Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለማዳበሪያ ግዥ 930 ሚሊዮን ዶላር መፈቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለ2016/17 ዓ.ም. የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግዥ 930 ሚሊዮን ዶላር መፈቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ለማዳበሪያ ግዥ የተፈቀደው 930 ሚሊዮን ዶላር (71.4 ቢሊዮን ብር) በመሆኑ በዕቅድ ከተያዘው 23.3 ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ የመግዛት አቅም ያለው መሆኑን፣ የግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና የግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በማዳበሪያ ግዥ ላይ ይታይ የነበረውን መዘግየት ዘንድሮ እንዲቀንስ በማድረግ፣ የመጀመሪያው መርከብ ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጂቡቲ እንደደረሰ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው ሒደት የመጀመሪያው መርከብ ጂቡቲ የደረሰው ታኅሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመት የግዥ ሒደቱን ካፈጠኑት አሠራሮች አንዱ የግዥ መመርያ መሻሻል በመሆኑ፣ በማዳበሪያ ግዥ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ተቋማት አመራሮች የቦርድ አባል እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤ ሳኖ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተወካይ፣ እንዲሁም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በአባልነት የተካተቱበት ቦርድ የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር የግዥ ሒደቱ እንዲፋጠን መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በዓለም ላይ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ፣ በጭማሪው ሳቢያም የአርሶ አደሮች የመግዛት አቅምን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም ገበያን ለማረጋጋት ታሳቢ ተደርጎ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ድጎማ ሲደረግ መቆየቱን ሚኒስትር ደኤታዋ ገልጸዋል፡፡

አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች የሚጠቀሙዋቸውን ዩሪያና ኤንፒኤስ ቦሮን ፋሚሊ የተባሉ የማዳበሪያ ግብዓት ፍላጎት አንፃር እጥረት እንዳይፈጠር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ከተደረጉት ድጋፎች ዋነኛው የማዳበሪያ ድጎማ እንደሆነ በመግለጽ፣ በአጠቃላይ በሦስት ዓመታት ውስጥ 51 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በ2014/15 የምርት ዘመን 15 ቢሊዮን ብር፣ በ2015/16 ደግሞ 21 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ዘንድሮ የተወሰነ ዋጋ ስለቀነሰ 16 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡

ጂቡቲ ከደረሰው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ወደ አገር መጓጓዙን አክለዋል፡፡

በግዥ ወደ አገር ውስጥ የገቡት የአፈር የማዳበሪያ ዓይነቶች ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ዩሪያና 11 ሚሊዮን ኩንታሉ ኤንፒኤስ ሲሆኑ፣ እስካሁን 11 ሚሊዮን ኩንታል ኤንፒኤስና ሦስት ሚሊዮን ኵንታል ዩሪያ ማዳበሪያ፣ በአጠቃላይ 14 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል። ቀሪውን ለመግዛትም ዋጋ የሚረጋጋበት ምቹ ወቅት እየተጠበቀ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራ ቀድሞ በመጀመሩ እስከ ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ጂቡቲ ከደረሰው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ወደ አገር ውስጥ መጓጓዙን ሚኒስትር ደኤታዋ አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ ከኅዳር 21 እስከ ታኅሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ኤንፒኤስ ቦሮን የተባለውን የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ ሦስት መርከቦች ጂቡቲ ወደብ ይደርሳሉ ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች