ወዲህ ብቻ 50 ሠራተኞች መልቀቃቸውን ገልጸው፣ የሰው ኃይል ፍልሰት የኮሚሽኑ ትልቁ ማነቆ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት ትልቅና አገራዊ ፋይዳ ያለው ሆኖ እያለ፣ ለሠራተኛው የሚከፈለው ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ በየጊዜው እየለቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ምናልባት የቀሩትም ሠራተኞች ሥራ ፍለጋ ላይ ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ፤›› ብለዋል።

ደመወዝ ዝቅተኛ መሆኑን ሲያብራሩ፣ ‹‹ለአብነት ያህል እኔ ኮሚሽኑ ውስጥ ለ21 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ ነገር ግን የሚከፈለኝ ደመወዝ አንድ ኩንታል ጤፍ አይገዛም፡፡ 100 ኪሎ ጤፍ ለመግዛት የሚከፈለኝ ደመወዝ ስለማይበቃኝ ተጨማሪ ገንዘብ ተበድሬ ነው የምገዛው፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

በመሆኑም በዚህ መጠን ደመወዝ የሚከፈለው ሰው የፀረ ሙስና ትግሉን ነፃ፣ ገለልተኛና የተረጋጋ አድርጎ ለመሥራት በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆንበት የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ኮሚሽኑ እንደ ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲታይ ምክር ቤቱ ዕገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለ2016 በጀት ዓመት የተመደበለት ዓመታዊ በጀት 62 ሚሊዮን ብር መሆኑንና ከዚህ ውስጥ 25 ሚሊዮን ለደመወዝ ሲያውለው ቀሪውን ለፀረ ሙስና ትግል የተመደበ የሥራ ማስኬጃ ስለመሆኑ አስረድተው፣ የሙስና ሥጋት ከፍተኛ በሆነበት አገር ውስጥ ባልተሰጠ በጀትና በሌለ ገንዘብ እንዴት አድርጎ ሥራውን በሚፈለገው መጠን እንዲሠራ ይጠበቃል? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1236 አማካይነት ኮሚሽኑ ከሲቪል ሰርቪሱ ነፃና ገለልተኛ ነው ብሎ የተደነገገ ቢሆንም፣ አሁን ሙሉ በሙሉ እየሠራ ያለው በሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሆኑን፣ አቶ ተስፋዬ አብራርተው፣ የወጣው አዋጅና የሚሠራው ሥራ የማይገናኝ በመሆኑ ኮሚሽኑ እንደ ሌሎች ተቋማት በሲቪል ሰርቪስ የሚገዛ በመሆኑ ነፃና ገለልተኛ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ የኮሚሽኑ ሥነ ምግባር ግንባታ ሥልጠና መሪ አስፈጻሚ አቶ ዳግም አላምረው በበኩላቸው፣ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዲፈጠር ከሚያደርጉት ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙ ቢሆንም፣ የተቋሙ አደረጃጀትና ጥቅማ ጥቅም ግን ከሌሎቹ የዴሞክራሲ ተቋማት በተለይም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለሥነ ምግባርና ለፀረ ሙስና ትግል ሥልጠና ለመስጠትና ትምህርት አዘል መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የሚያስፈልገው በጀት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ፣ ይህን ሥራ ማከናወን የሚችሉና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በሚከፈላቸው ደመወዝ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ተስኗቸው ተቋሙን ለቀው እየወጡ መሆኑን አክለው አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማ የሚመራበት በጀት የሌለው ስለሆነ ሥራውን እየሠራ ያለው ከአቻ፣ ከአጋርና ከመንግሥት ተቋማት ገንዘብ እየለመነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን ለመፍጠር በግልጽ መሥራት ከተፈለገ፣ ቋሚ ኮሚቴው ችግሩን ተረድቶ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እየሳቁብህ ሥራ፣ እየሳቁብህ አትብላ እንደሚባለው አባባል ሠርተን ሰዎችን መለወጥ እንችላለን፡፡ ስንሠራ ሁሉም ወደ እኛ ይመጣል፡፡ ነገር ግን አሁን ጥቅማ ጥቅም ብትጠይቁ መንግሥትም ሕዝቡም ምን ሠራችሁ ይላል፡፡ ውጤት ስናመጣ ግን ሁሉም ሰፍ ብሎ ለመደገፍ ይበረታታል፤›› ብለዋል።

ይሁን እንጂ ቋሚ ኮሚቴው ለመደገፍ ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ግን አሁን ካለበት ተለጥጦ ሊሠራ ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ተጠርጥረው የሚቀርቡ አካላትን ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ሥራ ማስጀመራቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...