Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሰሊጥ ላኪዎች የሽያጭ ውል ማረጋገጫ ሳይዙ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲገበያዩ ተፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ካለፈው ዓመት ታኅሳስ 9 ቀን 2015 ዓም. ጀምሮ ለሰሊጥ ላኪዎች የኤክስፖርት  የሽያጭ ውል ማረጋገጫ የማግኘት ግዴታ የነበረው አሠራር ላልተወሰነ ጊዜ መቆሙን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቁ፡፡

ለዚህ አሠራር መነሻ የሆነው በወቅቱ የምርት እጥረት ስለነበረ፣ ላኪዎች ያገኙትን ሰሊጥ ከሸጡ በኋላ ሌላ ምርት ለማግኘት በመቸገራቸውና አንዳንዶች ምርት በማከማቸት እጥረት እንዲኖር ምክንያት መሆናቸውን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቂ የሰሊጥ ምርት በመገኘቱ ላልተወሰነ ጊዜ በቀጥታ (ያለ ማረጋገጫ) እንዲገበያዩ መፈቀዱን፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዳዊት መሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ላኪዎች ከምርት ገበያ ሰሊጥ መግዛት ሲፈልጉ ቀድመው በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኤክስፖርት የሽያጭ ውል ማረጋገጫ ግዴታ እንደነበር ገልጸው፣ ይህ አሠራር በ2015 እና በ2016 ዓ.ም ምርት ዘመን የሰሊጥ አቅርቦቱ የተሻለ በመሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲገበያዩ መፈቀዱን አስረድተዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አማካሪ አቶ መስፍን አበበ የኤክስፖርት ማረጋገጫ ውል ያስፈለገበት ምክንያት ሲያስረዱ፣ የሰሊጥ ላኪዎች ከዓለም ገበያ ዋጋ በላይ ይገዙና በክምችት ይዘው በማቆየት የምርቱ ጥራት እንዲቀንስና እንዲባክን ይደረግ ስለነበር ነው ብለዋል፡፡

በቀጥታ ግብይት ከመፈቀዱ በፊት ለምርት ገበያ የሚቀርበው ሳምንታዊ ምርት አነስተኛ እንደነበር የገለጹት አማካሪው፣ ያለውን ምርት ቶሎ ቶሎ እንዲሸጡ ለማድረግ የኤክስፖርት  ውል ማረጋገጫ ያላቸው ላኪዎች ቢልኩት የተሻለ ውጤት ማምጣት ስለሚቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኤክስፖርት ውል ማረጋገጫ ያስፈለገው ሁሉም ላኪዎች በአንዴ የሚገዙ ከሆነ፣ የምርት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ ስለሚያስከት ነው ብለዋል፡፡

አንዳንድ ላኪዎች ቀድመው መግዛትና ማከማቸት የሚመርጡ ቢሆንም፣ በውድ ገዝተው በርካሽ ላለመሸጥ እስኪወደድላቸው ሲጠብቁ ምርቱ እንደሚበላሽ ተናግረዋል፡፡

‹‹የኤክስፖርት ውል ማረጋገጫን ግዴታ ማድረግና መተግበር ወቅቱ አይደለም፤›› ያሉት አቶ መስፍን፣ አሁን ብዙ ምርት እየገባ በመሆኑ ሁሉም ላኪዎች እኩል እንዲገበያዩ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በወጪ ንግድ ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ በፍጥነት ጊዜያዊ መፍትሔ መስጠት በማስፈለጉ የተወሰነ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም የሰሊጥ የምርት እጥረት ካጋጠመና በክምችት ምክንያት ምርት ከጠፋ ላልተወሰነ ጊዜ የተነሳው ግዴታ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኤክስፖርት ውል ማረጋገጫ መያዝ ግዴታ የነበረው ለነጭ ቦሎቄና ለሰሊጥ ምርቶቸ ብቻ መሆኑን፣ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን የማያካትታቸው በቂ ምርት ስለሚመረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰሊጥ ላኪዎች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኤክስፖርት ውል ማረጋገጫ ሳይኖር መገበያየት እንዳይቻል የተደረገው ውሳኔ ተገቢነት የሌለውና ላኪዎችን ከገበያ ውጪ ያደረገ አሠራር ነው፡፡

ለዚህ እንደ ምክንያት የጠቀሱት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተቋቋመው የሰሊጥ ዋጋ አውጪ ቦርድ የሚተምነው ዋጋ፣ ከዓለም ገበያ ጋር ሰፊ ልዩነት መፍጠሩን ነው፡፡

ላኪዎች ሰሊጥ ኤክስፖርት ለማድረግ ከገዥ ጋር ውል መፈራረም እንደሚገባ፣ በዚህ መሠረት ሚኒስቴሩ ውሉን ዓይቶ እንደሚፈቅድ (ማረጋገጫ እንደሚሰጣቸው) የአሠራር ሒደቱ ያስረዳል፡፡

አሁን ግን የዓለም የሰሊጥ ገበያ ዋጋ ስለወረደና መንግሥት ደግሞ እንዲሸጥበት የወሰነው ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥና የዓለም ገበያ ዋጋ የተራራቀ በመሆኑ ተፈራርመው ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚሄዱ ላኪዎች ቁጥር ማሻቀቡን ኤክስፖርተሩ አስረድተዋል፡፡

አሁን ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት በመሆኑ የዋጋ ተመን ማሻሻያ ሳይደረግ ላኪዎች ከገዥዎች ጋር ውል መግባት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ መግለጻቸው፣ በአዲሱ ውሳኔ ሊተላለፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ዋጋ ሲተምን የዓለም ዋጋ መረጃ ላይ ተንተርሶ ቢሆን እንደሚመረጥ የገለጹት ላኪው፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሰሊጥ ዋጋ እንዲቀንስ የሚያደርጉ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ በወጪ ንግድ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የዓለም የሰሊጥ ዋጋና የአገር ውስጥ የመግዣ ተመን የማይመጣጠን ከሆነ ላኪዎችን ለኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ መሸጥ እንደማይችሉ፣ አብዛኛዎቹ ላኪዎች በዚህ ምክንያት ሳይገበያዩ ማቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በምሳሌነት በዓለም የሰሊጥ ገበያ በቶን ከ1,400 እስከ 1,600 ዶላር ሲሸጥ እንደነበር ጠቅሰው ያለፉትን ጊዜያት ያስረዱት ላኪው፣ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ግን ከ1,800 እስከ 2,000 ዶላር እንደሚደርስ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች