Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎች ከመንግሥት አቅም በላይ ሆነዋል ተባለ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎች ከመንግሥት አቅም በላይ ሆነዋል ተባለ

ቀን:

በቅርቡ ምሥረታውን ባካሄደው አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ለተከሰቱት የወባ፣ የኩፍኝና የአባላዘር ወረርሽኞች፣ መንግሥት ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ በተለይ የሕፃናት ሞት አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በመድኃኒትና በሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች እጥረት የጤና ተቋማት ለወረርሽኞች ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉና ሠራተኞቹም ለወራት ደመወዝ ሳያገኙ እንደሚቆዩ ተገልጿል፡፡

በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን በሚገኘው የበቹማ የመጀመሪያ ሆስፒታል ብቻ ካለፈው ነሐሴ ወዲህ 11 (አሥራ አንድ) ሰዎች በሆስፒታሉ ከደረሱ በኋላ በኩፍኝ መሞታቸውን፣ በወባ ምክንያት ደግሞ ከ40 ሰዎች በላይ ካለፈው ዓመት ወዲህ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ እንደሞቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ይህ ቁጥር ወደ ሆስፒታል ሳይደርሱ የሞቱትን በርካታ የወረርሽኝ ሰለባዎችን አያጠቃልልም፡፡ አሁንም በየቀኑ ቢያንስ 30 ሰዎች ወደ ሆስፒታል እየደረሱ ቢሆንም፣ በቂ ሕክምና መስጠት አልተቻለም፡፡ በአካባቢው የጤና ተቋም ባለመኖሩና በርቀት፣ እንዲሁም በዝቅተኛ ግንዛቤ ምክንያት በርካታ ሕዝብ ወደ ሆስፒታሉ አይመጣም፡፡ ሪፈር የሚላከው ወደ ሚዛን አማን ከተማ ቢሆንም፣ አንድ አምቡላንስ ብቻ ስላለ፣ አንዱ ታካሚ መንገድ ላይ እያለ ሌላው ይሞታል፤›› ሲሉ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምሴ ሳፒ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ሊኖረው ከሚገቡ 300 የተኝቶ ታካሚ አልጋዎች ውስጥ 33 አልጋዎች ብቻ እንዳሉት፣ በዞኑ ባሉት ሰባት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በሁሉም ወረርሽኝ መንስራፋቱን፣ በአጎራባች ዞኖች በተለይ በደቡበ ኦሞ ዞን ተመሳሳይ ችግር ተባብሶ መቀጠሉን ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡ ከወባና ከኩፍኝ በተጨማሪ የአባላዘርና ከፍተኛ የምግብ እጥረት መፈጠሩ ተገልጿል፡፡

‹‹ችግሩ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ነው፡፡ ለክልሉና ለፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ ብንገልጽም ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም፡፡ ከአካባቢው ተመርጠው ፓርላማ የገቡ የሕዝብ ተወካዮችን ጠርተን ብናሳይም ምንም ለውጥ አልመጣም፤›› ሲሉ አቶ ደምሴ አስረድተዋል፡፡

የሆስፒታሉ የድንገተኛና የተኝቶ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ጀማል ናስር በበኩላቸው፣ ከፍተኛ የበጀት እጥረት በመኖሩ ያለውን ገንዘብ ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ ብቻ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹እንኳን ብዙ ወረርሽኞች በአንድ ጊዜ ተከስተው ይቅርና በመደበኛ ጊዜ ራሱ የሚመደበው በጀት በቂ አይደለም፤› ብለው፣ በአካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ መድኃኒትና ክትባት ቢመጣም ማቀዝቀዣ ባለመኖሩ ጥቅም ላይ ሳይውል ወደ ውኃ እንደሚቀየር ዶክተሮቹ አስረድተዋል፡፡

በአካባቢው ለሃያ ዓመታት ትክክለኛ ክትባት ባለመኖሩ በተለይ የወባ በሽታ ራሱን ለውጦ፣ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ መድኃኒት የማይድን የወባ ዝርያ መፈጠሩንም ሐኪሞቹ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሚመጣው መድኃኒት ወባውን ማከም አልቻለም፡፡ አዲስ የወባ በሽታ ዝርያ መፈጠሩን ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴና ለዓለም ጤና ድርጅት አሳውቀን ተጨማሪ ምርመር እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሰን የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን አልተጀመረም፤›› ብለዋል፡፡

የክልሉ ባለሥልጣናት ከፌዴራል የሚመጣው በጀት አናሳ በመሆኑና መንግሥት የሚጠቀመው ከ15 ዓመታት በላይ በቆየ የሕዝብ ቆጠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል በተደረገ ቆጠራ የምዕራብ ኦሞ ዞን ሕዝብ 350 ሺሕ ነው ቢባልም፣ በተጨባጭ ግን ከአንድ ሚሊዮን እንደማያንስ ይነገራል፡፡

ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ምክንያቶች ችግሩን መቋቋም አዳጋች እንደሆነ ከነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

መንግሥት አቅሙን እስኪያሳድግ ድረስ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወደ አካባቢው ዘልቀው እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ እስካሁን በክልሉ ለተፈጠሩት ወረርሽኞች ምላሽ እየሰጠ ያለው ‹‹ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን›› የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሕዝብ ከሞት እየተረፈ ያለው በፈጣሪና በቡድኑ ዕርዳታ ብቻ ነው፤›› ሲሉ አቶ ደምሴ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ከአንድ ወር ወዲህ በዞኖቹ ወረርሽኞቹን ማከም ከመጀመሩ በፊት፣ በየቀኑ በበቹማ ወረዳ ብቻ እስከ ሦስት ሕፃናት ይሞቱ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በክልሉ የጤና ችግርና በጀት ጉዳዮች ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና የጤና ሚኒስቴር የሚመለከታቸው ኃላፊዎችን ለማነጋገር ሪፖርተር ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርግም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...